ዛሬ የበለጸጉ ናቸው ብለን የምንጠራቸው አብዛኛዎቹ አገራት የኢኮኖሚ ልማታቸው የመጣው በተፈጥሮ ሀብት ሳይሆን አገራቱ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ምቹ ሁኔታን በመፍጠራቸውና ጠንክረው በመስራታቸው ነው። እነ ጃፓን ጀርመንና ቻይናን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በተለይ እንደ ጃፓን፣ ሕንድና ቻይና ያሉ አገራት በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻቸው ወደ አገራቸው በመሄድ በኢንቨስትመንት በመሰማራትና ከሚኖሩበት አገር ወደ አገራቸው ገንዘብ በመላክ ለዕድገታቸው ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ያነሳሉ።
ኢትዮጵያም ለዜጎቿ የተመቸች፣ የበለጸገችና ሰላሟ የተጠበቀ እንዲሆን ዲያስፖራው ከፍተኛ ድርሻ ሊኖረው ይገባል። አገር የምትበለጽገው በምኞት ሳይሆን ሕዝቡና መንግሥት ከሚሰሯቸው የልማት ሥራዎች በተጨማሪ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ጭምር አገራቸውን በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በኢንቨስትመንት መደገፍ ሲችሉም ነው።ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች እንደማንኛውም አገር ዲያስፖራ ወደ አገራቸው ተመልሰው ኢንቨስት ቢያደርጉ አገራቸውንም ሆነ እራሳቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ። በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪ መስኮች ቢሰማሩ ጥሬ ዕቃው በአገሪቱ ስለሚገኝና ገበያው ስላለ ይበልጥ ይጠቀማሉ። በውጭ አገር ያገኙትን ልምድና እውቀትም ለሌሎች ያስፋፋሉ። ለብዙ አምራች ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።
በኢትዮጵያ የተለያዩ የውጭ አገራት ባለሀብቶች ኢንቨስት በማድረጋቸው ስኬታማ እየሆኑ ነው። ዲያስፖራውም ተቀባይነት ያለውና አዋጭ የንግድ ዕቅድ ይዞ ከመጣ ራሱ ተጠቅሞ አገሩንም መጥቀም ይችላል። እርግጥ ነው በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በአገራቸው ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ አሻራቸውን ለማኖር በማሰብ ኢንቨስት እያደረጉና ኢንቨስትመንት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እያሳዩ ናቸው።
ዲያስፖራዎች በአገልግሎቱ ዘርፍ ላይ በስፋት የተሰማሩ ሲሆን በግብርናና በሪልስቴት ዘርፍ የሚያደርጉት ተሳትፎም የማይናቅና በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኝ ነው። ዲያስፖራዎች ለአገራቸው ከሚያመጡት የውጭ ምንዛሬ በተጨማሪ፥ በውጭ አገራት ቆይታቸው ወቅት የቀሰሙት ክህሎትና የሥራ ባህልም እንዲሁም ቴክኖሎጂ ሽግግር ለኩባንያዎቻቸውና ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአገሪቷ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለማስፋፋት ከሚያስችሉት ምቹ ሁኔታዎች መካከል ዋነኛው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በስፋት እያካሄደች ትገኛለች። የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን አስተማማኝ ከማድረግ አኳያ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለጎረቤት አገሮች የሚተርፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን በማጠናቀቅ ላይ ናት። ይህም በተለይ በኢንዱስትሪ መስክ ለሚሰማሩ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችና የውጭም ባለሀብቶች ያለምንም ስጋት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ያስችላል።
ዲያስፖራው በኢንቨስትመን፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በክህሎትና በልምድ ብቻ አይደለም የአገሩን ልማት እያፋጠነ የሚገኘው። በአገር ቤት ለሚገኙ ወዳጅ ዘመዶቻቸው የሚልኩላቸው ገንዘብም ለአገር ኢኮኖሚ ልማት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለአብነት ያህል በ2013 ዓ.ም ባለፉት ስምንት ወራት ዲያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ ወዳጅ ዘመዶቹ ከላከው ገቢ (ሬሚታንስ) ሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት 39 ዲያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት፤ በ2013 በጀት ዓመት ከሬሚታንስ አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል። በእቅዱ መሠረትም በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ዲያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ ሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መላኩን ገልጸዋል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሬሚታንስ አፈጻጸሙ ላይ ተፅእኖ ቢያደርግም ዲያስፖራው ችግሩን ተቋቁሞ ገንዘቡን እየላከ ይገኛል። ሆኖም ዲያስፖራው ገንዘቡን ወደ ወዳጅና ዘመዶቹ ሲልክ በሕጋዊ መንገድ ተከትሎ ወደ አገር ቤት መላኩን መቀጠል ይኖርበታል። ዲያስፖራው ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ ወደ አገሩ ቢልክ ራሱንና አገሩን ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል።
በተመሳሳይም ባለፉት ስምንት ወራት 4 ሺህ 822 ዲያስፖራዎች የባንክ ሂሳብ ቁጥሮችን በመክፈት ከአምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረጋቸውን ኤጀንሲው ገልጻል። በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራትም 39 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል። እነዚህ ዲያስፖራዎችም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስ፣ በቱሪዝምና በአገልግሎት ኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ናቸው። አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ዲያስፖራዎቹ እስካሁን ወደ ሥራ የገቡባቸው አካባቢዎች መሆናቸው ተጠቅሷል።
ዲያስፖራው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ አሁንም ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያን ለማበልጸግና የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ወደ ፊትም የዲያስፖራው ተሳትፎ በእጅጉ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ለማፋጠን ብዙ ኢንቨስትመንቶች መካሄድ አለባቸው። በአገራችን ገና ያልነካናቸው ተዝቀው የማያልቁ የማዕድን ሀብቶች አሉ። ብዙ ያልተጠቀምንባቸው የእርሻ መሬቶች ይገኛሉ። ያልተሰማራንባቸው የኢንዱስትሪ መስኮች በርካታ ናቸው። የመስኖ ልማቶች ያስፈልጋሉ።
ስለዚህ ይህ ሁሉ በአገር ውስጥ ዜጎችና መንግሥት ብቻ በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ አይገመትም። እነዚህን ልማቶች ማስቀጠል የሚቻለው በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተናቦ ሲሰራ ነው።በአሁኑ ጊዜ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች የተሻለ ደረጃ ላይ ነው ያለችው። የውጭ ኢንቨስተሮችን መሳብ ችላለች። ከውጭ የመጡ የሕንድ፥ የቱርክ፥ የፓኪስታን፥ የቻይናና ሌሎች አገሮች ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው ይገኛሉ። ይህ ጅማሮ ጥሩና አዎንታዊ በሆነ መልኩ የሚታይ ነው። ሌላው ደግሞ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንቱን በምናይበት ጊዜም በእርሻ የኢንቨስትመንት መስክ እያለሙ የሚገኙ አሉ። ከተማ ውስጥ የሕንፃ ግንባታ የሚካሄዱ አሉ። በኢንዱስትሪውና በአገልግሎቱ ዘርፍም እንዲሁ በርካታ ባለሀብቶች ኢንቨስት እያደረጉ ናቸው። ስለዚህ ኢንቨስትመንቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
ይሁንና አሁን ያለው ኢንቨስትመንት በቂ አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና ለውጥ እያሳየ ቢሆንም እንደ አገር ለመበልጸግ የበለጠ ኢንቨስትመንት ላይ ያለው ተሳትፎ ያስፈልገናል። ምክንያቱም ብዙ ያልተሟሉ አገልግሎቶች አሉ። አሁንም ብዙ ሀብቶቻችን ጥቅም ላይ አልዋሉም። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ለማሟላት ግለሰቦችም ሆኑ መንግሥት ኢንቨስትመንት ማካሄድ ይኖርባቸዋል። በተለይ ዲያስፖራዎች በሚኖሩበት የበለጸጉ አገራት ተሞክሮ ልምድና ሀብት ይዘው በመምጣት ለአገራቸው ልማት መትጋት ይኖርባቸዋል።ይህን ኢንቨስትመንት አጠናክሮ ለመቀጠልና ለዲያስፖራው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠርም ደግሞ በመንግሥት በኩል የተሻለ አስተዳደር፥ ፈጣን የመሬት አቅርቦትና ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎት መፍጠር አለበት።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2013