ባለፈው ሚያዝያ 27 ቀን የአርበኞች የድል በዓል 80ኛ ዓመት መከበሩ ይታወቃል፡፡ ቀኑ በአድዋ ድል ሽንፈትን የተከናነበችው ጣሊያን ዳግም ከ40 ዓመት በኋላ በ1928 ኢትዮጵያን መውረሯ ይታወቃል፡፡ ወረራውን ለመመከት ጦርነት በገጠሙ ኢትዮጵያውያን ላይም በአለም የተከለከለ የመርዝ ጋዝ እና ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችን ጭምር የተጠቀመችው ጣሊያን በኢትዮጵያ የቆየችው ግን ለአምስት ዓመታት እስከ 1933 ዓ.ም ነበር፡፡
የጣሊያን ወረራ ያስቆጣቸው ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደል ተጋድሎ አድርገው በ1933 ዓ.ም ጣሊያንን ድል በማድረግ ድል የተቀዳጁት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህ ተጋድሎ መላው ሕዝብ በአንድነት ተዋድቋል፡፡ ንጉሡ ባይኖሩም በየጫካው የጎበዝ አለቃ እየመረጠ የአርበኝነት ተጋድሎ በማድረግ ድልን መቀዳጀትና ጣሊያንን ከሀገሩ ማስወጣት ችሏል፡፡
የፋሽስት ወረራ ከአድዋ መራር ሽንፈት ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ በቂም በቀል ዳግም ተዘጋጅተው ወረራ የፈፀሙበትም ስለመሆኑ ግልፅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በእብሪት የተሞላውን ሃይል ጀግኖች እናትና አባት አርበኞች በዱር በገደሉ በመዋደቅ፤ የአምባገነኑን ሙሶሎኒ ጦር ድል አድርገዋል፡፡ በዚህም ለኢትዮጵያንም ዳግም የማሸነፍና ነፃነትን ጠብቆ የመኖር ታሪክ ላይፋቅ በደማቅ ቀለም ተፃፈ። ለዚህም ነው በዓሉ በየዓመቱ በዚህ ቀን በብሔራዊ ደረጃ የሚከበረው። አዲሱ ትውልድ በሉዓላዊነቱ ላይ እንዳይደራደር ለማስተማርና ለዚህ ግዙፍ ድል መስዋዕት የሆኑትን አርበኞች ለመዘከር ጭምር ነው፡፡
ዛሬ ይኼን ጉዳይ ያነሳንላችሁ ያለምክንያት አይደለም። ከቀናት በፊት በሸኘነው የሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ደምቆ በዋለው የአርበኞች የድል ቀን የኦሮሚያ ሰዓሊያን ማኅበር መስቀል አደባባይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ሙዚየም ‹‹ዳግም አድዋ በተስፋ ምድር›› በሚል ለሦስት ሣምንት የሚቆይ የሥዕል ዐውደ ርዕይ (ኤግዚቢሽን) ተከፍቶ ነበር፡፡ በሥዕል ዐውደ ርዕዩ አንጋፋና ወጣት ሠዓሊያንን ጨምሮ 26 አባላት 60 ሥዕሎችን ለተመልካቾች አቅርበዋል፡፡ እኛም ይህን ጉዳይ ከዚህ እንደሚከተለው በዘመን ጥበብ አምዳችን ላይ ልንዳስሰው ወደናል።
ማኅበሩ ያቀረበው ዐውደ ርዕይ ዓላማ የሀገራችንን ባህልና ታሪክ በቀለምና በብሩሽ ማስቀመጥ ነው። ከዚህ ባለፈ ለጥበብ አፍቃሪያን ለእይታ ክፍት ማድረግና ለቱሪስት መስህብም እንዲሆን ለማስቻል መሆኑን በመድረኩ ተገልጿል፡፡
የኦሮሚያ ሠዓሊያን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ቡልቲ በወቅቱ እንደተናሩት፤ የሥዕል ዐውደ ርዕዩ ዋና ዓላማ ለሀገራችን ባለውለታ የሆኑ አያትና አባት አርበኞችን እንዲሁም የስነ ጥበብ አርበኛ የነበሩትን የክቡር ዶ/ር አርቲስት ሻምበል ለማ ጉያን መዘከር ነው፡፡
ማኅበሩ በክልሉ የተወለዱ የሁሉም ብሔር ተወላጆች የሚታቀፉበት እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው፤ አባላቱ ከሁለተኛ ዲግሪ እስከ ሰርተፊኬትና እንዲሁም በልምድ የሥዕል ዕውቀት ያካበቱ፤ ፍቅሩና ፍላጎቱ ያላቸው መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የጣሊያን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ሲወርር “እምቢ ለሀገሬ ለጥቃት አልበገርም” በማለት እነ ደጃች ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ራስ መስፍን ስለሺ፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ፣ ኃይለማርያም ማሞ፣ ሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ጄኔራል ታደሰ ብሩና ገብረማሪያም ጋሪ ሌሎችም ያልተዘመረላቸውን አርበኞች ለማስታወስ ጭምርም ነው፡፡
የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፋይዛ መሐመድ የሥዕል ዐውደ ርዕዩን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ቅርሶችና የጥበብ ሥራዎች ለህዝብ ዕይታ የሚያዘጋጁ ባለሙያዎችን ቢሯችን ያበረታታል ብለዋል፡፡ የሥዕል ዐውደ ርዕዩን በአዲስ አበባ ሙዚየም ለሕዝብ እንዲቀርብ በነፃ ቦታውን መፍቀዳችን ቢሮውና የአዲስ አበባ ሙዚየም ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ ጎን መሆናችንን ለማረጋገጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሰዓሊያኑ ስለ ዐውደ ርዕዩ ምን አሉ?
በዐውደ ርዕዩ ስዕላቸውን ካቀረቡት መካከል አርቲስት ምናለ ፍቅሩ አንዱ ነው፡፡ ሰዓሊው ሥዕልን በግል ትምህርት ቤት ለሦስት ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በፋይን አርትስ ዲዛይን ለአራት ዓመት ተምሯል፡፡ በተለያዩ የሰዓሊያን ክበቦች ውስጥ ተሳትፎም ያውቃል። በሩሲያ ፑሽኪን የባህል ማዕከል የሥዕል ዓውደ ርእይ በተለያየ ወቅት የስእል ስራዎቹን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
በሙያው ከአስር ዓመት በላይ እንደቆየ የሚጠቁመው አርቲስቱ፣ ማኅበሩ ባዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ለሦስተኛ ጊዜ መሳተፉን፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ስዕል እየሠራ ዓውደ ርዕይ እንደሚያቀርብ ይገልጻል፡፡ የአርበኞችን ድል ገድል ለመዘከር ይዞ የቀረባቸው ሥዕሎች ድልን ከገዳ የፍትህ ስርዓት ጋር አያይዞ የማቅረብ ስልትን የተከተለ መሆኑን ይገልጻል።
አርቲስት ዳዊት ለማ ጉያም ሥዕላቸውን በአውደ ርእዩ አቅርበዋል። በአርበኞች ቀን ላይ አባታቸው የክቡር ዶክተር ሻምበል ለማ ጉያ በመዘከራቸው ልዩ የደስታ ስሜት እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ፡፡ “አባታችን በአየር ኃይል የሻምበል ማዕረግ ደርሷል፤ አርበኝነቱ በውትድርናውም በስዕሉም ሙያ መሆኑን አስበው ከዕለቱ ቀን ጋር ተከብሮ እንዲውል በማድረጋቸው በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡” ሲሉ አርቲስት ዳዊት ለማ ይገልጻል፡፡
አርቲስት ዳዊት በስነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ እንደተናገረው፤ በሀገሪቱ አንድ የሥዕል ትምህርት ቤት ብቻ ነው ያለው። እርሱም በጣት የሚቆጠሩ ተማሪዎች በዓመት ይቀበላል፤ ለስዕል የሚሆኑ ግብዓቶች የሉም፤ ተማሪው ሠዓሊ ሆኖ ወጥቶ የሥዕል ግብዓት ካላገኘ ምንም መሥራት አይችልም፡፡ ከሥዕል ሌላ ተጨማሪ ሙያ ከሌለውና ራሱን ማኖር የማይችል ከሆነ በቀቢፀ ተስፋ ሊወድቅ ይችላል፡፡
ሥዕል ከአባቴ ተምሬ ነው እዚህ የደረስኩት፤ አባቴ ግን ራሱን በራሱ አስተምሮ ነው ዝነኛ የሆነው፡፡ እኛንም ሌሎችንም ከውጪ የሚመጡ ዜጎች የቆዳ ላይ የአሳሳል ጥበብን አስተምሯል ሲል ሰዓሊው ያብራራል፡፡ ያላስተማሪ የስዕል መማሪያ የሚል መጽሀፍም አባቱ ሻምበል ለማ ጉያ መጻፋቸውን አስረድቷል፡፡
የኦሮሚያ ሰዓሊያን ማኅበር አባል እንደሆነ የጠቆመው አርቲስት ዳዊት ለማ፣ በኢግዚቢሽኑ ያቀረበው ስዕልም ነፍስ ሔር ሻምበል ለማ ጉያ የሚስሉበትን የቆዳ ላይ አሳሳል የተከተለ ነው፡፡ ቆዳው ላይ የተሳለው የሻምበል ለማ ጉያ ምስል ነው።
እንደ መውጫ
በስፍራው ተገኝተን ያነጋገርናቸው አርቲስቶች የመገናኛ ብዙሃን በስነ ጥበብ ዙሪያ የሚዘጋጁ መሰናዶዎችን ሽፋን በመስጠት በኩል ክፍተት መኖሩን ጠቁመውናል። ኅብረተሰቡ ጥበብ አፍቃሪ እንዲሆን በጋዜጦችና በራዲዮ በማስተላለፍ የጥበብ ቤተሰቡ ጋር ተደራሽ እንዲሆን መሥራት ይኖርበታል በሚል ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2013