ለግብርና ኢንቨስትመንት ከተላለፈው መሬት እየለማ ያለው ከ50 በመቶ አይበልጥም

አዲስ አበባ፡- ለግብርና ኢንቨስትመንት ከተላለፈው ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እየለማ የሚገኘው ከ50 በመቶ እንደማይበልጥ ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የሚኒስቴሩን የስድስት ወር አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ እስከአሁን እንደ ሀገር ለኢንቨስትመንት የተላለፈው የመሬት ይዞታ በአጠቃላይ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ እስካሁን የለማው መሬት 50 በመቶ አይበልጥም፡፡

ዋናው ተግዳሮት መሬት መስጠት አይደልም የሚሉት ሚኒስትሩ፤ እስካሁን ለኢንቨስትመንት ከተሰጠው መሬት ላይ እየለማ ያለው ከ50 በመቶ አይበልጥም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በግብርና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍቃድ አውጥተውና መሬት ወስደው ወደ ልማት ያልገቡ ወደ ልማት እንዲገቡ ከባለሀብቶቹና ከሚመለከታቸውባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ መድረኮች ወይይት መደረጉን አውስተው፤ ሰፋፊ እርሻዎች ያሉባቸው ቆላማ አካባቢዎች ከጸጥታና ከመሠረተ ልማት ጉዳዮች ላይ ቅሬታዎች እንደሚነሱ ነው የተናገሩት፡፡ ከዚህ መነሻነትም ክልሎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ መሬት የወሰዱ ባለሀብቶች ቶሎ ወደ ሥራ እንዲገቡ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ከግብርና ኢንቨስትመንት አንጻር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድርሻ መሬት በመለየት ካርታ የማውጣት እና የቴክኒክ ድጋፎችን ማድረግ እንደሆነ ገልጸው፤ መሬቱን የሚያስተላልፉት ክልሎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት የመሬት ልየታ ከማድረግ፣ ለሆልቲ ካልቸር እና ለሰብል ልማት ለባለሀብቶች ለእርሻ ኢንቨስትመንት የሚሆን መሬትን ከማስተላለፍ አንጻር የተከናወነው አፈጻጸም ጥሩ የሚባል መሆኑን አመልክተው፤ ነገር ግን ለእንስሳት እርባታ የሚውል መሬት በማስተላለፍ ረገድ የሚቀር ነገር አለ ብለዋል፡፡

ግርማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 48 ሺህ ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ለመለየት ታቅዶ፤ 117 ሺህ ሄክታር መሬት መለየት

ተችሏል፡፡ ለአብነትም ለሰብልና ሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት 70 ሺህ ሄክታር መሬት ለማስተላለፍ ታቅዶ 88 ሺህ ሄክታር መሬት ለማስተላለፍ ተችሏል፡፡ ይህም ከተቀመጠው እቅድ በላይ ነው፡፡

ለእንስሳትና ዓሳ ልማት ኢንቨስትመንት 17 ሺህ ሄክታር መሬት ለማስተላለፍ ታቅዶ 11 ሺህ ሄክታር መሬት የተላለፈ ሲሆን፤ ከእቅድ አንጻር 64 በመቶ ነው፡፡ ለሰፋፊ እንስሳት እርባታ ኢንቨስትመንት በበጀት ዓመቱ 20 ሺህ ሄክታር መሬት ለማስተላለፍ ታቅዶ፤ በስድስት ወር ስምንት ሺህ ሄክታር መሬት ተላልፏል ብለዋል፡፡

በተያያዘም በግማሽ ዓመቱ 133 ሺህ ቶን የቡና ምርት ለመላክ ታቅዶ 204 ሺህ ቶን የቡና ምርት ለውጭ ገበያ መላኩን ገልጸው፤ ሻይና ቅመማ ቅመም ስምንት ሺህ ቶን ለመላክ ታቅዶ ዘጠኝ ሺህ ቶን ተልኳል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት 113 ሺህ ቶን አትክልት ለመላክ ታቅዶ 66 ሺህ ቶን አትክልት ለውጭ ገበያ መቅረቡን አመልክተው፤ 55 ሺህ ቶን አበባ ለመላክ ታቅዶ 47 ሺህ ቶን አበባ እና 33 ሺህ ቶን ፍራፍሬ ለመላክ ታቅዶ 20 ሺህ ቶን የፍራፍሬ ምርት መላኩን ገልጸዋል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ጥር 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You