
ዳራ ኦቲልቾ፡- ለረጅም ጊዜያት ሲያነሷቸው ለነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የክልሉ መንግስት ምላሽ እየሰጣቸው መሆኑን በሲዳማ ክልል የዳራ ኦቲልቾ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
የወረዳው የሌላዎ መሬራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አስፋው አለሙ እንደተናገሩት ፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች እየመለሰ ይገኛል። በዚህም በተደጋጋሚ በወረዳው ነዋሪዎች ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩት የመንገድና የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፤ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እየተመለሱ ይገኛሉ።
በዚህም ህብረተሰቡ ደስተኛ እየሆነ በመምጣቱ በቀጣይም ከመንግስት ጋር በመሆን የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን አቶ አስፋው ጠቅሰው፣ «በወረዳው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ እንዲሆን ለበርካታ አመታት ስንጠይቅ ቆይተናል። ዛሬ በየአካባቢያችን የመጠጥ ውሃ ምንጮች ተገንብተው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆን ችለናል።» ብለዋል።
ሌላው የሌላዎ ሆንቾ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ማቲዎስ ዮሐንስ ወረዳው ራሱን ችሎ ከተደራጀ በኋላ ህብረተሰቡ ለረጅም ጊዜያት ሲያነሳቸው የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መምጣቸውን በመጥቀስ የአቶ አስፋውን ሀሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የመንገድ መሰረተ ልማቱም ቢሆን በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስፋፋ ይገኛል። በተለይም የወረዳው ዋና ከተማ የሆነውን የተፈሪ ኬላ ከተማን ከተለያዩ ቀበሌዎችና ወረዳዎች የሚያገናኝ መንገድ መሰራቱ ለአካባቢው ነዋሪ ትልቅ እፎይታን ሰጥቷል።
ጅጌሳ በሚባለው ወንዝ ላይ የነበረው የእንጨት ድልድይ በተደጋጋሚ እየተጎዳና ወንዙ ሲሞላ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ጉዳት ያደርስ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ድልድዩ በኮንክሪት በመገንባቱ ችግሩ ተፈትቷል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በልማቱ መደሰታቸውን ጠቅሰው፣ ነዋሪዎቹ እንደ መንገድ እና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሁሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎታቸውም እንዲመለስ ጠይቀዋል።
በሲዳማ ክልል የዳራ ኦቲልቾ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ሁሞ በበኩላቸው፤ የወረዳው ነዋሪ ለረጅም ጊዜ ሲያነሳ የነበረው የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደርና የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ሰፊ ሥራ እየተሰራ ይገኛል። በመልካም አስተዳደር ረገድ ወረዳው በ2011 ሲቋቋም ነዋሪዎች ርቀው ሳይሄዱ ፍትህ ማግኘት እንዲችሉ የፍትህ ተቋማት ተመስርተዋል። የባለሙያ ድጋፍ የሚፈልጉ የትምህርት፣ የጤናና የግብርና ሥራዎችም በባለሙያ ድጋፍ ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
በሌላ በኩል የህዝቡን የመልማት ፍላጎት እንዲሁም ሲቀርብ ለነበረው ሰፊ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ መሰጠቱን የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፤ ለአብነትም ወረዳው ከተቋቋመ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የኮብል ስቶን ሰፋፊ የጠጠር መንገዶች ሥራ መከናወናቸውን አመልክተዋል። ከተማዋን ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ከሚያገናኙ መንገዶች መካከልም ከተፈሪ ኬላ ወደ ሳፋ ኢንተርናሽናል መንገድ እንዲሁም ከተፈሪ ኬላ ወደ ሀገረ ሰላም የሚወስዱት መንገዶችና የሌሎች መጋቢ መንገዶች ግንባታዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ በሲዳማ ክልል መንግስት ድጋፍም ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በጂጌሳ ወንዝ ላይ ድልድይ ተሰርቷል። የወረዳው ቢሮ ህንጻ ግንባታም ሃምሳ በመቶ ደርሷል። ሌሎችም የልማት ጥያቄዎች እየተመለሱ ሲሆን፣ የወረዳው መመስረትም ለነዋሪዎች ሰፊ ጥቅም እያስገኘ ነው።
ንጹህ የመጠጥ ውሃን በተመለከተም አይ ኤር ሲ ከተባለ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር በርካታ የገጠር ቀበሌዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን እያገኙ ናቸው ያሉት አቶ ሰለሞን፤ በተያዘው በጀት አመት ብቻ አራት ቀበሌዎች ላይ 58 ንጹህ የመጠጥ ውሃ ግንባታ መከናወኑን በአብነት ጠቅሰዋል። በቀጣይም በገጠሩ አካባቢ ንጹህ የመጠጥ ውሃን በስፋት ለማዳረስ የተያዙ እቅዶች መኖራቸውንና በከተሞች አካባቢም ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም