በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉ ተቀማጭ ገንዘብ ሁለት ነጥብ 74 ትሪሊዮን ብር ደርሷል

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ተቀማጭ ገንዘብ ሁለት ነጥብ 74 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ። ከዚህ በተጨማሪም የፋይናንስ ተቋማት ብድር ሁለት ነጥብ 72 ትሪሊዮን መድረሱን ዋና ገዢው ጨምረው ገልጸዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉ ተቀማጭ ገንዘብ ሁለት ነጥብ 74 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። ከዚህ የምንረዳው የባንኮች አቅም ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ያሳያል። የሀገሪቱ ባንኮች ከዓመት ዓመት በተቀማጭ ገንዘብ፣ አጠቃላይ ባላቸው የፋይናንስ እሴት በጣም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በቅርቡ የውጭ ባንኮች ሀገር ቤት ገብተው እንዲሠሩ የጸደቀው አዋጅ በዋናነት የውጭ ባንኮች እና ኢንቨስተሮች በባንክ መስክ ተሰማርተው ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ነው ያሉት አቶ ማሞ፤ በተጨማሪም የዘርፉን ተወዳዳሪነትና ውጤታማነት በማሻሻል ባንኮች በኢኮኖሚው ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና ከፍ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ማሞ ገለጻ፤ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ወደፊት ማስኬድ የሚችሉት የሀገር ውስጥ ባንኮች ናቸው። የባንክ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ ማለት የኢትዮጵያ ባንኮች ችግር ላይ ይወድቃሉ ማለት አይደለም። ባንኮቹ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው የሀገር ውስጥ ባንኮች አዳዲስ አሠራርና አገልግሎት ተምረው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ይጨምራል የሚል እምነት በመኖሩ ነው።

የውጭ ባንኮች በባንክ ዘርፍ ላይ የሚገቡበት መንገድ በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ስር መሆኑን ጠቅሰው፤ የውጭ ባንኮች ሲመጡ የሀገራችን ባንኮች ይፈርሳሉ የሚለው ስጋት ትክክል አለመሆኑን አብራርተዋል።

ባንኮች በሂደት አቅማቸውን እያጠነከሩ በሄዱ ቁጥር እንደ ስትራቴጂያቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሠሩት ሁሉ ሌላ ሀገር ሄደው ሊሠሩ የሚችሉበት ሁኔታ ወደፊት ሊፈጠር እንደሚችልም አመልክተው፤ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ዘርፉ ጤናማ እና ተወዳዳሪ እንዲሆን ይሠራል፤የኢትዮጵያ ባንኮችም ሀገር ውስጥ ያለውን ሰፊ ገበያ ከማርካት አልፈው ወደ ሌሎች ሀገራት የሚሄዱበት አሠራር በሂደት የሚታይ ይሆናል ነው ያሉት።

ከዚህ በተጨማሪም የባንኮች ውህደት አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ የተረጋጋ እንዲሆን በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ አለው ያሉት አቶ ማሞ፤ የተቆጣጣሪ አካል የሚያወጣውን ሕግ የበለጠ አክብረው ሥራቸውን የሚሠሩበት ቁመና ላይ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ ማሞ፤ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሥርዓቱን የመቆጣጠር አቅም አንጻራዊ እና ሂደት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፤ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ በእስከአሁኑ ሁኔታ እንደ ብሔራዊ ባንክ የአቅም ግንባታ እና ተያያዥ የሆኑ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኘ ገልጸዋል።

በቀጣይም ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ በራሱ ሊያስገኝ የሚችለው አቅም እንደተጠበቀ ሆኖ የተጀመሩ የአቅም ግንባታ እና የሪፎርም ሥራዎች ጎን ለጎን ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥር 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You