«ፋይዳ መታወቂያ ሌሎቹን መታወቂያዎች የሚተካ አይደለም»  – አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ዋና አስተባባሪ

ዓለማችን በተለያየ የእድገት ሂደት ውስጥ ስትጓዝ ቆይታለች። ግብርና የመጀመሪያውን የሰው ልጅ ሥልጣኔ ያመጣ ሲሆን በተራው ደግሞ የተሻለ ካፒታልና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለሚሻው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ቦታውን አስረክቧል። የኢንዱስትሪው ዘርፍ በርካታ ሀገራትን ለዕድገትና ለብልፅግና አብቅቷል፤ የተሻለ የአኗኗር ሥርዓትን ፈጥሯል። አሁን ደግሞ ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ነው። ዘመነ ዲጅታላይዜሽን ዓለም በየዕለቱ አዳዲስ ክስተቶችን እንድታስተናግድና በፍጥነት እንድትጓዝ እያደረጋት ይገኛል።

ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና ገንዘብ፤ ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልፅግና የማይተካ ሚና ይጫወታል። በተለይም በአሁኑ ጊዜ የአገልግሎት አሰጣጥም ሆነ የኢኮኖሚ ዝውውሩ በቀጥታ የታያዘው ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው ጋር በመሆኑ የሀገራት ዕድገትም ሆነ ውድቀት ለዘርፉ በሰጡት ትኩረት ልክ የሚለካ ነው።

ይህንኑ እውነታ በመገንዘብም ኢትዮጵያ ከአምስቱ የዕድገት ዘርፎች ውስጥ አንዱ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲሆን ፈቅዳ ወደ ሥራ ገብታለች።ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025″ ስትራቴጂን በመቅረጽም ሀገሪቱ በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚን ለመገንባት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። ይህ ስትራቴጂም በዋናነት የዲጂታል መሠረተ ልማት በመገንባት እና በማስፋት የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየተገበረች ያለችው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስትራቴጂ የመንግሥትን አገልግሎት በዲጂታል የታገዘ እንዲሆን በማድረግ ዜጎች ባሉበት ሆነው የመንግሥትን አገልግሎቶች በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። የዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት እንዲቀላጠፍም መሠረት ይጥላል።

ለዚህ አንዱ መሠረት የሚሆነው ደግሞ ብሔራዊ መታወቂያ(ፋይዳ) የተሰኘው የመታወቂያ ዓይነት ነው። ፋይዳ መታወቂያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ለዜጎች እየተሰጠ ይገኛል። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የፋይዳ መታወቂያ ምንነት፤ ሀገራዊ ጠቀሜታ እና ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር ያለው ጥቅም ምንድን ነው ስንል ለፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ዋና አስተባባሪ ለአቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ ጥያቄዎችን አቅርበናል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡የብሔራዊ መታወቂያ አጀማመር ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከማየት ብንጀምር?

አቶ ዮዳሄ፡የመታወቂያ ወረቀትን እንደ መተማመኛ የተጠቀሙት ስዊዘርላንዶች ናቸው። ስዊዞች ይህንን ማድረግ ያስፈለጋቸው ደግሞ የሰዎች ዝውውር የተቀላጠፈ እንዲሆንና የንግድ ልውውጡም የሰፋ እንዲሆን ከማሰብ ነው። በተወሰነ አካባቢ ታጥሮ የነበረውን የሰዎች እና የሸቀጦች ዝውውርን በፈጠሩት መታወቂያ የተነሳ ወደ ሰፊ አካባቢ ማዳረስ ችለዋል።

ቀረብ ወዳለው ጊዜ ስንመጣ ደግሞ አሜሪካኖች ሶሻል ሴኩሪቱ ቁጥር ከጀመሩ 100 ዓመታት አልፏቸዋል። 1900 ላይ አሜሪካ ውስጥ እያንዳንዱ አሜሪካዊ የሶሻል ሴኩሪቲ ቁጥር ነበረው። እያንዳንዱ ሰው የወረቀት መታወቂያ ማሳየት አይጠበቅበትም። መለያ የሆነውን ቁጥር በማሳየት ብቻ ማንነቱን መግለጽ ይችላል። ለምሳሌ ትራፊክ ቢያስቆመው መንጃ ፍቃድ ወይም መታወቂያ ሳያስፈልገው መለያ የሆነውን ቁጥር በመንገር ብቻ ከትራፊኩ ጋር መግባባት ይችላል። እኛ ሀገር ሲደረግ እንደቆየው አንድ ሰው የትራፊክ ጥሰት ቢፈጽም ታርጋውን መንቀል ወይም መንጃ ፈቃዱን መንጠቅ ሳያስፈልግ በሰውዬው መለያ ቁጥር በመግባት አስፈላጊውን ቅጣት መቅጣት ይችላል።

አዲስ ዘመን፡በአሁኑ ወቅት በኢትዮ ጵያ ብሔራዊ መታወቂያ እንዲኖር ያስፈለ ገበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ዮዳሄ፡ኢትዮጵያ 1284/2015 የዲጂታል መታወቂያ አዋጅን አጽደቃለች። ይህ አዋጅ ያስፈለገበት ምክንያት በመግቢያው ላይ በዝርዝር ተቀምጧል። ዲጂታል መታወቂያ በርካታ ጥቅሞች አሉት። ከብሔራዊ ደህንነት፤ ከመልካም አስተዳደር፤ ከሥራ ቅልጥፍና፤ ከኢኮኖሚ እድገት እና ከመሳሰሉት አንጻር ዲጂታል መታወቂያ የማይተካ ሚና ይጫወታል። አሁን ከደረስንበት ዓለም አቀፋዊም ሆነ ሀገራዊ ሁኔታ አንጻር ያለ ዲጂታል መታወቂያ እድገትን ማረጋገጥ አንችልም።

ቴክኖሎጂ ዓለምን እየቀየረ ነው። የተቀየረ ዓለም ደግሞ የተቀየረ አሠራር ይፈልጋል። ቀደም ሲል በወረቀት ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች በሙሉ አሁን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውስጥ ገብተው ሰው ባለበት ሆኖ አገልግሎቱን የሚያገኝበት አገልግሎት እውን ሆኗል። ቀደም ሲል ሰዎች መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ቀበሌ ወይም ሌላ አንድ መንግሥታዊ ተቋም የመሄድ ግዴታ ነበረባቸው። ዛሬ ግን አገልግሎቱ ቤታቸው ድረስ እየመጣ ነው። ፊት ለፊት አገልግሎት ሰጪና ተቀባይ የሚገናኙበት አሠራር እያበቃለት ነው። ውል የሚፈጽሙ ሰዎች እንኳን ‹‹እርጥብ ፊርማቸውን ካላስቀመጡ ውሉ የጸና አይሆንም›› የሚለው የተለመደ አባባል ቀርቶ ዛሬ ዲጂታል ፊርማ እውን ሆኗል።

መታወቂያንም በተመለከተ በርካታ ሀገራት ከወረቀት በመላቀቅ ወደ ዲጂታል መታወቂያ ተሸጋግረዋል። ለዘመናት ስንገለገልበት የቆየነው በቦርሳችን ይዘናት የምንዞረው መታወቂያ በብዙ ሀገራት እየቀረች መጥታለች። በምትኩ የወረቀት ሕትመት ሳይኖር ቁጥር ብቻ የአንድ ሰው መታወቂያ ለመሆን በቅቷል። የወረቀት መታወቂያ ለበርካታ ማጭበርበሮች የተጋለጠ ነው። በቀላሉ ፎርጅድ ስለሚሠራም ዜጎችም ሆኑ ሀገር ለኪሳራ ይጋለጣሉ።

ፎርጅድ በተሠራ መታወቂያ ከባንክ ገንዘብ ይወጣል፤ መሬት ካርታ ይሸጣል፤ ግብር ይጭበረበራል፤ አንድ ሰው ሆኖ በበርካታ ስሞች በርካታ መታወቂያዎችን፤ የንግድ ፍቃዶችን ማውጣት እና የፈለገውን ወንጀል መሥራት ይችላል። ዛሬ ግን ይህ ሁሉ አክትሞለታል። የፊት ዐሻራን ብቻ በመውሰድ ግለሰቡ የትም ቢሄድ የሚታወቅበት አሠራር ተዘርግቶ እየተሠራበት ነው። የፋይዳ መታወቂያም አንዱ ጥቅም ይሄ ነው።

እንደ ቀድሞ ‹‹እኔ ሳላውቅ የባንክ አካውንቴ ውስጥ ገብተው ገንዘቤን አጭበረበሩኝ፤ ፎርጂድ የመሬት ካርታ ሰጡኝ፤ ወዘተ›› የሚሉ አቤቱታዎችን በፋይዳ መታወቂያ መፍታት ይቻላል። ከዚሁ ጎን ለጎን ፋይዳ መታወቂያ አገልግሎትን ለማሳለጥ እና ዜጎች ለሙስና እንዳይጋለጡ ያደርጋል። ለአብነት አንድ ሰው የቤት ኪራይ ውል ለመፈጸም ቀበሌ ወይም ወረዳ መሄድ ይኖርበታል። እዚያ ቁጭ ብሎ ወረፋ መጠበቅ እና መውጣት መውረድ ግድ ይለዋል። በዚህ ሂደት ቢያንስ ቢያንስ ግማሽ ቀን ይወስድበታል።

ይህ ደግሞ ሰውን ያማርራል፤ ሥራ ያስፈታል፤ ሰውዬው ምርታማ ሆኖ ሕይወቱን እንዳያሻሽል እንቅፋት ይፈጥራል። ስለዚህ ይሄን ኋላቀር አሠራር ልንቀርፈው እና በቶሎ ልንሻገረው የሚገባ ነው። ለዚህ ደግሞ ፋይዳ መታወቂያ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። ፋይዳ መታወቂያ ከባሕላዊ አሠራር ወደ ዘመናዊ አሠራር የሚወስደንን መንገድ የሚመቻች እና የሰዎችንም እንግልት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን ነው።

አዲስ ዘመን፡በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ብሔራዊ መታወቂያ የሕዳሴ ግድብ ያህል ሀገራዊ ፋይዳ አለው ሲሉ ተናግረዋል። ምን ማለታቸው ነው?

አቶ ዮዳሄ፤– ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄንን ያሉት ብሔራዊ መታወቂያ ያለውን ሀገራዊ ጥቅም በአግባቡ ስለሚያውቁት ነው። ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታላይዜሽን ባለመግባቷ ምክንያት እያጣች ያለችው ሀብት ከፍተኛ ነው። በየዕለቱ በሚደረጉ ማጭበርበሮች፤ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ያሉ ውጣውረዶች፤ በተደጋጋሚ ንግድ ፍቃዶች የሚሠሩ ደባዎች እና ግብር ስወራዎች፤ ከመሬት ጋር ያሉ ሌብነቶች እና ብልሹ አሠራሮች እና የመሳሰሉት ወደ ኢኮኖሚው ቢመነዘሩ ከፍተኛ ሀብት ለሀገር እና ለሕዝብ የሚያስገኙ ናቸው። እነዚህ ሀብቶች በትክክለኛው መንገድ ወደ ኢኮኖሚው ቢገቡ በርካታ ልማቶችን ለማከናወን የሚያስችሉ ናቸው።

ለአብነት አንድ ምሳሌ ላንሳ። በኢትዮጵያ ውስጥ 2ነጥብ 3 ሚሊዮን የመንግሥት ሠራተኛ አለ። ይህ ሠራተኛ በቁጥር ይገለጽ እንጂ በአካል ይገኝ፤ አይገኝ ለማወቅ ያስቸግራል። በማኑዋል አሠራር በየክልሉ ባሉ ተቋማት ያሉ ሠራተኞችን ጥርት አድርጎ ለማወቅ ያስቸግራል። ወደ ነጋዴውም ስንመጣ ሰዎች በሠሩት ልክ አለመክፈል እና ጭራሹንም ሰዎች ከነገዱ በኋላ አድራሻቸውን መሰወር የተለመደ ሆኗል። ከሕግ አንጻር ብንመለከተው አንድ ጥፋት ያጠፋ ሰው የፍርድ ሂደቱን ጨርሶ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ የሚታሰረው ሰው ግን ሌላ ሊሆን ይችላል። በገንዘብ ወይም በመደለያ አጥፊው ሌላ ታሳሪው ሌላ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ።

በሌላም በኩል አንድ ሰው ሁለት ቦታ ተመሳሳይ ክስ የሚመሰረትበት አጋጣሚ አለ። በአንድ ጉዳይ አዳማ እና አዲስ አበባ ክስ መስርቶ ሊከራከር ይችላል።ሕጉ የሚፈቅደው ግን በአንድ ጉዳይ አንድ ክስ ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ተደጋጋሚ ወንጀል ፈጽሞ እሱ መሆኑን ለመለየት ችግር የሚሆንበት ጊዜ አለ። የተለያዩ ወንጀሎችንም ፈጽሞ ከተማ እየቀያየረ መኖር ይችላል። በአጠቃላይ እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በዘመናዊ አሠራር ነው። ኢትዮጵያ የጀመረችውም ብሔራዊ መታወቂያ ይህንን ችግር የማስወገድ ብቃት አለው።

አዲስ ዘመን፡የፋይዳ መታወቂያ ከሌሎች የመታወቂያ ዓይነቶች በምን ይለያል?

አቶ ዮዳሄ፡በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያሉት የመታወቂያ ዓይነቶች ሁለት ዓይነት ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው። አንደኛው ማንነትን የሚገልጸው በተለምዶ የቀበሌ መታወቂያ ሲሆን ሁለተኛው አገልግሎት ተኮር የሚባለው ነው። ይህም እንደ ፤ የመንጃ ፍቃድ፤ ፓስፖርት እና የመሳሰሉትን የሚያካትት ይሆናል። እነዚህም አገልግሎት የሚሰጡት በዋናነት ለተዘጋጁላቸው ጉዳዮች ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው። የፋይዳ መታወቂያ ዓይነት ያለው አላማ የያዘ መሠረታዊ መታወቂያ ግን እስካሁን በሀገሪቱ አልነበረም። መሠረታዊ መታወቂያ ማለት የአንድን ሰው ማንነት በልዩነት ማሳየት የሚያስችልና ሁሉንም ዓይነት የመንግሥትና የግል አገልግሎቶች በአንድ መታወቂያ ሊያስጠቅም የሚያስችል ማለት ነው። የፋይዳ መታወቂያ ከየትኛውም የሀገሪቱ ቦታ እና የማህበረሰብ ክፍል የሚመጡ ዜጎችን አካታች በሆነ መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ይሆናል። መታወቂያው በሀገር ውስጥ ላሉ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጪም በመኖሪያ ፈቃድ፤ በሥራ ፈቃድ፤

 

በትምህርትና ሌሎች ጉዳዮች ከሀገር የወጡትንም ተጠቃሚ ያደርጋል። በተጨማሪ የውጭ ሀገር ሰዎችንና ስደተኞችንም የሚያካትት ይሆናል።

ፋይዳ መታወቂያ በብሔራዊ ደረጃ ወጥ የሆነ ይዘቶች ያሉት እና የትም የሚያገለግል ነው። ምሳሌ የአዲስ አበባ መታወቂያ አብዛኛው አገልግሎት የሚሰጠው ለአዲስ አበባ እና አካባቢው ነው። ፋይዳ መታወቂያ በርካታ መረጃዎችን በአንድ ላይ የያዘ እና ከግለሰቦች የሚሰበሰቡት መረጃዎችም ዓለም አቀፋዊ መስፈርቶችን ያሟላ ነው። ሆኖም ፋይዳ መታወቂያ ሌሎችን መታወቂዎች ይተካል ማለት አይደለም። ፋይዳ መታወቂያ ከሌሎቹ መታወቂያዎች ጋር እንዲናበብ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው እንጂ ሌሎችን መታወቂያዎች የሚተካ አይደለም። ፋይዳ መታወቂያም አገልግሎት እየሰጠ ሌሎችም መታወቂያዎች አገልግሎታቸውን ይቀጥላሉ ማለት ነው።

አንድ ምሳሌ ባነሳ፤ ‹‹ቲን ነምበርህን ካላመጣህ ንግድ ፈቃድህን አላድስልህም፤ ወይም የመንጃ ፈቃድ ቁጥርህን ካላስታወስከው መንጃ ፈቃድህ አይታደስም›› የሚለው ክልከላ ከዚህ በኋላ አይኖርም። ‹‹የመሬት ይዞታን ለማረጋገጥ ካርታ ይዘህ ና የሚለው›› አባባል ይቀራል ማለት ነው። ፋይዳ መታወቂያ ዲጂታል ስለሆነ እና ከተለያዩ አገልግሎቶች ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የፋይዳ ቁጥርን በማስገባት ብቻ ሁሉንም አገልግሎቶች ማግኘት ያስችላል። በሌላ አነጋገር አንድ ሰው የፋይዳ ቁጥሩን ተናግሮ ብቻ ሁሉንም አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችለው እና ፋይል ይዞ ከመዞር የሚያወጣው ነው። ስለዚህም ፋይዳ መታወቂያ የዜጎችን ሕይወት ያቀላል ማለት ነው።

በቀጣይ መንጃ ፈቃድ ለማደስ በአካል መገኘት አያስፈልግም። በቅርብ ጊዜ ውስጥ አንድ ሰው ቤቱ ቁጭ ብሎ ስልኩ ላይ መንጃ ፈቃድ ማደስ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን። ጎረቤት ሀገር ኬንያ እኮ መንጃ ፈቃድ የሚታደሰው ስልክ ላይ ነው። ኢትዮጵያም ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ያለችው አገልግሎቶችን ከሰው ንክኪ ነፃ ለማድረግ ነው። በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ በርካታ አገልግሎቶች ከሰው ንክኪ የጸዱ ይሆናሉ። ይህ ሲሆን አገልግሎቶችን በገንዘብ መግዛት፤ ጉቦ መስጠት፤ መውጣት መውረድ፤ ለአንድ አገልግሎት ቀን ሙሉ መዋል እና የመሳሰሉት እንግልቶች ይቀራሉ። በዚህም የዜጎች እርካታ ይጨምራል፤ በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት ይጨምራል።

ከላይ እንደገለጽኩትም የተለያዩ ወንጀሎችን ሰርቶ መሸሸግ አይችልም። ስለዚህም አንድ ሰው ወንጀል ሰርቶ መሸሸግ እንደማይችል ስለሚያውቅ ወንጀል ከመሥራት መቆጠቡ አይቀርም። አንድ ሰው በተለያዩ ስሞች የተለያዩ ንግድ ፈቃዶችን በማውጣት ሊያጭበረብር አይችልም። ከግብር ስወራ ጋር በተያያዘም መንግሥት ትክክለኛውን ግብር እንዲያገኝ ያስችለዋል። አንድ ሰው የመሬት ካርታ ቢጠፋበት አሁን ባለው አሠራር መሬት አስተዳደር ሄዶ፤ አመልክቶ ቢያንስ ሶስት ወራት መጠበቅ አለበት። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ግን ሰዎች ከስልካቸው የመሬት ካርታቸውን አውርደው ለሚፈልጉት ዓላማ ማዋል ይችላሉ። የተጭበረበረ የመሬት ካርታ የመሳሰሉት የማጭበርበሪያ ስልቶች ሊኖሩ አይችሉም።

በፋይዳ መታወቂያ ሙሉ ለሙሉ ጥርጣሬዎች እና ማጭበርበሮች ይቀራሉ። ፋይዳ መታወቂያ የመተማመኛ ማሕቀፍ ነው ሲባል ጥርጣሬዎችን እና ማጭበርበሮችን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ ስለሚያስችል ነው። ሰነድ ጠፋ፤ ሰነድ ተሰወረ የሚሉ አባባሎች ሙሉ ለሙሉ ይቀራሉ ማለት ነው። ሌሎቹ መታወቂያዎች ግን ይህንን የማድረግ አቅም የላቸውም።

አዲስ ዘመን፡በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ መታወቂያ ለምን ያህል ዜጎች ተዳርሷል ?

አቶ ዮዳሄ፡የፋይዳ መታወቂያ በሀገር አቀፍ ደረጃ መሰጠት የተጀመረው በ2015 ዓ.ም ነው። አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ 11 ሚሊዮን ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ ወስደዋል። በ2017 መጨረሻ ደግሞ 30ሚሊዮን ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ እንዲያገኙ እየተሠራ ነው። የሰዎች ግንዛቤ እየተሻሻለ በመምጣቱ የብሔራዊ መታወቂያ ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት አለ። አብዛኛው ኢትዮጵያ የብሔራዊ መታወቂያ እንዲኖረው ይፈልጋል። ሆኖም ከላይ እንደጠቀስኩት በማጭበርበር እና በወንጀል ውስጥ መቆየት ከሚፈልጉት ጥቂት ሰዎች በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚባል መልኩ የብሔራዊ መታወቂያ ባለቤት ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት አለው። በአሁኑ ወቅትም በሁሉም ክልል እና ከተማ አስተዳደሮች ብሔራዊ መታወቂያ እየተሰጠ ነው።

ሆኖም እዚህ ጋር የሚታዩ ክፍተቶችን ማረም ይገባል። አንዳንድ ባንኮች አካውንት ቁጥር ካልከፈታችሁ ፋይዳ መታወቂያ አንሰጣችሁም የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን እንደሚያስቀምጡ ደርሰንበታል። ይሄ አግባብ አይደለም። ፋይዳ መታወቂያን ለማግኘት የሚቀመጥ ቅድመ ሁኔታ የለም።

አዲስ ዘመን፡ሰዎች ብሔራዊ መታወቂያ ባለማውጣታቸው የሚከለከሉ አገልግሎቶች አሉ?

አቶ ዮዳሄ፡በጣም ጥቂት ከሆኑ አገልግሎቶች በስተቀር አብዛኛው አገልግሎት የብሔራዊ መታወቂያን የግድ የሚሉ አይደሉም። ከግብር፤ ሴፍቲኔት፤ ከመሳሰሉት እና ለመጭበርበር የተጋለጡ ዘርፎች ካልሆኑ በስተቀር አገልግሎት ለማግኘት የብሔራዊ መታወቂያ ግዴታ አይደለም። በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጂታል ካውንስል የሚባል አለ፤ ይህ ካውንስል በብሔራዊ መታወቂያ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን እየለየ በየጊዜው ማስተካከያ እየሰጠ ስለሚሄድ ችግሮች ከስር ከስሩ እየተቃለሉ ይሄዳሉ። ሆኖም ብሔራዊ መታወቂያ ካላወጣችሁ አገልግሎት አታገኙም የሚሉ ተቋማት ካሉ አሠራራቸው ትክክል ስላልሆነ ሊያስተካክሉ ይገባል።

አዲስ ዘመን፡በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ፋይዳ መታወቂያን ለማግኘት ረጃጅም ሰልፎች ይታያሉ፤ ከምን የመነጨ ነው ?

አቶ ዮዳሄ፡መጀመሪያ መታወቅ ያለበት ፋይዳ ቁጥር ነው። አገልግሎትም ለማግኘት የሚያስፈልገው ቁጥር እንጂ ካርዱ አይደለም። ካርዱ በፍላጎት የሚወጣ እንጂ አስገዳጅ አይደለም። ያው፤ ብዙዎቻችን መታወቂያ ሲባል የምናገናኘው ከካርድ ጋር ስለሆነ እንጂ ካርድ ማሳተም ግዴታ አይደለም። የሰውዬው መለያ ቁጥሩ እንጂ ካርዱ አይደለም። ስለዚህም ከወረቀት አስተሳሰብ መውጣት አለብን። የፋይዳን መታወቂያ ለማሳተም ወረፋ መጠበቅ የለብንም። ካርዱን ሳያሳትሙ በቁጥሩ ብቻ መገልገል ይቻላል።

ለምሳሌ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት አንድ ሰው ንግድ ቢሮ ሲሄድ የሚጠየቀው ቁጥሩን እንጂ ካርዱን መሆን የለበትም። የሰውዬው መታወቂያ ቁጥሩ እንጂ ካርዱ አይደለም። ካርድ ማሳተም እንደመስፈርት መቀመጥ የለበትም። የፋይዳ መታወቂያ ቁጥር እንጂ ካርድ አይደለም። ስለዚህም መሰለፍ እና ጊዜ ማባከን አይገባም። በተለይ በአሁኑ ወቅት ሁሉም የቴሌ እና የፖስታ ቤት እንዲሁም ፍቃድ ያገኙ ተቋማት አገልግሎቱን እየሰጡ ስለሆነ ሰዎች አቅራቢያቸው ወደሚገኙ አገልግሎት ሰጪዎች በመሄድ ያለ ሰልፍ መገልገል ይችላሉ።

አዲስ ዘመን፡አንዳንድ ተቋማት ቴሌና ፖስታ ቤትን ጨምሮ ካርድ በክፍያ ይሰጣሉ፤ ይህ አግባብ አይደለም ማለት ነው?

አቶ ዮዳሄ፡ይህ ግለሰቦች የፍላጎት ጉዳይ ነው። ከፈለጉ ካርድ አሳትመው መያዝ ይችላሉ፤ ካልፈለጉም ቁጥሩን በቃላቸው ይዘው ማንኛውንም አገልግሎት ማግኘት መብታቸው ነው። ግለሰቦችን ጨምሮ አንተም እንደጠቀስከው ቴሌ እና ፖስታ ቤት ጭምር ካርድ እያተሙ ይሰጣሉ። ይሄ ምንም ችግር የለውም። ካርድ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሰዎች ቢፈልጉ ከግለሰቦች አሊያም ከቴሌም ሆነ ፖስታ ቤት አሳትመው መጠቀም መብታቸው ነው። ሆኖም አንዳንድ ግለሰቦች ፎቶ ሾፕ በመሥራት ሀሰተኛ መታወቂያ እንደሚያትሙ መረዳት እና መጠንቀቅ ይገባል። በነገራችን ላይ ቤቱ ወይም ቢሮው ፕሪንተር ያለው ሰው ፖርታል ውስጥ ገብቶ የራሱን ፋይዳ መታወቂያ ማተም ይችላል። የተለየ ሚስጢር የለውም።

አዲስ ዘመን፡ኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያን ተግባራዊ ማድረጓ በኢኮኖሚዋ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ምን ያህል ነው?

አቶ ዮዳሄ፡– የብሔራዊ መታወቂያ በኢኮኖሚ ላይ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በተመለከተ የተደረጉ ጥናቶች አሉ። እነዚህ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የብሔራዊ መታወቂያ ተግባራዊ መደረጉ በኢትዮጵያ ላይ የ7 በመቶ ተጨማሪ ዕድገት ለማስመዝገብ ያስችላል። አሁን ኢትዮጵያ 200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ጂዲፒ ያላት ሀገር ነች። ስለዚህ የዚህን ሰባት በመቶ ተጨማሪ ሀብት ማስገኘት ያስችለናል ማለት ነው።

በኢኮኖሚው ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከሁሉም በላይ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። በዚህ ረገድ በመንግሥት በኩል ያለው ሲታይ ሁሉንም ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ማድረግ ግብር በሚሰበሰብበት ወቅት ከአንድ በላይ መታወቂያ በመያዝ ይከሰቱ የነበሩ ማጭበርበሮች ይቆማሉ። በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መታወቂያ የሌለው ማህበረሰብ የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት መሆኑ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያስችለው ይሆናል። ለምሳሌ የባንክ አካውንት መክፈት፤ የቴሌኮም ስልክ ሲም ካርዶች ማውጣት እና የመሳሰሉትን ባለማግኘቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የማህበረሰብ ክፍል መደበኛውን የኢኮኖሚ ሥርዓት ሳይቀላቀል ቆይቷል።

ዛሬም ድረስ ጥቂት የማይባሉ የማህበረሰብ ክፍሎች መታወቂያ ባለመያዛቸው የገንዘብ ዝውውር የሚፈጽሙትም ሆነ ገንዘባቸውን እያስቀመጡ ያሉት ተገቢ ባልሆነ መንገድ በየቤታቸው ነው። የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ ከዚህ ቀደም የተካሄደ ጥናት እንደሚያመለክተው እንደ ሀገር የብሔራዊ መታወቂያ መተግበር በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት በር የሚከፍት ይሆናል።

በተጨማሪ የፋይዳ መታወቂያ እንደ ሀገር ማንነትን የሚገልጽ ብቻ በመሆኑ እስካሁን ከነበረው በተሻለ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት ላይ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተተገበሩ ያሉት መታወቂያዎች በማንነትና በመልክዓ ምድር የተገደቡ ናቸው። ይህ ደግሞ ዜጎች ከቦታ ቦታ እንደልብ ለመንቀሳቀስ ተግዳሮት የሚፈጥሩ ሆነው ቆይቷል። ለቀጣይ ግን የፋይዳ መታወቂያ የያዘ ማንኛውም ግለሰብ በፈለገበት የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ማንነቱን በሚገልጸው መታወቂያ ይደርስበት የነበረውን ችግር ያስቀርለታል። በጥቅሉ የፋይዳ መታወቂያ መኖር ራስን ለማንቀሳቀስም ሆነ የተለያዩ መንግሥታዊና የግል አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ለማስገኘት የሚያስችል በመሆኑ ዜጎች ትኩረት በመስጠት በየአቅራቢያቸው ባሉ የመመዝገቢያ ጣቢያዎች በመገኘት ምዝገባውን ሊያከናውን ይገባል።

በተመሳሳይ ወንጀልን በመከላከልም ረገድ የፋይዳ መታወቂያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል ነው። ወንጀልና የማጭበርበር ተግባራትን የሚያከናውኑ አካላት አንድም ወንጀሉን በሚፈጽሙበት አልያም ከዛ በኋላ ማንነታቸውን መደበቃቸው አይቀርም። የፋይዳ መታወቂያ ተግባራዊ መሆን በአንድ በኩል ወንጀል ለመሥራት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ማንነታቸውን እንዳይደብቁ የሚያደርግ ይሆናል። በሌላ በኩል የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ወንጀል እና የማጭበርበር ተግባራትን ያከናወኑ አካላት እንደ ከዚህ ቀደሙ የተለያዩ ሀሰተኛ መታወቂያዎችን በመያዝ የሚደበቁበት እድል አይኖራቸውም። በኢትዮጵያም ገና ከጅምሩ ይህንን ሊያረጋግጡ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ከአዲስ አበባ እና ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች እንዲሁም ከፌዴራል ፖሊስ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። በተግባርም ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መተግበር ከጀመረ በኋላ ከተለያዩ ቦታዎች የቀበሌ መታወቂያ አውጥተው ወንጀል ይሠሩ የነበሩ በርካታ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተችሏል። ይህ ሲጠናቀቅ ደግሞ በተለይም እንደዚህ ዓይነት የጥፋት ተግባራት በስፋት ለሚስተዋሉባቸው ክልሎችም መፍትሔ መሆኑ አይቀርም።

አዲስ ዘመን፡ስለነበረን ጊዜ ከልብ እናመሰግናለን።

አቶ ዮዳሄ፡እኔም ስለሰጣችሁን እድል ከልብ አመሰግናለሁ።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You