በአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉ የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎች ጥቂት የማይባሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገቢያቸው የተመሰረተው በአጎዛ ገበያ ንግድ ስራ ላይ ነው። መተዳደሪያ ነውና ገቢያቸው የቤተሰቦቻቸውን ህይወት አስቀጥሏል።
እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በገበያው ውስጥ ቋሚና የተመቻቸ ቦታ አግኝተው የታወቁ ነጋዴዎች መሆን የዘወትር ምኞታቸው ነው። ሆኖም የምኞታቸውን ያህል ባይሳካላቸውና የልባቸው ባይሞላም ከንግዱ ቦዝነው አያውቁም። እሮቡ፣ ቅዳሜና የበዓላት ዋዜማዎችን ማልደው ወደ አጎዛ ገበያ ያቀናሉ። ጤፍ፣ገብስ፣የተከካ ሽሮ፣ ሽንብራ፣ ባቄላ፣ ቅቤ፣አይቤ፣ዶሮ፣እንቁላል በአህያ ጭነው፣ በጀርባቸው አዝለውና በትከሻቸው ተሸክመው በስፍራው ይገኛሉ።
ራቅ ካለ አካባቢ የሚመጡ ቢሆኑም ምልልሱ አይሰለቻቸውም። ርቀቱ አይገድባቸውም። በተለይ በአጎዛ ገበያ መነገዱን ከቤተሰቦቻቸው የወረሱት በመሆኑ ቦታውን ይመርጡታል።
ቅዳሜ የበዓል ዋዜማ ዕለት በስፍራው ተገኝቼ ካነጋገርኳቸው መካከል ወይዘሮ ወይንሸት አበራ አንዷ ናቸው። እሳቸው በልጅነታቸው ወላጆቻቸው ይዘዋቸው ይመጡ እንደነበር ያስታውሳሉ።ጤፍ፣ስንዴ፣ገብስ፣የሽሮ እህልና ሌሎች የእህል ዓይነቶችን በአጋሰስና በአህያ ጭነው በመምጣት ነበር የሚሸጡት።ከገበያው ደግሞ ለቤታቸው የሚያስፈልጋቸውን ጨው፣ስኳር፣ዘይት፣ የኩራዝ ጋዝ፣ክብሪት፣ሳሙናና ሌሎች ሸቀጦችን ይዘው ይመለሱ ነበር። አሁን ወላጆቻቸው በሕይወት ባይኖሩም የአደጉበትን ስራ እሳቸው ወርሰዋል። በአጎዛ ገበያ ሲነግዱ 30 ዓመታት ማስቆጠራቸውን ነው ያጫወቱኝ።
ወይዘሮ ወይንሸት የተሰማሩት በቅቤና አይብ ንግድ ነው። ነገር ግን እንደገበያው ሁኔታ ወቅቱን እያዩም ዶሮና እንቁላል ያቀርባሉ። በተለይ ለደንበኞቻቸው የሀበሻ ዶሮና እንቁላል በማምጣት ወዳጅነት ጭምር ማትረፋቸውን ይናገራሉ።
ኑሯቸው ከንግዱ በሚያገኙት ገቢ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ኑሮ ቢወደድም የሚያገኙት ትርፍ እየሳሳ ቢሄድም ወደ ገበያው መምጣትን አላቆሙም። ያለ አባት የሚያሳድጓቸውን አራት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉትና ኑሮን የሚገፉት በዚሁ ስራ ነው።
ሌላዋ ያነጋገርኳቸው ደግሞ ከለገጣፎ የመጡት ወይዘሮ ብዙነሽ ታደሰ የበዓላት ዋዜማን ጨምሮ ሰርክ ቅዳሜና እሮቡ ወደ አጎዛ ገበያ ቅቤና አይብ ለመሸጥ ይመጣሉ። በተጨማሪም እንቁላልና ዶሮ እንዲሁም የግብርና ምርቶችንም በማምጣት ይነግዳሉ። እርሳቸው እንደሚሉት አጎዛ ገበያ የለመዱት ቦታ በመሆኑ ነው እንጂ የተለየ ትርፍ የሚያገኙበት ስፍራ አይደለም። እንዳውም ከቦታው ርቀት አንጻር የትራንስፖርት ተጨማሪ ወጪ ያወጣሉ። ሆኖም ግን በለመዱበት የስራ ቦታ ተመላልሰው በመነገድ ስምንት ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩት ስራ በመሆኑ አይማረሩም።
አጎዛ ገበያ ከሾላ ገበያ ቀደምትና ዕድሜ ጠገብ ነው። በተለይ የኦሮሚያ ዙሪያ ወረዳ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ገቢ በዚህ ገበያ ላይ የተመሰረተ ነበር። የአካባቢው ነዋሪና በቅርብ ርቀት የሚገኘው ሕብረተሰብም በቀላሉ ግብይት የሚፈጽምበት ነበር። ቅዳሜና እሮብ ገበያው ደርቶ ይውላል። ሻጭና ገዢ ይገበያያል።
አቶ ናሆም ገነቱ በዚሁ ገበያ በቅመማ ቅመም ንግድ የተሰማሩ ናቸው። ገበያው ታዋቂና ታሪካዊ ቢሆንም የአስፋልቱ መሻገሪያ መንገድ በባቡር ሀዲድ በመዘጋቱ ነጋዴውን ለተጨማሪ ወጪ እያዳረገው መሆኑን ይናገራል። በተለይ ትራንስፖርቱ ፣የጫኝና አውራጁ ወጪ ተዟዙሮ የሚመጣበትና ዳገታማ ከመሆኑ አንፃር አስቸጋሪ ነው። መንግስት ገበያው የብዙ ዜጎች ህልውና መሆኑን ተገንዝቦ ምቹ ቦታ ቢሰጠን ሲል ይጠይቃል ።
‹‹በአዲስ አበባ ዙርያ ወረዳ በአህያና በአጋሰስ ጭነው ከሚመጡ ነጋዴዎች ገዝቶ በማትረፍ ኑሮውን ይመራ የነበረ ነጋዴ ቁጥሩ ቀላል አልነበረም››ያለንና አሁን ይሄ መቅረቱን ያጫወተን ወጣት ሲሳይ ነጋሽ በአትክልት ንግድ ነው የተሰማራው ። አሁን ላይ በባቡር ሀዲዱ ምክንያት መንገዱ በመዘጋቱ ከመርካቶ ጭኖ ለማምጣት ያስቸግራል። ቀጥተኛው መንገድ በመዘጋቱ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ይናገራል።
ወይዘሮ ሀና ተፈራ ከልጅነታቸው ጀምሮ አጎዛ ገበያ ተጠቃሚ ናቸው ። ወደ ገበያው ለመምጣት መቸገራቸውን ይናገራሉ። ። እሳቸው እንዳስተዋሉት መንገዱ መዘጋቱ በአካባቢው ነዋሪና በገበያው ተጠቃሚ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሯል ።ሆኖም ገበያው ነባር ከመሆኑና ብዙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሕይወታቸውን የሚመሩበት በመሆኑ መንግስት አማራጭ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዑራኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ወንዝ ዳር የሚገኘው የአጎዛ ገበያ የተመሰረተው አጎዛ በተባለ ግለሰብ ስም ነው። ግለሰቡ እሮቡና ቅዳሜ እንዲሁም የበዓላት ዋዜማ ቀን ከወንዙ ማዶ ዶሮና እንቁላል ይዞ ይቀመጥ ነበር። በተለይ በቅርብ ርቀት የሚገኙ ፈረንጆችና ሠራተኞቻቸው አዘወትረው ስለሚገዙት በገበያው መዋሉንና መሸጡን ቋሚ አደረገው ። ቀስ በቀስም እሱን በመከተል አንዳንድ ነጋዴዎች መጥተው አጠገቡ ይቀመጡ ጀመር። ገበያው እየሰፋ ወንዝ እስከመሻገር ደረሰ። በሰውዬው ስም ‹‹አጎዛ›› የሚል ስያሜ ተሰጠው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም