በምስራቅ ጎጃም በሞጣ ከተማ በኢንቨስትመንት መስክ የሚሳተፉ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በሚፈጠረው የስራ እድል ተጠቃሚ ለመሆን የሚጠባበቁ ወጣቶች በርካቶች ናቸው:: ይሁን እንጂ ኢንቨስት ለማደርግ የሚፈልጉ ባለሃብቶች በከተማ አስተዳደሩ የፈለጉትን የመሬት አቅርቦት ጥያቄ በቀላሉ ለማግኘት ችግር እንደገጠማቸው ይናገራሉ::
ይህንን ችግር የፈጠረውም ከዚህ በፊት በሞጣ ከተማ አስተዳደር ሥር ይተዳደሩ የነበሩ አራት የገጠር ቀበሌዎች በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ስር መተዳደራቸው መሆኑን ወጣቶች እና ባለሃብቶች ይናገራሉ:: ቀበሌዎቹ ወደ ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አስተዳደር መመለሳቸውም ከተማ አስተዳደሩ ያለውን የኢንቨስትመንት ተመራጭነት እየቀነሰው መሆኑንም አመላክተዋል::
በከተማዋ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ባለሃብቶች በፈለጉት ልክ ኢንቨስት ማድረግ ባለመቻላቸው ይፈጠርላቸው የነበረው የስራ እድል መስተጓጎሉን ወጣቶቹ ይናገራሉ:: ችግሩ ይቀረፍ ዘንድ ለሚመለከተው አካል አድርሱልን ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጠይቀዋል:: የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የስራ እድል ተጠቃሚ ለመሆን የሚጠባበቁትን ወጣቶች እና በከተማ አስተዳደሩ ለማልማት የሚፈልጉ ባለሃብቶችን ጥያቄ ይመለከተዋል ለሚለው ለሞጣ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ፅህፈት ቤት ሃላፊ ለሆኑት ለአቶ ፀሐዬ ወንድም በማቅረብ የሚከተለውን ምላሽ ይዞ መጥቷል::
የሞጣ የከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ፅህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ፀሐዬ ወንድም እንደገለጹት፣ አራቱ ቀበሌዎች ከሞጣ ከተማ አስተዳደር ወደ ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ መመለሳቸው ከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንትለማስፋፋት የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ ይገኛል::
ከተማ አስተዳደሩ እንደ ከተማ አስተዳደር ሲቋቋም በከተማው ስር በነበሩት አራት ቀበሌዎች እና አራት የገጠር ቀበሌዎች በአጠቃላይ ስምንት ቀበሌዎችን በማካተት ነበር ያሉት አቶ ፀሐዬ፤ ይህ አደረጃጃት ለስራ ፈላጊ ወጣቶች፣ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉም ባለሃብቶች እና በአጠቃላይ የከተማዋን ልማትን በማፋጠን ረገድ በጣም ምቹ እንደነበር አመላክተዋል:: የከተማ አስተዳደሩ ሲመሰረት አራቱን የከተማ ዙሪያ የገጠር ቀበሌዎች ማካተት አለበት በሚል የተጠናው ጥናት የከተማ አስተዳደሩን ሁለንተናዊ እድገቶች ለማፋጠን እጅግ በጣም ጥሩ እና ትክክል እንደነበር ጠቁመዋል::
በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ለተካተቱት የገጠር ቀበሌ አርሶ አደሮች ለግብርና ስራ የሚሆኑ የተለያዩ ግብዓቶች እንዲሁም ቴክኖሎጂ በወቅቱ ማድረስ አልተቻለም እና ቀበሌዎችን ከቀበሌዎች ለማገናኘት በከተማ አስተዳደር ስር ለሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች መንገድ አይሰራም መባሉን ተከትሎ በ2007 ዓ.ም በሞጣ ከተማ አስተዳደር ስር ይተዳዳሩ የነበሩት አራቱ የገጠር ቀበሌዎች ለሁለት እጁ እነሴ ወረዳ መሰጠቱን አቶ ፀሐዬ ገልጸዋል:: ይህም በመሆኑ ይላሉ አቶ ፀሐይ፣ አሁን ላይ የሞጣ ከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት በመሬት አቅርቦት ረገድ በጣም እየተቸገረ እንደሚገኘ አመላክተው፤ “ በአሁኑ ጊዜ የሞጣ ከተማ አንገቷን የተቆረጠች ከተማ ናት” ሲሉም ተናግረዋል::
እንደ አቶ ፀሐዬ ገለጻ ፤ በሞጣ ከተማ አስተዳደር ዙሪያውን ያሉ የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ስር የሚገኙ ቀበሌዎች ናቸው:: ከተማ አስተዳደሩ ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ቢፈለግ ከሁለት እጁ አመራሮች ጋር ተግባብቶ ካሳ ግምት አሰርቶ የሚመጣውን የኢንቨስትመንት ፍላጎት ለማስተናገድ የመሬት አቅርቦትን ጥያቄ መመለስ ይጠበቅበታል:: ይህን ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ጥያቄ ለመመለስ የከተማ አስተዳደሩ ከሁለት እጁ አመራሮች ጋር ተግባብቶ ለኢንቨስትመንት ለሚፈለገው ቦታ ካሳ ግምት አሰርቶ የሚመጣውን የኢንቨስትመንት ጥያቄን ለማስተናገድ በጣም ብዙ ጊዜ እየወሰደ ነው:: በኢንቨስትመንት ኮሚቴ እና በከንቲባው ተገምግመው እና ጸድቀው መሬት ይሰጣቸው የተባሉ ብዙ ባለሃብቶች አሉ:: የከተማ አስተዳደሩ እነኝህ ባለሃብቶች መሬት እንዲሰጣቸው ለሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አስተዳደር የካሳ ግምት እንዲሰራላቸው ፕላን ተሰርቶ የተሰጠ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አስተዳደር ምንም ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም ::
ዘንድሮ የከተማ ግብርና ፅህፈት ቤቱ ከመሬት ካሳ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዲሰራ የስራ ሂደት ያቋቋመ ቢሆንም ከሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ጋር ርክክብ ባለመደረጉ እና እስካሁን ወደ ስራ ባለመግባቱ የባለሃብቱን ጥያቄ መመለስ አለመቻሉን አቶ ፀሐየ ገልጸዋል:: በዚህ የተነሳ አርሶ አደሮችም ካሳ ለመውሰድ ከሞጣ ከተማ አስተዳደር ወደ ሁለት እጁ እነሴ፤ ከሁለት እጁ እነሴም ወረዳ ደግሞ ወደ ሞጣ ከተማ በመመላለስ ለአልተፈለገ እንግልትና ወጪ መዳረጋቸውን አቶ ፀሐዬ ጠቁመዋል:: ለዚህም መንግስት በአፋጣኝ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባው አመልክተዋል::
የሞጣ ከተማ በአራቱም አቅጣጫዎች የመሰረተ ልማቶች እየተዘረጉባት ያለች ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የንግድ ኮሪደር እየሆነች መምጣቷን የሚናገሩት አቶ ፀሐዬ፤ አሁን ላይ ብዙ ባለሃብቶች ከተማዋ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ አይናቸውን እንደጣሉባት ይናገራሉ:: በዚያ ልክም ብዙ ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ እየመጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል ::
አራት ቀበሌዎች በከተማ አስተዳደሩ ስር ባለመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ ራሱን ችሎ አመራር እየሰጠ አይደለም:: የባለሃብቱ የኢንቨስትመንት የመሬት ጥያቄ በአግባቡ ምላሽመስጠት አልተቻለም:: ይህን ማለት ግን በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ምንም አይነት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየተደረገ አይደለም ማለት እንዳልሆነ አቶ አቶ ፀሐዬ ጠቁመዋል::
እንደ አቶ ፀሐዬ ገለጻ፤ ከዚህ ቀደም ከይገባኛል ነጻ የነበሩና በተለይ የከተማ አስተዳደሩ ሲያስተዳድር የነበረውን ወደ ሃያ አንድ ነጥብ ሶስት ሄክታር መሬት ለባለሃብቱ መስጠት በመቻሉ አሁን ላይ ወደ ስራ ገብተዋል:: አብዛኛዎቹ ደግሞ ግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ናቸው:: ወደ ስራ ያልገቡት ደግሞ ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው :: ነገር ግን ሞጣ ካላት የመሬት አቀማመጥ እና ለኢንቨስትመንት ካላት ምቹነት አንጻር ከዚህ የበለጠ የኢንቨስትመንት ጥቄዎች ሊስተናገድባት የምትችል ከተማ መሆኗን ጠቁመዋል::
ሌላው አራቱ የገጠር ቀበሌዎች ወደ ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አስተዳደር ስር ሲጠቃለሉ በተፈጠረው ችግር ምክንያት የከተማ አስተዳደሩ እና ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አስተዳደር ወሰን በትክክል ማወቅ አለመቻሉን የሚናገሩት አቶ ፀሐዬ፤ ይህም ከተማዋ በምታደርገው የኢንቨስትመንት እንቅስቀሴ ላይ ከባድ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ማድረሱን አመላክተዋል:: እነኝህን ችግሮች ለመቅረፍ የሞጣ ከተማ አስተዳደር በጣም በርካታ ስራዎችን በማከናወን ብዙ ርቀቶችን እንደተጓዙ የገለጹት አቶ ፀሐዬ፤ ወደፊትም አራቱ ቀበሌዎች ወደ ከተማ አስተዳደሩ እንዲመለሱ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል::
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2013