ራስን መሳት ማለት ድንገታዊ የሆነ መዝለፍልፍ እና ነፍስ ያለማወቅ ሲኖርና ወዲያውኑ ሙሉ በሙሉ ሲመለስ እና መልሶ ሲነቃ ነው። የመደበት ስሜት ወይም መግለፅ የሚከብድ የራስ ማዞር/ መቅለል አይነት (lightheadedness) እንዲሁም የጡንቻዎች መዝለፍለፍ ነፍስን ሳይስቱ ሲከሰት ደግሞ ቅድመ-ራስ መሳት (presyncope) ይባላል። ራስን መሳት ከድንገተኛ የልብ ምት መቆም ችግር /cardiac arrest/ ጋር ማምታታት አይገባም። ምክንያቱም ድንገተኛ የልብ ምት መቆም ችግር ያለበት ሰው ራሱን በድንገት ቢስትም ህክምና ሳያገኝ በድንገት ህይወቱ ሊያልፍ ይችላልና ነው።
ድንገት ራሳቸውን የሚስቱ ሰዎች ወዲያውኑ ያለምንም ህክምና የሚነቁ ሲሆን በሚወድቁበት ወቅት ግን አደጋዎች ሊያጋጥማቸው ይችላል። በተደጋጋሚ እራስን መሳት የሚያስደነግጥ ነገር ሲሆን የልብ ችግር ያለባቸውና እራሳቸውን በተደጋጋሚ የሚስቱ ሰዎች ወደ ፊት ድንገተኛ የልብ ምት መቆም ችግር እንደሚከሰት ማሳያ ምልክት ስለሆነ ጥንቃቄና ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል። ራስን መሳት ሊያመጡ ከሚችሉ ችግሮች ውስጥ የደም ስኳር መጠን መቀነስ፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ (hyperventilation)፣ የሚጥል ህመምና ሌሎችም ሁኔታዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
ድንገት ተዝለፍልፎ መውደቅ በብዛት የሚከሰት የጤና ችግር ሲሆን አንድ ሶስተኛ በሚሆኑ ሰዎች ላይ በህይወት ዘመናቸው ውስጥ አንድ ጊዜ ሊከሰት ይችላል። ምንም እንኳ አንዳንዴ በተወሰኑ ከፍ ያለ የህክምና ችግር ባላቸው ሰዎች ላይ ቢከሰትም ብዙውን ጊዜ ራስን መሳት ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት አይዳርግም። በሽምግልና ዕድሜ ክልል ካልሆነ በስተቀር 75 በመቶ በላይ ለሚሆኑት የራስ መሳት/ሲንኮፕ መከሰት ምክንያታቸው መሰረታዊ የሆነ ጤና ችግር ምክንያት አይደለም። ሳይታሰብ በድንገት የሚወድቁ ሰዎች ለችግሩ መንስኤ መሰረታዊ የጤና ችግሮች ሊሆኑ ስለሚችሉ በድንገት ራስን መሳት የሚያጋጥማቸው ሰዎች የህክምና ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
መንስኤዎች
ንቁ ሆኖ ለመቆየት አንጎላችን የማይቆራረጥና በቂ ኦክስጂን ያለው የደም ዝውውር ይፈልጋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለተወሰነ ሰኮንድም ቢሆን በቂ ኦክሲጂን ያለው ደም ወደ አዕምሯችን ሳይደርስ ቀርቶ ቢቋረጥ እራስን መሳት / ሲንኮፕ ይከሰታል። እራስን መሳት ሊያመጡ የሚችሉ ችግሮች ብዙ ሲሆኑ ጥቂቱን ለመግለፅ ያህል፡-
የደም ስሮችና ነርቮች ስራ መዛባት /ቫዞ ቫጋል ሲንኮፕ/ ኒዩሮካርዲዮጄኒክ ሲንኮፕ (vasovagal/ neurocardiogenic syncope)፣ የልብ ምት ችግሮች ከልብ ወደ ሰውነት የደም ርጭት መዘጋት (Blockage of blood flow from the heart)፣ በአቋቋም መለወጥ ምክንያት የሚከሰት የደም ግፊት ማነስ (Orthostatic hypotension) ብዙውን ጊዜ ባይሆንም አንዳንዴ በልብችግር /heart attack/፣ የልብ ላይ ዕጢዎችና ወደ ሳንባ በሚሄዱ የደም ቅዳ ውስጥ ደም መርጋት ራስ መሳትን/ ሲንኮፕ እንዲከሰት ምክንያት ይሆናሉ። ችግሩን ለማወቅ ሊደረጉ የሚችሉ ነገሮች የህክምና ታሪክ፣ አካላዊ ምርመራና የላቦራቶር ምርመራዎችን ማድረግ ራስን መሳት በምን ምክንያት እንደመጣ ለማወቅ ይጠቅማሉ።
ሊደረጉ የሚችሉ ህክምናዎች
በአጠቃላይ ሲታይ ለራስ መሳት/ሲንኮፕ ሊደረግ የሚችል ህክምና እንደ መሰረታዊ መንስኤው ይለያያል። የህክምንው ዋና አላማ ችግሩ ተመልሶ እንዳይመጣና ከፍ ያለ የጤና ጉዳት/ ችግር እንዳይከሰት ለመከላከል ነው። ለምሳሌ ደም ሲያዩና የደም ናሙና ሲወሰድላቸው ድንገት ተዝለፍልፈው እራሳቸውን የሚስቱ ሰዎች ካሉ የደም ናሙናው በሚወሰድበት ወቅት እንዲተኙ ማድረግ፤ በየትኛውም ሁኔታ ድንገት ራስን የመሳት ችግሮች ካለዎ ደግሞ ወዲያውኑ መተኛትና ሁለቱንም እግሮች ወደላይ ከፍ አድርጎ መያዝ፤
- ካውንተር ፕሬዠር ማኑቨር፡- ይህ እጅዎትን ጨብጦ በመያዝ መወጠር፣ እግርዎን በመወጠር በማጠፍና በመዘርጋት/
leg pumping/ እንዲሁም እግርዎን ማነባበር የደም ዝውውሩን ስለሚያሻሽለው እንዳይስቱ ይረዳዎታል።• መድሃኒቶች፡- የልብ ምት ችግር ያላቸው ሰዎች መድሃኒቶች ሊታዘዙላቸው ይችላል። ከተቀመጡበት ወይም ከተኙበት ድንገት ሲነሱ ለራስ መሳት የሚጋለጡ ሰዎች ካሉ የሚከተሉትን ይሞክሩዋቸው፡-
- የሚሳቡና ግፊት ሊፈጥሩ የሚችሉ ስቶክንግ በእግር ላይ ማጥለቅ
- ከመቆምዎ በፊትና ቆመው እያሉ የእግር ጡንቻዎን መወጠር
- በሚነሱበት ወቅት ባንዴ ሳይሆን ቀስ በቀስና በዝግታ ማድረግ የመሳሰሉት ናቸው።
እንደሚታወቀው በእኛ ሀገር ሰው ድንገት ሲጥለው ክብሪት አፍንጫው ላይ መጫርና ማሽተት የተለመደ ነው። ይህ በህክምናው ምንም መሰረት የሌለው ስለሆነ ይህን ከማድረግ በመቆጠብ ድንገት የጣለው ሰው ካጋጠመው በቂ አየር እንዲያገኝ በማድረግ፤ ማንኛውም አካሉን ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮችን በማስወገድና ድንገተኛ ህክምና እንዲያገኝ በማድረግ ቢተባበሩ መልካም ይሆናል።
በተጨማሪም ህመምተኛው ድንገተኛ የሆነ የስኳር ወይም የፈሳሽ እጥረት ከሆነ ያጋጠመው ስኳር/ከረሜላ ወይም ለስላሳ በመስጠትና በቂ ፈሳሽ እንዲያገኝ ማድረግ ከችግሩ በቶሎ እንዲመለስ ይረዱታል።
ምንጭ፦ ስለ ጤናዎ
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2013