የውጪ ንግድ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ዓይነተኛ ሚና አለው። በኢትዮጵያ ከዚህ አንፃር ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። እ.ኤ.አ በ2020 ወደ ውጪ የተላከው ምርት ወደ 3 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ሲኖረው ከዚህም መካከል የግብርናው ዘርፍ 76 በመቶ ድርሻ አለው። ወርቅ፣ ኤሌክትርሲቲ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ጥራጥሬ፣ የቅባት እህል፣ ጫትን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ በአጠቃላይ የግብርና ውጤቶች እንዲሁም የቁም እንስሳትና ሥጋ ትልካለች። የዚህ የውጪ ገበያ መዳረሻ ሀገራት ደግሞ በዋነኛነት ቻይና ስትሆን ከኢትዮጵያ የምትገበየው 10 በመቶ ያህል መሆኑን ፕሪሳይስ ኮንሰልታንት ያስጠናው ጥናት ይጠቁማል።
ቻይና፣ ሶማሊያ፣ አሜሪካ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ጀርመን የምርቶቻችን ተቀባይ ሀገራት ናቸው። ተቋሙ በዘርፉ ያስጠናውን ጥናት መነሻ አድርጎም ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ለተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል። በዚሁ መድረክ ላይ ገለጻ ያደረጉት ሄለን ጌታው ናቸው።
እርሳቸው እንዳሉት ሀገራችን ያለችበት የኢኮኖሚ ሁኔታ ቢታይ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት በዓመት በሁለት ዲጂት ወይም ከ10 በመቶ በላይ ዕድገት እያሳየ መጥቷል። ሆኖም እኤአ 2000 ላይ ከነበረው 44 በመቶ በ2016 ላይ 23 በመቶ ዝቅ ያለበት ሁኔታ አለ። ይሄ ኢኮኖሚው የሚፈለገውን ያህል ዕድገት አለማስመዝገቡን የውጪ ንግድ ገቢውም ዝቅተኛ መሆኑን ያመለክታል። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንዱና ዋንኛው ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልከውና ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባው ምርት አለመመጣጠን ነው። ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የተለያዩ ምርቶችን ለማስገባት የምታወጣው ወጪ 13 ቢሊዮን ዶላር ነው። ወደ ውጭ እየላከች ያለችው ግን ከ2 ነጥብ 2 እስከ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ብቻ ነው ።
ሁለተኛው ውጤታማ ላለመሆኗ ሌላው ምክንያት ደግሞ ወደ ውጪ የምትልከው ምርት ጥራት መጓደል ነው።
ሚዛን እንዲያነሳ በሚል በርበሬ ላይ ውሀ ከማርከፍከፍ ጀምሮ በምርት አቅራቢዎች የሚደረጉ የተለያዩ ሻጥሮች ለጥራት መጓደል በምክንያትነት ይጠቀሳል። ለምሳሌ ያህል ሲጠቅሱም ‹‹ ውሀ የተርከፈከፈበት አንድ ፈረሱላ በርበሬ ቢሆንም እዚህ ላይ በተገኘው ፈንገስ ምክንያት ሌላው ችግር የሌለበትም በርበሬ ችግር እንዳለበት ተቆጥሮ አብሮ እንዲቃጠል ይደረጋል። ይሄ የጥራት መጓደል ለአቅራቢው ብቻ ሳይሆን ሀገራችን ከውጪ ገቢ የምታገኘውን ጥቅም ለኪሳራ የሚዳርግ ነው። ችግሩ በዚህ ብቻ ሳያቆም ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች ላይ ማስጠንቀቂያ የሚያሰጥ ከበድ ሲልም እገዳ የሚያስጥል ነው።›› ሲሉ ያስረዳሉ።
በተጨባጭም በተለያዩ ዓመታት የኢትዮጵያ የውጪ ንግድ ምርቶች ላይ ማስጠንቀቂያዎችና እገዳዎች መደረጋቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ ሄለን ከጥራት መጓደል ጋር ተያይዞ ጃፓን ቡናን፣ ዩናይትድ ኪንግደም ቅመማ ቅመምን ሀገራችን ወደ ውጪ እንዳትልክ አግደው እንደነበር አስታውሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኢኮኖሚ ዘርፍ አማካኝነት ኢኮኖሚውን ወደ ኋላ የሚጎትቱት ተብለው የተለዩ ስድስት ነጥቦች መኖራቸውንም አመልክተዋል። ከእነዚህም መካከል የምርት ጥራት ዝቅተኛ መሆኑ፣ ጥሩው የሚበረታታበትና ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ስርዓት አለመዘርጋቱ፣ ቀጣይነት ያለው ምርትና ምርታማነት አለመኖሩ፣ ማኒፋክቸሪንግና ዘመናዊ ግብርናም ቋሚ በሆነ አስተዳደግ አለመጓዛቸው፣ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ቢሮዎች ዕድገቱን ተከትለው በዕድገቱ ፍጥነት ሽግግር አለማድረጋቸው መጠቀሳቸውን ጠቁመዋል።
ሌላው ተግዳሮት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ እንደ አህጉር ተጠቃሚ የሚያደርጋትና የምትገባቸው የተለያዩ የንግድ ስምምነቶች አባል አለመሆኗ መሆኑንም የጥናቱ አቅራቢ ጠቅሰዋል።
ነገር ግን የተለያየ የንግድ ስምምነቶች አባል መሆን ኢኮኖሚዋ እንዲያድግ ከፍተኛ ዕድል ይሰጣል። አፍሪካ ኮንቲኔንታል ትሪትመንት አግዋ ዩኤስኤ ለአፍሪካ ሀገሮች የሰጠችው ፈቃድ ሲሆን ከግብር ነፃ ሆኖ የአፍሪካ ሀገራት ኤክስፖርት ሲያደርጉ መግባት የሚያስችል ነው። ኮሜሳ ሌላ ስምምነትና ለዕድገቱ በር የሚከፍት ነው። ደብሊውሲኦ ሌላው ለሀገራችን አባልነት አስፈላጊ የሆነ በመሆኑ ሀገራችን ወደዚህ አባልነት እንድትገባ ግፊት እየተደረገበት ነው። አባልነቱና ክፍተቶቻችንን ማረሙ ሀገራችን እኤአበ2022 መካከለኛ ገቢ ወደ አላቸው ሀገሮች ጎራ ለመግባት ያስቀመጠችውን ግብ ከዳር ያደርሳል።
የነብስ ወከፍ ገቢንም እንደታለመው በ8 ነጥብ 5 በመቶ ማሳደግ ያስችላል። በዕቅዱ እንደ ሀገር በ2022 በዓመት ይኖራል ተብሎ የተቀመጠው የነብስ ወከፍ ገቢ 1ሺህ 115 ዶላር ነው። በ2030 ይሄን ገቢ ወደ 2 ሺህ 200 ዶላር ከፍ እንደሚል ይታሰባል። ድህነትን መቀነስ፣ የውጪ ገበያን ማሳደግ የሚሉና ሌሎች የተቀመጡ የተለያዩ ግቦችን ማሳካት የሚቻለው ወደ ውጪ የሚላከውንና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ማመጣጠን ሲቻል ነው። ከግብርናው የሚገኘው 76 በመቶና ሌሎች የውጪ ግብይት ገቢዎችን ስኬታማ ሲሆኑ ነው።