
አዲስ አበባ፡- ‹‹ያለፉት 50 አመታት የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ በማክበር በባህልና በታሪክ ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲዳብር ያደረገ ነው›› ሲሉ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሐና አርዓያሥላሴ ገለጹ።
ዳይሬክተሯ ትናንት የአገራቱን የ50 ዓመታት ግንኙነት በማስመልከት በተከናወነው የቴምብር ምርቃ ስነስርአት ላይ እንደተናገሩት፤ ተግባሩ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከፍተኛ ፋይዳ አለው። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከርም ያግዛል።
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር በኢትዮጵያና በቻይና መንግስታት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በተመረቀው ቴምብር ላይ የቻይና አሻራ ያረፈበት የሸገር ፓርክና የቤጂንግ ኦሎምፒክ ምስል እንደተካተተበትም አመልክተዋል።
የቻይና መንግስት የኢትዮጵያ ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና የስራ መስኮች ላይ እንዲሰማሩና አጫጭር ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በርካታ እድሎች ማመቻቸቱን ጠቁመዋል። ሂደቱ የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በባህልና በታሪክ ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲዳብር ማድረጉን ተናግረዋል።
ባለፉት 50 አመታት የቻይና መንግስት በመንገድ ግንባታ፣ በባቡር፣ በአየር መንገድና በኢነርጂ ማስፋፊያዎች ላይ ከፍተኛ ድጋፍ ማደረጉን አንስተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤስያና የፓስፊክ አካባቢ ዳይሬክተር ጄነራል ሞላልኝ አስፋው በበኩላቸው፤ የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ከሁለትዮሽ ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት አድጓል ብለዋል።
ባለፉት 50 አመታት ኢትዮጵያና ቻይና በሁሉም መስክ በርካታ ድሎችን አስመዝግበዋል ያሉት ዳይሬክተር ጄነራሉ፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ የሁለትዮሽና በአለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ግንኙነት ከፍ ብሎ ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት መሸጋገሩን አመልክተዋል።
የአገራቱ ግንኙነት በመርህና በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሁለቱን ሀገር ህዝቦች እንደሚጠቅም አመልክተዋል። ግንኙነቱ ከፍ ሲልም ለአፍሪካ የሚጠቅም ስራ እንዲሰሩ ማድረጉንም ጄነራል ሞላልኝ ገልጸዋል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከፍተኛና መተማመን ያለበት ነው። በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በፋይናንስ ልማት ያለውን ግንኙነት በማስቀጠል የበለጠ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት በመስጠት ይሰራል።
ቻይና በቀጥታ ኢንቨስትመንት በማስገባት ለሀገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን በመጠቆምም፤ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት በፖለቲካ መተማመን ላይ እና በእኩልነት መርህ ላይ ያተኮረ መሆኑን አመልክተዋል።
ቻይናዎች በሌሎች ሀገር ጣልቃ ያለመግባት የሚል መርህ እንዳላቸው ተናግረው፣ ይህም መርህ ወደ ተሻለ ግንኙነት እንዲደርሱ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የአምባሳደሩ አማካሪ ዣ ቲያን የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 50 አመታት የሞላው ብቻ ሳይሆን ጠንካራና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ አድርጎ የቆየ መሆኑን አስረድተዋል።
ቻይና በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣ በኮንስትራክሽን፣ በግብርናና በኢንዱስትሪው ዘርፍ መሰማራቷን ተናግረዋል። ሀገራቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልን ጨምሮ በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሲሠሩ የቆዩትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
ሞገስ ጸጋዬ