ወጣትነት ለውጥ ናፋቂነት ነው።የአንድ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው ባላት ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን ያንን ተረክቦ በአደራ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚችል ትውልዳዊ ትስስር ሲኖር ነው። ይህንንም እንደ ድልድይ ሆኖ ከአንዱ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው ።
በማንኛውም አገር፣ ጊዜና ዘመን እያንዳንዱ ተተኪ ትውልድ የአገሩ ወራሽ፣ ተተኪና ተረካቢ፣ ጠባቂና ለሚቀጥለውም ትውልድ የማውረስ፣ የማስተላለፍና የማስረከብ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት። አገርን ከእነ ሙሉ ክብሯ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ከወጣቱ የዜግነት ግዴታዎች ውስጥ አንዱ ነው። አገር በአንድና በሁለት ትውልድ ብቻ የሚቆምና የሚያልፍ ሳይሆን የማያቋርጥ ቀጣይነት ያለው ትውልድ ሁሉ የሚቀባበለው፣ የሚጠብቀው ያለፈውንና የሚመጣውን ትውልድ ሁሉ የያዘና ያቀፈ የአገርና የሕዝብ የታሪክ ሂደት ነው።
ወጣት ለአንድ አገር በሦስቱም ዘርፍ ማለትም በማህበራዊ፣ በሥነ ምጣኔ ሀብታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርጋል። ለዚህም ነው ወጣት ለአንድ አገር የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው።
አንድ ሰው የተሳካለት ሥራ ፈጣሪ (አዲስና የተለየ የቢዝነስ ሃሳብ ወይም ዘዴ ይዞ የተነሣ) ለመሆን፣ የያዘው ሃሳብና ሃሳቡን ተግባራዊ ማድረጊያ ገንዘብ ወሳኝ መሆናቸው አይጠረጠርም። ሆኖም እነዚህ ሁለቱ ብቻ ስራ ፈጣሪው የተሳካለት የቢዝነስ ሰው እንዲሆን አያስችሉትም። የስራ ፈጣነት ስኬትን መቀዳጀት እንዲችል ወይም ጉዞው ወደ ስኬት የሚገሰግስ እንዲሆን ዓይነተኛ የሆኑ የሰብዕና መገለጫዎች ያስፈልጉታል። እንደ ስራ ፈጣሪ እነዚህ የሰብዕና መገለጫዎች ወይም ጠባዮች ካሉ ሊዳብሩ፣ ከሌሉን ደግሞ እንደ አዲስ በውስጣችን ኮትኩተን ልናሳድጋቸው ይገባል።
ለዛሬ ይዘን የቀረብነው ጉዳዮችን በፍጥነት ለመከወን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ስለፈጠረው ኬብሮን ደጀኔ ነው። ኬብሮን አሁን ወደ 32ኛ ዓመቱ እየተጠጋ ያለ ወጣት ነው።ይህን ቪዲቸር የሚባል የቴክኖሎጂ ድርጅት ካሊፎርኒያ ውስጥ ሲሊከን ቫሊ በተሰኘው የቴክኖሎጂ መናኸሪያ ውስጥ የዛሬ አራት ዓመት ሲያቋቁም ገና 30 ዓመት አልሞላውም ነበር።ድርጅቱን በዓለም አስፋፍቶ ከአሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውሮፓና ሲሪላንካ ሳይቀር ባለሙያዎችን ቀጥሮ የሚያሰራ ሰው ሆኗል።የቪዲቸር ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ መስራችና ባለቤት የሆነው ኬብሮንን ይበልጥ ደስ የሚያሰኘው ግን እሱም ሆነ ባለሙያዎችን ያሰባሰበው ድርጅት የሚሰሩት በወጣትነቱ ለተለያት አገሩ ኢትዮጵያ መሆኑ ነው፡፡
በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችን በመጠቀም ከአገራቸው ጋር የሚያገናኛቸውን ጉዳዮች በቀላሉ መፈጸም እንዲችሉ የሚያግዝ ቴኮኖሎጂ መፍጠር ችሏል።ቪዲቸር የተሰኘውን የቴክኖሎጂ ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች መካከል፣ የፍርድ ቤት ውክልና፣ ፓስፖርት ፣ መታወቂያና የተለያዩ የባንክና የጉዞ ሰነዶችን በርቀት ሆኖ በመፈረም፣ ከየትኛውም የዓለም ክፍል በቀላሉና በፍጥነት መቀባበል የሚያስችል ቴክኖሎጂ የሚገኝበት ነው።ከዚህ በፊት ወራትና ቀናትን ይፈጁ የነበሩ ጉዳዮች ዛሬ በደቂቃና ሰዓታት ውስጥ መጠናቀቅ ችለዋል።የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን ወደ አንድ ቋት በማምጣት፣ ባለጉዳዮች የትም መሄድ ሳያስፈልጋቸው ስልኮቻቸው ላይ ሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉዳዮቻቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግም ተችሏል፡፡
ኬብሮን ቀደም ሲል የሚኖረው በካሊፎርኒያ አካባቢ ሲሆን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጣው በ18 ዓመቱ ነበር። አሁን ግን መኖሪያውን በቨርጂኒያ አርሊንግተን አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ እየተመላለሰ በመስራት ላይ ይገኛል።ድርጅቱ ቪዲቸር ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከል ዋነኛው በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ውስጥ ያሉ ጉዳዮቻቸውን ለማስፈጸም በአካል መገኘት ሳያስፈልጋቸው፣ ሳምንታትና ወራትን መቆየትም ሳያሻቸው፣ በጥቂት ሰዓታትና ደቂቃዎች ውስጥ ጉዳዮቻቸውን ማቀላጠፍ የሚያስችላቸውን ቴክኖሎጂ መዘርጋት ነው፡፡
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን” በዓለም ላይ በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነውን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደሚገኙ የተለያዩ የመንግሥትና ማህበራዊ ተቋማት እንዲሁም ወደ ሌሎቹ አፍሪካ አገሮችም ለማስገባት እየሠራ ሲሆን አንዳንዶቹም በዝግጅት ላይ ናቸው።
የስራው አጀማመር
ኬብሮን ድርጅቱን የተለያዩ ቦታዎች ላይ የከፈተ ሲሆን ቀደም ብሎ በፋይናንስ አድሚኒስትሬሽን ተምሯል።ከዚያም በኋላ የቴክኖሎጂ ፍቅር ስለነበረው እራሱን በማስተማር ወደ ሲልከን ቫሊ የራሱን ቴክኖሎጂ ለመፍጠር ሄደ።ሰባት ዓመት ያክል በቴክኖሎጂው ዘርፍ ላይ እየሰራ ይገኛል። ቴክኖሎጂን ለመገንባት ብዙ አይነት እውቀቶች ያስፈልጋሉ።ከዚህም ውስጥ የቢዝነስና የቴክኖሎጂ እውቀቶች ወሳኝ ናቸው። በተጨማሪም የመሰረተ ልማትና የዲዛይን እውቀቶች ያስፈልጋሉ።እነዚህ ሁሉ ሲደባለቁ ነው ትልቅ ኩባንያ መመስረት የሚቻለው።
ከስድስት ዓመት በፊት ሲልከን ቫሊ ውስጥ የተጀመረው ቪዲቸር የተባለው ኩባንያ ኢ-ቪንድቸር የተባለውን ቴክሎኖጂ ወደ ሞደርን ዘመን በማሻገር በቪድዮ የታገዘ ፊርማ እንዲሰራ ነው የተመሰረተው ።ይህንንም ቴክሎኖጂ አሜሪካ፣ ቻይና እንዲሁም ካናዳ ውስጥ በማድረግ በቪድዮ የታገዘ የፊርማ ቴክኖሎጂ ለአለም በማስተዋወቅ ላይ ነው ።ቪድቸር አንድ ሰው ከሩቅ ሆኖ ማንነቱን በማረጋገጥ በቪድዮ ፊርማ መፈረሙን የሚያረጋግጥ ቴክኖሎጂ ነው።ከዚህ በፊት የነበሩ ሲስተሞችን አሁን ዲጅታል ለማድረግ ምስል ማንሻ ስለሌላቸው ቪዲቸር የፊርማ ስርዓቱን እንዲያሳልጥ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰርቪሶች በፊት ከአስራ አምስት እስከ ሃያ የሚደርሱ ሥርዓቶች የነበሩት ሲሆን ውክልና ለመስጠት ማፃፍ፣ ለተለያዩ ቢሮዎች መላክ እንዲሁም ሌሎች አሰልቺ ምልልሶች ነበሩት።አሁን በኦንላይን ሲስተም በተወሰኑ ደቂቃዎች ውስጥ በቪድቸር ቴክኖሎጂ ውክልና ለማን እንደሚሰጥ እንዲሁም ፊርማ በመፈረምና በመክፈል ወደ ቤታቸው መሄድ ይችላሉ።ሌላው ደግሞ ፓስፖርትና ቢጫ ካርድ ለማደስ ከዚህ በፊት አዲስ አበባ በመሄድ እስከ ሁለት ወር የሚፈጀውን አሰራር አሁን ከአስር እስከ አስራ አምስት ቀን ወደ ደንበኛው ማድረስ ተችሏል።ውክልና መስጠት እረጅም ጊዜ ይፈጅ የነበረውን ወደ አንድ ቀን ማሳጠር ተችሏል፡፡
ሥራው የተጀመረው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ከሶስት ዓመት በፊት ነበር።ስራው ወደ ተግባር የገባው ወይም ከተጀመረ አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ነው።ይህን አገልግሎት በአሜሪካ ውስጥ የተጀመረ ሲሆን ወደ ሌሎች አገሮች እየተስፋፋ ነው።ቴክኖሎጂው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ተደርጎ የተሰራ ሲሆን አሁን ሁሉም አገር የተለያየ ነገር ስላለው ተራ በተራ ወደ ሲስተሙ እንዲገቡ እየተደረገ ነው።ለምሳሌ በፈረንሳይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገብቷል።በተጨማሪም በጣሊያን እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ወደ ሲስተሙ እየገቡ ነው።
ቴክኖሎጂው ለተገልጋዩ ብቻ ሳይሆን በኤምባሲው በኩል ያሉትንም ዲጂታል እንዲሆኑ አስችሏል።ይህ ማለት ኤምባሲዎች በወረቀት የሚቀበሉትን ጉዳዮች በዲጂታል መልኩ እንዲቀበሉ በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ በፍጥነት ማስተላለፍ እንዲችሉ ያደርጋል።ስለዚህ አሰራሩ ፈጣን እንዲሆን ያደርጋል ማለት ነው።ሁሉም የቴክኖሎጂው ሲስተም ሲዘረጋ ኤምባሲዎች፣ ደንበኞች እንዲሁም ውጭ ጉዳይ አንድ መስመር ላይ እንዲገናኙ ለማድረግ ነው የተሰራው።በፊት በደብዳቤ ይደረጉ የነበሩ አሰራሮች በተለይ በውክልና አሰጣጥ ላይ የነበረውን መንዛዛት በአጭር ደቂቃ ውስጥ ማቃለል ተችሏል።
የቴክኖሎጂው ጥቅሞች
የውክልና አሰጣጥ መቅለል ትልቁ ነገር ዳያስፖራው በቀላሉ ጉዳዮችን እንዲቀላጠፍ አድርጎታል።ዳያስፖራው በቀላሉ ጉዳዩን መፈፀም ከቻለ በቀላሉ ቤቱን ማከራየት፣ አፓርትመንቶችና ኢንቨስትመንቶችን ማንቀሳቀስና መግዛት ይችላሉ ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህን ዳያስፖራዎች በቀላሉ ወደ አገራቸው ሳይመለሱ ውክልና ለሚፈልጉት ሰው በቀላሉ መስጠት ይችላሉ ማለት ነው።በዚሁ ልክ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መንቀሳቀስ ይችላል ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በሁለት መንገድ ከአገሩ ጋር መገናኘት ይችላል ።የመጀመሪያው ካለበት አገር ወደ አገሩ ተመልሶ የሚፈልገውን መስራት ሲችል ነው።ሁለተኛው ግን በቀላሉ ካለበት ሆኖ ጉዳዩን የሚከታተልበት ውክልና ነው ።አንድ ሰው ውክልና መስጠት ከቻለ ሰውየው ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ በኩል ስራ እንዲጀምር ማድረግ ይቻላል።ሁለተኛው ደግሞ አፓርትመንት ገዝቶ በየወሩ ብር በቀላሉ መላክ ከቻለ አገሪቱ በቂ የውጭ ምንዛሪ ታገኛለች።ሶስተኛው ደግሞ የግል ጉዳዮች የትምህርት፣ የጋብቻ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በቀላሉ እንዲፈፀምላቸው ይሆናል ማለት ነው፡፡
በውጭ አገራት የሚገኙ ዳያስፖራዎች በቀላሉ በአንድ ቀን ውስጥ በውክልና የሚፈልጉትን ነገር ማድረግ ከቻሉ ዳያስፖራው በቀላሉ ከአገሪቱ ጋር ማስተሳሰር ይቻላል ማለት ነው።በዚህም አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን ትችላለች ማለት ነው።አሁን በቴክኖሎጂው ብዙ ተጠቃሚዎች ያሉ ሲሆን በብዛት ቤቶችን የሚገዙና የሚሸጡ እንዲሁም ቤት የሚከራዩ ሰዎች አሉ፡፡
ሥራው ሲጀመር የነበሩ ፈተናዎች
ሥራው ሲጀመር በመጀመሪያ ኬብሮን የራሱን ጉዳይ ለመፈፀም ውክልና ለመስጠት የነበረውን ውጣ ውረድ ሲመለከት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ መሥራት ፍላጎቱ እንዲቀንስ አድርጎበት ነበር።በዛ ወቅት ድርጅቱን በሌሎች አገራት ውስጥ እየሰራበት ስለነበር ቀላል መስሎት የነበሩ አሰራሮችን ለማሻሻል ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሄደ።በወቅቱ ሁለት አመት ድረስ ሁኔታዎች ፈጅተውበታል።ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አሰራሩን ለመተግበር አስራ ሰባት ጊዜ በረራ አድርጓል።በአሜሪካ በሚገኙ ስቴቶች ውስጥም ጉዳዩን ወደ ተግባር ለመለወጥ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በማንኛውም አገር ላይ ሥራ ሲሰራ መንግሥት አንድን አሰራር በቀላሉ መቀየር አይችልም።ግን ሥራውን ወደ ተግባር ለማስገባት በነበሩ ሁኔታዎች እንቅፋቶች ነበሩ።ነገር ግን የሥራው አስፈላጊነት እየታወቀ ሲመጣ የኢትዮጵያ መንግሥት የቴክኖሎጂ ድጋፍ አድርጓል።አንድን አሰራር ለመቀየር ብዙ ነገሮች ይለዋወጣሉ።በዚህም በተደረገ ጥረት ጎታች የሚባሉ አሰራሮች ቀስ በቀስ እንዲቀነሱ ተደርጓል፡፡
ቀጣይ የኩባንያው እቅድ
ኬብሮን የመሰረተው ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሥራ ለመስራት ሀሳብ ያለው ሲሆን በአገሪቱ ያለው የስራ እድል በጣም ሰፊ ነው።ምንም አይነት ስራዎች ያልተከናወኑባቸው ዘርፎች በብዛት የሚገኙ ሲሆን በቴክኖሎጂ መሸፈን የሚቻሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ።በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለማስተካከልና መንግስት ትርፋማ እንዲሆን ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቃል።ድርጅቱም በተለያዩ ዘርፎች ላይ ለመስራት ሀሳብ አለው።ወደፊትም ቴክኖሎጂውን ወደ አገር ውስጥ የሚገባበት መንገድ ለመፍጠር ስራዎች ተጀምረዋል።
ቪዲቸር በቀን ከአስራ ስምንት ሰዓት በላይ እየሰራ ሲሆን ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ በመስራቱ ትልቅ ደስታ ይሰጣል።ከዚህም ባለፈ የሰውን ደስታ መመልከት በራሱ በተለይ አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሟቸው ውክልና በፍጥነት ለመስጠት፣ የህክምናና ሌሎች ጉዳዮች ለማስጨረስ ቴክኖሎጂው ጠቅሟቸዋል።ብዙ የአፍሪካ ኤምባሲዎች ቴክኖሎጂውን እየተጠቀሙበት ይገኛል።
በአጠቃላይ ወጣቶች በአጓጉል ስፍራ ከመዋልና ጊዜያቸውን በአልባሌ ምክንያት ከማሳለፍ ይልቅ ለሰው ልጅ አድካሚ የሆኑ ተግባራትን በፍጥነት ማከናወን የሚያስችሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ጥናት በማድረግ እና ስራ ላይ በማዋል ለሀገራቸው እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባቸው ከኬብሮን ተሞክሮ መገንዘብ ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለራሳቸው የሚሆን ነገር እንዲሰሩ ቴክኖሎጂ ውስጥ ገብተው እንዲመራመሩ መንግስት ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት። ወጣቱ ትውልድ ከራሱ አልፎ የሚኖርበትን ማህበረሰብ ጫና የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር የሚጫወተው ሚና ከፍ ያለ ነው። በዚህ መልኩ ለቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥተን ከሰራን ኢትዮጵያን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ከማድረግ የሚያግደን ነገር አይኖርም።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም