አምራች ኢንዱስትሪው በማይናጋ መሰረት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እድገት ለመመስረት የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። የምጣኔ ሀብት ምሁራንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለፀጉ እና ተወዳዳሪ መሆን የቻሉ አገራት የከፍታ መነሻ አምራች ኢንዱሰትሪዎቻቸውን በፖሊሲ እና በማበረታቻ ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ የመቻላቸው ውጤት ስለመሆኑ ይገልፃሉ። ድጋፍና ክትትሉም አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ተከታትሎ ለመፍታትና የሚያስፈልጓቸውን የፋይናንስ፣ የክህሎት፣ የማምረቻ ቦታና የቴክኖሎጂ ግብአቶች በፍጥነት ለማቅረብና ዕለት ተዕለት ቢዝነሱን የሚመሩበት እውቀት እንዲኖራቸው ማስቻልን የግድ እንደሚል አጽዕኖት ይሰጡታል።
ኢትዮጵያም የኢኮኖሚ እድገቷን በማይናጋ መሰረት ላይ ለመጣል ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠት ዘርፉን በሙያ፣ በዕውቀትና በገንዘብ በተደራጀ መልኩ በመደገፍ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶውን ለማጎልበት እየሰራች ትገኛለች። በዚህ ጥረትም የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም የአምራች ኢንዲስትሪው ኢንቨስትመንት ተሳትፎ በማጎልበት ከትርፉ መቋደስ ችላለች። ይሁናን የዘርፉ እና ተዋናዮቹ ችግሮች ዓመታትን ሲንከባለል የመጡ እንደመሆናቸ በቀላሉ መፍትሄ የሚያገኙ ሆነው አልተገኙም።
በተለይም የመስሪያ ቦታ፣ የገቢያ ትስስርና ማስታወቂያ፣ የውሃ፣ የመንገድና የመብራት መሠረተ ልማቶች፣ የሰላም እና ደህንነት፣ የውጭ ምንዛሪ፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ የሥራ ማስኬጃ የብድር አገልግሎት ችግሮች እንዲሁም ለዘርፉ ባለሀቶች የሚሰጠው አመለካከቶች መቃለል እንጂ መፍትሄ ማግኘት እንዳልቻሉ ከተዋናዮቹ አንደበት ሲገለፅ ይሰማል።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያዘጋጀው የአምራች ዘርፉ እና የመንግሥት የጋራ ምክክር መድረክ ከቀናት በፊት በሸራተን ሆቴል ሲካሄድም፣ በርካታ መሻሻሎች ቢኖሩም ከአምራች ዘርፉ ተዋንያን የተነሱ እና መንግሥት ምላሽ ቢሰጥባቸው በሚል ችግሮች ቀርበዋል።
የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ ከመድረኩ ተሳታፊዎች አንዱ ነበሩ። አምራች ዘርፉ ለአገሪቱ ጠቅላላ ምርት እድገት ወሳኝ ስለመሆኑ አጽዕኖት ሰጥተው ይናገራሉ። ቀደም ባሉት ጊዜያት የዘርፉን ተዋናይ ተገቢ ትኩረት እና አክብሮ የመስጠት ከሁሉም በላይ ባለሀብቱን በጥርጣሬ የመመልከት አባዜ ጎልቶ ይስተዋል እንደነበር ያስታውሳሉ። በአሁን ወቅት ይህ እሳቤ መሻሻል ቢያሳይም ፈፅሞ ሊወገድ እንዳልቻለ ጠቅሰዋል። አሁንም ጉምሩክ ባለስልጣንና ገቢዎች ሚንስቴር አካባቢ አመለካከቱ በግልፅ እንደሚንፀባረቅ አንስተዋል።
ያለ ደረሰኝ የሚካሄዱ ግብይትም ሌላው የዘርፉ ወቅታዊ ፈተና መሆኑንም አቶ ጀማል ይገልፃሉ። ይህ ሕገ ወጥ ተግባርም፣ ህጋዊው ባለሀብት ተወዳዳሪ እና ብቁ ሆኖ በገበያው እንዳይቀጥል በማድረግ ተስፋ እያስቆረጡት በመሆኑ የሚመለከተው አካላት ፈጣን ማስተካከያ ማድረግ እንዳለበት አጽዕኖት ይሰጡታል።የኢትዮጵያ ኬሚካል ውጤቶች ዘርፍ ማህበር ፕሬዚዳንት እና የቤክስ ኬሚካልስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ በቀለ ፀጋዬ የአምራች ዘርፉ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ለመውሰድ ሁነኛ መንገድ ስለመሆኑ ያሰምሩበታል።
ይህን ታሳቢ በማድረግ በአሁን ወቅት መንግሥት ለዘርፉ እና ለተዋናዮቹ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ችግሮቸን ለማስወገድ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ጥረቱም ሊያስመሰግነው የሚገባ መሆኑን ነው የመሰከሩት።ይህ ማለት ግን መንግሥት ለአምራች ዘርፉ የሚያደርገው ድጋፍ እና ክትትል በቂ ነው ማለት እንዳልሆነ የሚያስገነዝቡት አቶ በቀለ፣ የመሬት ጥያቄዎች እንዲሁም ከኬሚካል ምርቶች ጋር በተያያዘ የጉምሩክ አሰራር ችግሮች ምላሽ ማግኘት እንዳላቻሉም ይጠቁማሉ።
በአሁን ወቅት የተጀመሩ ጥረቶች ይበልጥ መጠናከር እና የግል እና የመንግሥት ትብብር ለማጎልበት ከዚህም በላቀ መልኩ መሥራት እንዳለበት የሚያስገነዝቡት ዳይሬክተሩ፣ የአምራች ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም ከአርሶ አደሮች ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችል አካታች አሰራር እና የኢንዱሰትሪ ልማት አቅጣጫ ብሎም መመሪያ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ሳይጠቁሙ አላለፉም።መንግሥት የውጭ ድርጅቶች የሚሰጠው ትኩረት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች መስጠት እንዳለበት ያስገነዘቡት ደግሞ የታፑ የበሰሉ ምግቦች ማዘጋጃ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማርቆስ ታደሰ ናቸው። ‹‹መንግሥት ውጭውን ሳይሆን ውስጡን በመመልከት፣ ለአገር ውስጥ አማራቾች ጥያዌ ፈጣን ማላሽ መስጠት አለበትም ነው››ያሉት።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በ2011 ይፋ የተደረገው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ካካተታቸው ቁልፍ ምሶሶዎች መካከል አምራች ዘርፉን ማጠናከር አንዱ ነው። በዚህ የውይይት መድረክም መንግሥት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተሰጠው ትኩረት መሰረት የአምራች ዘርፉን ለማጎልበት በርካታ ሥራዎች እያካሄዱ ስለመሆኑ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማብራሪያ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛውም አምራች ዘርፉ በአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ ወሳኝ ድርሻ ያለው መሆኑን እና ዘርፉ ካለው ግዙፍ አበርክቶ አንፃርም የተለየ ትኩረት እና ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ ነወ አጽዕኖት ሰጥተው የተናገሩት። ቀደም ባሉት ዓመታት አምራች ዘርፉን ለመደረግ የተደረጉ ጥረቶችም የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንዳላስቻሉ፣ ለችግሮቹ መፍትሄ የማፈላለግ ጥረትም የዘርፉና ዋነኛ ተዋናይ ብሎም ባለሀብቶች ያሳተፈ እንዳልነበር ያስታውሳሉ።
‹‹በየአምራች ዘርፉ ተሳትፎ ሲንከባለሉ የመጡ እና ወቅታዊ ችግሮች የተተበተበ ነው›› የሚሉት አቶ ኤፍሬም፣ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ብቃት ያለው አመራር እና የሰለጠነ የሰው ሃይል እጦት፣ ያልተናበበ አደረጃጀት፣ የቴክኖሎጂ ውስንነት፣ የክትትል እና የድጋፍ ማነስ፣ ተግዳሮቶችን የመመከት ብቃት እና ዝግጁነት ዝቅተኛ መሆን፣ የብድር አቅርቦት ውስንነት እና የውጭ ምንዛሬ እጦት ጎልተው የሚጠቀሱ ችግሮች ስለመሆናቸው ይጠቁማሉ።
ችግሩ በመንግሥት ወገን ብቻ የሚንፀባረቅ እንዳልሆነ እና አምራቾቹም የችግሩ ተዋናይ ሆኖው ማስተዋላቸውን የሚያስገነዝቡት አቶ ኤፍሬም፣ ባለሀብቶቹ ሥራ እና ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ ማበረታቻዎችን ለአብነትም መሬትን ከታለመለት አላማ ውጭ ለመጠቀም አጥሮ የማስቀመጥ ተግባር መፈፀማቸውን ይጠቁማሉ።ከጥራት እና ምርት እና ምርታማነት አንፃርም ተፎካካሪ እና ብቁ ለመሆን ሲቸገሩ እንደተስተዋሉና በተለይም በኢንቨስትመንት ተሳትፎ አርሶ አደሩን ያካተተ ልማትን ታሳቢ አድርጎ በመተግበር ረገድም የጎላ ችግር እንደነበረባቸው ያስተውሳሉ።
እንደ አቶ ኤፍሬም ገለፃ፣ መንግሥት ይህን ምስል ለመለወጥ እና የአምራጭ ዘርፉን ለማበረታታት ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። የተለያዩ ማእቀፎችን የማሻሻል ሥራ እያከናወነ ይገኛል። ከተማ አስተዳደሩም፣ የመሬት እና ቦታ ጥያቄዎችን ለመመለስ በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው የቆዩትን የማስመለስ ብሎም ለኢንቨስተሮች የማስተላለፍ፣ ለመሰረተ ልማት በተለይ ለኤሌክትሪክ ሃይል ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። ይህ ጥረት በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ይናገራሉ። ለችግሮቹ መፍትሄም ጠንካራ እና ተቋማዊ አደረጃጃቶች በመገንባት ተገቢ ምላሽ ይሰጠል። የተቀናጀ ክትትል እና ድጋፍ ሥርዓት ይዘረጋል። ህገ ወጦችን በመከላከል ረገድም ሕግን የማስከበር ሥራዎችን ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል ብሏል።
መንግሥት ይህን ሲያደርግ ባለሀብቶችም የራሳቸውን ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባቸው ያመላከቱት አቶ ኤፍሬም፣ ችግሮች ለአንድ ወገን ከመተው ይልቅ በጋራ የመታገል እሳቤን ማዳበር፣ ምርት እና ምርታማነታቸውን ለማጎልበት፣ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ መሆን እሴት ጨምሮ መላክን ቀዳሚ ልምድ ማድረግ እንዲሁም ከመንግሥት የሚሰጡ ማበረታቻዎችን ለታለመላቸው አላማ ብቻ መጠቀም ግድ እንደሚላቸው ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፣ አምራች ዘርፉ ለአገር ሁለንተናዊ እድገት ያለው ፋይዳ ጉልህ ቢሆንም ለዓመታት ሲንከባለሉ በመጡ ችግሮች ተፈትኖ መቆየቱን ይስማሙበታል።ከለውጡ በኋላ ባለሀብቱን ባሳተፈ መልኩ ችግሮቹን ለመፍታት በተደረጉ ጥረቶች አንዳንዶቹ መፍትሄ ማግኘታቸውን የሚያስገነዝቡት አቶ ጥራቱ፣ ለአብነትም ከመሬት በአግባቡ ከማስተላለፍ ጀምሮ ህገ ወጥነትን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ይገልፃሉ።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃም፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድም ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ያልቻሉ 400 በላይ ሠራተኞች በአዲስ እንዲተኩ ተደርጓል። የመሬት ጥያቄን በመመለስ ረገድ 44 አዳዲስ የአምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት እና 15 ተጨማሪ የማስፋፊያ በድምሩ 59 ጥያቄዎችን ምላሽ አግኝተዋል። ከዚህ ባሻገር የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እየተፈታ መምጣታቸውን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ፣ ችግሩ አሁንም ቢሆን ከፍተኛ የመፍትሄ ትኩረት የሚሻ እንደሆነም ሳያስገነዝቡ አላለፉም። የአምራች ዘርፉ ተዋዮች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ተፅእኖ ሠራተኞቻችሁን ሳትበትኑ ለውጡን ደግፋችሁ በመቆማችሁም ምስጋና ይገባቸዋልም ነው ያሉት።
የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ፣ መንግሥት የአምራች ዘርፉን ለመደገፍ ቆርጥ አቋም ስለመያዙ አፅእኖት ይሠጡታል። ባለፉት ስምንት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ 86 ቢሊየን ብር የገቢ ቀረጥ፣ ታክስ እና ሌሎችም የድጋፍ ማበረታቻ መስጠቱን የዚህ አንዱ ማሳያ ነው። ከዚህ ማበረታቻ ውስጥም አዲስ አበባም 6 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ድርሻ እንደወሰደች አስታውቀዋል። በገቢዎች አሰራር ላይ ከባለሀብቶ የሚነሱ ቅሬታዎች በየደረጃው መልስ እያገኙ መምጣታቸውንና ያልተቀረፉትም ቢሆን በቀጣይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ነው ያስገነዘቡት። ይህ ሲሆንም ባለሀብቶቹ የራሳቸውን ድክመት መቃኘት እንዳለባቸው ሳያስገነዘቡ አላለፉም።
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቶ መላኩ አለበል፣ ኢትዮጵያን ለድህነት እና ሁለንተናዊ ችግር ለማውጣት ኢንዱስትራላይዜሽን ዋናው ቁልፍ መሆኑን በመጠቆም፣ መንግሥት የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የአምራች ዘርፉ ወሳኝ ሚና እንዳለው በማመን ዘርፉን የመደገፍ እና የማጎልበት ተግባርን የሞት ሽረት አጀንዳው ስለማድረጉ ነው ያብራሩት።እንደ ሚኒስትሩ ገለፃም፣ በኢኮኖሚ የለውጥ መንገዱ በተለይ የአምራች ዘርፉን ለማጎልበት ባለፉት ሦስት ዓመታት መንግሥት በርካታ አሰራር እና የሕግ ማሻሻያዎችን ይፋ አድርጓል። ማሻሻያዎቹም ለአምራች ዘርፉ ልዩ ትኩረት የሚሰጡ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው።
ቀደም ባሉት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከብሔራዊ ባንክ ተበዳሪ የነበረው መንግሥት ነበር። ባለፉት ሦስት ዓመታት ዋነኛ ተበዳሪ የግል ዘርፉ እንዲሆን ተድርጓል። የውጭ ምንዛሬ በአብዛኛው ይወስድ የነበረው መንግሥትና የልማት ድርጅቶች ነበር። በአሁን ወቅት ይህ ታሪክ እየተቀየረ መጥቶአል። ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት የታክስ ማሻሸያ ፈፅሞ ታሳቦ አያውቅም። በአሁን ወቅት የታክስ ማሻሻያ አምራች ዘርፉን ሊደግፍ በሚችል መልኩ ተዘጋጅቶአል። በቅርቡም ወደ ሥራ ይገባል። ላለፉት ሃያ ዓመታት አይነኬ ሆኖ የቆየ የአገሪቱ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ በአሁን ወቅት ተሻሽሎ እና ተጠናቆ የአምራች ዘርፉን ግብረ መልስ እየተጠባበቀ ይገኛል።
መንግሥት መሰል ጥረቶች ሲያደርግ አምራች ዘርፉም በተለይ ምርት እና ምርታማነትን ከጥራት ጋር አዛምዶ መቀጠል ግድ እንደሚለው አጽእኖት የሰጡት ሚኒስትሩ፣‹‹በአመት ሦስት ቢሊየን ዶላር በላይ የማያወጡ ምርቶችን ለውጭ ገበያ እያቀረብን 15 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ እያስገባን መቀጠል የለብንም፣ ይህን ታሪክ ለመለወጥ አምራች ዘርፉ ጥራት እሴት የታከለባቸው ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል ነው›› ያሉት። በተለይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የአምራች ዘርፉ ተዋናዮች በመሰረተ ልማት ተደራሽነት እና ለአገልግሎት ሰጪ ተቀማት ቅርብ መሆን ጨምሮ መልካም መደላድሎች እና ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን ያመላከቱት ሚኒስትሩ፣ እነዚህን መልካም እድሎች በሚገባ በመጠቀም ከሌሎች በተሻለ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል አቅም በመፍጠር ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ተጽእኖም ፋባሪካዎች ሙሉ በሙሉ ከተዘጉ በኋላ መልሶ ወደ ሥራ ማስገባት እጅግ በጣም አስቸጋሪ በመሆኖ ሳይዘጉ እንዲቀጥሉ መንግሥት የታክስ፣ የብድር እና ሌሎችም ድጋፎችን ማድረጉን ያመላከቱት ሚኒስትሩ፣ ሌላው ቀርቶ ፍባሪካዎቹ ምርት ቀይረው ገበያው ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ በርካታ ተግባራት ስለመከናወናቸው ነው ያስረዱት።ከተደረገላቸው ድጋፍ በላይ ራሳቸውን አቅማቸውን የቻሉ አምራቾች በርካታ መሆናቸውን ያመላከቱት አቶ መላኩ፣ በየትኛው ዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በ10፣20 እና 30 በመቶ እያመረቱ ሕልውናቸው ማስቀጠል የቻሉ አማራቾች ያሉት ኢትዮጵያ ስለመሆኑም ነው ያስገነዘቡት።
አቶ መላኩ በሰላም ረገድ የሚነሱ ጥያዎች የተናጥል ሳይሆን የጋራ መፍትሄን እንደሚፈልጉ አፅእኖት ሳይሰጡ አላለፉም። ‹‹አምራች ዘርፉ ተዋናንያን የዚህ አገር ዋነኛ ባለድርሻ ናችሁ። በዚህ አገር ላይ ሰላምን እና ልማት ካለ በሁሉ ረገድ ትጠቀማላችሁ፣ በሰላም እጦት እንደምትከስሩት ሁሉ በሰላም መስፈን ማታረፍ ትችላላችሁ፣ ይህ እስከሆነም ለሰላም መስፈን ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ያለባችሁ እናንተ ናችሁ›› ነው ያሉት። እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፀጥታ እና የሰላም ችግር ፖለቲካዊ አይደለም። ኢኮኖሚውም ዋነኛ ችግር ነው። የኢኮኖሚውን ችግር ከመንግሥት ጎን በመቆም መፍታት ከተቻለ ለአስተማማኝ ሰላም ትልቅ አቅም ይፈጥራል። ሰላም የማስፈን ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚሰጥ ከሆነ ፍቱን መፍትሄ ማግኘት አይቻልም። ሁሉም የመፍትሄው አካል መሆን ይኖርበታል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2013