የሁለቱ አገራት የኬንያና ሶማሊያ ግንኙነት ወጣ ገባ ሲል ቆይቷል። እንዲያውም በቅርቡ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ተግባቦት ጀምረው ነበር።ባለፈው ማክሰኞ ኬንያ የወሰነችው ውሳኔ ግን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ዳግም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡
ኬንያ ለሦስት ወር ያህል ወደ ሶማሊያ የሚደረግ በረራ የለም ብላለች፤ በአንጻሩም ከሶማሊያ ወደ ኬንያም የሚደረግ በረራ የለም።አልጀዚራ እንደዘገበው ኬንያ ይህን ውሳኔ ስትወስን ምክንያቷ ምን እንደሆነ ግን አልገለጸችም።የኬንያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ምክንያት ሳያስቀምጥ ለሦስት ወር ያህል የማገድ ውሳኔውን አሳልፏል።
የኬንያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን እንዳስታወቀው፤ በክልከላው ወቅት ምንም አይነት በረራ ባይደረግም ለህክምና ቁሳቁሶችና ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታዎች ግን ተፈቅዶላቸዋል።ባለሥልጣኑ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጸው፤ ውሳኔው የተላለፈው በኬንያ መንግስት ነው።
ውሳኔው የሶማሊያ አቪየሽን እና የጉዞ ወኪሎችን አስደንግጧል ተብሏል።አንድ ስሙን ያልገለጸ የሞቃዲሾ አየር ማረፊያ ኦፕሬተር ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጸው፤ ስለምክንያቱም ምንም አያውቁም፤ በረራ ስለመቋረጡም የተነገራቸው ነገር አልነበረም።
ኬንያ ይህን ውሳኔ ያሳለፈችበት በግልጽ የተነገረ ምክንያት ባይኖርም ውሳኔው የተላለፈው ግን ሶማሊያ ከኬንያ የመጣ አደንዛዥ ዕፅ የቀላቀለ ጫት መያዟን ተከትሎ ነው።ሶማሊያ የጫት ቅጠሉን ከያዘች ከአንድ ቀን በኋላ ኬንያ ወደ ሶማሊያ የሚደረግም ሆነ ከሶማሊያ የሚመጣ በረራ ማገዷ መነሻ ሰበብ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወጣ ገባ ሲል የቆየ ነው።ይህ የበረራ እገዳ ከመተላለፉ ከአንድ ሳምንት በፊት ግን የሁለቱ አገራት ግንኙነት የጥሩ ጎረቤት ግንኙነት ነው ተብሎ ነበር።የሁለቱም አገራት መንግስታት ጥሩ ግንኙነት ይኖረናል ተባብለው፣ አንደኛቸው በሌላኛቸው ላይ ጣልቃ ላይገቡም በዲፕሎማሲ ቋንቋ ተማምለውም ነበር።
ከሦስት ወራት በፊት በታህሳስ ወር ደግሞ ኬንያ ከሶማሊያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዘግታ ነበር።ሶማሊያ ኬንያን በሶማሊላንድ ጉዳይ ትፈተፍታለች በሚል ወቅሳታለች።
በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት እውቅና የሌላት ሶማሊላንድ ስታወዛግባቸው ቆይታለች።ሁለቱ አገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ የግዛት ውዝግብም አለባቸው።የሚወዛገቡበት ግዛት የነዳጅ ክምችት ያለበት መሆኑ ነገሩን ያጦዘዋል።
ሶማሊያና ኬንያ በዳዳብ የስደተኞች መጠለያም ሲቆሳሰሉ ቆይተዋል።ኬንያ መጠለያውን እዘጋለሁ እያለች ተደጋጋሚ ውሳኔ ብታሳልፍም የኬንያ ፍርድ ቤት ከልክሏታል።ኬንያ መጠለያውን ለምን ትዘጊዋለሽ ስትባልም ‹‹ለአገር ውስጥ ደህንነቴ ያሰጋኛል›› የሚል ምላሽ ሰጥታለች።
ዋነኛው ተጠርጣሪ አልሸባብ ቢሆንም ሶማሊያን ለማስቀየም ነው የሚሉ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል።ሁለቱ የቀጠናው አገራት በዚህ ውዝግብ ውስጥ መሆናቸው ወቀሳ ለማይለየው የአፍሪካ ቀንድ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም