ከአንድ ሺ 500 በላይ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችለውን የቀርከሃ ተክል ህንድ፣ ቻይና፣ ጃፓን እና ሌሎች ሀገራት በአግባቡ እየተጠቀሙት ይገኛሉ። ሀገራቱ ቀርከሃን በመጠቀም የተለያዩ ቁሳቁሶችን ከመስራት ባለፈም ለመድኃኒት ቅመማ እንዲሁም ዘመን ተሻጋሪ ድልድዮችን እየሰሩበት ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፤ ለምግብነት የሚውል የቀርከሃ ዝርያም መኖሩ ይነገራል።
ሀገሪቷ ምንም
እንኳን ቀርከሃን እንደ
ቻይና ህንድና ሌሎች
ሀገራት ባትጠቀምበትም ከቅርብ
ጊዜ ወዲህ የተለያዩ
ቁሳቁሶች፣ ጌጣ ጌጦችን
እና ሎጂዎችን በመስራት
ጭምር ቀርከሃን ጥቅም
ላይ በማዋል የሥራ
ዕድልም እየተፈጠረበት ይገኛል።
በዛሬው የስኬት እንግዳችንም
በቀርከሃ ሥራ ተቀጥረው
ከመስራት ጀምረው የራሳቸውን
ድርጅት ከፍተው የተለያዩ
የቀርከሃ ምርቶችን በማምረት
እንዲሁም የተለያዩ ሆቴሎችን
በባህላዊ መንገድ በቀርከሃ
የማሳመር ሥራ ላይ
የተሰማሩ ግለሰብን የሥራ
እንቅስቃሴ የሚዳስስ ነው።
የቀርከሃ ሥራዎች ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ መግባር ቢረሳው ይባላሉ። ትውልድና ዕድገታቸው ቀርከሃ በብዛት ከሚበቅልበት ኢንጅባራ ነው። ተወልደው ባደጉበት ኢንጅባራ አካባቢ ቀርከሃ ሲበቅል ሲያድግና በባህላዊ መንገድ አገልግሎት ሲሰጥ እያታዘቡ አድገዋል። ለቀርከሃ እጅግ ቅርብ ከመሆናቸው የተነሳ ጥቅሙንና አይነቱን በሚገባ ለይተው ያውቁታል። ከቀርከሃ ጋር አብሬ ነው ያደግሁት የሚሉት አቶ መግባር፤ አዲስ አበባ መጥተው ከቀርከሃ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ከሚሰራ ግለሰብ ጋር ተቀጥረው ሰርተዋል። ለቀርከሃ ካላቸው ፍቅር የተነሳም ሙያውን ይበልጥ ለማወቅና በዘርፉ ለመስራት እንዲያስችላቸው የቀርከሃ ምርቶችን ከሚያመርት ባለሙያ ጋር ለሦስት ወራት ከደመወዝ ውጭ በነጻ አገልግለዋል። በጊዜና በጉልበታቸው ዋጋ በመክፈል ሙያውን ቀስመዋል።
ውድ ጊዜና ጉልበታቸውን መስዋዕት በማድረግ ግለሰብ ጋር ተጠግተው ባገለገሉበት ወቅት ሙያውን በሚገባ ተለማምደዋል ። በዚህ ጊዜ ሙያቸውን አዳብረው በግላቸው መስራት እንደሚችሉ ሙሉ ዕምነት ነበራቸው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቀርከሃ ሥራ ውስጥ ተሰማርተው ለሚገኙ ባለሙያዎች ሥልጠና የሚሰጥበት አጋጣሚ ተፈጠረ። እርሳቸውም አጋጣሚውን በመጠቀም የዳበረ ልምድና በእጃቸው ያለውን ሙያ ይዘው ሥልጠናውን ተቀላቀሉ።
ቢሮው በቀርከሃ ሥራ ላይ የተሰማሩ እና ወደ ዘርፉ ለመግባት በዝግጅት ላይ ለሚገኙ 40 ለሚደርሱ ባለሙያዎች ነበር ሥልጠናውን ያዘጋጀው፤ በወቅቱ ሥልጠናውን ሊሰጡ የተዘጋጁት ቻይና ሀገር ሄደው በዘርፉ የሰለጠኑ ሰዎች ናቸው። ይሁንና አሰልጣኞቹ ከሰልጣኞቹ የተሻለና የዳበረ ዕውቀት ይዘው አልቀረቡምና ከአሰልጣኞቹ ይልቅ ሰልጣኞቹ ተሽለው ተገኝተዋል። ከሰልጣኞቹ መካከልም አንዱ የሆኑት አቶ መግባርን ጨምሮ ሌሎች ሰልጣኞች በወቅቱ ያላቸውን ዕውቀት አሳዩ። ቢሮውም ያሳዩትን ዕውቀትና ችሎታ በመገንዘብ እውቅና ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም ስልጠናውን እንዲሰጡ በማድረግ አሰልጣኝ የተባሉትን አሰልጥነው ተመልሰዋል።
በ1996 ዓ.ም መንግሥት በጥቃቅንና አነስተኛ ለመደራጀት በሰጠው እድል ተጠቅመው ሌሎች በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ጋር በመደራጀት ወደ ሥራ ገብተው ሲሰሩ ቆይተዋል። ሁለት ሺ ብር መነሻ ካፒታል ይዘው ወደ ስራ የገባው ማህበር በዘርፉ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ከመንግሥት ባገኙት ቦታ የቀርከሃ ምርቶችን አምርተው ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ሆነዋል። ይሁንና ማህበሩ የነበረው ቆይታ እስከ 2009 ዓ.ም ብቻ ነበር።
‹‹መንግሥት በሚያመቻቸው ዕድል ተጠቅሞ በጋራ ተደራጅቶ መስራት ጠቃሚ ቢሆንም ያደራጀው የመንግሥት አካል በሚያጋጥመው የተለያዩ ችግሮች ምክንያት ወደኋላ መመለስ ያጋጥማል›› ያሉት አቶ መግባር፤ ከመንግሥት ያገኙት የማምረቻ ቦታ በመፍረሱ እንዲሁም የማህበሩ አባላት በገጠማቸው የተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከማህበሩ ሊወጡ ተገድደዋል። ይሁንና አቶ መግባር ሙያው በእጃቸው ያለና የዳበረ በመሆኑ በግላቸው በመስራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማመን በግላቸው መስራት ጀመሩ።
ከ2010 ዓ.ም ጀምረው በግላቸው የተለያዩ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን ከቀርከሃ በመስራት ለገበያ ማቅረብ ጀምረዋል። በተለይም በአሁን ወቅት ሆቴሎችን በባህላዊ መንገድ በቀርከሃ በማሳመር ሎጆችን ይሰራሉ። በሚሰሩት ሥራ እጅግ ደስተኛ የሆኑት አቶ መግባር፤ በአሁን ወቅት በስፋት ሆቴሎችን በባህላዊ መንገድ እያስዋቡ የሚገኙ ሲሆን በቀን በአማካኝ አምስት ለሚደርሱ ሰዎች የስራ ዕድል በመፍጠር አብረው ይሰራሉ። የቀርከሃ ሥራ እጅግ ያስደስተኛል የሚሉት አቶ መግባር በአሁን ወቅት እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለውጠው የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
ለዘርፉ ካላቸው ጥልቅ ፍቅርና ቅርበት የተነሳ የሚሰሩት ሥራ እጅግ ጥራቱን የጠበቀ ለመሆኑ በተለያየ ቦታ የሚገኙት የእጅ ሥራ ውጤቶች ምስክር ናቸው ይላሉ። አንድን ሥራ ለመስራት ሲነሱ ለሥራው የሚያስፈልገውን ቀርከሃ በቅድሚያ ይመርጣሉ ፤ እያንዳንዱ ቀርከሃ ለምን አገልግሎት እንደሚውል ለይተው ያውቃሉ። ለደንበኞቻቸውም የትኛው ሥራ በምን አይነት ቀርከሃ እንደሚሰራና ጉዳትና ጥቅሙን ጭምር ያስረዳሉ። ምክንያቱም ለቀርከሃ ምርት ቅርብ ሆነው አድገዋል። በዚህም የተነሳ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ችለዋል።
ነቀዝ የሚበላቸውና የማይበላቸው የቀርከሃ አይነቶች ስለመኖራቸው የሚናገሩት አቶ መግባር፤ ነቀዝ የሚበላቸውንና የማይበላቸውን በተፈጥሯቸው አይተው ይለያሉ። በመሆኑም ለፈርኒቸር፣ ለአልጋ፣ ለጌጣ ጌጦች የሚውሉትን በቀላሉ በመለየት እንደየአገልግሎት በመጠቀም ያመርታሉ። ለደንበኞቻቸውም ልዩነቱን አስረድተው ለረጅም ጊዜ የሚገለገሉበትን አይነት ሥራ ይሰራሉ። በዚህ የተነሳም አምስትና አራት ዓመታትን ያስቆጠሩ ሥራዎቻቸው አዲስ ሆነው አሉ። ከእነዚህም መካካል ሸጎሌ አካባቢ ናታን ሆቴል፣ ቃሊቲ እሴት ሆቴልና ቤተ ሆቴል፣ ሀና ማርያም ዳሞ ሆቴል እንዲሁም እንቁላል ፋብሪካ እና ሌሎችንም ለአብነት የሚጠቀሱ ሥራዎቻቸው ናቸው።
ሆቴሎቹ ሙሉ ለሙሉ በቀርከሃ ባህላዊ በሆነ መንገድ የሚሰሩ ሲሆኑ፤ በብዛት የሆቴሎቹ መግቢያም ባህላዊ በሆነ የጎጆ ቅርጽ ይሰራል። በሆቴሉ ውስጥ አስፈላጊ የተባሉ ቁሳቁሶች ጭምር በቀርከሃ ይሰራሉ። አጠቃላይ ባህላዊ በሆነ መንገድ ይዋባል። የባህል አዳራሽ ከመስራት ጀምሮ እስከ ሜኑ ወይም የምግብ ዝርዝር የሚቀርብበትን ባህላዊ በሆነ መንገድ በቀርከሃ ይሰራል።
አቶ መግባር በቀርከሃ ከሚሰሯቸው ባህላዊ ጎጆዎችና ሎጆች በተጨማሪ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችና ሥዕሎች በቆዳ ተስለው በቀርከሃ የሚዋቡ የግድግዳ ጌጦች የስራቸው አካል ነው ። ወንበርና ጠረጴዛን ጨምሮ በርካታ መገልገያ ቁሳቁሶችንም ይሰራሉ። በየአካባቢው ለሚገኙ የቡና ጠጡ ቤቶች ውስጥም የቀርከሃ ውጤት የሆኑትን የሲኒ ማስቀመጫ ረከቦትን ጨምረው በማምረት ያቀርባሉ። አጠቃላይ ከትላልቅ ሆቴሎች ላይ ከሚሰራው ባህላዊ ሥራ ጀምሮ እስከ ዝቅተኛ የቡና ጠጡ ቤቶች እንዲሁም የተለያዩ የቀርከሃ ውጤቶችን አምርተው ለቸርቻሪዎች ያስረክባሉ። አሁን አሁን በትላልቅ ሆቴሎች አካባቢ በስፋት የሚታዩት የቀርከሃ ባህላዊ ቁሳቁሶች እና ሆቴሎች ላይ በመሳተፍ አሻራቸውን እያኖሩ ይገኛሉ።
ለዘርፉ እጅግ የላቀ ፍቅር አለኝ ያሉት አቶ መግባር፤ በተለይም ያላቸውን ዕውቀት ተጠቅመው በሀገራቸው ምርት ሀገር በቀል የሆኑና ባህላዊ ይዘቱን የጠበቁ ሥራዎችን በመስራታቸው ዕውቅናን እያተረፉ ይገኛሉ። ዘርፉ ገና ብዙ ሊሰራበት የሚችልና ያልተሰራበት ነው። ምርቱ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይገኛል። ነገር ግን በሚፈለገው ልክ አልተጠቀምንበትም። ስለዚህ ልንጠቀምበት ይገባል ይላሉ። በተለይም ሀገር በቀል በሆነው ምርት ላይ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ መስራት እጅግ ጠቃሚ ነው። በአሁን ወቅት ህዝቡ በራሱ ወደ ባህሉ እየተመለሰ ያለበት ጊዜ በመሆኑ ተደብቆ የለውን የቀርከሃ ሥራ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ነው።
‹‹ቻይና የምትቀድመን ከቀርከሃ ቲሸርት በመስራቷ ብቻ ነው›› እንጂ ማንኛውንም ነገረ ከቀርከሃ መስራት ይቻላል። እኔም ብፌ ብቻ ሲቀረኝ ሌሎች ማንኛቸውንም የቤት ውስጥና የቢሮ ዕቃዎች እንዲሁም የተለያዩ ጌጣጌጦችን እሰራለሁ። የተጠቃሚዎችን ፍላጎት በመከተል ዘመናዊ አልጋን ጨምሮ የፍራፍሬ እና የሲኒ ማስቀመጫ ሼልፎች፣ ወንበር ጠረጴዛና ሌሎች ምርቶችም ከቀርከሃ ይመረታሉ። ነገር ግን ሌሎች ሀገራት ቀርከሃን እየተጠቀሙበት እንዳለው ኢትዮጵያ ውስጥ መጠቀም አልተቻለም በማለት በቁጭት ይናገራሉ።
የቀርከሃ ሥራ ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል እንደመሆኑ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል። በተለያየ ጊዜም በዘርፉ ለባለሙያዎች የሚሰጠው ሥልጠና ጥራቱን የጠበቀና ወደ ተግባር ሊለወጥ የሚችል ሥልጠና መሆን ይገባዋል። ለዚህም አንደኛ ሰፋ ያለ ጊዜ በመስጠት ፍላጎት ያለው ሰው ከስልጠናው ተጨባጭ የሆነ እውቀት ይዞ እንዲወጣ ቢደረግ ከዘርፉ መጠቀም የሚገባንን ያህል ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል አቶ መግባር ተናግረዋል።
ከሙያው ያገኙትን ጥቅም ሲናገሩም ሦስት ወራት ጊዜና ጉልበታቸውን ከፍለው ባገኙት ዕውቀት እንዲሁም በሁለት ሺ ብር መነሻ ካፒታል የጀመሩት የቀርከሃ ሥራ ዛሬ በስፋት እየሰሩበትና እየታወቁበት በርካታ ደንበኞችን ማፍራት አስችሏቸዋል። ከዚህም ባለፈ ሙያውን ለበርካቶች ማስተላለፍ ችለዋል። በአሁን ወቅትም ከዘርፉ አተረፍኩ የሚሉትና ትልቁ ሀብታቸው ሙያውን በየጊዜው እያሻሻሉ መምጣታቸው አንዱ ሲሆን፤ ሙያውን የተጋሯቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የራሳቸውን የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ምክንያት መሆን ችለዋል። አሁንም ሙያውን ለሚፈልግ ሥልጠና መስጠት ያስደስታቸዋል። በተጨማሪም ከዚሁ ሥራ ባገኙት ገቢ ሦስት ሚሊዮን ብር የሚገመት የመኖሪያ ቤት ሰርተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጥሩ ኑሮ መኖር መቻላቸው ትልቁ ስኬታቸው ነው።
በቀርከሃ ሆቴሎችን በባህላዊ መንገድ የማስዋብ ሥራ በአማካኝ ከመቶ ሃምሳ ሺ እስከ ሁለት መቶ ሺ ብር ይጠይቃል። ይሁንና እንደ ሆቴሉ ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን በዋናነት ከውስጥ ቁሳቁሶች በተጨማሪ በቀርከሃ የሚሰራው ኮርኒስና ግድግዳው ነው። ግድግዳውና ኮርኒሱን ለመስራት የቀርከሃ ግብዓቱ ሙሉ ለሙሉ የሚያቀርበው ባለሙያው ከሆነ በካሬ እስከ 450 ብር ድረስ ወጪ ይጠይቃል። ነገር ግን ግብዓቱን ባለ ሆቴሉ ካቀረበ ከ150 እስከ 200 ብር በካሬ የሚጠይቅና እንደ አካባቢው ርቀትና ቅርበትም የሚወሰን ይሆናል።
ለሥራው የሚያስፈልጉት ግብዓቶች በዋናነት ጎጃም አካባቢ የሚገኝ ቀርከሃና ከደቡብ ክልል ጉራጌ አካባቢ የሚመጣ ጅባ ሲሆን፤ ከባህርዳር የሚመጣ ቆዳም ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ጨርቆች፣ ገመድ፣ ኮላና ቫርኒሽ ያስፈልጋል። ከቫርኒሽ ውጭ ያሉት ግብዓቶች በሀገር ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው በቀላሉ አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ይቻላል።
‹‹ቀርከሃ በሀገሪቷ በበቂ ሁኔታ አልተጠቀምንበትም በየአካባቢው ለአጥር አገልግሎት እየዋለ ይገኛል›› ያሉት አቶ መግባር፤ ስለዚህ አጥኚዎች በቀርከሃ ላይ ብዙ መስራትና በሚገባ ተረድተው ለማህበረሰቡና ለአርሶ አደሩ ማስረዳት ይጠይቃል። ምክንያቱም ገበሬው ባለማወቅ አጥር እያጠረበት ይገኛል። ቢበዛ 30 ብር የሚሸጠው አንዱ ግንድ ቀርከሃ ወደ ለተለያዩ ሥራዎች ቢቀየር በአማካኝ እስከ አንድ ሺ ብር ይጣራል። አንድ ሺ ብር ደግሞ ቢያንስ ሦስት ቆርቆሮ መግዛት ያስችላል። ስለዚህ ቀርከሃ በሀገሪቷ በከፍተኛ መጠን እየባከነ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2013