ተወልደው ያደጉት በጎንደር ደባርቅ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተወልደው ባደጉበት ደባርቅ ከተማ ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ተምረዋል። በመቀጠልም ከመምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ በመምህርነት ሙያ በሰርተፍኬት ሰልጥነው በበለሳ የማስተማር ስራቸውን አንድ ብለው ጀመሩ። ለሁለት አመት ያህል ካስተማሩ በኋላም ለተሻለ ትምህርት ፍለጋ በለሳን ለቀው ወደ ጎንደር አቀኑ። በጎንደር ከተማ ቀን ቀን በመምህርነት እየሰሩ በማታው መርሃ ግብር በመምህራን ኮሌጅ በመግባት በእንግሊዝኛ ቋንቋ በዲፕሎማ ተመረቁ። ከማስተማር ስራቸው ጎን ለጎንም በወንዶች ፀጉር ስራ ተቀጥረው በመስራት ጊዜያቸውን ከፋፍለው ለለውጥና ለውጤት ጥረት ማድረግ ቀጠሉ።
ብዙም ሳይቆዩ ባጠራቁሙት 8 ሺህ ብር ጎንደር አራዳ አካባቢ የራሳቸውን ፀጉር ቤት በመክፈት የግል ስራን አሃዱ ብለው ጀመሩ። ከነበራቸው 8 ሺህ ብር ላይ በቅድሚያ የስድስት ወር የቤት ኪራይ በመክፈል በግማሹ ብር ሁለት ባለሙያ ቀጥረው እራሳቸውም እንደ አንድ ባለሙያ ሆነው ስራቸውን ተያያዙት። አንድ ሁለት እያሉ ስራን ሳይንቁ ደከመኝ ብለው ሳይሰላቹ ሰርተው ከብዙ ውጣ ውረድና ፈተናዎች በኋላም ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ባለቤት ለመሆን ቻሉ- አቶ ወርቁ አያና።
ሁለት የፀጉር ባለሙያዎች ቀጥረው ከእነሱ የሚገኘውን ገቢ ለወጪ መሸፈኛ በማድረግ የራሳቸውን ገቢ ደግሞ በየሳምንቱ እቁብ በመጣል ብር ማጠራቀም የጀመሩት አቶ ወርቁ፤ ይህ ተግባራቸው አሁን ላሉበት ደረጃ ከፍተኛ ሚና ተጫውቶላቸዋል። የደባል ሱስ ተጠቂ አለመሆናቸው ደግሞ ስራቸውን በትክክል እንዲሰሩ አስችሏቸዋል። ለትምህርት ቤት ክፍያ ከሚያወጡት ወጪ በስተቀር የሚያጠፉት ገንዘብም አልነበራቸውም። ቀደም ሲል ወንዶች ፀጉራቸውን ‹‹በቶንዶስ›› የሚስተካከሉበት ግዜ የነበረ ቢሆንም እርሳቸው ፀጉር ቤት ሲከፍቱ የፀጉር ማስተካከያ ማሽን በመምጣቱ ስራቸውን አቀላጥፎ ለመስራት ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረላቸው። በየቀኑ ሰርተው የሚያገኙት ገቢም ብርታት ሆኗቸው ጠንክሮ ለመስራት ጉልበት አገኙ።
የሁለት አመት እቁብ 35 ሺ ብር ሲደርሳቸው ተጨማሪ ብር ከባንክ በመበደር ቴዎድሮስ ሙዚቃ ቤትን በመግዛት ወደ ተሻለ የንግድ አማራጭ ሄዱ። በሂደትም ሙዚቃ ቤቱን ወደ አሳታሚነት አሸጋገሩ። የመጀመሪያውን የሄለን በርሄን፣ የአምሳል ምትኬን፣ የደረጄ ዱባለንና የፋሲል ደሞዝን ጨምሮ የበርካታ ታዋቂ ሙዚቀኞች ስራም አተሙ። ይሁን እንጂ የሙዚቃ ቴክኖሎጂ መልኩን የቀየረበት ወቅት በመሆኑና የካሴት ስራም እየተዳከመ በመምጣቱ ከሙዚቃ አሳታሚነት ወደ ኤሌክትኖኒክስ እቃዎች ንግድ ተሸጋገሩ። የሞባይል ቀፎዎችን፣ ጂፓሶችን፣ ማቀዝቀዣዎችንና ቴሌቪዥኖችን በስፋት በመሸጥም የኤሌክትሮኒክስ እቃ ንግዱን አደሩት።
አቶ ወርቁ በግዜው የጀመሩት የኤሌክትኖኒክስ ንግድ አዲስና አዋጭ በመሆኑ ብሎም በሸማቹ ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት በማግኘቱ በቀላሉ ትርፋማ ለመሆኑን ቻሉ። ጥራት ያላቸው የኤሌክትሮኒክ እቃዎችን ለገበያ በማቅረባቸውም በርካታ ደምበኞችን አፈሩ። ይህ የቢዝነስ አካሄዳቸው ለግዜው ተጠቃሚ ባያደርጋቸውም በሂደት ግን በርካታ ደንበኛችን ለማፍራት ረዳቸው። እቃ የሚገዛ ሰው ተበድሮ አልያም ደግሞ እቁብ ደርሶት ሊሆን ስለሚችል የሚገዛው እቃ ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግል የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በጥራትና በታማኝነት ለገበያ ማቅረባቸውንም ቀጠሉ። ተመሳስለው የሚሰሩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ቢኖሩ እንኳን በጥንቃቄ ጥራት ያላቸው እቃዎችን ለደንበኞቻቸው መሸጣቸውን ተያያዙ።
በ2002 ዓ.ም በደባርቅ ከተማ ተዘጋጅቶ በነበረው ባዛር ለመሳተፍ በሄዱበት ወቅት በሊዝ ጨረታ ካልተሸጡ ቦታዎች ውስጥ አንዱ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄያቸው ምላሽ በማግኘቱም በ2004 ዓ.ም ቦታው ተፈቅዶላቸው የሆቴል ግንባታ ስራ ጀመሩ። በመጀመሪያ የተፈቀደላቸው 2 ሺ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ቢሆንም መሬት እንዳይባክን በሚል 1 ሺህ 500 ካሬ ሜትር እንዲወስዱና ወደፊት የስራቸው ውጤታማነት እየታየ እንደሚጨመርላቸው ቃል ተገባላቸው። ከኤሌክትሮኒክስ እቃ ንግዱ ጎን ለጎን ወደ ሆቴል ንግድ ዘርፍ በመቀላቀልም በአምስት አመት ውስጥ ግንባታውን አጠናቀው ‹‹ራስ ደጀን›› የተሰኘና ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል አስመርቀው ስራ አስጀመሩ።
አዲስ ስራ ሲጀመር በቅድሚያ በሁለት እግሩ ማቆም እንደሚያስፈልግ የተረዱት አቶ ወርቁ፤ ሁለት ስራ በአንድ ግዜ መስራት እንደማይችሉና ይህም ለኪሳራ ሊዳርጋቸው እንደሚችል አስቀድመው በመገንዘባቸው ሙሉ አቅማቸውን በሆቴል ስራ ላይ ብቻ ለማድረግ ከባለቤታቸው ጋር ተነጋግረው ወሰኑ። ጠንካራና ታታሪ የሆኑት ባለቤታቸውም ቀደም ሲል የሽያጭ ስራውን እንዳገዟቸው ሁሉ በሆቴል ስራውም አስተዋፅኦዋቸው ጉልህ ነበር።
በግዜው ሆቴሉን ሲገነቡ የግንባታ እቃዎች ዋጋ ውድ በመሆናቸው ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ብዙ ተፈተኑ። ሆቴሉ ተገንብቶ ከተጠናቀቀም በኋላ መሟላት ያለባቸው ቀሪ እቃዎች ስለነበሩ እቃዎቹን ለማሟላት በርካታ ውጣውረዶችን አለፉ። እነዚህን የሆቴል እቃዎች ለማሟላትም ለመጀመሪያ ጊዜ ከባንክ 50 ሺ ብር ተበደሩ። አሁንም ከባንክ ጋር እየሰሩ ሲሆን ሰርተው የሚያገኙትን ትርፍ በአግባቡ ወደ ስራ በማዋላቸው የብድር አመላለስ ስርዓት ላይ ችግር አልገጠማቸውም። በአሁኑ ወቅትም 10 ሚሊዮን ብር ተበድረው እየሰሩ ይገኛሉ።
ብድርን ወስዶ በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ስራን ለማሳካት ያግዛል የሚሉት አቶ ወርቁ ፤ሰዎችን የሚቀይረው ብድር እንደሆነና ነገር ግን ጥሩ የአመላለስ ዘዴን መከተልና ጥሩ ደንበኛ መሆንን እንደሚፈልግ ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ ሰዎች የሚሰሩትን አውቀው ከተበደሩ ኪሳራ እንደማይኖረውና እርሳቸውም በዚህ ሂደት ውስጥ በማለፍ ጥሩ ቦታ መድረሳቸውን ይገልፃሉ። የብድር ልምድ የሌለው ሰው ችግር ሊያጋጥመው ስለሚችል ብድሩን ከመውሰዱ በፊት የሚሰራውን ስራ መለየትና ብድሩን እንዴት በስራው ላይ ማዋል እንዳለበት ሊገነዘብ እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
