አዲስ አበባ ከተማ ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡትንም እንግዶች ተቀብላ ማስተናገድ የየዕለት ተግባሯ ነው። በአሁኑ ጊዜ ለከተማዋ ችግር የሆነባት አልፎ ሂያጁ ሳይሆን በከተማዋ ገብቶ ሰምጦ የሚቀረው ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ፈልሰው ኑሮአቸውን በከተማዋ ላደረጉ ዜጎች መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት አዳጋች እየሆነበት ይገኛል።
ወደመዲናዋ የሚፈልሱ ዜጎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ተለውጠው ያሰቡት ደረጃ ላይ ሲደርሱ እምብዛም በተግባር አይታይም። ምናልባት ለዕለት የሚሆናቸውን የምግብ ፍላጎት አግኝተው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እነርሱም መጠለያ ሳያገኙ በጎዳና ላይ ብርድና ፀሐይ ተፈራርቆባቸው ለከፋ የጤናና ለተለያየ ችግር ተዳርገው፣ የከተማ አስተዳደሩም ከነዋሪው በሚቀርብለት የተለያየ የሥጋት ጥያቄ ውስጥ መገኘቱ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል።
ሰዎች ሊሟሉላቸው ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል መጠለያ ወሳኝ ነው። አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ እንኳንም ለከተማዋ አዲስ ለሆኑ ነዋሪዎች ቀርቶ ተወልደው ላደጉባት ረጅም ዘመን ለኖሩባት ነዋሪዎችዋም መጠለያ ለማዳረስ ፈተና ሆኖባታል። ሌላው ቀርቶ መንግሥት እያለማና ለነዋሪዎች እየሰጠ ያለውን የጋራ መኖሪያ ቤት በዕጣ ለማግኘት በ1997 ዓ.ም ተመዝግበው እስካሁን የቤት ባለቤት ያልሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች በተስፋ በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ። በየጊዜው ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው የከተማዋ ነዋሪ፣ የቤት ልማቱና የመሬት አቅርቦቱ አለመመጣጠን፣ አዳዲስና ችግር ፈቺ የሆኑና ጠንካራ አሰራሮች መዘርጋት ባለመቻሉ ክፍተቱ እንደተፈጠረ አንዳንዶች ይገልጻሉ።
የመፍትሄ አቅጣጫ አለመዘርጋቱ ደግሞ ለህገወጥ ግንባታ መሥፋፋት መንገድ ከፍቷል። የከተማ አስተዳደሩ ህገወጥ ግንባታዎችን ለመከላከል የተገነቡትን በማፍረስ ጭምር እርምጃ እየወሰደ ቢንቀሳቀስም በዘላቂነት ማስቀረት ግን አልቻለም። በከተማዋ ዳርቻዎችና የማስፋፊያ ቦታዎች ህገወጥ ግንባታዎች እየተስፋፋ ይገኛል። በተለምዶ የጨረቃ ቤቶች የሚባለው አይነት። የዚህ ችግርም በሁለት መንገድ ይገለጻል።
አንዱ ዜጎች ደፍረው የህገወጥ ግንባታ ውስጥ ሲገቡ ምን ያህል በመኖሪያ ቤት እየተፈተኑ እንደሆነ ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ በከተማዋ ለግንባታ ምቹ ሁኔታ አለመፈጠርና ህገወጥነትን ህጋዊ አድርጎ የማየት ሁኔታም ይስተዋላል። ይሁንና ዜጎች በየትኛውም መንገድ መጠለያ ማግኘት ካልቻሉ የመጨረሻ የሆነውን አማራጭ ህገ ወጥነትን ተጠቅመው መጠለያ ሲሰሩ ይስተዋላሉ።
ህገወጥ ግንባታ በከተማ አስተዳደሩና ግንባታውን ባካሄደው አካል መካከል ብዙ ውዝግቦችን በማስነሳት፣ ህገወጥነትን ለመከላከል በተወሰደ እርምጃ የሰው ህይወት እስከመጥፋትና ንብረት እስከ መውደም፣ ለከተማዋ ልማትም እንቅፋት ሲፈጥር በተለያየ ጊዜ አጋጥሟል። በዚህም ማህበራዊ ቀውስ ተፈጥሯል። ኢኮኖሚያዊ ጉዳትም ደርሷል።
ምንም እንኳን ህገወጥነቱ በመኖሪያቤት እጥረት ምክንያት እንደሆነ ቢታመንም በከተማዋ የጨረቃ ቤት እየተባለ እየተስተዋለ ያለው የመሬት ወረራ ጉዳይስ እንዴት ይታያል? መፍትሄው ምን ይሆን፤ እንዲህ ያለውን ህገ ወጥነት አስቀድሞ መከላከል አይቻልም ወይ፤ ሰዎች ህግን ተላልፈው የመሬት ወረራ ሲፈጽሙስ የሚመለከተው የመንግስት አካል ሥራው ምን ነበር ስንል ላነሳነው ጥያቄና አጠቃላይ በከተማዋ የሚፈጸሙ የመሬት ወረራዎችን አስመልክቶ ዜጎች ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ እንዲጠቀሙና የመንግስት ሀላፊዎችም ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ፣ በቀጣይ መሰል ችግሮችን መቅረፍ እንዲቻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አማካሪ አቶ ሀሊድ ነስረዲን ምላሽ ሰጥተዋል።
እንደ አቶ ሀሊድ ገለጻ የመሬት ወረራ መፍትሄ ሳያገኝ ለረጅም ጊዜ የቆየ ጉዳይ ነው። ሀገሪቱ ውስጥ ለውጥ ከመጣ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የከተማ አስተዳደሩ ከሚያከናውናቸው የተለያዩ ተግባራት የመሬት ወረራን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን፣ ከነዋሪው የሚደርሱትን ጥቆማዎች መሠረት በማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህ መልኩ የከተማ አስተዳደሩ በህገወጥ ተይዘው ታጥረው የተቀመጡትንና ያለሥራ ክፍት የነበሩትን ወደ መሬት ባንክ በማስገባትና ህጋዊነት ላለው አካል በማስተላለፍ ለልማት አገልግሎት እንዲውሉ አድርጓል።
‹‹ የህገ ወጥ የመሬት ወረራ መነሻ ምክንያት የመኖሪያ ቤት እጥረት የፈጠረው ችግር ነው። በከተሞች ዳርቻዎች ላይ በህገወጥ መንገድ የሚገነቡ ቤቶችም ለዚህ ማሳያዎች ናቸው። ነገር ግን እስካሁን ካጋጠሙት የመሬት ወረራዎች መረዳት የቻልነው የመሬት ወረራ የሚያካሂደው መኖሪያ ቤት የተቸገረው ሰው ብቻ ሳይሆን ባለሀብቱ ጭምር ነበር። ስለዚህ በከተማዋ የሚስተዋሉት የመሬት ወረራዎች በከተማዋ ካለው የመኖሪያ ቤት እጥረት የተነሳ ነው ተብሎ ከተወሰደ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም የጥናት ግኝቱም ይህን አያሳይም። ይሁንና የመኖሪያ ቤት እጥረት አንድ ምክንያት ነው›› ሲሉ አቶ ሀሊድ አስረድተዋል።
እንደ አቶ ሀሊድ ገለጻ፤ ከተማ መሬት ላይ የተለያዩ ፍላጎቶች የሚስተዋሉበት እንደመሆኑ ይህንንም መልክ ለማስያዝ የከተማ አስተዳደሩ በቢሮ ደረጃ የጀመራቸው ሥራዎች አሉ። ከዚህ በተጨማሪም ባለሙያዎችን በመፈተሽ ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተያያዥ የስነምግባር ግድፈት ያለባቸው 422 ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል። ከሁሉም በላይ ከተማውን በዘላቂነት ሊያሻግር የሚችለውና በፕላን የምትመራ ከተማ እንድትሆን ከማድረግ አኳያ ህገ ወጥነትን የመከላከል ሥራ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ማህበረሰብ ሀላፊነት እንደሆነ መረዳት ተገቢ ነው።
ባለፉት 10 እና 20 ዓመታት የከተማ መሬት ይመራበት የነበረው መንገድ በአንድ ጊዜ መንደር የመመስረት፣ በተለያየ መልኩ የማስፋፋትና በነበረ ይዞታ ላይ ያለፈቃድ ህገ ወጥ የሆኑ ግንባታዎችን ማከናወን ነበር። በዚህ ወቅት የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ በሚል ይሰጥ የነበረው መፍትሔ መልሶ ህጋዊ ማድረግ ነበር። ይህ እርምጃም ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ ጎኑ ያመዘነ በመሆኑ ትልቅ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።
በመሆኑም በአሁን ወቅት በምሽት ከመንግስት የሥራ ሰዓት ውጭ ህገ ወጥ ግንባታን በማከናወን፤ እንዲሁም ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታንና አለመረጋጋቷን ግምት ውስጥ በማስገባት ታስቦ የሚፈጸም የመሬት ወረራን በመመሪያ ሽፋን ተሰጥቶት በዘላቂነት መፍታት አይቻልም። በዚህ ረገድ ባለፉት ጊዜያት ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ህጋዊ ማድረግ ህገወጥነትን ለማስፋፋት አንዱ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። በየጊዜው በወረራ የሚያዙ ቦታዎችን መንግስት መመሪያ እያወጣ ህጋዊ እንዲሆኑ ወደ ማድረግ መሄዱ በማህበረሰቡ ያልተገባ እሳቤ እንዲያድግ መነሻ ሆኗል።
እንዲህ አይነት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በቀጣይነት ህግን የማስከበር፣ መመሪያዎችን ተግባራዊ የማድረግ፣ ህገ ወጥነትን ገና ከጅምሩ በመከላከል ማንኛውም ያገባኛል ከሚል ማህበረሰብ ጋር በጋራ የሚደረግ ትግልን ይጠይቃል። ያ ካልሆነ ግን ለጊዜው ብለን የምንሰጠው መፍትሔ አዲስ አበባን የሚያክል ትልቅ ከተማ በፕላን እንዳትመራ ያደርጋታል። ከዚህ በተጨማሪም ጥናት የሚፈልግ ነገር እንዳለው የሚሰማቸው መሆኑን እና በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ እንደሚያየው ያላቸውን እምነት አቶ ሀሊድ አካፍለውናል።
የከተማ መሬትን የማስተዳደር ሀላፊነት ያለበት ከወረዳ እስከ ከተማ ያለው የመንግስት አካል ህገ ወጥ ግንባታ ሲገነባ፣ ከግንባታ ፈቃድ ውጭ የሚሰጡ ግንባታዎችን በመቆጣጠር ረገድም የግንባታ ተቋማትና የተለያዩ አመራሮችና ባለሙያዎችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው። ይሁንና ምን ያህል ውጤታማ ነው የሚለው ተጨማሪ ሥራን ይጠይቃል። ከዚህ ባሻገር በአስተሳሰብ ሌብነትን የሚጠየፍ አመራርና ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ የመጀመሪያ ስራ ሊሆን ይገባል። ነገር ግን ሰው ችግር ውስጥ ከገባ በኋላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ለሌላው ትምህርት ይሆናል እንጂ ዋናውን ችግር በመሰረታዊነት ይፈታል ተብሎ አይታሰብም። በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ በሁለቱም መንገድ ህገወጥነትን ለመከላከል እየሰራ ይገኛል።
በመሬት ተቋም ላለው ብልሹ አሰራር አንዱ ምክንያት ተብሎ የሚጠቀሰው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመሬት አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት አለመኖሩ ነው ያሉት አቶ ሀሊድ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍም ቢሮው 263 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ለዚህም ከአዲስ አበባ አይ ሲ ቲ ተቋም ጋር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ከሆኑና ቴክኖሎጂውን ከሚጠቀሙ ተቋማት ጋር በውል ስምምነት ተፈጽሞ ተቋሙን ለማዘመን የተጀመረ ሥራ አለ። ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ሲቀየር የማህበረሰቡና የከተማ አስተዳደሩ ችግር ይቃለላል ተብሎ ይታሰባል።
በገጠር ከተሞችም ይሁን በዋና ከተሞች እንዲሁም በየትኛውም አካባቢ የሚስተዋሉ የመሬት ሽሚያዎች በርካታ ምክንያቶች አላቸው። ከምክንቶቹ መካካል አንዱ የመኖሪያ ቤት እጥረት በከተሞች መኖሩ ነው። ይሁን እንጂ ከተማ ላይ የበርካታ ሰዎች ፍላጎት እንደመሆኑ ከተማዋ ላይ የተወረሩ ቦታዎች ሁሉ መኖሪያ ቤት አልተገነባባቸውም። የንግድ ስራ ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ፣ አፓርታማ የነበሩ፣ ድርጅቶች የነበሩባቸውና ባለቤት የሌላቸው ህንጻዎች ተገንብተው የተገኙ ቦታዎች አሉ። በተመሳሳይም መንደር ምስረታ በሚመስል መንገድ የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን ለመቅረፍና በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶችም አሉ።
ስለዚህ በሁለቱም መንገድ የተፈጠሩትን ህገ ወጥነት ሚዛናዊ ሆኖ ማየት የሚገባ መሆኑን አቶ ሀሊድ አንስተዋል። እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይም እንደ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የቤት አቅርቦት እጥረትን በመቅረፍ መኖሪያ ቤት ጥያቄ ለሆነባቸው ነዋሪዎች ምላሽ መስጠት የሚቻለው ከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው የቤት ልማት ፓኬጅ መሰረት ነው። ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ የሚመራ ከሆነ ግን ህገ ወጥነትን ማስፋፋት ይሆናል። ህገ ወጥነትን አይቶ በማለፍና ወሰን ባለማስከበር የነዋሪዎችን ጥያቄ መመለስ አይቻልም፤ ዘላቂ መፍትሔም አይመጣም።
ለዚህም መሬት አስተዳደሩ በከተማዋ ከሚሰሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በዋናነት በተለይም ለቤቶች ልማት መሬት የማዘጋጀት ሥራዎችን ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተጠናከረ መንገድ ቀጥሏል። ከልማት ሁሉ የቀደመውን በቤቶች ልማት ላይ የተሰራው ሥራም ውጤታማ ነው። ለአብነትም በማህበር ቤት መገንባት የሚችሉ ነዋሪዎችን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ሰፋፊ መሬት ተዘጋጅቶ ወደ ቤቶች አስተዳደር ኮርፖሬሽን የመሬት አቅርቦት እየተሰራ ይገኛል። የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላላቸውም በግል አልሚዎች ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ ነው። መንግስት በተለይም በሁለቱ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ በዚህ አግባብ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብና መስራት ያስፈልጋል። ነገር ግን ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ የመሬት አስተዳደር ስርዓትን ልቅ ማድረግ የነዋሪውን የቤት ልማት ጥያቄ አይመልስም።
ከተማ ውስጥ የሚደረግ የትኛውም ህገወጥ የመሬት ወረራ በተዘዋዋሪም ይሁን በቀጥታ እያንዳንዱን የማህበረሰብ ክፍል ይጎዳል። በመሆኑ የጋራ የሆነውና በቀላሉ ሊተካ የማይችለውን ውስን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። በተለይም ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ሲያደርጉ ከነበረው በተሻለ መሬት በህገወጥነት ሲወረር የመከላለከል፣ የማጋለጥና ለሚመለከታቸው አካላት አሳልፎ በመስጠት ተገቢውን ሚና ሊወጡ ይገባል። ህገወጥነት ለከተማዋ ዕድገት አንዱ ማነቆ እንደመሆኑም አመራሩና ባለሙያው ተቀናጅቶ ቢሰራ ለውጥ ይመጣል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013