የዛሬው ትዝብታችን ዋና ነጥብ በብድር ገንዘብ ድል ያለ ሰርግ ደግሰው የሚሞሸሩ ጥንዶች ጉዳይ ነው። ብድሩ ከባንክ፣ ከቁጠባ ማህበር ወይም ከግለሰብ ሊሆን ይችላል። ሆኖም በብድር የቆመ ጎጆ መዘዙ ብዙ ነው። እንደውም ይሉኝታ ላላቸው ሙሽሮች በሕዝብ ታጅበው በተሞሸሩበት አደባባይ ይጀምራል። ታዳሚው እየበላ፣ እየጠጣና እየደነሰ አሼሼ ገዳሜ በሚልበት የሠርግ ስነ ስርዓታቸው ላይ ፍዝዝ ቅዝዝ ብለው ስለተበደሩት ገንዘብ ያሰላስላሉ። ይሄንኑ ዕዳውን በመክፈል ዙሪያ ሠርግ ስነስርዓታቸው ላይ አንዱ በሌላው ጥፋትን በማላከክ የሚጨቃጨቁም ሙሽሮች አይጠፉም። እነዚህ ጥንዶች በአብዛኛው ሠርጋቸውን በብድር የሚደግሱት በቤተሰብ ወይም በጓደኛ አልያም በሠርግ መጋባት የሚያስገኘውን ደስታ በመሻት ነው። ብድሩን የሚበደሩትም ከልባቸው መቶ ለመቶ ለመክፈል ነው። በእርግጥም የሚከፍሉ በመሆናቸው ምስጉን ናቸው። በሠርጋቸው ስነስርዓት ሳይቀር ክፍያው የሚያሳስባቸውም ለዚህ እንደሆነ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
ሆኖም ይሄ ለሠርግ ድግስ የዋለ ብድርን የተመለከተ ጭቅጭቅ እስከ ጫጉላ የማይዘልቅበትና ለጥንዶቹ ጋብቻ መፍረስ ምክንያት የማይሆንበት የለም። ውሎ ሲያድር ጎጆውን ከማሞቅ ይልቅ የሚያቀዘቅዝበት አጋጣሚ ቀላል አይደለም።ብሎም እስከ ፍቺ የሚያደርስበት ጊዜ ብዙ ነው። ‹‹አበስኩ ገበርኩ!›› አሉ እትዬ አስካለ! ከዚህ ሁሉ ሰርጉ ቢቀርስ? እረ ሙሽሮች እንዲህ ጋብቻቸውን አደጋ ውስጥ በሚጥል በብድር ገንዘብ ባይሰረጉስ? በእርግጥ አንዳንድ ጥንዶች በብድር ገንዘብ መሰረግን አልፎ ተርፎም በዚሁ ገንዘብ የቤት ዕቃ ማሟላትን እንደ ባህል አድርገው ይዘውታል። በዚህ ዓይነቱ ልምድ ከመካናቸው የተነሳ ሆን ብለውና አስበውበት ብድር የሚበደሩና ሠርጋቸውን የሚደግሱ የቤት ዕቃቸውንም ከሠርጋቸው ቀድመው በተገቢው መንገድ የሚያሟሉ ጥንዶች አሉ። እነዚህ ጥንዶች ቢመቻቸው በሠርጋቸው ወቅት የተከራዩትን የግለሰብ ቤት በማጭበርበር ጭምር የራሳቸው ከማድረግ አይመለሱም። የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ዕድለኞች አካባቢ የሚሰሩ ከሆነማ ዕምነት የሚጣልባቸው አይደሉም። የራሳቸውን የተደላደለ ኑሮ ብቻ ስለሚያዩ ተዓምር ፈጥረው የአንዱን ዕድለኛ ቤት የራሳቸው ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም።
የእነዚህ ጥንዶች ክፋት እንደ የዋሆቹ ሙሽሮች ለሠርግ የተበደሩት ክፍያ የሚያሳስባቸው አለመሆኑ ነው። ሲበደሩትም እንደማይከፍሉት አውቀውና አቅደው ነው። እንደማይከፍሉ ቢያውቁም ከጽኑ ህመም ህክምና ጀምሮ ወሳኝ ለሆኑ ጉዳዮች ግለሰብ ያስቀመጠውን ገንዘብ ያለምንም ሰብዓዊነት ስሜት በእጅ በእግር ገብተው መበደሩን ያውቁበታል። የሚቀርቡት ተለማማጭና የሚያሳዝኑ ፍጡር ሆነው ነው። ከባንክም ሆነ ከሚሰሩበት ከብድርና ቁጠባ ማህበር ለመበደር ዓይናቸውን አያሹም። እንደማይከፍሉት ስለሚያውቁ የሚበደሩት ደግሞ ከፍተኛ ብር ነው። እነዚህ ጥንዶች የብድሩ ክፍያ እንኳን በሠርግ ስነስርዓታቸው ላይ ልጅ ወልደው በመዳር የልጅ ልጅ እስኪያዩም ድረስ ትዝ አይላቸውም።የሠርግ ስነ ስርዓታቸውንም ሆነ የጫጉላ ጊዚያቸውን በደስታ ነው የሚያሳልፉት። ሥራቸው ብድራቸውን ሳይከፍሉ አበዳሪያቸውን እያቆሰሉ በኑሯቸው ሁሉ መደሰት ነው። የሌላው ህመም ወይም ጉዳት ቅንጣት አይሰማቸውም። በአበዳሪው ዕዳውን እንዲከፍሉ ከተጠየቁ የሚያቀርቡት ሰበብ አስባብ ተቆጥሮ አያልቅም። ጫን ካላቸው በነሱ ብሶ ሊሰድቡትና ሊጎናደሩበት ይችላሉ። ባለውለታቸው ሳይሆን ጭራሽ ጠላታቸው አድርገው ይቆጥሩታል። የማይለቅ ኃይለኛ አበዳሪ ከገጠማቸው የተበደሩትን ዕዳ ላለመክፈል ስልክ ከማጥፋት ጀምሮ ቤት እስከ መቀየር ይደርሳሉ። ሥራ እስከ መልቀቅና ሀገር ጥለው እስከ መጥፋት የሚደርሱም አሉ። የሚገርመው ይሄን የሚያስቡትና የሚያመቻቹት ድል ያለ ሠርግ የደገሱበትንና የቤት ዕቃ ያሟሉበትን ገንዘብ ከመበደራቸው ቀድመው ነው።
እዚህ ጋር የእኔን ገጠመኝ ላካፍል። ሙሽራው የሥራ ባልደረባዬ ነው። ከመሥሪያ ቤታችን የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ማህበር ለሠርጉ መደገሻ ገንዘብ የተበደረው እኔንና ሌሎች ባልደረቦቹን ዋስ አድርጎን ነበር። ሌላዋን ባልደረባችንን ደግሞ አዲሱ ጎጆውን የሚያደምቅበት የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ ዋስ አድርጓታል። በተለይ እኔ ዋስ እንድሆነው የጠየቀኝ እኔም ከማህበሩ ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ ተበድሬ ዋስ በሆነልኝ ወር እንኳን ሳይሞላ ነው። ፍጥነቱ ቢያስገርመኝም ከበስተጀርባው አንዳች ነገር እንዳለ ቢያስጠረጥረኝም ቅርበት ሳይኖረን ዋስ እየፈለግኩ ባለበት አጋጣሚ ድንገት ዋስ ለመሆን ፈቃደኛ የመሆኑ ጉዳይ አስገድዶኝና አሸንፎኝ ዋስ የሆንኩት።
ወደዚሁ ከሥራ መታገዱን ሰማን። ከመታገዱ በፊት ለሦስት ወራት ዕዳ መክፈልም ሆነ መቆጠብ አቁሞ ነበር። ሲታገድ የሦስት ወሩን ጨምሮ ለሠርግ የተበደረውን ዕዳ በሙሉ እኛ እንድንከፍል ቁጠባና ብድር ማህበሩ ወሰነብን። ሆኖም ሲታገድ ተፈቅዶልኛል ያለውን የሦስት ወር ደሞዝ እንኳን የሦስት ወር ውዝፍ ዕዳውን መሸፈኛ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነልንም። ምክንያቱ ደግሞ ሥራ ፈትቼ ቁጭ ብያለሁ ከየትም አምጥቼ ልከፍላችሁ አልችልም የሚል ነው። ‹‹ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም›› እንዲሉት ተረት የመክፈል ፍላጎቱ ካለው የአማረ እጅ እግር ያለውና ቢያንስ አንዱ ካፌ ውስጥ በአስተናጋጅነት ተቀጥሮ ዕዳውን መክፈል የሚችል ወጣት ነው።
በእዚህ ላይ ባለቤቱ ሙሽሪት ያማረ ሥራ አላት። ገንዘቡ የዋለው ለስቱዲዮ ፎቶ ስነስርዓትም ሆነ ለምግብ ድግስ የተደገሠው ሠርግና የተሟላው የቤት ዕቃ የጋራ በመሆኑ ወደደችም ጠላችም ዕዳውን መክፈሉ እሷንም ይመለከታታል ።ሕግም ቢሆን ሁለቱንም አይለቃቸውም። የሚገርመው ሠርገኛው አሁን ላይ ሥራ እየሠራ ነው። ከዛሬ ነገ ፈቃደኛ ሆኖ ዕዳውን ይከፍላል ብለን ስንጠብቀው ቆይተን ሥራ መጀመሩን ስንሰማ እንዲከፍል ብንጠይቀው እንኳን ለእናንተ ለኔም አይበቃኝ ብሎ አረፈው።
ሙሽራው ሆን ብሎና አስቦ የፈፀመው መሆኑ ይሄኔ ነው የተገለፀልኝ። አሁንማ አድራሻውን ሁሉ አጥፍቷል። ደግነቱ ማንን ፈርቼ ብሎ ነው መሰለኝ ለእኛ ባያነሳልንም ስልኩን አላጠፋም። ያነሳ በነበረበት ወቅት ዕዳውን እንዲከፍል በየፊናችን ደጋግመን ስንጠይቀው ታድያ ምን አለ መሰላችሁ? ‹‹በእሱው ብሶ አላበዛችሁትም እንዴ ምን አድርግ ነው የምትሉኝ? ካሁን በኋላ እየደወላችሁ ብትጠይቁኝ ወዮላችሁ!›› ብሎ ዛተብን። ‹‹እምዬ ፍሰሽ እምዬ ፍሰሽ አንቺ የሰው ጃኖ ለብሰሽ እኔን በዕዳ ለውሰሽ›› አለ አሉ ሰውዬው፤ የእናቱን አስከሬን ሲሸኝ። እኛ በየፊናችን የእሱን ዕዳ በመክፈል ተወጥረናል። ዕቅዳችን ተጨናግፏል። ኑሯችን ተናግቷል። ለሕክምና ያሰብነው ለእሱ ብድር በመዋሉም ጤናችን አደጋ ላይ ወድቋል። እሱ ምን አለበት ዛሬም በየሎጂው ዘና ፈታ ሲል በየፌስ ቡኩ ይታያል። ተረጋግቶ የሞቀ ኑሮውን ይመራል። ሆኖም በብድር የተገነባ ጎጆ መቼም አይቆም። የሌሎች ጡር ስላለበት አይባረክም። እናም አንጀቴ በማረሩ ትዳሩ ቢያንስ አንድ ቀን ዕዳውን ለመክፈል መፍረሱ አይቀርም! ብዬ ብሶቴን ተንፍሻለሁ፡፡ ሰላም!
ጌቴሴማኔ ዘ-ማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም