ሥፍራው ከሃይማኖታዊ ሥርዓት በተጨማሪ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የሙዚቃ ኮንሰርት ማቅረቢያ፣ ህዝባዊ ሰልፎችና ትርኢቶች ማሳያ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ፣እነዚህና ሌሎችም ማህበራዊ ኩነቶች አገልግሎት መስጫ ሆኖ ዘመን ተሻግሯል። ኤግዝቢሽን ማዕከል፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሙዚየም፣ የሰማዕታት መታሰቢያ፣ ሴንጆሴፍ ትምህርት ቤትና ሌሎችም ተቋማት በአካባቢው ይገኛሉ ።
በተለያዩ ተቋማት መካከል ሆኖ እንዲህ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው መስቀል አደባባይ ሰፊ አገልግሎት የመስጠቱን ያህል እይታን የሚስብ አልነበረም። በአቅራቢያው መፀዳጃ ቤት ባለመኖሩም አላፊ አግዳሚው፣ በአካባቢው የተለያየ ነገር በማከናወን የሚቆየውና የጎዳና ተዳዳሪዎች በሥፍራው በመጸዳዳት ንጽህናው እንዲጓደል በማድረጋቸው በአካባቢው ላይ ይደርስ የነበረው ተጽዕኖ በተለያየ መንገድ ይገለጻል። ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችንም የሚፈታ ባለመኖሩ ከነችግሮቹ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል ። በዚህ ረገድ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ሙዚየም በጽዳት መጓደል በገጽታው ላይ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። ለጎብኝዎችም የደህንነት ሥጋት ሆኖበት ቆይቷል።
በአደባባዩ ዙሪያ መቼ እና እንዴት እንዲህ አይነት ሁኔታ እንደተፈጠረ በመረጃ ማስደገፍ ቢያስቸግርም ቀደም ሲል አሁን ከፊትለፊቱ ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘው ሐያት ሪል ኤጀንሲ ሆቴል አካባቢ የህዝብ መፀዳጃቤት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአደባባዩ ጥግ ላይም ለመኖሪያነት ውሎ እንደነበር አይታወቅም ። በአሁኑ ጊዜ ከመስቀል አደባባይ እስከ መዘጋጃ ቤት ድረስ ያለው ፕሮጀክት የግንባታ ሥራን በማማከር የሚሰራው ቢጂደብሊው አማካሪ አርክቴክቶች፣ፕላነሮችና ኢንጂነሮች አማካሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ዳይሬክተር አርክቴክት ብሥራት ክፍሌ ከነክፍተቶቹ የተለያዩ ኩነቶችን ሲያስተናግድ የነበረው መስቀል አደባባይ ይዘቱ ሳይቀየር ነገር ግን ብዙ ነገሮችን አሟልቶ በአዲስ መልክ ተገንብቶ ለምረቃ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ለመሆኑ መስቀል አደባባይ ምን መልክ ይዟል። ግንባታውን ማን አከናወነው። በምን ያህል ዋጋ የሚሉትንና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከዳይሬክተሩ አርክቴክት ብሥራት ጋር ቆይታ አድርገናል ። በቅድሚያም መስቀል አደባባይ ስለነበረው ይዞታ እንዲህ አስረድተዋል። በመስቀል ደመራ ወቅት አምሮና ደምቆ ሥርዓቱ ካበቃ በኋላ ግን ትኩረት የሚሰጠው ባለመኖሩ ቆሻሻ መጣያ፣ወጣቶችም ከሥነምግባርና ከማህበረሰቡ ተጻራሪ የሆኑ ነገሮች በመፈጸም፣ በአደባባዩ ዙሪያ የማይቀየሩ ከዓመት ዓመት ሸራ ወጥረው ንግድ የሚያከናውኑ፣ ከማህበራዊም ከፖለቲካም ተቃራኒ የሆኑ መልዕክቶች የሚተላለፉበት የማስታወቂያ ሰሌዳዎች የሚሰቀሉበት፣ በአጠቃላይ የከተማውን ውበት የሚሸፍኑ፣ ጽዳት የሚያጎድሉና ጸያፍ የሆኑ ነገሮች የሚስተዋሉበት ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ደረጃውን የጠበቀ አልነበረም። ከመስቀል አደባባይ እስከ ማዘጋጃቤት እየተከናወነ ያለው የግንባታ ፕሮጀክት እነዚህን ሁሉ ክፍተቶች ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አርክቴክት ብሥራት፤አደባባዩ የቀድሞ ይዞታው ሳይቀየር የማጽዳት፣የማስዋብና ከዚህ በፊት ያልነበሩ ተጨማሪ ሥራዎችን በማካተት ሰፊ ተግባራት ተከናውነው ለምረቃ ዝግጁ ሆኗል።
በአዲስ ግንባታ ሥራው በተጠናቀቀው መስቀል አደባባይ ከአንድሺህ ሦስት መቶ በላይ መኪኖችን ለማቆም የሚያስችል(ፓርኪንግ)፣ ከአንድ መቶ በላይ መፀዳጃ ቤቶች፣ ከ20 በላይ የመታጠቢያ ቤቶች፣ለተለያየ የንግድ አገልግሎት የሚውሉ 30 ያህል የንግድ ሱቆች ተገንብተዋል። እነዚህ ሁሉ 24 ሰዓት አገልግሎት ሲሰጡ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሥራቸው እንዳይስተጓጎል ከግንባታው ጋር ጀኔሬተር አብሮ ተሟልቷል።
አደባባዩ ለእይታም ማራኪ እንዲሆን፣ለጥላና ለነፋሻ አየር የሚሆን የአበባ ማስቀመጫ ሥፍራዎችም አብሮ ተመቻችቷል። ችግኞችም ተተክለዋል። በተጨማሪም ለውበቱ ማድመቂያ ፋውንቴን ተሰርቷል። አደባባዩ ሙሉውን ብርሃን ሆኖ እይታ እንዲኖረውም ዙሪያውን መብራቶች ተገጥመዋል። አካል ጉዳተኞችንም ታሳቢ ያደረገ ግንባታ በመከናወኑ ተደራሽ ሆኗል። ለደህንነትና አንዳንድ አስቸኳይ ለሆኑ ነገሮች እንደአስፈላጊነቱ የመኪና አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታም ተለይቶ ተሰርቷል።
አሁን ለመቆሚያና ለመቀመጫ የተሰሩት ደረጃዎችም ሰዎች አንድ ያልተጠበቀ ክስተት ቢያጋጥማቸው በፍጥነት ሮጠው ከሥፍራው ለመሄድ የሚያስችሉ ናቸው። ይሄ ቀደም ሲል ለአደጋ አጋላጭ የነበረውን በማስወገድ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ለማስታወቂያ አገልግሎት የሚውሉ አምስት ምስል፣ ድምጽንና ጽሁፍን በአንድ ላይ አጣምረው ለመልዕክት ማስተላለፊያነት የሚውሉ ሰሌዳዎች(ስክሪኖች) በተለያየ አቅጣጫ ተተክለዋል። ክፍተቶች በማሻሻልና ቀደም ሲል በአደባባዩ ውስጥ ያልነበረውን ሁሉ ያካተተ መሆኑ ግንባታውን ለየት ያደርገዋል።
ግንባታው ተጨማሪ ቦታ ስለመውሰዱ አርክቴክት ብሥራት ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ከአደባባዩ ውጭ ፈርሶ እንዲቀላቀል የተደረገ ነገር የለም። በአደባባዩ አቅራቢያ በሚገኘው በሰማዕታት ሐውልት አጠገብ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሙዚየም መግቢያ ላይ የግንባታ ፈቃድ ያልነበራቸው ስድስት ቤተሰቦች በመኖሪያነት ይጠቀሙበት ነበር። ይሄንን ያስተካከለ አካል ባለመኖሩ ነዋሪዎቹም መብታቸው አድርገው ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። አደባባዩ ቀስ በቀስም ይዞታው እየተሸረሸረ ነበር። ተበላሽቶ ጥቅም የማይሰጥም ሥፍራ ነበር ። እነዚህን ሥፍራዎች በማጽዳት ከአደባባዩ ጋር እንዲካተት በማድረግ ነው ግንባታው የተከናወነው።
ይሄ መካተቱም የአደባባዩን ሥፋት በተወሰነ ደረጃ እንዲጨምር አስችሏል። አሁን የአደባባዩ ስፋት አምስት ሄክታር ወይንም ከ50ሺ ካሬሜትር በላይ ነው። በዚህ መልኩ አደባባዩ ህብረተሰቡን ያማከለ ተደርጎ ዝግጁ በመሆኑ አካልጉዳተኞችን ጨምሮ ከህፃን እስካዋቂ ሊጠቀምበት ይችላል። ለግንባታ የወጣው ወጪ የለገሀር፣የቸርቸርን ጨምሮ እስከ ማዘጋጃቤት ያለውን የእግረኛ መንገድ ማስፋት ግንባታንም የሚያካትት በመሆኑ በድምሩ ቫትን ጨምሮ ሁለት ቢሊየን አምስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ሚሊየን ብር ወጭ ተደርጓል። ግንባታው አንድ አንድ ዓመት ጊዜ የወሰደ ሲሆን የግንባታ ሥራውንም ያከናወነው ከቤተመንግሥት ፊትለፊት የሚገኘውን የወዳጅነት ፓርክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ያስረከበና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ የቻይና ተቋራጭ ኩባንያ ነው።
እንዲህ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሲሰሩ በተለይም ልምድ ያላቸው የውጭ ተቋራጮች ሲሳተፉ ተሞክሮው ለሀገር ይተርፋል ። ከዚህ አንጻር በተለያየ መልኩ የተሳተፉ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ምን አተረፉ ለሚለው ጥያቄም አርክቴክተሩ እንዲህ ምላሽ ሰጥተዋል። በግንባታ ሥራው ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ሙያ ድረስ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሀገር ውስጥ ባለሙያ ነው የተሳተፈው። አማካሪ ድርጅቱም ሀገር በቀል ፣ከንድፍ(ዲዛይን) ሥራው ጀምሮ የማማከር ሥራው የተከናወነው በሀገር ውስጥ ባለሙያ ነው ። ከዚህ አንጻር የሙያ ክህሎት እና የሥራ ዕድል በማግኘት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
የቴክኖሎጂና የሙያ ሽግግር ተገኝቷል። የተገኘው ተሞክሮ የሥራ ሰዓትን አክብሮ ከመሥራት ይጀምራል። በኢትዮጵያ ውስጥ 24 ሰዓት ያለማቋረጥ መሥራት አልተለመደም። በዚህ ፕሮጀክት ክረምት ከበጋ ያለማቋረጥ ሥራዎች ሲሰሩ ነበር። ይሄ እንደ አንድ ልምድና ተሞክሮ ይወሰዳል። የቻይና ኩባንያውም ለሥራ የሚጠቀምባቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂ በማሳወቅ ልምዱን አካፍሏል። በጣም በጥሩ መልኩ ከሚወሰደው ተሞክሮ ደግሞ በአግባቡ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ በቀን ሥራ የተቀጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሞክሮውን ቀስመው ማሽኖችን ማንቀሳቀስ ችለው በሥራው ላይ የጎላ ሚና መጫወት መቻላቸው እንዲሁም በኤሌክትሪክ ሥራዎችንም በረዳትነት በመሥራት አቅም መገንባት መቻላቸው ይጠቀሳል።
ከአርክቴክቱ እንደተረዳሁት አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ሥራ ተጠናቅቆ አንዳንድ የእርማትና የጽዳት ሥራ ነው የሚቀረው። በአንድ ዓመት የሥራ ቆይታው በጠንካራና በተግዳሮት ሊነሱ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ። ከዚህ አንጻርም እንደጠንካራ ጎን ከጠቀሷቸው መካከል በእርሳቸው እምነት እንዲዚህ ፕሮጀክት በመንግሥት ድጋፍ ያገኘ የለም። ከዚህ ቀደም በነበረው የግንባታ ሥራ አንድ ለግንባታው የሚያስፈልግ ቦታ ላይ የሚገኝ የመብራት ምሶሶ ለማስነሳት ከባድ ውጣ ውረድ ነበረው። ለፕሮጀክቶች መጓተትም በዋናነት የሚነሳ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። በዚህ ፕሮጀክት ሥራ ግን ሂደቶችን በማሳጠርና ተባባሪ በመሆን በሚመለከተው ባለድርሻ አካል የተሳለጠ አገልግሎት ተገኝቷል። ለሥራው ቶሎ መጠናቀቅ አግዟል። የህብረተሰቡም ተሳትፎ ትልቅ ሚና ነበረው። ትብብራቸው የሚፈርሰውን አብሮ በማፍረስ ጭምር ይገለጻል። የፕሮጀክቱን ጥቅም የተረዳ ማህበረሰብ ነበር ማለት ይቻላል።
እንደተግዳሮት የጠቀሷቸውና ለቀጣይ የፕሮጀክቶች ሥራዎች መታረም አለባቸው ብለው ካነሷቸው መካከልም ነገሮችን አቀናጅቶ በመፈጸም ለአብነትም ለግንባታ የሚውሉ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች በቅንጅት ምክንያት መስተጓጎል ማጋጠማቸውን ነው። የወደብ መጨናነቅና የመርከብ መዘግየቶች ተጽዕኖ ነበራቸው። ሥራው ከመጀመሩ በፊት እነዚህ ነገሮች ቀድመው ታሳቢ መደረግ ነበረባቸው።
ከጥራት ጋር ተያይዞም በግንባታው ላይ ስለተሰጠው ትኩረት በተለይም ግንባታዎች አገልግሎት ሳይሰጡ ተመልሰው የሚቆፈሩበት ሁኔታ በስፋት ስለሚስተዋል ይሄን ችግር የሚያስቀር ስለመሆኑና በግሌም በእግረኛ መንገድ ላይ እየተከናወነ ሥላለው የድንጋይ ንጣፍ የጥራት መጓደል ያስተዋልኳቸውን ክፍተቶች እንዲሁም ባለድርሻ ከሆኑት ከቴሌና ከመብራት ኃይል ተቋማት ጋር ተናብቦ በመሥራቱ ረገድ ስለነበረው ሁኔታ ለአርክቴክት ብሥራት አንስቼላቸው‹‹በፕሮጀክቱ ውስጥ የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን በሙሉ በቅንጅት በአዲስ መልክ ለመሥራት ነበር የታቀደው።
በጀቱ ከፍተኛ በመሆኑ የታሰበውን ማድረግ አልተቻለም። ባለው ሁኔታም ሌሎች መሠረተልማቶች አሁን ባሉበት ሁኔታ በጥሩ ሁኔታ አገልግሎት እየሰጡ በመሆናቸው ለመቀየር አስገዳጅ ሁኔታ የለም። ነገር ግን መንገድም አስፓልትም አንዴ ከተሠራ በኋላ መቶ በመቶ እንዳይነካ ማድረግ አይቻልም። በተቻለ መጠንም በቅርብ ጊዜ እንዳይቆፈሩ ለማድረግ ተሞክሯል። አንድ ነገር ማድረግ የሚቻለው ግን መቆፈር ሳያስፈልግ የመሠረተልማት ሥራውን ማከናወን ነው›› በማለት ነው የገለጹት። በእግረኛ መንገድ ሥራው ላይ የሚታረሙ ስራዎች ይኖራሉ። የጥራት ማስተካከያ የአንድ ዓመት ጊዜ በመኖሩም ችግሮች ካጋጠሙ ተቋራጩ ያለተጨማሪ ክፍያ የእርማት ሥራ ያከናውናል።
የእግረኛ የመንገድ ሥራው ማስፋፋትን ያካተተ በመሆኑ የተቋማት አጥርና አንዳንድ መኖሪያቤቶችም ፈርሰው የተከናወነ በመሆኑ በምን ያህል ስፋት እንደጨመረ አርክቴክቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ‹‹ከመስቀል አደባባይ እስከ ለገሀር ያለው መንገድ በፕላን የተሠራ በመሆኑ በነበረበት ነው የተሰራው። ከለገሀር እስከ ቸርችል ያለው ግን ሥፋቱ ይለያያል። ከ40 እስከ 50 ሜትር ስፋት ያካተቱ ናቸው። በዚህ ምክንያት ትላልቅ ህንፃዎችም በተወሰነ ደረጃ የምድር ወለላቸው ወደ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል። በመንገድ ሥራው ትልቁ ጥቅም ተደርጎ የሚወሰደው ወደ እግረኛ ተካትቶ መሠራቱ ነው›› ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከተማና የአርክቴክቸር ቅርስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ፋሲል ጊዮርጊስ፤አዲስ አበባ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ አደባባይ እንዲኖራት መደረጉን አድንቀዋል ። እርሳቸው እንዳሉት ቅርስ አደባባይንም የሚጨምር በመሆኑ ይዘቱን ሳይለቅ መሠራቱ ፣ 24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ ኮንስትራክሽን መካሄዱ ሌላው ጠንካራ ጎን ነው።
እንዲህ ከፍተኛ ወጭ ወጥቶባቸው በውጭና በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ተሳትፎ የተገነቡ ሥራዎች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አዲስነታቸውን ይዘው ሲቀጥሉ አይስተዋልም። መብራቶችና ሌሎችም ጥገና የሚያስፈልጋቸው በወቅቱ ዕድሳትና ጥገና ሳይደረግላቸው ከደረጃ በታች የሚሆኑበት አጋጣሚ ይበዛል እና ከዚህ አንጻርም የግል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ‹‹ትልቁ ነገር ይሄ ይመስለኛል። ከቀላሉ ነገር ብንጀምር ነገ ማነው የሚገባውንና የሚወጣውን ሰው የሚቀበለው። ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል። እንደባለሙያ የምሰጠው አስተያየት የተገነቡት ሁሉ በአንድ መዋቅር ውስጥ ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ነው። የአስተዳደሩ ሥራ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ በቅንጅት ሊሆን ይችላል። የመንግሥት ሚና በቁጥጥሩ ላይ ቢያተኩር ውጤታማ ይሆናል። በዚህ መልኩ ከተሠራ አሁን ያለው ውበትና ጥራት ሳይጓደል ይቀጥላል››ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከተማና የአርክቴክቸር ቅርስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ፋሲል ጊዮርጊስ፤ የመስቀል አደባባይ አምሮ የበለጠ ለህዝብ ጥቅም እንዲውልና ከተማዋም ደረጃውን የጠበቀ አደባባይ እንዲኖራት መደረጉን እንዲሁም ቅርሱን በጠበቀ የማልማት ሥራው መከናወኑን አድንቀዋል። የእግረኛ መንገድ የማስፋፋት ሥራንም በተመለከተ እንደገለጹት ትክክለኛ እርምጃ ነው። ከነዋሪው 54 በመቶ የሚሆነው በእግሩ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ሰፊ መንገድ አስፈላጊ ነው።
ይህን ያህል ተጠቃሚ እያለ ነገር ግን ትኩረት የሚሰጠው ለመኪና ነው። ይሄ አግባብ አይደለም። ተቋማት በአጥር የያዙት የእግረኛ መንገድ አግባብ እንዳልሆነም ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ ። እርሳቸው እንዳሉት አጥር ለመኖሪያ እንጂ ለተቋማት አስፈላጊ አይደለም። ብክነት ነው ። ከመንገድ ዳር ርቀው መገንባት ይኖርባቸዋል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ብሄራዊ ቴአትር አካባቢ ያለው ነው። ተቋማትን በአጥር መገንባት የከተማ ፕላንም አይደለም። በጥሩ የህንፃ ግንባታ ማስዋብ ነው የሚመከረው። በተለይ ዋና የሚባሉት የከተማ መንገዶች ሰፋ ያለ የእግረኛ መንገድ ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ወደፊት እንደሚሻሻሉ ተስፋ አደርጋለሁ ይላሉ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2013