ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ክራር ማጥናት ከጀመረበት የልጅነት ዕድሜው አንስቶ እስካሁን ድረስ ከኪነ ጥበቡ ዓለም አልተለየም። ድምፀ መረዋና በሙዚቃ ዕውቀቱ አንቱታን ያተረፈ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ነው። በሥራዎቹ ተወዳጅነት የተነሳ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና የተለያዩ የአፍሪካ አገራት በመዘዋወር ብቃቱን አሳይቷል። የዛሬው የዝነኞች የእረፍት ውሎ እንግዳችን ሰለሺ ደምሴ በስፋት በመድረክ ስሙ የሚታወቀው (ጋሽ አበራ ሞላ)። በውጭው ዓለም ስኬታማ ድምፃዊ በመሆን ቢቆይም ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ እናት አገሩ ተመልሷል። በኪነ ጥበቡ ያገኘውን ዝናና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ተጠቅሞ የትውልድ ከተማው አዲስ አበባ የተፈተነችበትን ማህበራዊና አካባቢያዊ ችግሮች ለመቅረፍ አያሌ እንቅስቃሴ በማድረጉና ውጤት በማምጣቱ ይታወቃል።
የእርሱን ስራዎች ከማንም ጋር ማወዳደር እንደሚቸግር ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሥራዎቹ ሙሉ በሙሉ የራሳቸው የሆኑ ጥፍጥናና ቃና አላቸው። አብዛኛውን ጊዜ ሙዚቃዎቹ በክራር የታጀቡ ናቸው። ግርማ ሞገስን በደረበ ድምፅና ግጥሞቹ ተወዳጅ ዜማዎችን ያሰማል። ታሪክ፣ ወግ፣ ባህልና ኢትዮጵያዊነትን የሚያወድሱ በርካታ ዜማዎችን ተቀኝቷል። ለዚህም ነው የሕዝብ ጆሮን ቆንጥጦ የመያዝ አቅም እንዳለው በብዙሃኑ የሚነገርለት።
የሙዚቃ መሣሪያዎችን መጫወት ብቻ ሳይሆን በመስራትና በማስተማርም ይታወቃል። ከዚያም በላይ የታሪክ አዋቂ ነው። ለልጆች ደግሞ ጥሩ የተረት አባት። አርቲስት ስለሺ በሚያስደንቅ ጥበባዊ የፈጠራ ችሎታ ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ባሳደረው አዎንታዊ ተጽዕኖም ይታወቃል። ወጣቶቹ የአካባቢያቸውን ንፅህና እንዲጠብቁ እና ተዛማጅ የጤና ጉዳዮችን እንዲቋቋሙ በማበረታታት አስገራሚ ሥራ ሰርቷል። በተለይ ይህ ምግባሩ በአዲስ አበቤዎች ዘንድ ጎልቶ የታየ ነው። ይሁን እንጂ በዋና ከተማ ብቻ ሳይገደብ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉትን የከተሞች ገጽታ እንዲለወጥ በማገዝ ዘመን አይሽሬ ተግባር ፈፅሟል። የንጹህ አካባቢ አስፈላጊነት በማስተማር ብቻ ሳይሆን በድርጊት በመሳተፍም አነሳስቷል።
የእርሱን ፈለግ የተከተሉ ወጣቶች ቆሻሻ እየለቀሙ ጎዳናዎችን በማፅዳት የመናፈሻ ሥፍራዎችን በማቋቋም ተግባራዊ ውጤት እንዲያመጡ ምሣሌ ሆኗል። በተለይ ሰዎች እንደ ቆሻሻ መጣያ የሚጠቀሙባቸው ቦታዎች ወደ አረንጓዴ ቀጠናነት ተለውጠዋል። ይህንን ተግባር መላው ህብረተሰብ እንዲሣተፍ እስከማበረታታት ደርሷል። የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች እንኳን በጊዜው ያልሞከሩትን ተግባር ነበር የፈፀመው።
የጋሽ አበራ መንገድ
የሙዚቃ ሥራው የተለያዩ የሥነ-ቃል ግጥሞች በድምፅ ጥራዝ የሚሰጠን፤ መድብለ-ትውፊት፤ መድብለ ሥነ-ቃል፤ ድንቅ ጥበብ የሚስተዋልበት ስለመሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ። አርቲስቱ አሁንም ከኪነ ጥበቡ ዓለም ሳይርቅ ተዋናንያንን፣ ተወዛዋዦችንና ሙዚቀኞችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል። እስካሁን ያልተደመጡ አዳዲስ ሥራዎችን ለሕዝብ ለማድረስ እየሰራ መሆኑንም በነበረን ቆይታ ወቅት ገልፆልናል። ከጥበብ ሥራዎቹ በተለየ በበጎ ፈቃደኝነት፣ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላዎች በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፈ መሆኑን ይናገራል።
“ትንሣኤ” የሚል በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን የአንድነት፣ የሠላም፣ የፍቅር ሁኔታዎችን የሚያወሳ ሙዚቃዊ ተውኔት ለማሳየት ሥራውን ወደማጠናቀቁ ላይ ደርሷል። ይህ ጥበባዊ ውጤት የፊታችን ማክሰኞ በሸገር ፓርክ እንደሚቀርብ ነው አርቲስቱ የገለፀው። ሥራው ሰፊ እንደሆነና ለየት ባለ መንገድ ማርሽ ባንድን ጨምሮ የብሄራዊ ቴአትር ተወዛዋዦችና ድምጻውያን እንዲሁም ሌሎች ከያኒያንን አካትቶ እንደሚቀርብ ከአርቲስቱ ለመረዳት ችለናል።
የእረፍት ውሎ
አርቲስቱ ብዙ ጊዜ ብቻውን እንደሚያሳልፍ ነው የሚናገረው። ነገር ግን ከቤተሠብ ጋርም ቤተሰባዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ይሣተፋል። የሚያከናውናቸው ተግባራት በሙሉ በቀጥታ ከሥራው ጋር ተያያዥነት ስላላቸው ትርፍ የሚባል ጊዜ ባይኖረውም የራሱን ሙዚቃዎች በመስራትና መጻሀፍትን በማንበብ የእረፍት ጊዜውን ማሳለፍ ያዝናናዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም ከሙያው ጋር የተገናኙ ልምምዶችን በማድረግ ጊዜውን ይጠቀማል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወደ ክፍለ አገር በመሄድ የደን ተከላና የአካባቢ እንክብካቤ ሥራዎችን በማማከርና አብሮ መሥራት የውሎው የክንዋኔ አካላት ናቸው።
በተለይ አካባቢን በአረንጓዴ ልማት የማበልፀጉ ጉዳይ ከበፊት ጀምሮ ሲሰራው የቆየ ተግባር መሆኑን የሚናገረው አርቲስቱ፤ በ23 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በየክፍላተ አገራት በመጓዝና ማህበረሰቡን በማነቃቃት መንግሥትና የግል ድርጅቶችን፣ ባለ ሀብቶችንና ተማሪዎችን የደን ተከላና የአካባቢ ጽዳትን እንዲጠብቁ በማድረግ ከዳር እስከ ዳር ሲሰራ መቆየቱን ይናገራል። በዚህም ትላልቅ የዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት ማግኘቱን አስታውሷል።
በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀመሩትን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብርን በመደግፍ በርካታ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል። የችግኝ ተከላውን እያስተባበረ መሆኑንም ይገልጻል። ኮቪድን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች ቢከሰቱም የአካባቢ ጥበቃ አካል የሆነውን የደን ልማትን ተሳትፎ አስፈላጊነት የማስገንዘብ ሥራዎችን ከመሥራት አልተቆጠበም።
መልዕክት
ጋሽ አበራ ሞላ ኢትዮጵያ ለ30 እና 40 ዓመታት በተበላሸ ፖለቲካ ውስጥ ተዘፍቃ ከርማለች። ትውልዱ በትምህርት የጎለበት እንዳይሆንና፣ ለጥሩ ነገር ዝግጁ ከመሆን ይልቅ ወደ ብሄርና ግለሰብነት እንዲያዘነብል አድርጓል። ኋላ ቀር በሆነ ሁኔታ ዘርና ጎጥ ላይ እንዲያተኩር ምከንያት እንደሆነው ይገልፃል።
“ይህንን ያህል ጊዜ ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ሊጎትት የቻለው በየጊዜው በሚመጣው ሥርዓት ላይ የሚቀመጡና መንግሥት ነን የሚሉ አካላት የፀዱ አይደሉም። አስተሳሰባቸው የወረደ ነው። በአገሪቱ ላይ የሚያመጡትም ኪሳራ ትውልድን የገደለ ነው። ትውልዱ ሰብዕናው እንዲወርድ ድንበር ከልለውበት፣ ዓይኑን ሸፍነውበት ከሰው ጋር እንዳይገናኝና እንዳይወያይ አድርገውታል። ትልቅ ነገር መስራት እየቻለ በፖለቲካው ምክንያት በወረደ አመለካከት ውስጥ እንዲሆን አድርገውታል። ስለዚህም ወጣቱ ትውልድ የአንዳንድ ፖለቲከኞችን ድርጊት በፍጹም መቀበል የለበትም” ይላል አርቲስት ስለሺ ደምሴ።
እንደ መውጫ
በዚህ ሁለትና ሦስት ዓመት ውስጥ ፖለቲካው እንዲለወጥ ለመሥራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የሚናገረው አርቲስቱ፤ ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ ዴሞክራሲ እንዳይሰፍንና ትውልዱ የአንድነት መንፈስ እንዳያዳብር በርካታ እንቅፋቶች እንደነበሩ ያስረዳል። ከዚህ በመነሳት ወጣቱም ሆነ ማንኛውም ግለሰብ በዘር ልጓም ሣይሆን እንደ ሰው እንዲያስብ፤ የሌላውን ወንድሙን ችግርና ሥሜት እንደራሱ እንዲረዳ፤ ከብሄርና ከጎጥ አስተሳሰብ መውጣት እንደሚኖርበት ምክረ ሐሳቡን ሰጥቷል። በመቋጫ መልዕክቱ ላይም “ወጣቱ ትውልድ ለፖለቲካው መጠቀሚያና መስዋዕትነት መሆንም የለበትም” ሲልም እጽንኦት በመስጠት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር የነበረውን ቆይታ አጠናቋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2013