ዓለም አቀፉ የፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ ከዓመት ዓመት ከፍተኛ እመርታን እያስመዘገበ ይገኛል።የገበያ ድርሻውም በእጅጉ ከፍ ብሏል። መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ዓለም አቀፍ የፋርማሲቲካል ገበያ 1 ነጥብ 27 ትሪሊየን ዶላር ዋጋ አውጥቷል። ይህ አሃዝም እኤአ በ2001 ከነበረው የ390 ቢሊየን ዶላር አስተዋፅኦ ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ እጅጉን ሰፊ እድገቱም ከፍተኛ ስለመሆኑ ምስክር ይሆናል።
የግሎባል ኒውስ ዋየር መረጃም ዓለም አቀፉ የፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ በ2023 በጠቅላላ 1 ነጥብ 57 ትሪሊየን ዶላር ዋጋ እንደሚዘወርበት ያመላክታል። በተጠቀሰው ዓመትም የሰሜን አሜሪካ አገራት የዘርፉን ገበያ መምራታቸው፣ የእሲያ ፓስፊክ ቀጠናም ሁለተኛነቱን እንደሚያስቀጥል ግምቱን አስቀምጧል።
ዘርፉ በቀጣይ ዓመታትም ከዚህም በላቀ መልኩ እድገት ለማስመዝገብ አይቸገርም። በዓለም አቀፍ ደረጃ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱም ለዘርፉ እድገት ስኬት ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል። ይህን ዋቢ የሚያደርጉ ምሁራን አፅንኦት ሰጥተው እንደሚያስረዱትም፣ የዘርፉ መጎልበት (ስኬት) የኢኮኖሚ ጥቅም ብቻ አይደለም። መድህኒቶች ቀጥታ ከሰው ልጅ ደህንነት እና ጤና ጋር የተቃራኘ በመሆኑ የዘርፉ ማደግ በተዘዋዋሪ ጤናማ ማህበረሰብን መጨመር እንደሆነ ሊታሰብ የግድ ይላል።
አህጉራችን አፍሪካ የፋርማሲዩቲካል ገበያ በአንፃሩ በተለያዩ ፈተናዎች የተተበተበ ነው። በአሁን ወቅትም ከአፍሪካ ህዝብ ግማሽ ያህሉ መሰረታዊ መድሃኒትና የጤና አገልግሎት የማግኘት አቅም የለውም። በዚህም ምክንያት በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች በወባ፣ በሳንባ ነቀርሳ፣ በጉበት በሽታዎች ሕይወታቸውን ለማጣት ይገደዳሉ። በተለይ በአዳጊ ሀገራት መድሃኒት የሚያስፈልጋቸው ብዙ ህሙማን ይገኛሉ። ይሁንና አስፈላጊ የሚባሉ መድሃኒቶቹን በቀላሉ ለማግኘት ይቸገራሉ። ከስቃይ ብሎም ሞት ሊገላግሏቸው የሚችሉ መድሃኒቶችን በቀላሉ ለመግዛት አልታደሉም።
በተለያዩ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ለተያዙ ህሙማን ‹‹መድሃኒት የለም›› ማለት የሚያስከትለውን ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ እጅጉን ከባድ ብሎም የበርካቶችን ህይወት የሚያሳጣ ጥፋት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም። ይሁንና ጊዜውን በጠበቀ መልኩ ተገቢ እና በተመጣጣኝ ዋጋ መገኘት የሚችሉ መድሃኒቶች እንዲሁም የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ ቢቻል እነዚህን ሁሉ በሽታዎችንና ሞትን መቀነስ አሊያም በቀላሉ መከላከል ይችላል።
በአጠቃላይ አፍሪካ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስት ሪው አበርክቶ በሚፈለገው እና መሆን ባለበት ልክ አይደለም። በአፍሪካ ተመርቶ ተጠቃሚ ዜጎች ዘንድ የሚደርሰው መድሃኒት ከሁለት በመቶ እንደማይበልጥ የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ። የአፍሪካ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ በሚመለከት ሰፊ ሐተታን አፍሪካን ሬኔዋል የተባለው መጽሔት ላይ ያሰፈረችው ጃኔት ባያሩንጋም፣በአሁን ወቅት አፍሪካ 80 በመቶ የሚሆነው የመድሃኒትና የህክምና ግብአት ፍላጎታን የምታሟላው ከውጭ አገራት በማስገባት መሆኑን ታስረዳለች።
‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም አፍሪካ መሰረታዊ የሚባሉ መድሃኒቶች እና ግብአቶችን የማሟላት አቅም እንዳልገነባች በገሃድ አስመስክራል›› ያለችው ፀሐፊዋ፣ በዘርፉ ኢንቨስትመንት ረጅም ርቀት መራመድ እንደሚጠበቅባት አፅንኦት ሰጥታዋለች። ምንም እንኳን አንዳንድ አገራት በተለይም በደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ እና ግብፅ የፋርማሲዩቲካል ኢንቨስትመንት ተሳትፎ የጎላ ሆኖ ቢጠቀስም፣ አህጉሪቱ 80 በመቶ መድሃኒቶችን ከውጭ ከመግዛት እንድትገላገል ማድረግ ግን አልቻሉም።
ቡባካር ዲያሎ አፍሪካ ቴክ በተሰኘ ገፅ ላይ ባሰፈረው ሰፊ ትንታኔ እንደሚያስረዳው ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚመረተው መድሃኒትም የአፍሪካ አስተዋፅኦ ከሦስት በመቶ የሚበልጥ አይደለም። ምንም እንኳን ደቡብ አፍሪካ እና ሞርኮን የመሳሰሉ አገራት ከ 70 እስከ 80 በመቶ የፋርማሲዩቲካል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ባይቸገሩም ማዕከላዊ አፍሪካ ያሉ አገራት በአንፃሩ 99 በመቶ የመድሃኒት ፍላጎታቸውን የሚያማሉት ከውጭ በማስገባት በተለይም ከእሲያ አገራት በመግዛት ነው።
በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያካሄዱ ተቋማት እና ምሁራን ታዲያ ይህን ችግር ለመሻገር ዋነኛ መፍትሔ አገር ውስጥ የማምረት አቅምን በመፍጠር ጥራታቸውን የጠበቁ መድሃኒቶችን በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚ የማቅረብ አቅም ማዳበር እና ከውጭ መድሃኒቶችን ከማስገባት መቆጠብ የግድ የሚል መሆኑን ያስገነዝባሉ። ከአፍሪካ አገራት በተሻለ የኢትዮጵያ የፋርማሲ ዩቲካል ኢንዱስትሪ ይበልጥ አማላይ ነው። መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም፣በኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካል ገበያው ድርሻ በዓመት ከ 400 ሚሊየን እስከ 500 ሚሊየን ዶላር ይደርሳል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም በከተ ማም ሆነ በገጠር የጤና ስርዓት ተደራሽነት መሻሻል እና መጎልበት የመድሃኒት ብሎም የገበያው ፍላጎት እንዲጨምር እንዳደረገው ይገለፃል። አገሪቱ ከአፍሪካ በህዝብ ቁጥር ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ እና የህዝቦቿ ቁጥርም እየጨመረ የሚሄድ እንደመሆኑም የፋርማሲዩቲካል ምርቶችን የሚፈልጉ ዜጎች ከፍተኛ በሆነ መጠን እንዲያሻቅብ ማድረጉ አይቀሬ ነው።
ኢትዮጵያ እኤአ በ2015 በአስር ዓመት ውስጥ ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን እና በተለይ የአገር ውስጥ አምራቾችንና ተዋናዮችን ሚና የማጎልበት እና እኤአ በ2025 የፋርማሲዩቲካል ማኑፋክቸሪንግ ማዕከል የመሆን ራእይን አስቀምጣለች። በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ እና እስትራቴጂ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ዘርፉን ታሳቢ ያደረገ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብቷል። ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ከአስር ደቂቃ የተሽከርካሪ ጉዞ በኋላ የሚገኝ 270 ሄክታር መሬትም ተዘጋጅቶለታል።
ዘርፉን በሁሉ ረገድ ለማጎልበት የሚያግዙ የልማት ኢንስቲትዩቶችን እንዲሁም ድጋፍ የሚሠጡ ባለድርሻ ኤጀንሲዎችም ተቋቁመዋል። እነዚህ ተቋማትም ከጥናት እና ምርምር እስከ ፕሮጀክት ትግበራ ባሉ ሂደቶችን ኢንቨስተሮችን የማገዝ የተለያዩ ተግባራት እያካሄዱ ይገኛሉ።
ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ኢንቨስተሮች እና አምራቾችን የመመዝገብ፣ ፈቃድ የመስጠት፣ ማበረታቻ ዎችን የማቅረብ እና ሌሎም ተግባራት ይከናውናል። የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ባለስልጣን፣ የቁጥሩን ኃላፊነት ተረክቧል። የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽንም ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን የማልማት ብሎም የማስተዳደር ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
የምግብ፣ የመጠጥና የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለዘርፉ ተዋናዮቸ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላቸውን አቅም እንዲፈጥሩ ለማገዝ የተቋቋመ ነው። የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ፣የህክምና ግብአቶችን ወደ ጤና ተቋማት እና ህዝብ እንዲሁም ወደ ግል ተቋማት ተደራሽ የማድረግ ሥራ ይሠራል።
የትምህርት ተቋማትም ዘርፉን ለመደገፍ ስልጠና ከጀመሩ ቆይተዋል። ከአስር በላይ የፋርማሲ ትምህርት የሚሰጡ ተቋማት አሉ። አዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ ጂማ እንዲሁም አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመሳሰሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ለማጎልበት ይረዳ ዘንድ ዘርፉን ብቻ የሚዳስስ የስፔሻላይዜሽን ትምህርት ፕሮግራም ጀምረዋል። ይሁንና የኢትዮጵያ የፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ ዘርፉ እየተራመደ የሚገኝበትን ፍጥነት የሚመለከቱ የዘርፉ ምሁራን፣በምርት፣አቅም፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራ እጅግ ዝቅተኛ ተሳትፎ እያስመዘገበ ስለመሆኑ ይመሰክራሉ። ዘርፉም ከፍተኛ በሆነ መልኩ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተንጠለጠለ ነው።
ይህ ማለት ግን አገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎች የሉም ማለት አይደለም። የእነዚህን ተዋናዮች የአገር ውስጥ ፍላጎት ለማሟላትም ሆነ ኢትዮጵያ ከዘርፉ ገበያ ተጠቃሚ እድትሆን በማገዝ ረገድ አፍን ሞልቶ ለመናገር የሚያስደፍር ክንውን የላቸውም። የኢንቨስትመንት ተሳትፏቸውም ዘርፉ ከሚያመ ነጨው ከግማሽ ቢሊየን ዶላር የገበያ ድርሻ ከአስር በመቶ የሚባልጥ አይደለም። በርካቶቹም ከውጭው አቻዎቻቸው ጋር ሲነፃፀር ተፎካካሪ መሆን የሚያስችላቸውን አቅም ማዳበር አልሆነላቸውም።
በእርግጥ በአሁን ወቅት የተለያዩ የደጋፉ ተቋማት በዘርፍ የተሰማሩ መድሃኒትና የህክምና መገልገያ ቁሳቁስ አምራች ኩባንያዎች የምርት መጠናቸውን እንዲያሳድጉና በጥራት እንዲያቀርቡም የተለያዩ እገዛዎች እያደረጉ ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን መስፈርት በጠበቀ ሁኔታ እንዲያመርቱ ለማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎች ይሰጣሉ።፡
ይሁንና አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ 80 በመቶ የመድኃኒት እና ፋርማሲዩቲካል ፍላጎቷን ከውጭ እያስገባች ትገኛለች። ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ፍላጎት ሀገር ውስጥ በማምረት ማቅረብ የተቻለው 15 በመቶ አይበልጥም። ለዚህም የተለያዩ ችግሮች በምክንያትነት ይዘረዘራሉ። የመድሃኒትና የህክምና መገልገያዎች ጉዳይ ከሁሉም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ይሁንና የዘርፉን ችግሮች መፍታት የሚችል አቋም እና አቅም ውስንነት እንደሚስተዋል ይነገራል። የውጭ ምንዛሬ እጥረትም ሌላኛው የዘርፉ ፈተና ሆኖ ይቀርባል።
የጥሬ እቃ፣ የግብአትና የኃይል አቅርቦት፣ጥራቱን የጠበቀ ምርት አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ውስንነትም ይነሳል። በተቋማት መካከል የተናበበ አሠራር አለመኖሩም ዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዳያስገኝ ምክንያት መሆኑ ሲነገር ይደመጣል። የኢትዮጵያ የፋርማሲቲካል ገበያው በየዓመቱ በ15 በመቶ እድገት እያስመዘገበ የገበያ ድርሻውም እስከ 1 ቢሊየን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ። በአሁን ወቅትም የተለያዩ አገራት ግዙፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ላይ ተክለዋል። ቻይና ፣ህንድ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንዲሁም የአውሮፓ ኢንቨስተሮች ግዙፍ ኩባንያዎችም ኢትዮጵያ ከከተሙ ዋል አደር ብለዋል። በተለይ የቻይና ተሳታፎ በከፍተኛ መጠን እና ፍጥነት እየተጋዘ ይገኛል።
ዘ ቻይና አፍሪካ ፕሮጀክት Development Reimagined ዋቢ በማድረግ በተለይ የአፍሪካ እና ቻይና አጋርነት እና የዘርፉ ተሳትፎ በሚመለከት ሰፊ ሀተታን አስነብቧል። የየሁማንዌል ሔልዝኬር ግሩፕ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሊ ዌን ሼንግ ጋር ቃለ ምልልስ በማዘጋጀት በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ የቻይና ኢንቨስትመንት ተሳትፎን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርጓል።
እንደ ዘገባው ከሆነም ከ55ቱ የአፍሪካ አገራት 34 የሚሆኑት በየደረጃው የፋርማሲዩቲካል ምርቶችን ያቀርባሉ። አንዳንዶቹም በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ማበረታቻዎችን በማቅረብ በራቸውን ክፍት አድርገዋል። በዚህም ዕድልም ግዙፍና ስመጥር ኢንቨስተሮች ተሳትፈዋል። ዕድሎቹም በተለይ ቀደም ባሉት ዓመታት ከሁሉ በላይ በህንድ ኢንቨስተሮች እና አምራቾች ተመራጭ ሲሆኑ ቆይተዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደሚገልጹት፣የአፍሪካ የፋርማሲቲካል ዘርፍ አዝጋሚ ልማት ሲያስመዘግብ ስለመቆየቱ ለክርክር የሚቀርብ አይደለም። በአብዛኞቹ አገራትም ከውጭ በሚገባ ምርት ላይ ጥገኛ ናቸው። ይህም በኢኮኖሚያቸው ላይ የሚያሳድረው የፋይናንስ ጫና በቀላሉ ሊታይ የሚገባው አይደለም።
ከዓመታት ቀድሞ አዲስ የቻይና አፍሪካ ትብብር እውን የሆነው የዘርፉን እድገት ለማጎልበት ነው። የቻይና መንግሥት በየዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው መድሃኒት ለአፍሪካ ድጋፍ ያደርጋል። በአሁን ወቅትም የቻይና ኢንቨስተሮች አፍሪካ የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ለመደገፍ በተለያዩ መንገዶች በመራመድ የተለያዩ ተግባራት እያከናወኑ፣ኢንቨስተሮች ለሁለንተናዊ የአቅም ግንባታ የሚያግዝ ስልጠና እየሰጡ ይገኛሉ።
በአፍሪካ የየዘርፉ ኢንቨስትመንት እየጎለበተ መምጣቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው አፅንኦት የሚሰጡት ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ውጤቱም ከውጭ በገፍ የሚገቡ መድሃኒቶችን ለማስቀረት፣ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው መድሃኒቶች እንዲጨምሩ ከሁሉም በላይ ህገ ወጥ እና ተመሳስለው የሚሠሩ መድሃኒቶችን ወደ አህጉሪቱ እንዳይገቡ እንደሚከላከል ነው ያስረዱት።
አምራቾች በአገር ውስጥ በሚፈጠሩበት ጊዜ ፋብሪካዎች ለውስጥ ገበያው ፍላጎት የሚመቹ ምርቶችን እንዲያቀርቡ፣ መንግሥታትም አቅምቸውን በማጎልበት ለዜጎቻቸው ፈጣን እና ውጤታማ የጤና አገልግሎትን ለዜጎቻቸው ተደራሽ እንዲያደርጉ ዕድል ይሰጣል። ምርቶችን ከቦታ ቦታ፣ከአገር አገር ለማዘዋወር የሚከፈል ከፍተኛ ገንዘብ ያስቀራል። ለመድሃኒቶች የዋጋ መናር ዓይነተኛ ምክንያት የሚሆነውን ይህና የሎጅስቲክ ፈተና በማቃለልም ዜጎች መድሃኒቶችን በፈጣን እና በቀላሉ ዋጋ እንዲያገኙ አቅም ይፈጥራል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አፍሪካ ከፋርማሲዩቲካል ዘርፉ ከእንቅልፏ እንድትነቃ እና ተጠቃሚነታን እንድታረጋግጥ ከሁሉ በላይ በከፍተኛ ወጪ ብሎም መጠን ከውጭ የምታስገባቸውን መድሃኒት በማቆም፣ጥራት ያላቸው ምርቶችን በአገር ውስጥ የማምረት አቅም እንዲኖርት ከሁሉም በላይ የመሰረተ ልማት ውስንነት መቅረፍ ወሳኝ ስለመሆኑም አፅንኦት ሳይሰጡት አላለፉም።
መሰል ፈተናዎች መሻገር በተለይ የአገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታት ከተቻለም የአፍሪካ የፋርማ ሲዩቲካል ዘርፍ በርካታ ዕድሎች ከፊቱ የሚጠብቁት እንደሚሆንም ተመላክቷል። በተለይ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ለዘርፉ ተጨማሪ የንግድ ቀጠና እና አማራጭ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። የንግድ ቀጠናው 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ህዝቦችና ከ3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የአገር ውስጥ ምርት ያላቸው አገራትን የሚያቅፍ በመሆኑ ለአገሪቱ አምራቾች ትልቅ የገበያ ዕድል መሆኑ ተስፋ ሰጪ ያደርገዋል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2013