ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዓለም ህዝብ ለመመገብ ሀገራት የመስኖ እርሻ የመፍትሄው አካል አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። መኖን በመጠቀም ሳይታረሱ የቆዩ መሬቶችን ማልማት እና መስኖን በመጠቀም በፊት በዓመት አንዴ ሲታረሱ የነበሩ መሬቶችንም በዓመት ሁለቴና ሶስቴ በማልማት ምርትና ምርታማነታቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ። ከዚያ አለፍ ሲልም ለዜጎቻቸው ሥራ እድል እየፈጠሩበት ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ካላት የወንዞች ሀብትና ምቹ መሬት አንጻር መስኖን በሚገባው ልክ እየተጠቀመች ነው ማለት አያስደፍርም።ሆኖም አሁን የመስኖ ልማት ሥራን ለማስፋፋት ጥረት እያደረገች ትገኛለች። በተለይም ካለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ወዲህ የመስኖ ግድቦች ግንባታ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። የመስኖ ልማቱም አንዳንዱ በፌዴራል ሌሎች ደግሞ በክልሎች አማካይነት የሚገነቡ ናቸው። የመስኖ ልማት ሥራዎች አንዳንዶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ባይጠናቀቁ እንኳ የተወሰኑ ተጨማሪ ዓመታትን ፈጅተው ወደ ሥራ መግባት ሲችሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አሁንም ሊጠናቀቁ አልቻሉም።
በፌዴራል መንግስት እየተገነቡ ካሉና ከዘገዩ ፕሮጀክቶች መካከል አርጆ ዴዴሳና መገጭ ግድብ ግንባታ፣ ርብ የመስኖ መሬት ዝግጅት፣ ዘሪማ ሜይ ዴይ ግድብ ግንባታና የጊዳቦ የውሃ ቦይ እና የማህበራዊ ተቋማት ግድብ ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው።እነዚህ ፕሮጀክቶች እያንዳንዳቸው ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞላቸው ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም ፕሮጀክቶቹ ግን ከአምስት እስከ 10 ዓመት ፈጅተዋል። ከለውጡ በፊት በነበረው ሁኔታ በወቅቱ ለማጠናቀቅ ጥረት ቢደረግም ማጠናቀቅ ያልተቻሉ ናቸው። እነዚህ ፕሮጀክቶች አብዛኞቹ በሶስት ዓመት አለፍ ሲልም በአምስት ዓመት ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞላቸው ቢሆንም ፕሮጀክቶቹ ሳይጠናቀቁ እስከ 10 ዓመታት ለሚዘልቅ ጊዜ ተጓተዋል።
የመስኖ ልማት ኮሚሽን የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደሚሉት አምስቱም የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ከ2003 እስከ 2008 ባሉት ዓመታት የተጀመሩ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ግን በመገባደድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። አርጆ ዴዴሳ የዋናው ግድብ ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የትርፍ ውሃ ማስወጫ እና የኮርቻ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል በአጠቃላይ ግድቡ በአማካይ 82 በመቶ ላይ ደርሷል ። መገጭ 70 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም ርብ 79 በመቶ ላይ ይገኛል።
ጊዳቦ ሁለት ሎት ያለው ሲሆን አንደኛው 99 ነጥብ 5 በመቶ ፤ ሁለተኛው ሎት ደግሞ 49 ነጥብ 5 በመቶ ነው። ዘሪማ ሜይ ዴይ ግድብ ግንባታ በትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የግንባታ ሥራው እስከቆመበት እስከ ጥር ወር ድረስ 93 በመቶ ደርሷል።ከለውጡ በፊት በነበረው ጊዜ ፕሮጀክቶቹ የፋይናንስ እጥረት አንዱና ዋነኛው ችግር ነበር። ከለውጡ በኋላ ተግዳሮቶቹን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል። የአማካሪዎችና የኮንትራክተሮች አቅም ውስንነት፣ የወሰን ማስከበር ፣ የሲሚንቶ እጥረት፣ ፕሮጀክት አንድ ኮንትራክተር ብቻ እንዲይዝ መደረጉ እና የሀገሪቱ አለመረጋጋት ተጠቃሽ ናቸው።
ችግሮቹን ለመቅረፍ ኮሚሽኑ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከክልል መንግሥታት እና ከሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ያብራሩት አቶ ብዙነህ፤ ከኮንትራክተሮቹና ከአማካሪዎቹ ጋራ ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገው አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። በሥራው ላይ ያሉ ኮንትራክተሮች የሥራቸውን የተወሰነ ክፍል ለንዑስ ተቋራጮች እንዲያስተላልፉ አቅጣጫ መቀመጡን አብራርተዋል።
በዚሁ መሰረት አንዳንድ የተጓተቱ ግድቦች ግንባታ ላይ እስከ ስድስት የሚደርሱ ንዑስ ኮንትራክተሮች ገብተዋል። የአቅም ማነስ ችግር የባሰባቸውን ፕሮጀክቶች ደግሞ ሥራ ተቋራጮችን የማሰናበት እርምጃ ተወስዷል። ህጋዊ ሂደትን ተከትሎ አዳዲስ ኮንትራክተሮች እንዲገቡ ተደርጓል። ከዚህ ባሻገርም የሥራ ተቋራጮች በየጊዜው አቅማቸውን እያሳደጉ መስራት እንዳለባቸው አቅጣጫ ተሰጥቷል።
ፕሮጀክቶቹን ያጓተተው ሌላኛው ምክንያት የወሰን ማስከበር ሲሆን ይህንንም በክልልና ከዛ በታች ባሉ የመዋቅር አካላት ጋር በጋራ በመወያየት ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ነው። ሲሚንቶች የዘርፉ ሌላኛው ችግር ሆኖ መቀጠሉን ያብራሩት አቶ ብዙነህ፤ ይህንንም ለመፍታት ኮሚሽኑ እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኮንትራክተሮቹ በቀጥታ ከፋብሪካዎች መግዛት እንዲችሉ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። ይህም የተወሰነ ችግር ቢፈታም በሚፈለገው ልክ ግን አለመሆኑን ይናገራሉ።
ኮሚሽኑ እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመቀናጀት ዘርፉን እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በተሰራው ሥራ የመገጭ ግድብና የጊዳቦ ውሃ ቦይና የመሰረተ ልማት ሥራዎች በተያዘው ዓመት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃሉ። አርጆ ዴዴሳ እና ርብ በ2014 ዓመት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው። የዘሪማ ሜይ ዴይ ግድብ ቀሪ ሥራዎች ለማጠናቀቅ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ሥራ የሚጀመርበት ሁኔታ ላይ ውይይት ይደረጋል። በዚሁ መሰረት በሚሰጠው አቅጣጫ ኮንትራክተርና አማካሪ ጋር በመነጋገር ለማስቀጠል እየተሰራ ነው።
ፕሮጀክቶቹ መጓተት ያስከተለውን አሉታዊ ኢኮኖሚያዊ ጫና ዙሪያ እስካሁን የተሰሩ ጥናቶች ባይኖሩም ግድቦቹ ተጠናቀው ወደ ሥራ ባለመግባታቸው ተጨማሪ ምርት ወደ ገበያ በማስገባት ገበያውን ማረጋጋት ካለመቻሉም ባሻገር መስኖውን በመጠቀም መሬታቸውን ሊያለሙ የተዘጋጁ አርሶ አደሮች እና የፋብሪካዎች ላይ አሉታዊ ጫና አሳድራል። ሀገሪቷ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ማግኘት ያለባትን ምንዛሪ እንድታገኝ አድርጓል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013