ኢሉስትሬተር፣ ግራፊክ ዲዛይነር፣ ሚኖሎሮጂስት፣ አርቲስት ነው። ይህ ሁለገብ የሥነ ጥበብ ባለሙያ በእውነተኛ ስሙ ዌስሊቫንኢደን፣ በሌላ መጠሪያው ደግሞ ሪስቦርግ ይባላል። የደቡብ አፍሪካ ዜጋ ነው። በጎዳና የሥዕል ሥራ እውቅናን አትርፏል። ሥራዎቹ በስዕላዊ ንድፍ፣ ጽሁፍን፣ ምስልንና ስዕልን በጋራ በማጣመር መልዕክት የሚያስተላልፉ ሲሆኑ፤ በዚህ ሙያውም በተለያዩ ሀገራት የመዟዟር ዕድል አግኝቷል። ከሰሞኑ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኝቶ ከኢትዮጵያውያን ሰዓሊያን ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ሣር ቤት ተብሎ በሚጠራው አደባባይ በአስፓልት ግራና ቀኝ በሚገኙ ግንቦች ላይ በጽሁፍና በሥዕል ተዋህደው ትምህርታዊ መልዕክት ያላቸውና ለአካባቢውም ውበት የሚሆኑ የሥዕል ሥራዎችን ሲሰራ ነበር ያገኘሁት።
ሁለገቡ ባለሙያ እንዳጫወተኝ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ምስልንና ጽሁፍን በማዋሀድ መልዕክት ያለው የጎዳና ላይ ስዕል ለመሳል አጋጣሚውን ያገኘው የአውሮጳ እና የአፍሪካ ህብረት በጋራ የሚያከብሩትን የአፍሪካ ቀንን አስመልክቶ በተለይም የአውሮጳ ህብረት ባዘጋጀው ምስልን ከጽሁፍ በማዋሀድ የጎዳና ላይ ስዕል ውድድር ላይ ተሳትፈው በማሸነፍ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ከጋና፣ ከጣሊያንና ስፔን እርሱ ደቡብ አፍሪካን በመወከል አንዱ አሸናፊ ነው።
በውድድሩ አሸናፊ የሆነው የስዕል ሥራም ለሕዝብ ክፍት እንዲሆን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ በጎዳና ላይ እንዲሳል የተደረገው። ስለ ስዕሉ መልዕክትም እንደነገረኝ ሠላም በአፍሪካ፣ በአህጉሮች ብሎም በኢትዮጵያ እንዲሰፍን ሲሆን፤ መልዕክቱ የአውሮጳ ህብረት ዋና አጀንዳ ጭምር በመሆኑም ተመርጧል። ሠላም የሚለው ጽሁፍ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ነው የሰፈረው። ከጽሁፉ ጋር ተዋህዶ የተሳለው ስዕልም የተለያዩ ሀገራትን ባህል የሚያንፀባርቅ መልዕክት ያለው ሲሆን፤ በስዕሉ ላይ የሚታዩት አንዷ የጣሊያን፣ ሌላኛዋ ደግሞ ከሌሴቶ ናት።
ሁለቱም የአካባቢያቸውን ባህልና እሴት የሚያንፀባርቁ ተምሳሌቶች ናቸው። ሌሴቶ ትንሽ ሀገር ስትሆን፣ ሶስት ሚሊየን ሕዝብ የሚኖርባት ሀገር ናት። ሌሴቶዎች ሰፋፊ የሆኑ ኮፍያዎችን በመጠቀም ይታወቃሉ። በመሆኑም መለያቸው ሆኗል። የነዚህ የተለያዩ ሀገር ሰዎች በአንድ ላይ የመሆናቸው ሚስጥር አንዱ ከሌላው ጋር ተዋድዶና ተፈቃቅሮ መኖር እንደሚችል ለማሳየት ነው።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የተለያየ የእምነት ተከታዮች በአንድነት ተከባብረው የሚኖሩባት በመሆኗ ይህን መልካም የሆነ እሴት በስዕል በማስፈር ማህበረሰቡን ማስገንዘብና ማስተማር እንደሚቻል ሰዓሊው ሀሳብ ሰጥቷል።
