የግሉ ዘርፍ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑ ቢታመንም ላለፉት በርካታ ዓመታት በበቂ ሁኔታ ተሳታፊ ሳይሆን ቀርቷል።አጠቃላይ የንግዱ ዘርፍ ጤናማ ባልሆነ መንገድ ሲመራ በመቆየቱ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የቁልቁለት ጉዞ ውስጥ ቆይቷል።በመሆኑም ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከት የሚችለው የግሉ ዘርፍ ከጨወታ ውጭ ሆኖ ኢኮኖሚው በከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ከርሟል።
ይሁንና በአሁን ወቅት መንግስት ኢኮኖሚው ከገባበት ቅርቃር መንጭቆ ለማውጣት ያስችላል ያላቸውን የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀመና ፖሊሲዎችንም እያሻሻለ ይገኛል።ከእነዚህም መካከል ለግሉ ዘርፍ የብድር አቅርቦት ማመቻቸትና ማበረታታት አንዱ ነው።በመሆኑም በ2010 ዓ.ም ለግሉ ዘርፍ ከግማሽ በታች ወይም 44 በመቶ ይቀርብ የነበረው የብድር አቅርቦት በ2012 ዓ.ም ወደ 64 በመቶ ማደግ ችሏል።ይህም ከጠቅላላው ብድር ውስጥ የግሉ ሴክተር የሚወስደው ብድር መጨመሩ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ተደራሽነትን መሻሻል ያሳያል።መሻሻሉን አስመልክቶ አጠቃላይ የፋይናንስ እንቅስቃሴው ምን መልክ አለው ምንስ ይቀረዋል ብለን ላነሳነው ጥያቄ በኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ተሾመ አዱኛ የሚከተለውን ብለዋል፡፡
ከለውጥ በኋላ የብድር አቅርቦትና የፋይናንስ ተደራሽነት በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል።ከለውጡ አስቀድሞ መንግስት ብድር የሚያቀርብ ቢሆንም አብዛኞቹ ብድሮች በመንግስት ተቋማትና በፐብሊክ ኢንተርፕራይዞች ይወሰዱ ነበር።ይህ ሁኔታም ከፍተኛ ችግር የነበረበት መሆኑ ይታወቃል።ሆኖም በአሁን ወቅት አብዛኛው የመንግስት ብድር ለግል ዘርፉ መሰጠት መቻሉ በለውጡ የመጣ ውጤት መሆኑን ነግረውናል፡፡
የግል ዘርፉ ሙሉ ለሙሉ ጠንካራ ነው ማለት ባይቻልም በባህሪያቸው ከመንግስት የተሻለ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ።ከዚህም ባለፈ የግሉ ዘርፍ ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና አለው።በተለይም የመንግስት አቅም ደካማ በሆነባቸውና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ።የግል ዘርፎች ቴክኖሎጂ ያላቸው የፈጠራ ችሎታቸው ከፍተኛ የሆነና ተደራሽነታቸውም የሰፋ ነው።ስለሆነም ለእነዚህ አካላት ብድር እንዲደርስ ማድረግ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ማሳደግና ማሻሻል ነው።
ከዚህ ቀደም ለግሉ ዘርፍ ብድር ከማመቻቸት ጀምሮ ከመንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንዲሁም እገዛ ባለማግኘታቸው ከዘርፉ ተገፍተዋል።መንግስት ብድሩን እራሱ እየሰጠ ለራሱ የሚወስድ ከሆነ ብዙ መስራት የሚችሉት የግሉ ዘርፎች ይህን ዕድል ባለማግኘታቸው ከኢኮኖሚው እንቅስቃሴ በቀላሉ ይገለላሉ ።
በአሁን ወቅት ግን መንግስት የግል ዘርፉ ብድር ማግኘት እንዲችል እያደረገ ነው።ይህም ሀገሪቷ ከግሉ ዘርፍ መጠቀምና ማግኘት የሚገባትን ጥቅም በሀገር ደረጃ እንድታገኝ ያስችላታል።በተጨማሪም የሀገሪቱ ኢኮኖሚው ጠንከራ ይሆናል። የሀገሪቷ ኢኮኖሚ ጠንካራ ላለመሆኑ ዋናው ምክንያትና ችግሩ የግል ዘርፉ በሚገባው ልክ አገልግሎት እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩ ነው።ስለዚህ እንዲህ ባለ መንገድ ብድር እየሰጡ የግል ዘርፉ እንዲጠናከር ማድረግ ጠንካራና ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚን በሀገሪቱ መፍጠር ያስችላል።ጠንካራ የግል ዘርፍ ፈጠርን ማለት ደግሞ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል።
የግሉ ዘርፍ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ባለፈ በቀጣይም ተከታታይ ድጋፍና ክትትል የሚያገኙ ከሆነ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን መፍጠር እና በሀገሪቱ የገጽታ ግንባታ ላይም የተሻለ ስዕል ለመገንባት ያስችላል።ስለዚህ ከለውጡ በኋላ የመጣው የፋይናንስ አቅርቦት በእጅጉ የሚበረታታ እና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባው እንቅስቃሴ ነው። ከዚህም ባለፈ ሀገሪቷ ላለፉት በርካታ ዓመታት ያልተጠቀመችበትን የግሉን ዘርፍ በመጠቀም ውጤታማ እየሆነች መጥታለች፡፡
ካለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ገደማ መንግስት ብድሩንም እራሱ በመውሰዱ ምክንያት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሁለት መንገድ ጉዳት ሲደርስበት ቆይቷል።ለአብነትም መንግስት ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት የሚያገኘውን ብድር እንደ ቴሌኮሙኒኬሽንና መብራት ሀይል ለመሳሰሉ ግዙፍ ተቋማት ይሰጥ ነበር።አንደኛ እነዚህ ተቋማት ብድሩን መጠቀም የሚገባቸው ትክክለኛ ተቋማት አልነበሩም።ሁለተኛ ደግሞ ተቋማቱ ብድሩን ወስደው ውጤታማ በማያደርግ ሥራ ላይ አውለውታል።ስለዚህ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ ቆይቷል።ነገር ግን አሁን ከለውጡ ወዲህ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል እየተሰራ ያለው ሥራ ትክክለኛና ውጤት ማስመዝገብ የቻለ ነው።
በሀገር ደረጃ ገንዘብ የመቆጠብ አቅም ትሪሊዮን የገባበት ሁኔታ መኖሩን ያስታወሱት ዶክተር ተሾመ፤ ነገር ግን ብር በብዛት መኖሩ ብቻ ሳይሆን ብሩን የምንጠቀምበት መንገድ ለኢኮኖሚው መሻሻል ትልቅ ድርሻ አለው።በተለይም ገንዘቡን ማንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን ገንዘቡን በትክክል የሚመለከታቸው አካላት እንዲጠቀሙበት ማድረግ ውጤታማ ያደርጋል።የግሉ ዘርፍም ውጤታማ ሊያደርጋቸው በሚችል መንገድ መጠቀም ከቻሉ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ መለወጥ ይቻላል።
በፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም