ነጻ አእምሮ ሀገር ከምትገነባባቸው መሰረታዊ እሴቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? ነጻ አእምሮ አቅምንና ኃይልን እውቀትን በበቂ ሁኔታ መጠቀም የሚያስችል ጉልበት እንደሆነስ? ነጻ አእምሮ ከነጻ አስተሳሰብ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው:: ነጻ አእምሮ ለህዝብ ስልጣንና ኃላፊነት መስጠት ነው:: ሁሉም ሰው በሚሰራው ሥራ ላይ ኃላፊነት እንዲሰማው መፍቀድ ጭምርም ነው:: ነጻ አእምሮ ለግለሰቦች ያልተገደበ ነጻነት መስጠት ማለት ነው:: የመማር፣ የመስራትና የመለወጥን ኃይል የሚያቀጣጥል ነው::
እድገትና ስልጣኔ እንደ ውሀ በጠማን ጊዜ ላይ የግለሰቦች የአእምሮ ነጻነት ዋጋ አለው ብዬ አምናለው:: ለውጥ ከመማርና ከመስራት ባለፈ በነጻነት የሚፈጠር የእያንዳንዱ ዜጋ መልካም አስተሳሰብ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነት ያላገኙ በርካታ የለውጥና የብልጽግና ሀሳቦች አሉ:: እነዚህ ሀሳቦች የሚወጡት ደግሞ አፋኝ ሥርዓት ተወግዶ ህዝባዊ ሥርዓት ሲሰፍን ነው:: ህዝብ ከመንግሥት ጋር መንግሥትም ከህዝብ ጋ እጅና ጓንት ሆነው ለአንድ አላማ መስራት ሲችሉ ነው:: ህዝብ ያልተረዳው መንግሥት፣ መንግሥት ያልተረዳው ህዝብ ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም::
እዛም እዚህም እድል ቢያገኙ የሚሰሩ እጆች ብዙ ናቸው:: የሚናገሩ አንደበቶች አሉ፣ ሀሳብ አፍላቂ ጭንቅላቶች አሉ:: ነጻነት በመስጠት ወደ ህዝብና መንግሥት እንዲደርሱ ማድረግ መልካም ነው:: እንዲህ አይነት ህዝብና መንግሥት በጋራ የተጋመዱበት ስርዓት ያስፈልገናል:: ነጻ አእምሮ የማይደርስበት የማህበረሰብ ክፍል የለም::
የአሁኑ የአውሮፓና የእስያ ስልጣኔ ለግለሰቦቻቸው በሰጡት አእምሮአዊ ነጻነት የመጣ ነው:: “ትናገርና ዋ“ ተብሎ ገደብ በተበጀለት ማህበረሰብ ውስጥ የሚመጣ ለውጥ የለም:: ለውጥ ማሰብ ነው…ለውጥ የብዙ አስተሳሰቦች ፍጭት ነው:: የተለያዩ ሀሳቦች እንዲወጡ፣ እንዲፈጠሩ የግለሰቦች የነጻነት መብት ወሳኝነት አለው እላለው:: መማራችሁ መስራታችሁ መነሳት መውደቃቸው አላማው ነጻነት ነው:: ብዙዎቻችን ለምን እንደምንማር ለምን እንደምንሰራ ይሄን ሁሉ ውጣ ውረድ ለምን በበጎ እንደተቀበልን ስንጠየቅ የምንመልሰው መልስ አለን..እሱም ምንድነው የተሻለ ነገን ለመፍጠር ነው የሚል ነው::
ህይወት ያለነጻነት ምንም ናት:: በህይወት ውስጥ ሁሉ ቢኖረን ሁሉን ብንታደል ነጻነት ከሌለን ግን የህይወት ትርጉሙ፣ የመኖር ዋጋው ይጠፋናል:: በዓለም ዙሪያ ያሉ በስነልቦና አስተምህሮ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች ከርዕሶቻቸው አብዛኞቹ የአእምሮ ነጻነት የሚሉ ናቸው:: የአእምሮ ነጻነት የሌሎች ነጻነቶች መፈጠሪያ ስፍራ ነው:: የአእምሮ ነጻነት ሳይኖራችሁ የምታሳኩት ትልቅ ግብ የለም::
የአእምሮ ነጻነት ሳይኖራችሁ የምትፈጥሩት ብሩህ ነገ የለም:: ሁሉም ነገራችን ባለን የመስራት፣ የማሰብ፣ የመለወጥ ነጻነት ውስጥ የተደበቀ ነው:: መጀመሪያ አስሮ ከያዛችሁ ትላንትና ውጡ ከዛ ቤተሰቦቻችሁ፣ ቀጥላችሁም በህይወታችሁ ላይ ዋጋ ከሌለው የጓደኞቻችሁ ተጽዕኖ ትላቀቃላችሁ:: ነጻነት ህይወትን ውብ ከምናደርግባቸው ትሩፋቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው:: ቅድም እንዳልኳችሁ በህይወታችሁ የቱንም ያክል ስኬታማና እድለኛ ብትሆኑ ለነጻ ፍቃዳችሁ የሚሆን አእምሮአዊ ነጻነት ከሌላችሁ ትርፋችሁ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም::
ብዙዎች መኖርን እንደ ትልቅ ነገር ይቆጥሩታል..አዎ እውነት ነው መኖር ትልቅ ነገር ነው ግን ካለነጻነት ከመኖር አለመኖር ይሻላል:: ህይወት የትም አለ…ገነት ውስጥም ሲኦል ውስጥም የሰው ልጅ አለ:: በድህነትና በባለጸጋነት የምንኖርም ሞልተናል:: ጎዳና ላይና ቤተመንግስት የምንኖርም አለን:: ዋናው መኖራችን ሳይሆን ለመኖር የሚያስፈልገን በረከት አለን እንዴ? የሚለው ነው:: ነጻነት የትም ቦታ ዋጋዋ ከፍ ያለ ነው:: ዛሬ ላይ በታሪክ፣ በባህል በሁሉ ነገራችን ከዓለም ቀድመን የምንኖረው እኮ አባቶቻችን በሰጡን ነጻነት ነው:: ለብዙ የአፍሪካና የዓለም ሀገራት ምሳሌ ሆነን በኩራት የምንጠቀሰው እኮ መስዋዕትነት በተከፈለበት ሰውነት ነው::
የሰሞኑን የአባይ ድርድር ብናየው እንኳን ግብጽና ሱዳን ለአሸማጋይነት አውሮፓና አሜሪካንን ደጅ ሲጠኑ ነጻነትን የምናውቀው እኛ ግን ‹የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን› በሚል አቋም ላይ ነን:: ይሄ ማለት እኮ ነጻነትን በሚያውቁና ነጻነትን በማያውቁ ሁለት ሀገራት መካከል የተፈጠረ የአስተሳሰብ ልዩነት እንደሆነ ማሰብ አይከብድም:: መቼም የትም ይሁን ነጻነታችሁን ለሌሎች አሳልፋችሁ አትስጡ::
ሀይላችሁ፣ ጥበባችሁ ያለው እሱ ውስጥ ነው:: ነጋችሁ፣ ለውጣችሁ ያለው እሱ ውስጥ ነው:: በትምህርት ቤት መምህራኖቻችሁ አሉታዊ ተጽዕኖን የሚያደርሱባችሁ ከሆነ በትምህርታችሁ ውጤታማ መሆን አትችሉም:: በሥራ ቦታ አለቆቻችሁ የአእምሮ ነጻነት ካልሰጧችሁ ለራሳችሁም ሆነ ለምትሰሩበት ድርጅት አመርቂ ሥራን መስራት አይቻላችሁም:: በትዳርሽ ውስጥ የባልሽ ተጽዕኖ ካለ ለልጆችሽ ጥሩ እናት ለባልሽም ጥሩ ሚስት መሆን አትችይም:: በትዳርህ ውስጥ የሚስትህ ተጽእኖ ካለ ለሚስትህ ጥሩ ባል ለልጆችህ ጥሩ አባት መሆን አይቻልህም:: በህይወት ውስጥ ለሚፈጠሩ ማናቸውም ሰውኛ ችግሮች አመክኒዮ ባላቸው የጋራ ሀሳቦች ለመፍታት መሞከር እንጂ በአንድ ሰው የበላይነት እንዲፈቱ ማድረግ ነጻነትን ለሌሎች አሳልፎ እንደመስጠት ነው የሚቆጠረው:: ታላቅነታችሁ ያለው በታላቅ ነጻነታችሁ ውስጥ ነው::
እስካሁን ካለ ሙሉ ነጻነት ስትጎድሉ ኖራችኋል:: ተምራችሁ እውቀታችሁን በበቂ ሁኔታ እንዳትጠቀሙ ሳንካ ተፈጥሮባችኋል:: መናገር እየቻላችሁ..ትላላቅ ጠቃሚ ሃሳቦችን ይዛችሁ እንዳትናገሩ ሆናችሁ የኖራችሁባቸው ጊዜአቶች ብዙ ናቸው:: እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን በሚል አጉል ማህበረሰባዊ አመለካከት ተጠፍንጋችሁ ኖራችኋል:: በአጉል እምነት በአጉል ባህል ሃይላችሁን ሳትጠቀሙበት በከንቱ ኖራችኋል:: ከእንግዲህ በራሳችሁ ላይ የራሳችሁን የነጻነት አብዮት ፍጠሩ:: ካለነጻነት የምትኖሩት ህይወት የምትመሩት ቢዝነስ፣ እውቀት ትዳራችሁ ዋጋ የለውም:: ታላቁ እናንተ ያለው በታላቁ ነጻነታችሁ ውስጥ ነው:: እስካሁን ድረስ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተደረጉ አለመግባባቶች ሁሉ መነሻቸውም መድረሻቸውም ነጻነት ነው:: እስካሁን ድረስ የተፈጠሩ ጦርነቶች፣ ውይይቶች ሁሉ ነጻነትን በመሻት የሆኑ ናቸው::
ከዚህ በኋላም የሚመጡ ማናቸውም ልዩነቶች በነጻነት ሰበብ የሚፈጠሩ ናቸው:: ነጻነት ዋጋ ባይኖረው ኖሮ ይሄን ያክል ዋጋ ባልተከፈለበት ነበር:: ከሁሉም ምርጡ ነጻነት ግን በመነጋገር የሚፈጠረው ነው እላለሁ:: በመነጋገር ውስጥ መስማማት አለ ::በጦርነት ውስጥ ግን መስማማት ሳይሆን የአንድ ወገን የበላይነት ነው የሚንጸባረቀው:: በጥልና ክርክር የመጣ ነጻነት ዋስትና የለውም:: በጦርና በአፈሙዝ የመጣ ነጻነት እድሜ የለውም::
እውነተኛ ነጻነት በመነጋገር የሚገኝ የብስለት ውጤት ነው:: እናተም ብትሆኑ ነጻነታችሁን ከጥልና ክርክር ውጪ በሆነ መንገድ ለማግኘት ሞክሩ:: ለታላቅ ክብር ሰው ሆነናል..በማሰብ እንድንኖር ተፈጥረናል ከሁሉ ትልቁ እውነታችን ይሄ ነው:: ካለማሰብ የምንኖረው ህይወት ከጉዳት ባለፈ ይዞልን የሚመጣው አንዳች በረከት የለም:: በእያንዳንዳችን ህይወት ላይ ጥቁር አሻራን ትተው ያለፉ መጥፎ አጋጣዎች ሁሉ አንድ ወቅት ላይ ባለማሰብ የሆኑ ናቸው:: ማሰብ በህይወት የመኖራችን አንዱና ዋነኛው ማረጋገጫ ነው:: በነገራችን ላይ ብዙ ፈላስፎች ማሰበን ከመኖር ጋር ያገናኙታል:: የሰው ልጅ ኖረ የሚባለው ማሰብ ሲጀምር ሲሆን ሞተ የሚባለው ደግሞ ማሰብ ሲያቆም ነው ይላሉ::
በህይወት እየኖረ መልካም ነገር የማያስብ ሰው እንደሞተ ነው የሚቆጠረው ማለት ነው:: ይሄ ማለት በህይወት እያለ ለራስም ሆነ ለሌሎች ጥሩ ነገር የማያስብ ሰው በህይወት ቢኖርም እንደሞተ ነው የሚቆጠረው ማለት ነው:: ከእንግዲህ ባለው ህይወታችሁ ጥሩ ነገር በማሰብ መኖር እንድትጀምሩ አደራ እላችኋለው:: ትልቁ ሞት የሚመጣው በህይወት ውስጥ ቀን በቀን በምንሞታቸው ትንንሽ ሞቶች በኋላ ነው ::ያ ማለት በተስፋ መቁረጥ፣ ባለማሰብ፣ ለራስ ክብርና ዋጋ ባለመስጠት በእነዚህ ሁሉ ከሞትን በኋላ ነው ለትልቁ ሞት እጅ የምንሰጠው ማለት ነው::
በማሰብ ሞታችሁን እንድትገሉት አደራ እላችኋለው:: ማሰብ በህይወት የመኖራችን ቀዳሚው ማሳያ ነው:: ማሰብ ሰውነትን ከእንስሳነት የሚለየው አንዱና ትልቁ መስፈርት ነው:: ማሰብ ስንል የሚጠቅመንንም የማይጠቅመንንም ማሰብ ማለት አይደለም:: ማሰብ ማለት መምረጥ ነው:: ወደ ፊት ሊያስኬደን የሚችልን እጅግ ዋጋ የለውን ነገር መርጦ ማሰብ ማለት ነው:: ሀገርና ወገን የሚጠቀሙበትን መልካም ሀሳብ ማፍለቅ ማለት ነው:: እውነተኛ ነጻነት በእውነተኛ ማሰብ ውስጥ የተደበቀች ናት:: አንዳንዶች ነጻነታቸውን ግሮሰሪ ቤት ይፈልጉታል:: ጫት ቤትና ሺሻ ቤት ነጻነታቸውን የሚፈልጉም ሞልተዋል:: ከትዳራቸው ሸሽተው ሴት ጉያ ውስጥ ነጻነታቸውን የሚፈልጉም ብዙዎች ናቸው:: በእነዚህ ነገሮች ውስጥ ነጻነት የለም::
ከትላንት እስከዛሬ እነዚህ ነገሮች ህልም አጨናጋፊዎች እንጂ ህልም ማፍሪያዎች ሲሆኑ አላየሁም:: ነጻነት ማሰብ ነው…ነጻነት ከማሰብ የሚጀምር ነገር ነው:: በእነዚህ ነገሮች ውስጥ ደግሞ ማሰብ የለም:: እስኪ እናስብ..ማሰብ የሚችል አንድ ሰው እንዴት አድርጎ ራሱን ፍለጋ ግሮሰሪ ቤት ይሄዳል? እስኪ አስቡት ማሰብ የሚችል አንድ ሰው ነጻነትን ፍለጋ ሺሻና ጫት ምን ሊያደርግ ይሄዳል? እስኪ አስቡት ማሰብ የሚችል አንድ ወንድ ከሚስቱ ሸሽቶ እንዴት ሌላ ሴት ጋ ይሄዳል? በእነዚህ ውስጥ ነጻነት የለም:: ካለም የሞት ነጻነት እንጂ የልዕልና ነጻነት አይደለም:: በእነዚህ ውስጥ ደስታ የለም:: ካለም ሴይጣናዊ ደስታ እንጂ አምላካዊ ደስታ የለም:: እነዚህ የብዙ ሞቶች የብዙ ጉስቁልናዎች መገኛ ናቸው:: እነሱ ማሰብ ያቆሙ ጭንቅላቶች የሚሰባሰቡባቸው የገሀነም ደጆች ናቸው:: ከትንሹ የህይወት ሞት ወጥተው ወደ ትልቁ የፍጻሜ ሞት የሚያደርጉት ግስጋሴ ነው:: ወንድም ሆናችሁ ሴቶች ከህይወታችሁ ላይ አንዲት ትንሽዬ ቅንጣት ጊዜ እንኳን ብትሆን በሌሎች ተጽዕኖ ውስጥ እንዲውል አትፍቀዱ::
በየትኛውም የህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ በእናንተ ህይወት ውስጥ የሌሎች ተጽዕኖ ካለ ህይወትን እንዳልኖራችሁት ቁጠሩት:: እናተም ከሌሎች ህይወት ላይ አለቅነትን አንሱ:: በህይወት ውስጥ ለሌሎች የምትሰጡት ከሌሎች የምትቀበሉትም ብዙ ነጻነት ይኑራችሁ:: ከልመናና ከመጠበቅ ወጥታችሁ የራሳችሁን ውብ ዓለም ገንቡ:: ብዙዎች ነጻነታችንን የምናጣው ሌሎች በእኛ ህይወት ላይ እንዲያዙ እድል ስንሰጥ እና የሌሎች ጥገኛ ስንሆን ነው::
ነጻነት የህይወት ጌጥ ናት..የነፍስ ሁሉ አሸክታብ:: የክረምት ጣይ….የበጋ ጥላ…የሰው ልጅ ሁሉ ጥያቄ እንዲህም:: ካለ እሷ መድመቅ አትችሉም..ካለእሷ ሁሌም ደብዛዛ ናችሁ:: መኖራችሁ፣ መፈጠራችሁ፣ ህይወትና ለህይወት የሚያስፈልጓችሁ ነገሮች ሁሉ በእሷ ውስጥ ነው ያለው:: ሁሉም ነጻነት ደግሞ መልካም አይደለም:: ህይወት አስተውለን በተራመድነው ልክ የምትሰምር ናት::
ነጻነት አለን ብለን እንደፈለግን የምንሆንና ያልተገባ ነገር የምናደርግ ከሆነ አጥፊያችን ነው የሚሆነው:: አሁን ላይ ሀብትና ዝናቸውን ተጠቅመው ሀገርና ህዝብ እያገለገሉ ያሉ እንዳሉ ሁሉ ለሀገርና ህዝብ ነቀርሳ ሆነው የሚኖሩም አሉ:: ህዝብ በሰጣቸው ስልጣን ሀገር ከመጥቀም ባለፈ ባገኙት እድል ተጠቅመው መጥፎ ሥራን የሚሰሩም ሞልተዋል:: ከትላንት እስከዛሬ ባገኙት ነጻነት ሳያተርፉ የከሰሩ ብዙ አሉ:: ብዙዎች በርተው ጠፍተዋል:: ብዙዎች ደምቀው ደብዝዘዋል:: ኃላፊነትን በአግባቡ መጠቀም ህይወትን በአግባቡ ከመጠቀም ጋር አንድ ነው:: ነጻነት አለን ብለን ህይወታችንን፣ ትዳራችንን፣ ስራችንን መበደል የለብንም::
ነጻነት ትርፍ የሚኖረው ለበጎ ነገር ስንጠቀመው ብቻ ነው:: ብዙዎች ገንዘብና ነጻነት አለን በሚል አጉል አመለካከት ራሳቸውን ለሱስና ለአላስፈላጊ ነገር ሰለባ አድርገው ከሥረው የሚኖሩ ናቸው:: አዳምና ሄዋን እንኳን የገነትን በለስ የበሉት በተሰጣቸው ገደብ የለሽ ነጻነት ነው:: ወደዚህ ዓለም ስንመጣ በሚገሉንና በሚያኖሩን ሁለት ገደብ የለሽ ነጻነቶች ታጅበን ነው:: ነጻነት ያኖረናልም ያጠፋናልም:: አዳምና ሄዋን ህልም በሚመስል ደስታ ገነት ውስጥ ነበሩ:: በእልፍ ነጻነታቸው ምክንያት በሰሩት ስህተት ግን ለአለሙ ሁሉ ሞትን አስከትለዋል:: ነጻነት በራስ ላይ ገነትንም ሲኦልንም መፍጠሪያ ስፍራ ነው::
አስተውሎ የሚራመድ ብቻ ነው የነጻነትን ጣፋጭ ፍሬ የሚበላው:: ሁሌ ባይሆንም አንዳንድ ጊዜ የሚቆጡንና የሚቆጣጠሩን ሰዎች መኖራቸው ዋጋ አለው ብዬ አምናለው:: በሌሎች ቁጥጥር ፍሬ ያፈራን አለንና:: እንደዚሁም ደግሞ ለህይወታችን ዋጋ ያላቸው ማህበራዊ ክልከላዎችና ገደቦች ስላሉ ለእነሱም ክብር እንስጥ እያልኩ አበቃሁ:: ቸር ሰንብቱ::
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2013 ዓ.ም