የከበሩና በከፊል የከበሩ ማእድናት በስፋት ከሚገኙባቸው የአማራ ክልል ዞኖች ውስጥ አንዱ ዋግህምራ ነው። በዞኑ በዋናነት የብረት፣ሴራሚክ፣ እምነበረድ፣ወርቅ፣ኦፓልና ኴርትዝና የመሳሰሉ ከአስራ ሰባት በላይ የሚሆኑ ማእድናት እንደሚገኙ ከዞኑ የማእድን ስራዎች ፍቃድ አስተዳደር የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከነዚህ ማእድናት ውስጥም እስከ 53 ዓመት ድረስ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ሴራሚክ በዞኑ እንዳለ በጥናት መረጋገጡንና በተመሳሳይ 200 ዓመታት ያህል ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የብረት መአድን እንዳለ በማእድንና ኢነርጂ ሚንስቴር ተጠንቶ መረጋገጡንም እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ። 23 ካራት የሚሆን የወርቅ ክምችት እንዳለ መረጋገጡንም መረጃዎቹ ያሳያሉ።
የዋግህምራ ዞን የማእድን ስራዎች ፍቃድ አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ፀሃዬ ካሳ እንደሚሉት በዞኑ በርካታ የከበሩና ከፊል የከበሩ ማእድን ሃብት ክምችቶች ይገኛሉ። የሴራሚክ፣ብረትና ወርቅ ማአድናት ክምችትም በጥናት ተረጋግጧል። ይሁንና ከነዚህ መአድናት ውጪ ያሉት የክምችት መጠናቸው እስካሁን ድረስ በጥናት አልተረጋገጠም። ማእድናቱ እንዳሉ የማስተዋወቅ ስራም በስፋት አልተሰራም። የሴራሚክ፣ብረትና ወርቅ ማእድናት ክምችት በጥናት የተረጋገጠ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ወደ ስራ አልተገባም። ነገር ግን ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት ወርቅ በባህላዊ መንገድ እየተመረተ ይገኛል።
በጥናት የተረጋገጡ የማእድን ሃብቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የዞኑ የማእድን ስራዎች ፍቃድ አስተዳደር
የሚመለከታቸውን አካላት በተለይም የክልሉን አስተዳደርና የመአድን ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ድጋፍ ጠይቋል። ባለሃብቶች ወደዞኑ መጥው ስራ እንዲጀምሩም የተለያዩ የማስተዋወቅ ስራዎችን እያከነናወነ መሆኑን ይናገራሉ።
ይሁንና ሰፊ የማስተዋወቅ ስራ ባለመሰራቱ በዞኑ ያለውን የመአድን ሃብት አውጥቶ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም። የማእድን ሃብቱ ክምችትና የምርት መጠን ታውቆ ለባለሃብቶችና በማእድን ዘርፉ ገብተው መስራት ለሚፈልጉ በሚገባ ባለመተዋወቁም ሃብቱ በሚገባ ጥቅም ላይ አልዋለም። ከሁሉ በላይ ደግሞ የዞኑን ማእድን ሀብት የሚያስተዳደር ባለቤትና አደረጃጀት ባለመኖሩና በዚህም ምክንያት ባለሃብቶች እስካሁን ድረስ ስራ ባለመጀመራቸው የማእድን ሃብቱ ወደ ምርት አልተሸጋገረም።
እንደ ቡድን መሪው ገለፃ በአሁኑ ወቅትም የዞኑን ማእድን ሃብት ክምችት መደበኛ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ለማስተዋወቅ ጥረት ቢደረግም የታሰበውን ያህል ውጤት ማምጣት አልተቻለም። በጥናት ክምችታቸው ከተለዩ ማእድናት ውስጥ አንዱ በሆነው ሴራሚክ የማምረት ስራ በዚህ አመት ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አይታይም። በተመሳሳይ የብረትና የወርቅ ማእድናት ክምችታቸው አለ ከማለት ውጪ እስካሁን ድረስ ወደማምረት አልተገባም። በወርቅ ማእድን ላይ የተወሰኑ አርሶ አደሮች በባህላዊ መንገድ እያመረቱ የነበረ ቢሆንም በአካባቢው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለማምረት ስለተቸገሩ ስራው ቆሟል።
እስካሁን ድረስ በተጠናው ጥናት ልክ የዞኑን የመአድን ሃብት ጥቅም ላይ ማዋል ያልተቻለው ሃብቱን ለማስተዋወቅ የተደረገው ጥረት ውጤት ባለማምጣቱና ከዚህ በፊት በማእድን ማውጣት ስራ ፍቃድ የወሰዱ ባለሀብቶችም ወደ ስራ ባለመግባታቸው ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ማእድን አውጪዎቹ ስራቸውን እንዲያቆሙ የዞኑ ማእድን ስራዎች ፍቃድ አስተዳደር በተደጋጋሚ ደብዳቤ ፅፏል። ከላይ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ትኩረት ሰጥቶ የማእድን ሀብቱ ወደ ስራ እንዲገባና ህብረተሰቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ አኳያም ውስንነቶች አሉ።
በመሆኑም የሚመለከተውና በዚህ ስራ መሳተፍ የሚፈልግ የግል ባለሀብት እስካለ ድረስ ገብቶ መስራት እንደሚችል የዞኑ ማእድን ስራዎች ፍቃድ አስተዳደር አሁንም የማስተዋወቅ ስራዎችን በስፋት እየሰራ ይገኛል። ፀጥታ ስራውንም ሃላፊነት ወስዶ ለመስራት ዝግጁነት አለ። የማእድን ሃብቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ለዞንና የክልል አመራሮች በግልፅ የማስተዋወቅ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። እነርሱም የማእድን ዘርፉን አስፈላጊነት በመረዳት በስፋት እያስተዋወቁ ነው። በተለይ ደግሞ አመራሮቹ የማእድን ሃብቱ እስካሁን ድረስ ለምን በስፋት ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆንና ጥናት እንዲካሄድ በማድረግ ለችግሩ መፍትሄ እያፈላለጉ ይገኛሉ።
በይበልጥ ደግሞ ችግሮቹ ተቀርፈው የማእድን ሃብቱ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ከማድረግ አንፃር የዞኑ የማእድን ስራዎች ፍቃድ አስተዳደር ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ከማቅረብ ወደኋላ አይልም። በቀጣይም ይህንኑ አጠንክሮ ይገፋበታል። የማእድን ሃብቱ ወደምርት ተሸጋግሮ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የማስተዋወቅ ጥረቱንም አጠናክሮ ይቀጥላል። ይህም የመገናኛ ብዙሃን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና ጥረት ይጠይቃል።