አዲስ አበባ፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ በትብብር እንደምትሰራ የአሜሪካ አፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጄፈሪ ፊልትማን ማረጋገጣቸውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት በሰጡት ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፈሪ ፊልትማን ከተለያዩ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር ጄፈሪ ፊልትማን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በነበራቸው ውይይት ፣ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ በትብብር እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።
ጄፈሪ ፊልትማን ኢትዮጵያ የአሜሪካ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ፤ አሜሪካ በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች በተጠናከረ መልኩ ከኢትዮጵያ ጋር መተባበር እንደምትፈልግ መግለጻቸውንም አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል።
አገራቸው አሜሪካ በህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ በሚሳተፉት አገራት መካከል ሰላማዊ መፍትሄ ያለው ውጤት እንዲመዘገብ የበኩሏን እገዛ እንደምታደርግ መናገራቸውን የገለጹት አምባሳደር ዲና፤ በሌላ በኩልም በመጪው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ፤ በትግራይ ክልል ስለሚከናወን የሰብዓዊ ድጋፍ እና የሱዳን ድንበር ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።
በውይይቱ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ማመልከታቸውን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል። የአቶ ደመቀ እና የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ መካከል የተደረገው ውይይት በመግባባት መንፈስ መጠናቀቁንም አመልክተዋል።
ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ ከአሜሪካ እና ከሩሲያ እንዲሁም ከአውሮፓ ሕብረትን እና ከአፍሪካ ህብረት የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ምርጫውን ለመታዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ አስታውቀዋል።
እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ ፤ ከአሜሪካ ከሁለት ተቋማት የተውጣጣ ቡድን፤ ከአውሮፓ ሕብረት የተውጣጣ ስድስት አባላትን የያዘ ቡድን፣ ከሩሲያ እና ከአፍሪካ ሕብረት ምርጫውን የሚታዘቡ ባለሙያዎች ለመምጣት ዝግጅት እያደረጉ ነው።
ከምርጫ ታዛቢዎች ጋር ተያይዞ የአውሮፓ ሕብረት ታዛቢ ለመላክ ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በተመለከተ የተለወጠ ጉዳይ ባለመኖሩ በቀጣይ የሚመጡ ታዛቢዎችም የአገሪቷን ሕግ ባከበረ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ይደረጋል ብለዋል።
ከህዳሴ ግድብ ውይይት ጋር በተያያዘ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበርና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሺሴኬዲ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚካሄደውን ድርድር በተሳለጠ መልኩ ማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ሺሴኬዲ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት በታችኞቹ የአባይ ወንዝ ተፋሰስ አገራት ግብጽ እና ሱዳን ቆይታ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አምባሳደር ዲና፤ በኢትዮጵያም በሚኖራቸው ቆይታ ከተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩና በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሚካሄደውን የሶስትዮሽ ውይይት ለማስቀጠል ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል።
በሌላ በኩል አምባሳደሩ በመግለጫቸው፣ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኒጀር በነበራቸው ቆይታ፥ በአገራዊ ምርጫ፣ በህዳሴ ግድብ ድርድር እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የተሳካ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በደቡብ አፍሪካ ባደረጉት ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ፣ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
ጌትነት ተስፋማሪያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም