ከፍቅርና ከጥቂት ነፍሳዊ ሀቆች ቀጥሎ የዚህ አለም ምርጡ ቃል እችላለሁ ይመስለኛል። ደግሞም ነው በዚህ ጥርጥር የለኝም። እችላለው..እስኪ ቃሉን በሉት ደስ አይልም? በኔ ህይወት ውስጥ ካሉ ደማቅና አንጸባራቂ እውነቶች ውስጥ አንዱ ይሄ ቃል ነው። በኑሮዬ ውስጥ እንዲጠፋ የማልፈልገው፣ ሁሉም ቦታዬ ላይ በሙልዐት እንዳገኘው የምናፍቀው ቅዱስ ቃልም ነው።
እችላለሁ በጠንካራ ልቦች ውስጥ የበቀለ በቅሎም የጸደቀ፣ ጸድቆም መቶ ያፈራ ምርጥ ዘር ነው። የሰውነት የብዙ ህልሞች፣ የብዙ ሀሳቦች መጋዘን እንዲህም ነው። በመኖር ውስጥ ታላቅና አስፈላጊ ሆነን ለመቆም ያሰብንውን ያክል ውስጣችን የእችላለው መንፈስ ቢኖር አሁን ላይ አለምን ከለወጡ ከዋክብቶች ውስጥ አንደ አንዱ እንሆን ነበር እላለው። እችላለው ከምንምነት ወደ ተዐምር ፈጣሪነት የምንሸጋገርበት የሎጥ መንገድ ነው። ሰው የሆንበትን አላማ ለመፈጸም የሚያስችለን ቀዳሚው ሀይልም ነው።
ብታምኑም ባታምኑም የእኔና የእናተ አለም የተገነባው ትላንት ላይ እችላለው ብለው በተነሱ ጥቂት ግለሰቦች ነው። አለም እንኳን የአሁኑን ውብ ገጽታዋን የያዘችው እችላለው ብለው ባመኑ አምነውም ታላቅ ነገር በፈጠሩ ልበሙሉዎች ነው። በዘመናት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተከሰተው የህይወትና የኑሮ ልዩነት በማመንና ባለማመን መካከል የተፈጠረ ነው። አለማችን የሚገነባው ባሰብንው ባመነውና በይቻላል መንፈሳችን ልክ እንደሆነ የሚናገሩ በርካታ የስነልቦና ባለሙያዎች አሉ። አንድን ነገር ለመስራት ከመነሳታችን በፊት ያን ነገር የማድረግ ውስጣዊ ሀይልም መላበስ ይኖርብናል።
አብዛኞቹ ነገሮቻችን በአልችለውምና አይሳካልኝም በሚሉ አፍራሽ አመለካከቶች የሚጀመሩ ናቸው። በእንዲህ አይነት አመለካከቶች የተጀመሩ ማናቸውም ነገሮች መልካም ፍጻሜ አይኖራቸውም። ከሁሉ በፊት እችላለው የሚልን ጠንካራ መሰረትን በውስጣችን መገንባት ይኖርብናል። አንድን ነገር ስንጀምረው ከፍጻሜ እንደምናደርሰው በማመን ይሁን። በህይወታችን ውስጥ ተዐምር መከሰት የሚጀምረው ከፈጣሪ ቀጥሎ በራሳችን ያመንን ቀን ነው። በራሳችን ካላመንን ልንተማመንበት የሚያስችል ሌላ ምንም ሀይል አናገኝም።
ሁሌም እችላለው ብሉ..ምክንያቱም ከተሞከረ የማይቻል ነገር የለምና። እችላለው ማለት በታላቅ የለውጥ ሀይል ውስጥ ልብንና አእምሮን መጠቀም ነው። አሁን ላይ አብዛኞቻችን ጀማሪዎች ነን፣ ጀምረን መሀል ላይ የምናቆም እንጂ ከፍጻሜ የምንደርስ አይደለንም። ምርጥ ነገር ያለው ደግሞ መጨረሻ ላይ ነው። የልፋታችንን ውጤት ምርጡን ነገር ሳናይ ተሰላችተን መሀል ላይ እንቆማለን። ከዛም እኔ አልችልም ወደሚል አመለካከት እንሸጋገራለን ። በዚህ አመለካከታችንም ምንም ነገር እንዳንጀምርና እንዳናሳካ ሆነን እንኖራለን።
በነገራችን ላይ የምታስቡት፣ የምታልሙት ቢሳካልኝ የምትሉት ምርጥ ነገራችሁ ሁሉ በእችላለው ውስጥ የተቀመጠ ነው። እችላለው ብሎ የሚያምን ልብ በመሞከር የሚያምን ቢሳሳት እንኳን ልክ እስኪሆን ድረስ እስከመጨረሻው የሚሞክር ነው። የአንፖል ፈጣሪው አሜሪካዊው ኤድሰን አንፖል ለመስራት በተነሳበት ወቅት ዘጠኝ ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ጊዜ ተሳስቶ ነበር። ይሄ ጽናት ዝም ተብሎ አይገኝም። ይሄ ብርታት ይህ ቁርጠኝነት በማንም ልብ ውስጥ አይገኝም። ይሄ ማንነት ያለው እችላለው ብለው በተነሱ ልቦች ውስጥ ነው።
ከሁሉም የሚገርመው ከዚህ ሁሉ ሙከራ በኋላ ኤድሰን የተናገረው ነበር..አንፖልን ለመፍጠር በሞከርኩት ሙከራዬ ውስጥ ያባከንኩትም ሆነ የተሳሳትኩት አንድም ነገር የለም። በሙከራዬ ውስጥ አንፖል ሊሰሩ የማይችሉ ዘጠኝ ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ መንገዶችን አውቄአለው ነበር ያለው። በእችላለው ውስጥ የሚባክን ጊዜ የለም። ልክ የማይመስሉን ነገሮች በጥንቃቄ ካየናቸው ዋጋ ያላቸው ሆነው ነው የምናገኛቸው። ብዙ ሰዎች ኤድሰን ያን ሁሉ የተሳሳተ ሙከራ ሲያደርግ ጊዜውን እንዳባከነ ያስቡ ነበር። ለኤድሰን ግን የባከኑ ጊዜአቶች አልነበሩም።
በህይወት ውስጥ ምንም የማይችል ማንም የለም። እንዳንችል አድርገን ራሳችንን ካላበጀነው በስተቀር ሁሉን እንድንችል፣ ሁሉን እንድናደርግ ነው የተፈጠርነው። በተፈጥሮአችን ሀያላን ነን። ምንም ነገር ሞክረን እንዳይሳካልን ሀይላችንን የምንገለው ራሳችን ነን። በዙሪያችን እኛ ተመኝተንው ያጣንውን ሌሎች ሲያገኙ ስናይ በመሞከር ፈንታ እንቀናለን ወይም ደግሞ ሌላ አላስፈላጊ ስሞችን እንሰጣቸዋለን። የምንፈልገውን የሆነ ነገር የሆነ ሰው ጋ ስናዬው ያንን ነገር ለማግኘት ከመልፋትና ከመሞከር ይልቅ አይናችን ደም የሚለብስ ብዙዎች ነን።
አልችልም አይሳካልኝም ብሎ ማሰብ አእምሮ ምንም ነገር እንዳይችል አበላሽቶና አሰናክሎ ማስቀመጥ ማለት ነው። አልችልም ብሎ ማሰብ በሌሎች ስኬትና እድገት እየተደነቁ መቀመጥ ነው። በሌሎች ለውጥና መሻሻል እየቀኑና እየጎመጁ መኖር ነው። አይሳካልኝም ብሎ ማሰብ ለሀገርና ለወገን ሸክም ሆኖ ለመኖር ራስን ማዘጋጀት ነው። አልችልም ምንም ነገር ብሞክር አይሳካልኝም እስከዛሬም ብዙ ነገር ሞክሬ አልተሳካልኝም የሚሉ ልቦች የሀገርና የቤተሰብ ውለታ በል ናቸው። እነርሱ የራሳቸውን አለም አፍርሰው የሌሎችን አለም ለመገንባት መዶሻና ሚስማር የሚያቀብሉ ናቸው። እነርሱ በሌሎች ሰርግና መልስ ላይ አጨብጫቢዎች ናቸው።
ስልጣኔ የሚመጣው እችላለው ብሎ ከሚያስብ አእምሮ ውስጥ ነው። በአልችልም ውስጥ ምንም የለም። እኚህን ነፍሶች ፈጣሪ እንኳን አያውቃቸውም። ምክንያቱም ወደዚህ አለም ሰው ሆነን ስንመጣ ባዶ እጃችንን አልመጣንም መክሊት ተሰቶን በተሰጠን መክሊት እንድናተርፍና ሀገርና ወገን እንድንጠቅምበት ነው። የተሰጠንን እውቀትና ማስተዋል ለሀገርና ለህዝብ ማዋል ካልቻልን የመፈጠራችንን ምክንያት አናውቀውም ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሀገርን ድህነት ከሚያባብሱት ውስጥ አንዱና ቀዳሚው ነው ማለት ነው።
ሀገር የምትበለጽገው፣ የህዝቦች ችግር የሚፈታው፣ በውስጥም በውጭም ያሉ ሀገራዊ ጥያቄዎቻችን መልስ የሚያገኙት በእንችላለን ስሜት ሀይል በተሞሉ ዜጎች ነው። ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንኳን አሁን ላይ እየተገነባ ያለው እንችላለን ብለው በተነሱ ህዝቦች እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። ድሀ ልንሆን እንችላለን፣ ሌሎች አይችሉም ብለውን ሊሆን ይችላል፣ ብዙ ነገሮችን ሞክረን አልተሳኩልን ይሆናል። በአንድነት የቆምን ጊዜ ግን ለብዙዎች መደነቂያ መሆናችን የማይቀር ነው።
አሁን ላይ ሁላችሁም እንደምታውቁት የህዳሴ ግድባችንን ጨርሰን ልናስመርቅ ሁለት አመታትን ብቻ ነው የምንጠብቀው። ብዙዎች አይችሉም ቢጀምሩ እንኳን መሀል ላይ ያቆሙታል እያሉ ሲሳለቁብን ነበር ። እኛ ግን በተባበረ ክንድ ገንዘባችንን ብቻ ሳይሆን፣ እውቀታችንን ብቻ ሳይሆን፣ ጊዜአችንን ብቻ ሳይሆን ሁሉ ነገራችን ሰጥተን እንሆ ትንሳኤው ላይ ደርሰናል። ከእንግዲህም በተባበረና በእንችላለን መንፈስ ብዙ የህዳሴ ግድቦችን በመስራት ከምስራቅ አፍሪካ አልፈን በአፍሪካ ላይም ልዕለ ሀያል ሀገርና ህዝቦች ምንሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ጀግንነት ሀያልነት ብርቃችን አይደለም አብረን ቆመን ተዐምር ሰርተን አለም ያውቀናል። አብረን ተሰልፈን የማይቻል ችለን ታሪክ ሰርተናል።
በህይወታችሁ በኑሯችሁ ውስጥ ድንቅ ነገር እንዲከሰት ከፈለጋችሁ ደካማ መንፈሳችሁን ገላችሁ እችላለው በሉ። እርሱ በእያንዳንዳችን ውስጥ ተዐምር መፍጠሪያ ሀይል ነው። በሚቻልና በሚሞከር ነገር ላይ ራስን አልችልም ብሎ መግታት ራስን በራስ ከመግደል ጋር አንድ ነው። በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ዝነኛና ስኬታማ ሰዎችን ፕሮፋይል ብታጠኑ ሁሉም ማለት ይቻላል እችላሰለው ብለው በተነሱ ማግስት ስኬታማ የሆኑ ናቸው። በቅርባችን እንኳን ጀግናው አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረ ስላሴ በይቻላል መንፈስ በአለም አቀፍ ደረጃ በአትሌቲክሱ ዘርፍ የሰራውን ታላቅ ጀብድ ሁላችሁም የምታውቁት ነው። ሀይሌ በይቻላል ፍልስፍናው ዛሬም ድረስ ተዐምር በመስራት ላይ ነው። ይቻላልን እስካላቆመ ድረስ ተዐምር መስረቱን አያቆምም። ተዐምር መስራት የምናቆመው ይቻላልን ስናቆም ብቻ ነው።
የይቻላል መንፈስ ከምንምነት ወጥተን ወደ ላቀ ሰዋዊ እርከን የምንሸጋገርበት ድልድያችን ነው። የምንፈልገውን ለማግኘት መሮጥና መልፋት ብቻውን ዋጋ የለውም። ዋጋ ያለው ራሳችንን በማሸነፍ ሀሳብ ስንሞላ ነው። አንዳንድ ሰዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት በይቻላል ጥበብ ጥግ ድረስ የሚሮጡ ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ በአልችልም ስሜት የበይ ተመልካች ሆነው የጥግ ላይ የሚቀመጡ ናቸው። በከተማችን በመንደራችን ባጠቃላይ በዙሪያችን እንደእነዚህ አይነት ሰዎችን ማየት የተለመደ ነው። አንድ ነገር አልሳካ ሲለን መተው ሳይሆን እስኪሳካልን ድረስ መሞከር ነው።
ህይወት ለተረዷት ቀላል ቀመር ናት። ላልተረዷት ግን ተራራ ናት። ለምንም ነገር ይቻላል የሚሉ ሰዎች ተራራ አናት ላይ ያለን ህብስት ለማግኘት አሳንሰር ይሰራሉ። ደካሞች ግን ተራራው ሩቅ ነው..አይሞከርም..አደገኛ ነው ሲሉ በተስፋ መቁረጥ ሀይላቸውን ይዝላል። በአቅማችን ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን ታላቅ ነገር መፍጠር እየቻልን በተስፋ መቁረጥ የሌሎች ስኬት እያዩ ከነፈር እንደመምጠጥ ህመም የለም። ለመጀመር ጠንካራ ሀይል እንጂ ሌላ ምንም አያስፈልግም።
ሁሉንም ነገር ከምንምነት ጀምሩ። ገንዘብ እስኪኖራችሁ፣ ቦታ እስክታገኙ፣ አዲስ አመት እስኪመጣ አትጠብቁ ውስጣችሁን በይቻላል መንፈስ ሞልታችሁ ወደምትፈልጉት ሂዱ። ጎዳናችሁን ማንም መጥቶ እስኪጠርግላችሁ አትጠብቁ። ወጀቡ አጠገብ ቆማችሁ መሻገሪያ ድልድያችሁን ገንቡ እንጂ ሌሎች መጥተው እስኪያሻግሯችሁ አትጠብቁ። ለሌሎች የሚተርፍ ብርሀንን አብሩ እንጂ በሌሎች ብርሀን ብቻ ለመድመቅ አትሞክሩ። የእችላለው መንፈስ ውስጣችሁ ካለ ወደ ሌላ ሳትሄዱ፣ ወደ ሌላ ሳታዩ በተማራችሁበት የትምህርት መስክ ብቻ ውጤታማ መሆን ትችላላችሁ። ራሳችሁን ለለውጥና ልብልጽግና ካዘጋጃችሁ አሁን ካላችሁበት በመነሳት ወደምትፈልጉበት ከፍታ መምጠቅ ትችላላችሁ። ውስጣችሁ የእችላለው ሀይል ከሌለ ግን ምንም አይነት እውቀትና ጥበብ ቢኖራችሁ ለበጎ ነገር አትበረቱም።
ሀገራችሁን በብዙ የምትጠቅሙበት ምርጥ ጊዜ ላይ ናችሁ። ውስጣችሁ ሀቅና እውነት ካለ ለሀገራችሁ የምታስፈልጉበት ጊዜ ላይ ትገኛላችሁ። ሀገር መጥቀም በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይችላል። በይቻላል መንፈስ ራስን አድሶ ለስራና ለልማት መትጋት አንዱና ዋነኛው የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው። አሁን ካላችሁበት አደንዛዥ ሁኔታ ወታችሁ ለህዝብ ወደሚበጅ ማንነት ተመለሱ። በስራችሁ፣ በተግባራችሁ ባላችሁበት የስራ መስኩ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት የሚፈልገውን የባህሪ ለውጥ በማምጣት ለሀገርና ህዝብ ከሚቆረቆሩት ከምርጦቹ ጎን መሰለፍ ይቻላችኋል። ራሳችሁን ለመለወጥ በምትሮጡት ሩጫ፣ በምተጉት ትጋት ምንም ነገር አያስፈራችሁ።
የይቻላል መንፈስ እየወደቁ ማሸነፍ፣ እየሞከሩ መለወጥ ነው። ለውጥ ራስን ከመለወጥ አመለካከትን ከመግራት የሚጀምር ነው። በማመንታት ውስጥ ወርቃማ እድል፣ ስኬታማ ህይወት የለም። አልችልም ከሚሉት የምትለዩት ውስጣችሁ ባለው ታላቅ የማሸነፍ ሀይል ነው። ዛሬና ከዛሬ ቀጥሎ በሚኖራችሁ ህይወት ለራሳችሁም ሆነ ለሀገራችሁ የምትበጁ ጠቃሚ ዜጋ እንድትሆኑ ራሳችሁን በማሸነፍ ሀሳብ ሙሉት። መስራት እየቻላችሁ፣ መለወጥ እየቻላችሁ ማሰብና ማመን እየቻላችሁ ውስጣችሁ ባስቀመጣችሁት የአልችልም ምስል የአልጋ ቁራኛ ሆናችኋልና እንደ መጻጉ ለዘመናት ከኖራችሁበት ክፉ ደዌ ትፈወሱ ዘንድ በይቻላል መንፈስ ራሳችሁን ቃኙ። ከነእውቀታችሁ፣ ከነሀይላችሁ ወደ መቃብር ከመውረዳችሁ በፊት ሰው የሆናችሁበትን ትልቁን የይቻላል ጥበብ ውስጣችሁ ትከሉ። አበቃሁ። ቸር ሰንብቱ።
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2013