
አዲስ አበባ፦ ፋብሪካው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የድንጋይ ከሰል ምርት ከማሻሻል ባሻገር ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል እንደፈጠረ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የተገነባውን የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ትናንት መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በዳውሮ ዞን የተገነባውን የኢቲ ማዕድን ልማት አ.ማ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ መርቀን ሥራ አስጀምረናል ብለዋል።
ፋብሪካው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የድንጋይ ከሰል ምርት ከማሻሻል ባሻገር ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል እንደፈጠረም አስታውቀዋል።በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን ለልማት ለማዋል በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የግሉ ዘርፍ ይበልጥ ተሳታፊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ይህ ሥራም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
የጎበኘነው ልማት የሚያሳየው የተገለጠ ዓይን እና የጠራ ሃሳብ ሲኖር በአጠረ ጊዜ ውስጥ ሀገር መቀየር የሚያስችል ዕድል መኖሩን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፣እንዲህ ያለው ዕድል ተግቶ የማየት እና የመሥራት ልምምድ ሲጨመርበት ደግሞ በአጭር ጊዜ ከድህነት ለመውጣት እንድንችል ያደርገናል ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ ኢኮኖሚው ብዝኃ ዘርፍ እንዲሆን በማድረግ አዲስ የእይታ መስክ ተፈጥሮ ሲሠራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።ይህን ተከትሎ ከዚህ በፊት በቱሪዝም እና በማዕድን ልማት እምብዛም የማይታወቀው ዳውሮ ዞን ቀደም ሲል በሀላላ ኬላ የቱሪስት መዳረሻ የጀመረው የአካባቢው ለውጥ አሁን ደግሞ በማዕድን ልማት ቀጥሎ የአካባቢው እምቅ አቅም እየወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማዕድን ዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተደብቀው የነበሩ የተፈጥሮ ፀጋዎች ለሕዝብ ጥቅም መዋል ጀምረዋል ያሉት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የክልሉን ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን አንስተዋል።
ክልሉ በግብርና ልማት በስፋት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ እምቅ የማዕድን ጸጋ የሚገኝበት መሆኑንም አመልክተው፤እንደ ሀገር ለማዕድን ዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተደብቀው የቆዩ የከበሩ የማዕድን ጸጋዎች ለሕዝብ ጥቅም መዋል መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካም መንግሥት ጸጋን መለየት እና ሀብት መፍጠር ላይ ስኬታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ማሳያ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የፋብሪካው መገንባት ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሪ ጫናን የሚቀንስ መሆኑንም አመላክተዋል።
ለአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትና ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) በዚሁ ወቅት የተመረቀውን ፋብሪካ ጨምሮ በዚህ ዓመት ተጠናቀው ወደ ሥራ የሚገቡ አራት የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ምርቱን በመተካት የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የታጠበ የድንጋይ ከሰል ከውጪ ስታስገባ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅም መሥራት ሲጀምሩ በዓመት ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል በተጨማሪ እስከ 400 ሺህ ቶን ትርፍ ማምረት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ተመርቆ ሥራ የጀመረው ፋብሪካም በዓመት 450 ሺህ ቶን ያለቀለትና ጥራት ያለው የድንጋይ ከሰል ማምረት እንደሚችል ተናግረዋል።
ይህም የሀገሪቱን 25 በመቶ የድንጋይ ከሰልን ፍላጎት እንደሚሸፍንም ነው የጠቆሙት።
ፋብሪካው በዓመት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል የመፍጨት አቅም እንዲኖረው የሚያስችል ማስፋፊያ እንደሚደረግለት የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ በፍቃዱ አሰፋ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
በተያያዘ ዜናም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በጅማ ከተማ ገብተዋል። ከተማዋ ሲገቡም የጅማ ከተማ ሕዝብ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር