በአገሪቱ የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥና ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከተቀየሱት ስትራቴጂዎች አንዱ የበቆሎን ምርትና ምርታማነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳደግ ነው። መንግሥትም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተለያዩ የበቆሎ ምርጥ ዘሮችን በማባዛት በየዓመቱ በመኸር የዘር ወቅት ለአርሶ አደሮች በስፋት ያሰራጫል።
አርሶ አደሩም ምርጥ ዘር ተጠቅሞ በመዝራቱ ምርቱ ከዓመት ዓመት ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ይህን ተከትሎ አርሶ አደሩ የዘር ወቅት ሲደርስ ከፍተኛ የበቆሎ ምርጥ ዘር ፍላጎት አለው፡፡በዚህ ምክንያት ምርጥ ዘር በነጋዴዎች እጅ እየገባ በውድ ዋጋ እየተሸጠ በመሆኑ አርሶ አደሩ ለከፍተኛ ወጪ ከመዳረጉ ባሻገር ለሰው ሰራሽ የምርጥ ዘር እጥረት ሲያጋጥመው ይስተዋላል።
አሁን ላይ ወቅቱ በቆሎ የሚዘራበት በመሆኑ የምርጥ ዘር ብሎም ሌሎች የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ ላይደርሰን ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው በአማራ ክልል የአዊ ዞን የተወሰኑ አርሶ አደሮች የበቆሎ ምርጥ ዘር ቀድሞ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተሰራ ያለው ስራ ምን ይመስላል? ሲሉ በስልክ አድራሻችን የሚመለከተውን አካል ጠይቀን ምላሽ እንድንሰጣቸው ጠይቀውናል።
በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት የመኸር ወቅት በክልሉ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት በማልማት 131 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷ አሁን ላይ የተለያዩ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ የእርሻ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በዚህም በክልሉ ለማረስ ከታቀደው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት ውስጥ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ የታረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ 49 ሺህ 863 ሄክታር መሬት በ331 ትራክተር ታርሷል።
አሁን ጊዜ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በሚባል መልኩ ዝናብ በማግኘቱ በክልሉ በሁሉም ቦታ የእርሻና የዘር ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በዚህም ቢሮው የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ የግብዓት አቅርቦትና የስርጭት ስራ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት አኳያ እየተሰራ ያለውን ሥራ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ፤ በክልሉ 7 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ማዳበሪያ በአዲስ መልክ ለማስገባት ከተያዘው እቅድ ባሻገር 852 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ የከረመ መኖሩን ጠቅሰው፤ በድምሩ ወደ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በክልሉ ለመጠቀም እቅድ ተይዟል። በዚህም አዲስ ለማስገባት ከታቀደው 7 ሚሊዮኑ ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ድረስ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወይም ደግሞ 53 በመቶው ማዳበሪያ ከፌዴራል መንግስት ቀርቧል። ከዚህ ውስጥ ወደ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮኑን ኩንታል ማዳበሪያ ለሕብረት ስራ ማህበራት ተሰራጭቶ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጸዋል።
ቀሪው ወደ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮኑ ኩንታል ማዳበሪያ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ መጋዘኖች ተከማችቶ እንደሚገኝና በዕቅዱ መሰረት ከፌዴራል መንግስት መቅረብ ያለበትን ማዳበሪያ በወቅቱ ለማቅረብ ከበላይ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ወደ ፊት በተያዘለት እቅድ መሰረት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሌላው ከምርጥ ዘር አቅርቦትና ስርጭት ጋር በተያያዘ አቶ ተስፋሁን እንደገለጹት፤ አሁን ላይ አርሶ አደሩ ቀድሞ የሚዘራው በቆሎ ከመሆኑ አኳያ በክልሉ 91 ሺህ 154 ኩንታል የተለያዩ ዝርያ ያላቸው የበቆሎ ምርጥ ዘሮችን ለማቅረብ ታቅዶ 91 ሺህ 147 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ቀርቧል። ከዚህ ውስጥ 71 ሺህ 953 ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ ቀድሞ ተሰራጭቷል። ስለዚህ ቀሪውን የበቆሎ ምርጥ ዘር የበቆሎ የመዝሪያው ወቅት ሳያልፍ በዚህ ሳምንት ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው በሶስተኛ ደረጃ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራጨ ያለው ሌላው የግብርና ግብዓት ኖራ መሆኑን ጠቁመው፤ በአማራ ክልል 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት ክፉኛ በአሲድ የተጠቃ ሲሆን 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ በአሲድ የተጠቃ ነው። በመሆኑም ክልሉ ካለው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት ውስጥ ወደ 3 ሚሊዮን ሄክታሩ የእርሻ መሬት በአሲድ የተጠቃ ነው። በዚህም በተለይ በክልሉ ስንዴ አምራች የሆኑ አካባቢዎች ምርታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ይናገራሉ።
ስለዚህ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በአሲድ የተጠቃውን መሬት በኖራ ቴክኖሎጂ ማከም ግድ ስለሚል በዘንድሮው የክረምት ወራት 111 ሺህ ኩንታል ኖራ ለማሰራጨት እቅድ ተይዟል። እስካሁን ድረስ 23 ሺህ ኩንታል ኖራ ለህብረት ስራ ማህበራት የቀረበ ሲሆን 2ሺ ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል። አፈጻጸሙ ዝቅተኛ በመሆኑ በዚህ ሳምንት በስፋት የኖራ የማሰራጨት ስራው ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ሥራ ተጠናቆ በቀጣይ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የገብስ፣ የማሽላ ወዘተ ምርጥ ዘሮችን በስፋት ለአርሶ አደሩ ከማቅረብ ጎን ለጎን ሌሎች የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብአቶችንም በወቅቱ የማቅረብ ስራ እንደሚሰራ ገልጸው፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ይበልጥ በአገሪቱ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ አርሶ አደሩ በተለይ ግብዓት በሚወስድበት እንዲሁም የእርሻ ስራውን በሚያከናውንበት ወቅት አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ በማድረግ አካላዊ እርቀቱን ጠብቆ ግብዓቱን እንዲወስድና ስራውን እንዲያከናውን አሳስበዋል።
እንዲሁም ሰላም ከለሌ አርሶ አደሩ የእርሻ ስራውን አከናውኖ ምርታማ መሆን ስለማይችል አርሶ አደሩ የአካባቢውን ሰላም ተቀናጅቶ እንዲጠብቅ እና ጸጉረ ልውጥ ሰዎች በአካባቢው ሲገጥመው ለሚመለከተው የፍትህ አካላት ወይም የጸጥታ አካል በማሳወቅ የእርሻ ስራውን ከማከናወን ጎን ለጎን ለአገሩ ሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት ጭምር አሳስበዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም