አሰልጣኝ መምህር ተስፋዬ ታደሰ ይባላል። በወራቤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሜታል ማኑፋክቸርንግ ኢንጂነርንግ ቴክኖሎጂ አሰልጣኝ መምህር ነው። ከዚህ ቀደም እምቦጭን ለማስወገድ በአገራችን በተለያዩ ተቋማት የተሰሩ ማሽኖች ላይ የሚስተዋልባቸውን ክፍተቶችን የሚደፍን የእንቦጭ አረም መንቀያ ማሽን መሥራቱን ይናገራል። ማሽኑ የእምቦጭ አረምን ከነስሩ በመንቀል ዳግም እንዳያቆጠቁጥ የሚያደርግ፣ የእንቦጭ አበባ እንዳይበተን በጥንቃቄ የሚያስወግድ፣ በአነስተኛ ዋጋ የሚሸጥ እንዲሁም በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ ለማንቀሳቀስ ምቹ የሆነ ነው።
በሁለተኛው አገር አቀፍ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ እና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር ሲምፖዚየም እና አውደ ርዕይ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት የእምቦጭ ማስወገጃ ማሽኑን ይዞ የቀረበው መምህር ተስፋዬ “ማሽኗ ወደ ሥራ ስትገባም ብዙም ውስብስብ አይደለችም። በውሃ ላይ እንድትንሳፈፍ ትደረጋለች። ከተንሳፈፈች በኋላ አረሙን እየቆነጠጠች ትነቅላለች። ከነቀላ በኋላ ምንም አበባ ሳይበተን በማሽኑ በኋላ በኩል ባለው መፍጫ ይፈጫል። ከፈጨ በኋላ በተዘጋጀ ቦታ ላይ እንዲፈስ ያደርጋል። ተፈጭቶ በአንድ ቦታ የሚሰበሰበውም ለማዳበሪያነትና ለክሰልነት እንዲያገለግል ይደረጋል›› ብሏል።
መምህር ተስፋዬ ከሀዋሳ ሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በ2003 ዓ.ም ነው የተመረቀው። በወራቤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መምህርና የፈጠራ ባለሙያ በመሆን ሥራ የጀመረው ደግሞ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ነው። መምህርና የፈጠራ ባለሙያው ብዙዎችን ከእውቅት ማዕድ ተቋዳሽ ማድረግ ችሏል። የኮሌጁ አሰልጣኞች ከማሰልጠን ሥራ ጎን ለጎን የህብረተሰቡን ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን እንዲያስተዋውቁ የሚያበረታታ በመሆኑ መምህር ተስፋዬም ከሌሎች የኮሌጁ አሰልጣኞች ጋር በመሆን የአካባቢውን ችግሮች መሰረት በማድረግ ጥናቶችን ያካሂዳሉ። በጥናቶቹ መሰረትም የተለያዩ ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በመሥራት ለኢንተርፕራይዞች በማቅረብ በኢንተርፕራይዞቹ አማካኝነት ለማህበረሰቡ እነሆ ብሏል።
አሁን ደግሞ የአገራችን አድባር የሆነውን ጣና ሃይቅን ጨምሮ በሌሎች ሃይቆች ላይ በመንሰራፋት የሀገሪቱ ሥጋት የሆነውን ወራሪውን የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የሚያስችል ማሽን ሠርቷል። ‘‘ክህሎት ያለው ዜጋ ለኢትዮጵያ ብልጽግና ’’ በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ከሚያዝያ 12 እስከ 17 2013 ዓ.ም በተካሄደው ሁለተኛው አገር አቀፍ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ እና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር ሲምፖዚየም እና አውደ ርዕይ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልን ወክለው በሲምፖዚየሙ ከተሳተፉ ስድስት ቴክኖሎጂስቶች አንዱ ነው።
መምህሩ እንዳለው፤ የኮሌጁ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከመሥራ ታቸው በፊት የአካባቢውን ችግሮች መሰረት በማድረግ ጥናት ያደርጋሉ። ጥናቱን ካካሄዱ በኋላ የልማት ኮሪደሮችን ይለያሉ። ከለዩ በኋላም የእሴት ሰንሰለቱን ይሠራሉ። የእሴት ሰንሰለቱ መነሻ በማድረግም የአካባቢውን ችግሮች የሚቀርፉ መሣሪያዎችን ይሠራሉ። በዚሁ መነሻነት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ትልቅ ሥጋት የሆነውን የእንቦጭ አረምን ማስወገጃ ቴክኖሎጂ ለመሥራት አቅዶ መነሳቱን ያብራራሉ።
የእምቦጭ አረም የሀገሪቱ ትልቁ ሃይቅ የሆነው ጣና ሃይቅ ላይ ከባድ ሥጋት ከመደቀኑ ባሻገር በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአርባምንጭ አካባቢ በሚገኘው በአባያ ሃይቅ ላይም መከሰቱን ያብራረው መምህር ተስፋዬ፤ ይህን ችግር መቅረፍ የሀገሪቱን አንድ ሥጋት መቅረፍ እንደሆነ በማሰብ ማሽኑን መሥራቱን አብራርቷል። የወራሪውን አረም ሥጋት ለመቆጣጠር እንደ ሀገር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ለመወጣት ማሽኑን መሥራቱን ጠቁሟል።
ሰሞኑን ሲምፖዚየሙ ላይ ያቀረበውን ማሽን ከመሥራቱ አስቀድሞ አነስተኛ የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ሠርቶ እንደነበር ያብራራው መምህሩ፤ የክልሉ እና የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሃላፊዎች ማሽኑን ካዩት በኋላ ተለቅ ያለ ማሽን እንዲሠራ ስላበረታቱት አሁን የሠራውን ማሽን ለመሥራት መነሳሳቱን ተናግሯል። ከማበረታታትም ባሻገር ጣና ሃይቅ ድረስ ሄደው እንዲያይ ሁኔታዎችን በማመቻቸታቸው ጣና ሃይቅ አካባቢ ለ15 ቀናት ቆይቶ መመለሱን ያብራረው አሰልጣኝ መምህር፤ ከጣና ሃይቅ ላይ እምቦጭን በማስወገድ ላይ የሚገኙ እና በተለያዩ ብልሽቶች ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ማሽኖችን ማየቱን ጠቁሟል። በኬኒያ፣ በቻይና እና በፊልፒን አካባቢዎች የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ማሽኖችን ከበይነ መረብ በማውረድ አስፈላጊውን ምርምር አካሂዷል። እያንዳንዱ ማሽኖች ላይ ያለውን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን ለይቶ መመለሱንም ጠቁሟል።
እንደ ተስፋዬ ማብራሪያ፤ ከጣና ሃይቅ እምቦጭ ያስወግዳሉ ተብለው በሀገር ውስጥ የተሰሩ እና ከውጭ አገራት የገቡ አንዳንድ ማሽኖች እምቦጭ ለማስወገድ ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ቢያበረክቱም አንዳንድ ማሽኖች ግን እንቦጭ ያስወግዳሉ ተብለው ገብተው ጣና ውስጥ እስካሁን የቆሙ አሉ። ማሽኖቹ ዋጋቸውም እጅግ ውድ ናቸው። በቀላሉ ለመግዛት የሚቻል አይደለም። መምህር ተስፋዬ እንደሚለው ከጣና ሃይቅ ከተመለሰበት ማግስት ጀምሮ ነው ማሽኑን መሥራት የጀመረው። ከጣና ጉብኝት መልስ የሠራው ማሽን በተለያዩ የሀገር ውስጥ ዩንቨርሲቲዎች ተሠርተው እና ከውጭ አገራት በግዥ ገብተው በአሁኑ ወቅት በጣና ሃይቅ አካባቢ ካሉት በመጠን የሚያንስ ነው። በመሆኑም በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ ይቻላል።
በተለይም ከውጭ በግዥ የመጡት ማሽኖችን ፈትቶ መልሶ ለመግጠም እጅግ አዳጋች መሆኑን የጠቆመው አሰልጣኝ መምህር ተስፋዬ፤ በሱ የተሰራው ማሽን በቀላሉ ተፈቶ የሚገጠም መሆኑን አንስቷል። ከዚያ ባሻገርም ብልሽት ቢያጋጥመው እንኳ የተበላሸውን የማሽኑን አካል በቀላሉ በሀገር ውስጥ መተካት እንደሚቻል ያስረዳል። በአሁኑ ወቅት በጣና ሃይቅ ላይ ያሉ እምቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች ውስጥ አንዳንዶቹ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው መሆናቸውን ያብራረው መምህር ተስፋዬ፤ በእሱ የተሰራው ማሽን በ126 ሺህ ብር የተሠራ መሆኑን አንስቷል። ማሽኑን ለመሥራት የወጣው ወጪ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ኢንተርፕተራይዞች በአነስተኛ ዋጋ ማሽኑን አምርተው እንደሚያቀርቡ አብራርቷል። በመሆኑም በአነስተኛ ዋጋ የሚቀርብ መሆኑ ማሽኑን ልዩ እንደሚያደርገው ጠቁሟል።
እንደ አሰልጣኙ መምህር ተስፋዬ ማብራሪያ የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የተሰሩ አንዳንድ መሣሪያዎች አረሙን ከመንቀል ይልቅ ወገብ ላይ በመቁረጥ እና አበባው በሃይቁ ላይ እንዲበተን በማድረግ እምቦጭን ከማጥፋት ይልቅ እንዲስፋፋ አድርገዋል። አሁን የተሰራው ማሽን ግን ይህን ችግር ሙሉ በሙሉ የሚቀርፍ ነው።
“ማሽኑ እምቦጭን ይነቅላል እንጂ ወገብ ላይ አይቆርጥም። በስህተት እንኳ አንዲት እንቦጭ አትቆረጥም። ሌላኛው ለየት የሚያደርገው ሌሎች ማሽኖች እንቦጭን በሚያስወግዱበት ወቅት አበባው የመበተን ባህሪይ አላቸው። በዚህም ምክንያት የእንቦጭ አረም እንደገና እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። አዲሱ ማሽን ግን የእምቦጭ አበባ ሃይቁ ላይ አይበተንም። የተነቀለው እንቦጭ በቀጥታ ወደ መፍጫ እንዲገባ ያደርጋል።”
ማሽኑን መሥሪያ ግብዓቶችን ኮሌጁ ከተለያዩ አካባቢዎች እንዳቀረበለት የተናገረው መምህሩ፤ አብዛኛው ግብዓት ከሀገር ውስጥ በጨረታ ተገዝተው እንደቀረቡለት አንስቷል። በመሆኑም ለማሽኑ አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንዳላወጣች አብራርቷል።በኮሌጁ የተደረገለትን ድጋፍ በመጠቀም ቴክኖሎጂውን ማቅረቡን ያብራረው ተስፋዬ በቀጣይ ኮሌጁ ቴክኖሎጂው ለኢንተርፕራይዞች እንደሚያሸጋግር ጠቁሟል። እንቦጭ አረም ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ኢንተርፕራይዞችም ማሽኖቹን በስፋት በማምረት እምቦጩን ለማጥፋት ለሚደረገው ርብርብ ይውላል ብሏል።
‹‹እምቦጭ ብዙ ጥረቶችን የሚፈልግ ወራሪ አረም ነው። በመሆኑም አረሙን ለማጥፋት የሚሰሩ አካላት ውስን ሥራዎችን ሠርተው መዘናጋት የለባቸውም። የተሻሻሉ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ለማፍለቅ በየጊዜው ጥረት መደረግ አለበት›› የሚል ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል። በመሆኑም እሱ ራሱ አሁን ሠርቶ ባጠናቀቀው ቴክኖሎጂ ብቻ ጥረቱን አላቆመም። የተሻለ የእምቦጭ መንቀያ ማሽን ለመሥራት ጥረቱን ቀጥሏል።
ተጠናቆ ለኢንተርፕራይዞች ለመሸጋገር ዝግጁ ከሆነው የእምቦጭ መንቀያ ማሽን የተሻለ ዲዛይን ማዘጋጀቱን የጠቆመው ተስፋዬ፤ አዲሱን ዲዛይኑን ከተለያዩ አካላት ጋር በመነጋገር ወደ ተግባር ለመቀየር ዝግጅት አድረጓል። ዲዛይኑን ወደ ተግባር መቀየር በሚችልበት ሁኔታ ዙሪያ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ለመነጋገር ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አብራርቷል።
የእምቦጭ ማስወገጃ ቴክኖሎጂ ለመምህር ተስፋዬ የመጀመሪያው የቴክኖሎጂ ሥራ ውጤቱ አይደለም። ከዚህ ቀደምም በግሉ እና ከሌሎች ቴክኖሎጂስቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ሠርቷል። በቆሎ መፈልፈያ፣ ስንዴና ገብስ መውቂያ እና መኖ ማቀነባበሪያ መሣሪያዎችን፣ የእንሰት መከትከቻ፣ የብሎኬት ማምረቻ የመሳሰሉ መሣሪያዎችን በመሥራት ለማህበራት አሸጋግሯል። ማህበራቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሮች እንዲቀርብም ኮሌጁ ክትትል እያደረገ ይገኛል።
አሰልጣኝ መምህሩ ተስፋዬ በተለያዩ ዘርፎች ለሠራቸው የማህበረሰቡ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ሥራዎቹ የተለያዩ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል። በፌዴራል፣ በዞን እና በክልል ደረጃ በገንዘብና በአይነት ተሸልሟል። በቀጣይም የማህበረሰብን ችግሮች ያገናዘቡ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን መሥራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2013