ስራ መስራት ያለመደ ሰው ብድር ቢያገኝም አጠቃቀሙን ስለማይችልበት ወደ ኪሳራ ሊያመራ እንደሚችልም አቶ ወርቁ ተናግረው፤ ከዚህ በመነሳት ከገንዘብ ይልቅ ስራን ማስቀደም አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታሉ። ውጤታማ መሆን ከተቻለ ስራው በራሱ ብድር እንዲመጣለት የሚናገር መሆኑንም ይጠቅሳሉ። መበደር ብቻ ሳይሆን በብድሩ በአግባቡ ሰርቶ ማትረፍ እንደሚያስፈልግና ይህ ካልሆነ ግን የባንኮች ወለድ ከፍተኛ በመሆኑ ብድር አስቸጋሪ ችግሮች ውስጥ ሊከሰት እንደሚችል ያሳስባሉ።
የአቶ ወርቁ ሀብት የሆነው ራስ ደጀን ሆቴል በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ የገባው አንድ ስራ አስኪያጅና ሰላሳ ሰራተኞችን በመቅጠር ነበር። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ሆቴሉ ወደ ስራ ከገባ ሁለት አመት ያሰቆጠረ ሲሆን ለሰላሳ ስምንት ሰዎች በልዩ ልዩ መስኮች የስራ እድል ፈጥሯል። በቀጣይ ሆቴሉን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር እንግዶች ተመራጭ እንዲሆን የማሳደግ ስራዎች እየተሰሩም ይገኛሉ። ሆቴሉ የባህላዊ እቃ መሸጫ፣ ባህላዊ መዝናኛ፣ ጂምና ሳውና ባዝ እንዲኖረው ለማድረግም ተጨማሪ ስራዎች ይከናወናሉ።
ለግዜው ትኩረታቸው በሆቴል ንግዱ ላይ ቢሆንም በሂደት ግን ወደ ሌላ ንግድ ዘርፍ የመሰማራት እቅድ እንዳላቸው አቶ ወርቁ ይናገራሉ። በተለይ የሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሆቴል አገልግሎት ዘርፍ ክፍተት የሚታይበት በመሆኑ ይህን ክፍተት ለመሙላት ከመንግስት የቦታ ፈቃድ ማግኘት እንደሚፈልጉም ይገልፃሉ። በሆቴል ዘርፉ ብቻ ተወስነው መቅረት እንደማይፈልጉም ተናግረው፤ ወደ ፊት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በመሰማራትና ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ሀገራቸውንና ራሳቸውን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሚፈልጉም ይጠቁማሉ።
‹‹ስራ የሚሰራው ብር በመያዝ ብቻ አይደለም›› የሚሉት አቶ ወርቁ፤ ስራ ለመጀመር በቅድሚያ ቁርጠኝነቱና ፍላጎቱ ይጠቅሳሉ። ሰርቶ የከሰረ ሰው እንደሌለና ነገር ግን ለስራ ትኩረት ባለመስጠትና የደባል ሱሶች ተገዢ በመሆን በራካቶች ለኪሳራ ሲዳረጉ እንደሚታዩም ያስረዳሉ። ገንዘብ ይዞ ምን ልስራ? ብሎ የሚጨነቅ እንዳለ ሁሉ ሙያ ይዞ ገንዘብ በማጣቱ ብቻ ስራ ያጣ ሰው እንዳለም ይገልጻሉ። ስራ በገንዘብም ሆነ በሙያ ብቻ የሚሆን ነገር ባለመኖሩ አዲስ ስራ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
አዋጭ ስራ የቱ ነው? ብሎ መለየትና ጥናት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በንግዱ አለም በአንድ ጊዜ የተሟላ ነገር ማግኘት የማይቻል በመሆኑ ገንዘብ ከስራ ከቀደመ ውድቀት መሆኑን ይገልፃሉ። የስራ ባህል ሳያዳብሩ ብር ማግኘት ስራን ለመምራትም ሆነ ገንዘብን በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋል እንደማያስችልም ይጠቁማሉ። ከዚህ አኳያ ስራ ቢቀድምና ከስራ በኋላ ገንዘብ ቢገኝ ስራውን የማስፋት እድል እንደሚኖር ያስረዳሉ። የስራ ልምድ ካለው ሰው ጋር በመዋል የስራ ልምድን መቅሰም እንደሚገባ ይህም ወደሚፈለገው ስራ ለመግባት ራስን አዘጋጅቶ በስራው ላይ ጠንካራ ሆኖ ለመስራት እንደሚያስችል ያመለክታሉ።
ከምንም በላይ ስራ ክትትል እንደሚፈልግና በተለይ ደግሞ እያንዳንዷ ገንዘብ የምትወድቅበትን ቦታ ማወቅ እንደሚጠይቅም አቶ ወርቁ ገልፀው፤ ትርፍ ማትረፍ የሚቻለው ገንዘብን መቆጣጠር ሲቻል እንደሆነም ያብራራሉ። ነጋዴ ማየት ያለበት ብዙ ማትረፉን ብቻ ሳይሆነ ገቢውን መቆጣጠሩንና አለማባከኑንም ጭምር ነው ይላሉ።
አቶ ወርቁ የንግድ ስራ ብዙ ውጣ ውረድና እንቅፋቶች የሚበዙበት ከመሆኑ አንፃር በንግዱ አልተሳካልኝም ብሎ እራስን ማግለል እንደማይገባና ኪሳራ ደርሶብኛል ብሎ ማቆም ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ይልቅ በንግድ ውጤት የሚገኘው በተደጋጋሚ በመስራትና ከኪሳራ ትምህርት በማግኘት መሆኑን ይጠቁማሉ። ወደ ስኬት ለመጓዝ ከትንሽ ጀምሮ መቆጠብ እንደሚያስፈልግም ይጠቅሳሉ።
ሆቴሉን ለማሻሻል የሚያስፈልጉና ቃል የተገባው የቦታ ድጋፍ ቢደረግ አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኑ ጥራቱን የጠበቀና ምቹ ሆቴል የማድረግ እድል እንዳለም አቶ ወርቁ ይጠቅሳሉ። ለዚህም የቦታ ማስፋፊያ ጥያቄያቸው እንዲመለስላቸው የሚመለከተውን አካል ይጠይቃሉ። የሆቴል ስራ ከሰላም ጋር የተገናኘና ኮሽታ የማይፈልግ በመሆኑ መንግስት ትኩረቱን ወደ ሰላም ማዞር እንዳለበት ያመለክታሉ።
‹‹በስራ ላይ መውደቅና መነሳት ብቻ ሳይሆን ተስፋ መቁረጥም አለ›› የሚሉት አቶ ወርቁ በአንድ ወቅት ንግዱ አልሳካ ቢላቸው ወደ ቀድሟቸው የመምህርነት ሙያ ተመልሰው ለሰባት ወር ያህል አስተምረዋል። ወደ ንግዱ አለም ዳግም በመመለስም የፀጉር ሙያ ሰርተው ከውጣውረዶች በኋላ የሆቴል ባለቤት ለመሆን ችለዋል። የፀጉር ስራ በመስራታቸውም በቤተሰቦቻቸውና በጓደኞቻቸው ተንቀዋል። ነገር ግን ይህ ሁሉ ተስፋ ሳያስቆርጣቸው በትጋት በመስራታቸው የዛሬ ስኬት ላይ ደርሰዋል። ለዚህም ስኬት ባለቤታቸው ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። ሁሉንም ስራዎች ከፊት በመሆን በታታሪነት መርተዋል። ለሆቴሉ አውን መሆንም ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። እርሳቸውና ባለቤታቸው ከጎንደር ወደ ደባርቅ በመጓዝ ስራን ሰርቶ ውጤማ መሆን እንደሚቻልም አስመስክረዋል። የከተማዋንና አካባቢውን የስራ ባህል ከማሳደግ አኳያም የራሳቸውን አስተዋኦ አበርክተዋል።
ሞገስ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም