
አዲስ አበባ፡- አዲስ የብድርና ቁጠባ ተቋም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1ነጥብ8 ቢሊዮን ብር ከቁጠባ ለማሰባሰብ አቅዶ ከውጥኑ በላቀ መልኩ 2ነጥብ6 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።
አዲስ የብድርና ቁጠባ ተቋም ለዝግጅት ክፍሉ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1ቢሊዮን 580 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 2 ቢሊዮን 697 ሚሊዮን 442 ሺ261 ብር ሰብስቧል።ይህም ከእቅዱ አኳያ 121 በመቶ ብልጫ አለው።
የብድር ገንዘብ አሰባሰብን በተመለከተም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከመደበኛ፣ከአዲስ አበባ እና ከፌደራል ወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር 1 ቢሊዮን 565 ሚሊዮን 630 ሚሊዮን 654ሺ ለማስመለስ ታቅዶ 1 ቢሊዮን 434 ሚሊዮን 820ሺ ብር መሰብሰቡን አስታውቋል።
በመደበኛ ብድር አሰጣጥ ሥርዓት ለ30 ሺ800 ሰዎች ሁለት ቢሊዮን ብር ለመስጠት ታቅዶ ለ18 ሺ 144 ሰዎች 1 ቢሊዮን 497 ሚሊዮን 970ሺ ብር ብድር ሰጥቷል።ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያም በሰው 94 ከመቶ በገንዘብ ደግሞ 28 ከመቶ ብልጫ አለው ብሏል።
እንደ መረጃው ከሆነ፤ ሴቶች ኢንተርፕራይዝ የልማት መርሐ ግብር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን ለዚሁ ዓላማ 209 ሚሊዮን ብር ጥቅም ላይ ውሏል።በተጨማሪም በሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽሕፈት ቤት ለማደራጀት 8ሺ742 ኢንተርፕራይዞች 567 ሚሊዮን 290 ሺ ብር ለመስጠት ታቅዶ 492 ሚሊዮን 213ሺ ብር ተደራጅተው ለመጡ 6ሺ710 ኢንተርፕራይዞች መሰጠቱን ገልጿል። ይህም ከእቅዱ 77 ከመቶውን እንደሚሸፍን አስታውቋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በነበረው አፈፃፀም በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም ከአርሶ አደርና ከከተማ ግብርና ኮሚሽን ጋር በተደረገው ሥምምነት መሰረት ለ165 ሕብረት ስራ ማህበራት 38 ሚሊዮን 249 ሺ ብር ተዘዋዋሪ ብድር መስጠቱን አመልክቷል።
አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በከተማዋ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በፋይናንስ በመደገፍ እንዲሁም የቁጠባ ባህል በማሳደግ ድህነትን እንዲዋጉ ለማስቻልና በከተማዋ የሚስተዋለውን የሥራ አጥነት ቁጥር በመቀነስ ረገድ የራሱን ሚና እየተወጣ መሆኑም በመግለጫው አመልክቷል።
በክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም