በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ፊታቸውን እንዲመልሱ ካደረጓቸው ሀገራዊ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ነው። የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ነው። ግድቡን ለየት የሚያደርገው፤ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በአንድ ዓላማ ያስተሳሰረ መሆኑ ነው። በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር ከውስጥ በመነጨ ስሜት በአንድነት ሆነው ድጋፋቸውን የገለጹበት ነው።
በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዲያስፖራዎች የግድቡ ግንባታ የሀገራቸውን መጻኢ ተስፋ ብሩህ እንደሚያደርገው በማመን ሀገራቸውን ለማልማት በአንድነት ቆርጠው የተነሱበት ወቅት እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ የሚችለውንና የአቅሙን በማዋጣት ሀገር ወዳድነቱን የሚገልጽ በርካታ አስተዋፅኦ አበርክቷል ።
በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩበት ሀገር ሆነው ‹አቤት አገሬ አለሁልሽ› በማለት በሀገራቸው ከመኩራት አልፈው እጃቸውን ለድጋፍ ዘርግተዋል። ያላቸውን ሁሉ ወደኋላ ሳይሉ ሀገራቸውን መደገፍ በመቻላቸው ውስጣቸው ሀሴት እያደረገ ከእነሱ የሚጠበቀውን ሁሉ በማድረግ ሀገራቸው ጉዳይ ላይ ከወገኖቻቸው ጎን ለቆመው ያሳዩት ድጋፍ ላቅ ያለ ነው።
ዲያስፖራው የተጀመረውን የሀገሩን ልማት ለማፋጠን ለግድቡ ግንባታ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች በማዘጋጀት፣ በቦንድ ሽያጭና በስጦታ በመሳተፍ በርካታ ድጋፎችን አድርጓል። የግድቡ ግንባታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስም በገንዘብ፣ በእውቀት እና በአድቮኬሲ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብቷል ። ይሁን እንጂ ከለውጡ በፊት ሀገሪቱ የነበረችበት ሁኔታ ዲያስፖራው የድጋፍ እጁን እንዲሰበሰብ ያደረገ ስለነበረ የዲያስፖራው ተሳትፎ ተቀዛቅዞ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ከለውጡ በኋላ መንግሥት በወሰደው እርምጃ የህዳሴ ግድብ ከነበረበት ችግር በመውጣት የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትን አከናውኗል። ይህንን ተከትሎ ዲያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ መነቃቃት በማሳየቱ ለህዳሴው ግድብ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ በሀገር ውስጥ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ እየሆነ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ዲያስፖራው ይህንን ተግባር በመደገፍ ለግድቡ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር በውጭ ያለው የዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ስለግድቡም ሆነ ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ያለውን ነባራዊ እውነታ ለማሳወቅ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ በ2013 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሰብሰቡን አስታወቋል። ይህ ድጋፉ የተሰበሰበው በቦንድ ሽያጭ፣ በስጦታና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች እንደሆነ ተገልጿል። አጄንሲው በዘንድሮ በጀት ዓመት ከዲያስፖራው 200 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ያቀደ ሲሆን፤ በዚህ በጀት ዓመት እስካሁን የተደረገው ድጋፍ ባለፈው በጀት ዓመት ከተሰበሰበው ገንዘብ ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለውም ተመላክቷል።
ኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንደገለጹት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በዲያስፖራው ላይ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩንና የውሃ ሙሌቱ አሁን እየተሰበሰበ ላለው ገንዘብ ያደረገው አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ነው ። ዲያስፖራው ለግድቡ ግንባታ ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ያላትን አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስረዳት ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተለይም ግብጽና ሱዳን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግድቡ ዙሪያ የተዛባና የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖረው የሚያደርጉትን ዘመቻ በመመከት ሚዛናዊ እይታ እንዲኖር ከማድረግ አኳያ ውጤታማ ሥራ እየሰሩ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዲያስፖራው ለህዳሴ ግድቡ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ እጅግ በርከት ያለ ነው። ለአብነት የዲያስፖራውን የቅርብ ጊዜያት ተሳትፎ እንኳን ብንመለከት፤ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ከ53 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንና 100 ሺህ ዶላር ለመስጠት ቃል መግባታቸውን የሚታወስ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በሚኒሶታና በሰሜን ማዕከላዊ የአሜሪካ ክፍል በሚገኙ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለግድቡ የ40 ሺህ ዶላር ድጋፍ አድርገዋል።
በተመሳሳይ ‘የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች’ በሚል መሪ ሃሳብ በጀርመን በርሊን የኢፌዴሪ ኤምባሲ እና ፍራንክፈርት ቆንስላ ጀኔራል አስተባባሪነት በተዘጋጀ የድጋፍ ማሰባሰቢያ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል ።
በጀርመን ለሚኖሩ የዲያስፖራ አባላት የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሚኒስትሩ የግድቡ ግንባታ 86 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸው። ስራውም በከፍተኛ የአገራዊ ፍቅር ስሜት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት ሳታስከትል የተፈጥሮ ሃብቶቿን ማልማቷን የምትቀጥል መሆኑን አስገንዘበዋል። አክለውም ግድቡን በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በቻሉት ሁሉ በመደገፍ ፍጻሜውን እውን ማድረግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በኤምባሲው በዓይነቱ ልዩ የሆነ የገንዘብ ስጦታ እና ቦንድ ግዥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ ቃል መግቢያ ቅጽ /pledge form/ የተዘጋጀ ሲሆን፤ የውይይቱ ተሳታፊዎችም የስጦታና የቦንድ ግዢ ቅጹን እየሞሉ ስጦታቸውን የመፈጸም ግድቡ እስኪጠናቀቅ በበለጠ የአገር ፍቅርና ወኔ ሁሉን አቀፍ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል የገቡበት መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው ።
ዲያስፖራው ለህዳሴ ግድብ እያደረገ ያለው ድጋፍና ተሳትፎ በዚህ የሚያቆም አይደለም። በመላ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን የሀገራችንን እድገት አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ ያለመውን የዘመናችንን አኩሪ ታሪክ ለመጻፍ ከሀገር ጎን በመሰለፍ የበኩሉን መውጣት ይጠበቅበታል።
መንግሥት ዲያስፖራው ለሀገሩ ልማት እያፈሰሰ ያለውን መዋለ ነዋይ ተግባር ላይ በማዋል የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲያጠናቀቁ በማድረግ ለውጤታማነታቸው ጥረት ማድረግ ይገባዋል። የዲያስፖራው ተሳትፎ በሁሉም መስክ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ለማድረግ ያለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት መወጣትም ይጠበቅበታል።በአጠቃላይ ዲያስፖራው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ለግድቡ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2013