ብዙ ጊዜ ሰዎች በተለያዩ ሁኔታዎች ሆነው ተስፋ የለኝም፤ ተስፋዬ ተሟጧል፤ የማረባ ሰው ነኝ፤ ከዚህ በኋላ ምን ሊሆን እና መሰል ንግግሮችን በቀን ተቀን ሕይወታቸው ሲጠቀሙ ይስተዋላል። ተስፋ መቁረጥ ወደ ግባችን/ ፍላጎቶቻችን እንዳንደርስ የሚያረገን ባህሪ ነው። በሕይወቱ ብዙ ጊዜ ተስፋ የሚቆርጥ ሰው ወደ ግቡ/እቅዱ የመድረሱ እድል በጣም አነስተኛ ነው። ወደ ጠቃሚ የሕይወት ግባችን አለመድረስ ደግሞ ድብርት፣ ጭንቀት፣ ፍርሃት፣ የበደለኝነት ስሜት ያመጣል።
አካባቢያዊ ምክንያት
በአካባቢያችን ያሉ የተለያዩ ሁኔታዎችና ገጠመኞች ፍላጎቶቻችንንና እቅዳችንን እንዳናሳካ ይከለክሉናል። በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ማድረግ የምንፈልገውን ነገሮች “አትችለውም፣ ይከብድሀል፣ ከዚህ በፊት አልተሞከረም፣ ሰው ምን ይልሀል” በማለት ተስፋ ሊያስቆርጡን ይችላሉ። በተጨማሪ ደግሞ ያደግንበት ባህል፣ የምንኖርበት አካባቢ ለማድረግ ያቀድነውን ነገር እንዳናሳካ በራሱ ሊይዘን ይችላል። ይሄ በሕይወታችን ተስፋ መቁረጥን ያስከትላል።
ግላዊ ብቃት/ክህሎት ማጠር
ይህ ደግሞ ፍላጎቶቻችንን እንዳናደርግ የሚገድበን አለመሙላት (ብቃት አልባነት) ነው። አንድን እቃ በጣም ወደነው ለመግዛት ስንፈልግ ከተወደደብንና ያለን ገንዘብ አነስተኛ ከሆነ ተስፋ ቆርጠን ላንገዛ እንችላለን። እዚህ ጋር ነገሩን ለመግዛት በቂ ገንዘብ አለመኖር የራሳችን የሆነ ጉድለት ይሆናል። ሌላው አንድን ነገር ለመስራት አስበን የግል ችሎታ /ብቃት/ ክህሎት ሲያንሰን “በቃ አልችልም” በማለት ተስፋ ለመቁረጥ መንስኤ ይሆናል።
የፍላጎት ግጭት
የመጨረሻው የግላዊ ፍላጎቶች/ ግቦች እርስ በእርስ ሲፃረሩ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። ተስፋ መቁረጡ የሚመጣው ሁለቱንም ግቦቻችንን ልናሳካ ባለመቻላችን ነው። አንዱን ግብ ብናሳካ ራሱ ሌላውን ስላላሳካን የመወላወል ተስፋ የመቁረጥ (የማዘን) ስሜት ይሰማናል።
ከእነዚህ ሶስቱ ዋና ዋና ምክንያቶች እጅግ በጣም ብዙ ሰው የሚያጋጥመው የመጨረሻው የፍላጎት ግጭት እንደሆነ የስነልቦና ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
የፍላጎት ግጭት ደግሞ በአራት ይከፈላሉ።
- ፍላጎት፥ ፍላጎት ግጭት፦ ይህ ግጭት ሁለት ነገሮችን በእኩል ፈልገን ነገር ግን መምረጥ የምንችለው አንዱን ብቻ ሲሆን ማለት ነው። ተማሪዎች ዩኒቨርስቲ ከገቡ በኋላ ዲፓርትመንት ሲመርጡ ብዙ ተማሪዎች
በሁለት ወይም ከዛ በላይ በሆኑ የዲፓርትመንት ምርጫዎች ይወጠራሉ፤ ነገር ግን መምረጥ የሚችሉት የወደዱትን ሁሉ ሳይሆን አንዱን ብቻ ስለሚሆን ግጭት ውስጥ ይገባሉ። ሌላው ገበያ ሂደን ሁለት ሱሪዎች በጣም ወደናቸው ነገር ግን መግዛት የምንችለው አንዱን ብቻ ከሆነ ይህ አይነት ግጭት ከራሳችን ጋር ይገጥመናል።
2. የማስወገድ ፥ የማስወገድ ግጭት፦ ይህ ደግሞ ከሁለት የማንፈልጋቸው ነገሮች የግድ አንዱን መምረጥ ግድ ሲለን ነው። ልጃችን በሰዎች ታግቶ ብር ካልከፈላችሁ ይገደላል ቢሉን፤ እዚህ ጋር ልጁ እንዲሞትም አንፈልግም፤ ለአጋቾቹ ብር መክፈልም አንፈልግም። ነገር ግን አንዱን መምረጥ ግድ ይለና።
3. የፍላጎትና ማስወገድ ግጭት፦ በአንድ ግብ ላይ የፍላጎትም የማስወገድም ስሜት ሲሰማን ነው።
ብዙ የፍላጎት ማስወገድ ግጭት፦ ሁላችንም በሕይወት ቆይታችን የሚያጋጥመን የዕለት ተዕለት ግጭት ነው። እያንዳንዱ የሚገጥመን ነገር ብዙ አወንታዊ እና አሉታዊ ነገሮች ይይዝና እሱን መምረጥ እና አለመምረጥ ችግር ይሆናል። ለምሳሌ፦ አንድ ሰው መልኩን፣ ገቢውን ወደን ፀባዩ አመለካከቱ ካላማረን ይሆነኛል አይሆነኝም ብለን ከራሳችን እንጋጫለን። ሌላው አንድን ስራ ስንሰራ በውስጡ ያሉ የተለያዩ ጥሩ እና መጥፎ ነገሮች ስገፉን ሲስቡን እንደዚህ አይነት ግጭት ውስጥ እንገባለን። ስለዚህ የመቁረጥ ስሜት በጊዜ ካልተፈታ ራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ ሲሆን ይህን ችግር ለመፍታት የችግሩን መንስኤ ማወቅ እና በተቻለ መጠን ከችግሩ ለመውጣት ራስን ዝግጁ ማድረግ እንዲሁም ከባለሙያ ጋር መመካከር ተገቢ ነው።
ምንጭ፦ ዶክተር አለ
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2013