ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሳይንቲስቶችን እና የሂሳብ ልህቃንን ቀልብ መሳብ ከጀመረበት እ.አ.አ ከ1950ዎቹ ወዲህ ሀገራት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ጥቅም ላይ የማዋል ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በተለይም ባለፉት 20 ዓመታት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የህትመት ውጤቶች በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅበዋል።
በርካታ ሀገራት እና ተቋማት የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ለመፍታት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እንደ መፍትሔ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ፈጣን እድገት እንዲያስመዘግብ በተለያዩ ወቅቶች አስተዋጽኦ ያበረከቱ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ላለፉት 16 ወራት ወይም አንድ ዓመት ከአራት ወር ገደማ ዓለምን ያስጨነቀው የኮሮና ቫይረስ ነው። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተለያዩ ዘርፎችን ባሽመደመደበት በዚህ ወቅት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጥሩ ስኬት እያስመዘገበ ይገኛል። በርካታ ተቋማት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እየተጠቀሙ ናቸው።
ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ማሽንስ ኮርፖሬሽን (አይ ቢ ኤም) የተሰኘው እውቁ የአሜሪካን የኮምፒዩተር አምራች የሆነው ድርጅት ሰሞኑን ያወጠው ሰው ሠራሽ አስተውሎት የ2021 ደረጃ አመላካች ሪፖርት እንዳሳየው፤ ዓለምን ያስጨነቀው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ከባድ ጫና ያሳረፈ እና ተፈላጊነታቸው እንዲቀንስ ምክንያት የሆነ ቢሆንም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተፈላጊነት ደግሞ በአንፃሩ እንዲጨምር ሰበብ ሆኖታል። በዚህም ምክንያት በርካቶች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እንዲጠቀሙ ተገደዋል።
በጥናቱ እንደተመላከተው፤ በርካታ ሀገራት፣ ተቋማት እንዲሁም ተመራማሪዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የመጠቀም ሁኔታ ጨምሯል። አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ የዓለማችን ተቋማት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን) በተለያየ መልኩ እና ሁኔታ ጥቅም ላይ እያዋሉ ይገኛሉ:: የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የተለያዩ ዘርፎች ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ያላቸው ፍላጎት መጨመር እንዲሁም የቴክኖሎጂው ተደራሽነት መሻሻል እና በስፋት ጥቅም ላይ ለመዋል ሂደቱን እንደ ምክንያትነት ተቀምጠዋል። በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ከሚገኙ የአርቲፊሻል ለዘርፎች መካከል ናቹራል ላንጉዌጅ ፕሮሰሲንግ ቅድሚያውን እንደሚይዝ ተጠቁሟል።
በዳሰሳ ጥናቱ ከተካቱት ግማሽ ያህል ተቋማት በናቹራል ላንጉዌጅ ፕሮሰሲንግ የሚታገዙ መተግ በሪያዎችን አገልግሎት ላይ ያዋሉ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ በተያዘው የአውሮፓውያኑ 2021 ተግባራዊ የማድረግ እቅድ እንዳላቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል። አይቲ ዘርፍ በፊትም ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በዋናነት ጥቅም ላይ የሚያውል ዘርፍ ቢሆንም የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ግን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ንግዶች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የመጠቀም ሁኔታቸው ከፍ እያለ ነው።
በዓለም ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት ከተደረገባቸው የኢንፎርሜሽ ቴክኖሎጂ (የአይ.ቲ) ባለሙያዎች መካከል ወደ 43 ከመቶው የሚሆኑት ኩባንያቸው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ – 19) ወረርሽኝ ሳቢያ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ጥቅም ላይ የማዋል ሁኔታን አፋጥኗል ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እየታየ ያለው መሻሻል ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተደራሽ እያደረገው ነው።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን የሚጠቀሙ አካላት ቁጥር ከማሻቀብ ባሻገር ወረርሽኙን ለማጥፋት ለሚደረገው ርብርብም ዘርፉ የላቀ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። የኮሮና ቫይረስን ለመዋጋት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) መጠቀም እጅግ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ መንግሥታት እና ሳይንቲስቶች በስፋት ጥቅም ላይ እያዋሉት ነው። ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) በሳይንሳዊው ማህበረሰብ መካከል የአመለካከት እና የመረጃ ልውውጥን በእጅጉ አመቻችቷል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ከኮቪድ 19 ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መድሃኒቶችን ለማግኘት የሚደረገውን ሚና በከፍተኛ ሁኔታ እገዛ አድርጓል። በዚህም ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኮቪድ 19ኝን ለመዋጋት ለሚደረገው ርብርብ የላቀ ሚና ተጫውቷል። በተለይም ስለ ወረርሽኙ ለሰፊው የዓለም ማህበረሰብ መረጃ በማጋራት ረገድ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የተጫወተው ሚና አይተኬ መሆኑን የዘርፉ ልህቃን ያስረዳሉ። ለአብነትም ስለ ክሊኒካዊ ሙከራዎች መረጃ ፣ በሽታው እንዴት እንደሚተላለፍ በማሳወቅ ረገድ የተጫወተው ሚና ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ምስጋና ይግባው የሚያሰኝ ነው።
የኮቪድ ምርምርን ለማፋጠን ከ500 በላይ ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች አካቶ የተቋቋመው ኮቪድ ሞንሾት የተሰኘው የዩኬ መንግሥት ፕሮግራም ሳይንቲስቶች በፈቃደኝነት በቫይረሱ ላይ በሚደረገው ምርምሮች ላይ እንዲሳተፉ ሁኔታ የሚያመቻች ነው። ይህ የሊህቃኖች ስብስብ የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት ብሎም ለማጥፋት በተደረገው ርብርብ ውስጥ የላቀ ሚና የተጫወቱ ናቸው። ሳይንቲስቶቹ ውህዶች እንዴት በቀላሉ እንደሚሰሩ ለመገምገም ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ጥቅም ላይ አውለዋል።
ሞንሾት የተሰኘው ቡድን ለወረርሽኙ መድሃኒት ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ከ2000 በላይ ግብችቶችን ያሰባሰበ ሲሆን፤ ይህንን ለማከናወን በሰው ኃይል አንድ ወር ሊፈጅ የሚችል ነው። ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም በ48 ሰዓታት ውስጥ መከወን ችሏል። ይህም ሰው ሠራሽ አስተውሎት የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ምን ያህል አስተዋጽዖ እያበረከተ እንደሆነ አመላካች ነው።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት( አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ለመድሃኒት ምርምር እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ ባሻገር በኢኮኖሚ ሊደርስ የሚችለውን ችግር በመከላከል ረገድ የላቀ ሚና መጫወቱን ነው ሪፖርቱ ያመላከተው። ምንም እንኳ የኮሮና ቫይረስ በተለያዩ ዘርፎች ከባድ ችግሮች ያስከተለ ቢሆንም በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች የቅጥር እና የግል ኢንቨስትመንት መሻሻል እንዲያሳይ አድርጓል።
በኮቪድ 19 በወረርሽኝ ምክንያት የተከሰተው ኢኮኖሚያዊ ማሽቆልቆል ቢኖርም ፣ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ከተካተቱ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ከተሰማሩት መካከል ግማሽ የሚሆኑ ምላሽ ሰጪዎች እንደተናገሩት፤የኮቪድ 19 ወረርሽኙ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ኢንቨስትመንታቸው ላይ ምንም ተጽዕኖ እንደሌለው ሲናገሩ 27 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ኢንቨስትመንታቸውን ማሳደጉን ገልጸዋል። ይህም የሚያመላክተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ላይ ያስከተለው ይህ ነው የሚባል ጫና እንዳልነበረ እና በቀጣይም የማስከተል ዕድሉ ጠባብ መሆኑን ነው።
ሪፖርቱ እንዳመላከተው ኮቪድ 19 ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት ምርምርና ኮንፈረንሶች ላይ በብዛት እንዲሳተፉ መንገድ ከፍቷል። በወረርሽኙ ምክንያት ኮንፈረንሶች በበይነ መረብ ማካሄድ የግድ የሆነ ሲሆን፤ ኮንፈረንሶቹ በበይነ መረብ በመካሄዱ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። በዚህም ምክንያት በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚካሄዱ ስብሰባዎች እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተሳትፈዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ በዘርፉ ያሉ ዕድሎችን ብቻ ሳይሆን እንቅፋቶችንም ጠቁሟል። በጥናቱ መሰረት ተቋማት ቴክኖሎጂውን በሥራ ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት የሚገዳደሩ የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉ። ከሚገጥማቸው ተግዳሮቶች መካከል በዘርፉ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል እና የእውቀት ውስንነት አንዱ ነው። ብቁ የሰው ኃይል እጥረትና የእውቀት ውስንነት የዘርፉ ተግዳሮት ነው የሚል ምላሽ የሰጡት ከጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል 39 ከመቶ በመያዝ የመጀመሪያውን ስፍራ ይዟል።
የዳታ ውስብስብነት እና ለብዙሐን ተደራሽ አለመሆን የዘርፉ ተግዳሮት ነው የሚል ምላሽ የሰጡት ደግሞ በ32 በመቶ ሁለተኛነቱን ሲይዝ፤ ቴክኖሎጂውን ለማበልፀግ ምቹ መድረኮች እና መጠቀሚያዎች ያለመኖር ተግዳሮት 28 በመቶ በማግኘት በሦስተኝነት ተቀምጧል።
በሌላ በኩል ተቋማቱ በሚቀጥሉት 12 ወራት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ የሚያጠናክራቸው ዘርፎች ተዘርዝረዋል። ከእነዚህም ውስጥ የዳታ ደህንነት፣ የሥራ ሂደቶችን አውቶሜት ማድረግ እና የደንበኞች አገልግሎት የመጀመሪያውን ሦስት ደረጃ በመያዝ ተቀምጠዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2013