ሰዓሊው በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው የሁለት ሳምንት ቆይታ የስዕል ጋለሪዎችን መጎብኘቱንና በስዕል ስራዎቹ ላይ ከኢትዮጵያውያን ሰዓሊዎች ጋር የሙያ ልውውጥ ስለማድረግ አለማድረጉ ላነሳሁለት ጥያቄ በሰሞኑ በዓል ምክንያት ዝግ ስለነበሩ ጋለሪዎችን ለማየት አለመቻሉን ነው የተናገረው። ልምድ በማካፈል በኩልም ቆይታው አጭር በመሆኑ በቂ ጊዜ እንዳላገኘና ነገር ግን በጎዳና ስዕሉ ላይ ወጣት ሰዓሊያን አብረውት በመሳተፋቸው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተሞክሮ አግኝተዋል የሚል እምነት እንዳለው ነው የነገረኝ።
ከሥዕል ሥራው ውጭ ስለነበረው ቆይታም ‹‹ኢትዮጵያ የመጣሁት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ቆይታዬ አጭር ጊዜ በመሆኑ ከተማዋን በደንብ ተዘዋውሬ የማየት ዕድሉን አላገኘሁም። ብዙ ጥሩ የሆኑ ነገሮች መኖራቸውን ግን ሰምቻለሁ። በቆይታዬም ጥሩ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን አግኝቻለሁ። ቤተሰቤን ይዤ መጥቼ ኢትዮጵያን በደንብ ለማየት አስቤያለሁ። ደግሞ እመጣለሁ አልቀርም። ›› በማለት አፍሪካዊ ወገኝተኝነቱንም ነበር የገለፀው።
የሰዓሊውን የአንደኛውን የአስፓልት አካፋይ የሥዕል ሥራና የያዘውን መልዕክት አይቼ በሌላኛው የአስፓልት ማካፈያ በኩል ወደተሳለው ስዕል አለፍኩ። በውድድሩ አሸናፊ በሆነው በጣሊያናዊ ሰዓሊ ኤድዋርዶ የተሳለ ሲሆን፤ ሥራው ቀድሞ በመጠናቀቁ ሰዓሊውን በሥፍራው አላገኘሁትም። የሰአሊያኑን ሥራ በማየትና በተለያዩ ተሳትፎዎች አብረዋቸው ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ሰዓሊያንና ስለስዕል ሥራው በአካባቢው ካገኘኋቸው ጋር ቆይታ አድርጌያለሁ።
በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ እጩ ተመራቂ የአርክቴክቸር ተማሪና በተጓዳኝ ደግሞ ሥዕል ከምትሞክረው ተማሪ ሔርሜላ ግርማ ጋር በነበረኝ ቆይታ የምትማረው ትምህርትና የሥዕል ሥራ ተቀራራቢ በመሆኑ የሁለቱም ሙያ ባለቤት የመሆን ፍላጎት ስላላት ጎን ለጎን በማስኬድ ላይ እንደሆነ ነው ያጫወተችኝ። በጎዳና ሥዕሉ ላይ ስለነበራት ተሳትፎም እንነገረችኝ እርስዋና ዳግም የሚባለው ጓደኛዋ ለሥዕሉ የሚያስፈልገውን ቅድመ ዝግጅት (ባክ ግራውንድ) በመሥራት ነበር ዋናውን ሰዓሊ ኤድዋርዶን ያገዙት። ከሥዕሉ በተጨማሪ አንድነት በልዩነት (ዩኒቲ ኤንድ ዳይቨርስቲ) የሚል በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተጻፈ ሲሆን፤ ለሥዕል ሥራው የተጠቀመው ቢጫና ጥቁር ቀለም ሰዎች በቀለማቸው መለያየት እንደሌለባቸው፣ የተለያየ ገጸ ባህሪ እንዲኖራቸው የተደረጉት ሰዎችም የተለያዩ ቢሆኑም ግን አንድነት እንዳላቸው ያመለክታል።
የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸውና በውጭው ዓለም ያለውን ጥበብ በዚህ አጋጣሚ በማግኘቷ ተደስታለች። የተለየ የአሰራር ጥበብ እንዳላቸውም ተሞክሮ አግኝታበታለች። በአጠቃላይ የቀለም አገባባቸውን፣ የካራክተር አጠቃቀማቸው፣ በቀላሉ የሚፈለገውን መልዕክት ማስተላለፍ የሚችል የሥዕል ሥራ መሆኑ ትኩረቷን ስቦታል። እንዲህ ያለው አሰራር በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ እንዳልሆነም ተናግራለች።
ተማሪ ሔርሜላ እንዳለችው በኢትዮጵያ የጎዳና ላይ የሥዕል ሥራ አልፎ…አልፎ ቢኖርም በጣም ሥፋት ባለው ሁኔታ የተለመደ አይደለም። እርስዋ ከጓደኞችዋ ጋር በመሆን በአንዳንድ የመዝናኛ ቤቶች ውስጥ የሳሏቸው ሥዕሎች በመሳል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ወደፊት ወደ ጎዳና በማሳደግና በመሥራት ተሞክሮዎችን ለማስፋት የውጭ ዜጎቹ የጎዳና ላይ የሥዕል ሥራ ፍላጎት አሳድሮባቸዋል። ሥራውም ከባድ እንዳልሆነ ከጣሊያናዊው ሰዓሊ ተሞክሮ አግኝተዋል። ሰዓሊው ሥራውን ለማጠናቀቅ ሰባት ቀናት ነው የወሰደበት። የቦታው ሥፋት ሊወስነው ስለሚችል እንደቦታውና እንደ ሥዕል ሥራው ቀኑ ሊጨምር ይችላል።
በዚህ ዙሪያ አጠቃላይ መረጃ የሰጠኝ አዲስ ስትሬት አርት የሚባል ድርጅት ተወካይ ሰዓሊ ሰለሞን ክፍሌ ነው። ሰዓሊው እንዳስረዳው፤ ከጋና፣ ከጣሊያን፣ ከስፔንና ከደቡብ አፍሪካ የተውጣጡት ሰዓሊያን አውሮጳ ህብረት ባዘጋጀው ውድድር ላይ ከተሳተፉት ከሁለት መቶ በላይ ተወዳዳሪዎች መካከል ያሸነፉ ናቸው።
ድርጅታቸው ከነዚህ አሸናፊ ሰዓሊያን ጋር በጎዳና ላይ የሥዕል ሥራ ተሞክሮ ያላቸው ስምንት ሰዓሊ ኢትዮጵያውያን አጋዥ ሆነው እንዲሰሩ አድርጓል። አዲስ ስትሬት አርት የተቋቋመውም የጎዳና ላይ የሥዕል ሥራን ለማስፋፋት በመሆኑ አሸናፊዎቹ ሰዓሊያን ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰሩ መደረጉ አጋጣሚው ለድርጅታቸው ጥሩ ሆኖለታል። በአጠቃላይ በአራቱ የውጭ ሰዓሊያንና በስምንቱ ረዳት ኢትዮጵያውያን የተለያየ መልዕክት ያላቸው አራት የሥዕል ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን፤ ሶስቱ በሣር ቤት አደባባይ አንዱ ደግሞ የአውሮጳ ህብረት ጽህፈት ቤት በሚገኝበት አጥር ላይ ነው የተሰራው። የሥዕሎቹ አጠቃላይ ይዘትም ሠላም በመስበክ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው። የተሰሩት የሥዕል ሥራዎችም በውድድሩ አሸናፊ ናቸው።
አውሮጳና አፍሪካ ህብረት በየዓመቱ እንዲህ ያሉ መልካም መልዕክቶችን በማስተላለፍ ዝግጅት ያደርጋሉ። በዓሉም ይከበራል። አምና በዓሉ የተከበረው በሙዚቃ ትርኢት ውድድር ነበር። ሰዓሊያኑ ከየአካባቢያቸው የባህል እሴት በመነሳት ያቀረቧቸው ሥራዎች ቢሆኑም መልዕክቱ ለሁሉም በሚሆን መልኩ ነው የቀረበው። ሥዕሉ የተሰራበት አደባባይም ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ፈቃድ ተገኝቶ በመሆኑ የተሳካ ሥራ ተሰርቷል ብሎ ድርጅታቸው እንደሚያምንም ሰዓሊ ሰለሞን ተናግሯል።
በአካባቢው ካገኘኋቸው መካከልም ሀሳቡን ያካፈለኝ ወጣት እያሱ ደርቤ አካባቢው ተወልዶ ያደገበት በመሆኑ በአካባቢው ላይ ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን ይናገራል። እርሱ እንዳለው አሁን ሥዕሉ ባረፈበት ግንብ ላይ በጽሁፍ አላስፈላጊ የሆኑ መልዕክቶች ይተላለፉበት ነበር። ግንቡ በተለያየ ቀለማት በመዥጎርጎሩ ለእይታም ጥሩ አልነበረም። በግንቡ ሥርም በጎዳና ላይ የሚያድሩ ልጆች ስለሚፀዳዱበት ንጽህናው የተጓደለ ነው። አሁን በባለሙያዎች በሥዕል መሸፈኑ ለአካባቢው ውበት ፋይዳው የጎላ ነው። የአካባቢው ወጣቶች ለጥምቀት በዓል አካባቢውን በማጽዳትና ለእይታ ያስጠላ የነበረውንም ቀለም በመቀባት ጥረት ያደርጋሉ። ችግሩ ስለማይቀረፍ በዓመት አንዴ ብቻ ነው የሚያፀዱት። የሚመለከተው አካል ትብብር ካደረገላቸው ግን ዘላቂ የሆነ እንክብካቤ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። በአካባቢው የአረንጓዴ መናፈሻ በመኖሩም ከሥዕሉ ጋር ልዩ ውበት እንዳለው አስተያየት ሰጥቷል። እርሱም የሥዕል ሥራ እንደሚሞክርና ሙያውን አሳድጎ ለመቀጠል አቅዷል።
ወጣት ልዑል መኩሪያ እና ስምኦን አሰፋ በየበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የሥዕል ሥራን ከጎዳና ውጭ ነው የሚያውቁት። በጎዳና ላይ ተሥሎ ማየታቸው አግራሞት ፈጥሮባቸዋል። እንደሚያዝናና እንደሚያመራምርም ለመረዳት የቻሉት በአካባቢው የተሳለውን ሥዕል ካዩ በኋላ እንደሆነ ነው።
‹‹እኔም ሰዓሊያኑን በማገዝ አስተዋጽኦ አበርክቻለሁ›› ያለው ወጣት ልዑል ሰዓሊያኑ የሚጠቀሙበትን መወጣጫ (ፎክልፊት) በሚፈልጉት መጠን ከፍና ዝቅ በማድረግ ነው እገዛ ያደረገው።
ወጣት ስምኦንም አሁን ካለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማያያዝ በሰጠው አስተያየት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሠላም እጦት በሰዎችና በንብረት ላይ እየደረሰ ላለው ጉዳት ትምህርት ሰጭ እንደሆነ ያምናል። አንድነትንና መተባበርን የሚያሳይ በመሆኑ ወዶታል። ብዙ ሰዎች በሚያዩት አካባቢ መሳሉ ደግሞ የበለጠ መልዕክቱ እንዲሰራጭ ያደርጋል ሲልም ሀሳብ ሰጥቷል። ከሰዓሊያኑ የተረፈውን ክፍት ቦታ ኢትዮጵያውያን እንዲያሟሉት ፍላጎት እንዳለውና እርሱም በሚችለው ለማገዝ መዘጋጀቱን ገልጿል።
አስተያየት ሰጭዎቹ እንዳሉት በአካባቢው ስለምመላለስ ጉድለቱን እኔም አውቀዋለሁ። ከድልድዩ በላይ በአረንጓዴ የተዋበ ሥፍራ ይገኛል። ለሰርግ፣ ለተለያየ ዝግጅት እና መዝናኛ ብዙዎች ይጠቀሙበታል። የስረኛው ክፍል ደግሞ ለመፀዳጃ አግልግሎት ውሏል ማለት ይቻላል። የጎዳና ተዳዳሪዎችም ማደሪያና ውሎአቸው በዚሁ ድልድይ ሥር ነው። የድልድዩ ግንብ ፀያፍና የተለያዩ መልዕክት ማስተላለፍያም ነበር። የፖለቲካ አጀንዳም ማስተላለፊያነትም ይጠቀሙበታል። ጽሁፉን ለማጥፋት የሚቀባው የተለያየ ቀለም ደግሞ የአካባቢውን ውበት አደብዝዞታል።
በውድድር አሸናፊዎች የተሳለው ሥዕል ይህን ገጽታ ያጠፋ ቢሆንም፤ ሙሉ ለሙሉ የነበሩ መጥፎ ገጽታዎችን ያጠፋ ባለመሆኑ ቀሪውን ለውጭ ሰዓሊያኑ ረዳት ሆነው የሰሩት የእኛ ሰዓሊያን እንደሚቀጥሉበት ተስፋ እናደርጋለን። አዲስ አበባ ከተማን ውብና ጽዱ ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት የሥዕል ሥራው መጨመሩ ውበቱን የሚያጎላ ነው። በአካባቢው ለሚያልፍ ሁሉ የዓይነ ማረፊያ፣ የስዕል ጥበብን ለሚያደንቅ ደግሞ መማማሪያ ይሆናል። በአንድ በኩል ውበት በሌላ መልኩ ጽዳት ነው።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም