በሀገራችን የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ንግድ ባንክ፣ ልማት ባንክ፣ ማይክሮ ፋይናንስ እና ኢንሹራንስ የመሳሰሉት ለማህበረሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። ከዚህም አንዱ ከማህበረሰቡ መጠነኛ ገንዘብ በመሰብሰብ በቁጠባ፣ ብድርና ኢንሹራንስ አገልግሎት ለኢንቨስትመንት አስተዋጽኦ ማድረግ ነው። ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ፣ የስራ ዕድል እንዲፈጠር እንዲሁም ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት እገዛ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ በሀገራችን የባንክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 35 በመቶ ብቻ መሆኑን የብሄራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል።
ፕሪሳይስ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል የተሰኘውና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሰራው የጥናት ቡድን የዝቅተኛው ማህበረሰብ የፋይናንስ ተቋማት አጠቃቀም እና የቢዝነስ ሪፖርት አቀራረብ በሚል ለጋዜጠኞች ባዘጋጀው ስልጠና ላይ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶችን ይፋ አድርጓል። በጥናቱም በሀገራችን የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መጠቀም ላይ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸውን ተመላክቷል። ወደ ፋይናንስ ተቋማት ሄዶ አገልግሎት ማግኘት፣ የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡትን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ላይ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸው ለማየት ተችሏል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ በሀገራችን 65 በመቶ ሰዎች የባንክ ተጠቃሚ አይደሉም ። ለዚህም ምክንያቱ ባንኮች ለሁሉም ተደራሽ አለመሆናቸው ነው። አብዛኛው ባንኮች የሚገኙት ከተሞች ላይ ነው። በተለይም አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የኤ ቲ ኤም አገልግሎቱም በተመሳሳይ በብዛት አገልግሎት የሚሰጠው እዚሁ ነው። ሌላው ደግሞ ሰዎች ለቴክኖሎጂ ያላቸው ርቀት ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች አለመሰራታቸው በተመሳሳይ በክፍተት ተነስቷል።
ባንኮች የሚሰጡት አገልግሎት እንደየባንኮቹ የተለያየ ነው። ለምሳሌ የንግድ ባንክ ከሚሰጠው የተቀማጭና የገንዘብ ዝውውር በተጨማሪ የአጭር ጊዜ የብድር አገልግሎት ይሰጣል። የልማት ባንክ ደግሞ ለትልልቅ ፕሮጀክቶች የሚውል ከፍተኛ መጠን ያለው እና ረጅም ጊዜ የሚቆይ የብድር አገልግሎት ነው የሚሰጠው። በተለይ ለመንግስታዊ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ነው።
ሌላው በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርጉት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ናቸው። እነዚህ ተቋማት ልክ እንደ ንግድ ባንክ ሁሉ ከማህበረሰቡ አነስተኛ ገንዘብ በመሰብሰብ የብድር አገልግሎት ይሰጣሉ። በተለይ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን ህብረተሰብ ዘንድ ደርሰው ገንዘብ በመቆጠብና የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ከሌሎች ባንኮች የተሻሉ መሆናቸው ተገልጿል። ማይክሮ ፋይናንሶች ከንግድ ባንክ የሚለዩት የውጭ ምንዛሬ የማያንቀሳቅሱ እና ከሌሎች ባንኮች ጭማሪ ያለው ወለድ የሚያስከፍሉ በመሆናቸው ነው።
አሁን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የአገልግሎት ክፍያቸውን (መብራት፣ ስልክ ፣ውሃ ፣ የትራፊክ ቅጣት) የመሳሰለውን በባንክ በኩል መክፈል ጀምረዋል። አልፎ አልፎም ቢሆንም ትልልቅ ሱፐር ማርኬቶች የካርድ ግብይት እያካሄዱ ናቸው። ይሁን እንጂ በሀገራችን የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽ ባለመሆን ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የግንዛቤ እጥረትና በሌሎችም ምክንያቶች በሚጠበቀው ልክ ተገልጋዮች እየተጠቀሙ አይደለም።
ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሰው አንዱ የአገልግሎት ክፍያ በባንክ በኩል መሆን እንዳለበት እና ገንዘብ በሰዎች እጅ እንዳይዘዋወር የሚከለክል አስገዳጅ ህግ ባለመኖሩ ነው። በዚህም የተነሳ በባንክ በኩል የአገልግሎት ክፍያ የሚፈጽሙ አካላት ጭምር አገልግሎቱን የሚጠቀሙት ወጥ በሆነ መልኩ አይደለም።
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እስከምን ያህል ገንዘብ ያበድራሉ? የወለድ ምጣኔውስ የሚለው ከጋዜጠሾች የተነሳ ጥያቄ ነበር። የባንክ ባለሙያው እንዳብራሩት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ይሄን ያክል ገንዘብ ማበደር ይችላሉ ተብሎ በግልጽ የተቀመጠ መመሪያ የለም። ነገር ግን የማበደር ምጣኔያቸው እንዳላቸው የገንዘብ አቅም ይወሰናል። ካፒታላቸው ከፍተኛ የሆነ ትላልቅ ማይክሮ የፋይናንስ ተቋማት ከባንኮች ባልተናነሰ መልኩ ከፍተኛ መጠን ያለው የብድር አገልግሎት ይሰጣሉ። ስለዚህ ምን ያህል ብድር መስጠት እንደሚችሉ የተቀመጠው በቁጥር ሳይሆን በመቶኛ ነው። ይሄውም ካላቸው ካፒታል ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ ማበደር ይችላሉ። በዚህ መሰረት ትላልቅ ማይክሮ ፋይናንሶች እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ሊያበድሩ ይችላሉ።
ወለድን በተመለከተ ማይክሮ ፋይናንሶች የሚሰጡት ወለድ ከባንኮች አንጻር ትልቅ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት የአስተዳደር ወጪያቸው ከሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ሰፊ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ አንድ ማይክሮ ፋይናንስ ከህዝብ በቁጠባ መቶ ሺህ ብር ሰብስቦ መቶ ሺህ ብሩን ለመቶ ሰዎች አንድ አንድ ሺህ ብር ቢሰጥ የአስተዳደር ወጪው በጉልበት፣ በጊዜ፣ በቁሳቁስ ከፍተኛ ነው። ለአንድ ሰው መቶ ሺህ ብር ከመስጠት ጋር ሲነጻጸር አገልግሎቱን ለመስጠት የሚወጣው ወጪ ሰፊ ልዩነት አለው ። በዚህ ምክንያት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የብድር ወለድ መጠን ከሌላው ባንክ ከፍ የሚል መሆኑን ማብራሪያ የሰጡት የባንክ ባለሙያ አስረድተዋል።
አልማዝ አያሌው
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2013