በሀገራችን የተለያዩ ግንባታዎችን ለማካሄድ ዲዛይን ተዘጋጅቶላቸው እና ጥናት ተሰርቶላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ከመደርደሪያ ጌጥነት ሳያልፉ ዓመታትን ሲያስቆጥሩ ማየት የተለመደ ነው። መሰል ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የዲዛይን እና ጥናት ክለሳ ሳይደረግ ወደ ስራ ለማስገባት አዳጋች ይሆናል። በመሆኑም ክለሳ ማድረግ የግድ ይላል። በሀገራችን ዲዛይንና ጥናቶች ተሰርቶላቸው ወደ መሬት ሳይወርዱ ከቆዩ ፕሮጀክቶች መካከል የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያ መስኖ ልማት ኮሚሽን ጥናት ተሰርቶላቸው እና ዲዛይን ተዘጋጅቶላቸው ዓመታትን ያስቆጠሩ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ከመደርደሪያ ወደ መሬት ለማውረድ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ይፋ አድርጓል። በመገባደድ ላይ ካለው ዓመት መጀመሪያ አንስቶ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውቋል።የመስኖ ልማት ኮሚሽን የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደሚሉት የስድስት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የጥናትና ዲዛይን ክለሳ እየተደረገ ነው። የመስኖ ጥናትና ዲዛይን ክለሳ ፕሮጀክቶቹ በሶስት ክልሎች ውስጥ ለማካሄድ ዲዛይንና ጥናት ተሰርቶላቸው ወደ ተግባር ሳይቀየሩ የቆዩ ናቸው።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት – ሦስት፣ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት -ሁለት እና በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አንድ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፤ በድምሩ ስድስት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ናቸው።የጥናትና ዲዛይን ክለሳ ከሚከናወንላቸው ፕሮጀክቶች መካከል የግልገል አባይ ግድብና መስኖ መሰረተ ልማት፣ የጅማ ግድብና መስኖ መሰረተ ልማት፣ የገላና ግድብና መስኖ መሰረተ ልማት፣ የጎሎልቻ ግድብና መስኖ መሰረተ ልማት እና የብላቴ ግድብና መስኖ መሰረተ ልማት ተጠቃሽ ናቸው።
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት ክለሳ እየተደረገላቸው ያሉ ፕሮጀክቶች ዲዛይኖቹና ጥናቶቹ ተሰርተው ወደ መሬት ሳይወርዱ ከአምስት እስከ አስር ዓመት በመደርደሪያ ላይ ቆይተዋል። በመሆኑም በአካባቢው ለውጦች ይኖራሉ። የመሬት አቀማመጥ እና ማህበራዊ ለውጦች ያጋጥመናል። ለዚህም ነው ጥናቶቹና ዲዛይኖቹ እንደገና መከለስ ያስፈለገው። የአንዳንድ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ክለሳ ተጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት በሚያስችል ደረጃ ላይ ሲሆን፤ የተቀሩት ደግሞ በመገባደድ ላይ ባለው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ክለሳው ይጠናቀቃል። በአጠቃላይ ለፕሮጀክቶቹ ጥናትና ዲዛይን ክለሳ 53 ሚሊየን ብር የተመደበ ሲሆን፤ ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት ከ7 እስከ 8 ሚሊየን ብር ተበጅቷል።
ፕሮጀክቶቹ ወደ ተግባር እንዳይለወጥ አድርገው የነበሩ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ለፕሮጀክቶቹ ዋነኛው ተግዳሮት ሆኖ የነበረው የገንዘብ እጦት እንደነበር ያስረዱት አቶ ብዙነህ አሁን ግን መንግስት ለመስኖ ከሰጠው ትኩረት አኳያ በአሁኑ ወቅት ገንዘብ ለመበጀት ቃል በመግባቱ ክለሳው ማስፈለጉን ነው የጠቆመው። የጥናትና ዲዛይን ክለሳ ስራውን እየሰሩ ያሉት የአምስቱን ፕሮጀክቶች የየክልሎቹ የጥናትና ዲዛይን ኢንተርፕራይዞች / ኮርፖሬሽኖች ሲሆኑ፤ አንዱን (የብላቴ ግድብና መስኖ መሰረተ ልማትን ) ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን መሆኑን ያብራሩት አቶ ብዙነህ፤ የፕሮጀክቶቹ የጥናትና የዲዛይን ክለሳው ስራ ተጠናቆ ወደ ግንባታ ሲገቡ 64 ሺህ 253 ሄክታር የማልማት አቅም እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
የሁለት የፕሮጀክቶች የጥናትና ዲዛይን ክለሳው ስራው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የጅማ ግድብና መስኖ መሰረተ ልማት ፣ የብላቴ ግድብና መስኖ መሰረተ ልማት እና የጎሎልቻ ግድብና መስኖ መሰረተ ልማት በቅደም ተከተል 60፣ 86 እና 90 በመቶ አፈፃፀም ላይ መድረሳቸውን አቶ ብዙነህ አብራርተዋል።
የግልገል አባይ ግድብና መስኖ መሰረተ ልማት የጥናትና ዲዛይን ክለሳ ስራ የአናት ስራው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የመስኖ አውታር ጥናትና ዲዛይን ክለሳ ስራው 70 በመቶ ደርሷል። የፕሮጀክቶቹ የጥናትና ዲዛይን ክለሳው ስራው በ2013 በጀት ዓመት የተጀመሩ ሲሆን፤ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ የሚጠናቀቁ ይሆናል።የጥናትና ዲዛይን ክለሳው ስራ ሲጠናቀቅ ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ ወደ ግንባታ የሚገቡ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የሚያስገኙ ሲሆን፤ በተለይም ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ የሚኖረው ሚና የላቀ እንደሚሆን ከወዲሁ ተስፋ ተጥሎበታል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2013 ዓ.ም