መሬት የያዙ ቤቶች በብዛት በሚታዩበት አካባቢ፣ ፎቅ ቤት ሲገነባ እንደብርቅ በሚታይባት አገር ወደላይ የሚገነቡ ሕንፃዎች እየበረከቱ መምጣታቸው ለብዙዎች አስደማሚ ነው። በተለይ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ትላልቅ ግንባታዎች ‹‹የሕንፃ ችቦ›› እስከ መባል ደርሷል። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሕንፃ ግንባታዎች በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዋና ከተማና የተለያዩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች በሚገኙባት ከተማ ደግሞ በመንግሥት፣ በማህበራትና በግለሰቦች ለመኖሪያና ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ሕንፃዎች በስፋት በመገንባት ላይ ናቸው። በከተማዋ ከተገነቡትና በመገንባት ላይ ካሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያስገነባው በሕንፃ ከፍታ የመጀመሪያው ሆኖ ይጠቀሳል። የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ፣ መሬትም እያነሰ ስለሚሄድ ወደላይ በመገንባት ሁሉም በፍትሐዊነት እንዲጠቀም ማድረግ ተገቢነት ያለው የሆነ ተግባር ነው።
ዛሬ ሁሉም እንደሚያስተውለው ለእርሻ አገልግሎት ይውሉ የነበሩ መሬቶች ሁሉ ለግንባታ ማስፋፊያ በመዋል ላይ ናቸው። ከተሜነት እየተስፋፋ፣ የሕዝብ ቁጥሩና የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱ እየጨመረ ሲሄድ ግንባታውን ማስፋት ግድ ብሏል። መኖሪያ ቤት ሲገነባ ደግሞ አብሮ የጤና፣ የትምህርትና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሟላት ስላለባቸው ለግንባታ ቦታ ወይም መሬት ያስፈልጋል። በተጨማሪም አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ለያዘችው ዕቅድ ለኢንዱስትሪ ግንባታ እንዲሁ በተመሳሳይ መሬት መዘጋጀት ይኖርበታል። በመሆኑም በከተማዋ ዙሪያ ሰፊ ቁጥር ያላቸው በመንግሥትና በግል ኢንዱስትሪዎች ተገንብተው የተለያየ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። ሁሉም አስፈላጊ በመሆናቸው ግንባታው ይበረታታል።
ነገር ግን እነዚህ አስፈላጊ የሚባሉ ግንባታዎች ሕንፃው ያረፈበት መሬት ወይንም ቦታ የመሸከም አቅሙ፣ በጥራት መከናወኑ፣ የአገልግሎት ዘመኑና ሕንፃዎቹ ተፈጥሯዊ የሆኑ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ያሉ አደጋዎች ቢያጋጥም የመቋቋም አቅማቸው፣ እንዲሁም ተጠጋግተው የሚገነቡ ሕንፃዎች አስፈላጊነትና ሊኖራቸው ስለሚችለው ስጋት፣ ለነዋሪው ምቹነታቸውና ለእይታም ሳቢነታቸው ግምት ውስጥ ገብቶ ግንባታው ካልተከናወነ ጉዳቱ ያመዝናል። አልፎ አልፎ እንደሚሰማው ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሳይበቁ በጅምር የፈረሱ ሕንፃዎች አጋጥመዋል። መንስኤው ተጣርቶ ለሌሎች ግንባታዎች ትምህርት እንዲሆን በማድረግ ረገድ የተኬደበት ርቀት ሲነገር አልተሰማም። ግን መሆን ነበረበት። በዚህ ዙሪያ የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች ሙያዊ አስተያየት ሰጥተውናል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከተማና የአርክቴክቸር ቅርስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ፋሲል ጊዮርጊስ ‹‹ግንባታ ከመከናወኑ በፊት ብዙ ነገሮች መታየት አለባቸው። የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት ስጋት ይሆናል ብዬ ከምጠቅሳቸው መካከል ፍልውሃ አካባቢ ያለው መሬት ውሃማ በመሆኑ ተጋላጭነቱ ይታየኛል። ሌላው ሥጋት ደግሞ ዝናብ ሲዘንብ አፈሩን አልፎ መሬት ውስጥ የሚጠራቀም ውሃ አለ። ይህ የተፈጥሮ የመሬት ውሃ ይባላል። የግንባታ መስፋትና የተጠጋጉ ሕንፃዎች መኖራቸው ለተፈጥሮ ውሃ መቀነስ ምክንያት ይሆናል። ለመጠጥና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ውሃ ጉድጓድ እየተቆፈረ ለሕዝቡ የሚዳረሰው ከመሬት ውስጥ ከሚገኘው የተፈጥሮ ውሃ ነው። ከወዲሁ ካልታሰበበት በረጅም ጊዜ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም።›› ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ለአረንጓዴ የሚሆን ቦታን ታሳቢ ያደረገና ክፍተት ያላቸውን ግንባታዎች ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ ሲባል ግን ጤናማ የሆነ የጥግግቶሽ ግንባታ መኖሩ መዘንጋት የለበትም። ተገቢ የሆነውን ጥግግቶሽና ትርፍ ለማግኘት ተብሎ የሚከናወነውን ግንባታን ለይቶ ማየት ያስፈልጋል። በመኻል ከተማ እና ከከተማ ውጪ ባሉ አካባቢዎች ያለው የግንባታ ፍላጎት ስለሚለያይ ይሄንን መፈተሽ የግድ ይላል። በአጠቃላይ ግን ጥሩ የሆነ የከተማ ፕላን አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ብዙ ሥራ ይጠብቀናል ሲሉ ይናገራሉ።
ከከተማ ፕላን አንጻርም ተባባሪ ፕሮፌሰሩ እንዳብራሩት፤ የሚገነቡት ሕንፃዎች ለአየር ዝውውር ምቹ የሆኑ መስኮቶች ያሏቸው ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ይጠበቃል። ነገር ግን ይህን ታሳቢ ማድረጉ ላይ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። በእርሳቸው ግምት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በግንባታ ዘርፉ የተሰማራው ትላልቅ ፎቆችንና የተጠጋጉ ግንባታዎችን ለማከናወን አስገዳጅ ከሆኑ ነገሮች አንዱ አሁን ያለው የመሬት መሸጫ ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ነው። ሌላው ቀደም ሲል ለእርሻ አገልግሎት ይውል የነበረ መሬት ለሕንፃ ግንባታ መዋሉ ችግር አይደለም። ነገር ግን መሬቱ በመለስለሱ ሕንፃውን ሊሸከም በሚችል መልኩ መሠረቱ ላይ በቂ ዝግጅት መደረግ ይኖርበታል። ይሄን ለማድረግ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ብዙዎች ይተገብሩታል ብሎ መጠበቅ አይቻልም። አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገና ትኩረት ካልተሰጠው ወደፊት ችግር ሊያጋጥም ይችላል የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ፋሲል እንደመምህርም፣ እንደዘርፉ ባለሙያም የታዘቡትንና መደረግ ያለበትን እንዲህ ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። ‹‹በጥናት ሳይደገፍ በዘልማድ የሚቀጥሉ የግንባታ ሥራዎች ጉዳታቸው ያመዝናል። እስካሁን ባለው ተሞክሮ ብዙ ርቀት ከተኬደ በኋላ ነው ለችግሩ መፍትሄ የሚፈለገው። ስህተትን ፈጥኖ ማረም ላይ ዘገምተኝነት ይስተዋላል። በቅርቡ በከተማዋ የተጀመረው የእግረኛ መንገድ የማስፋት ሥራ በጎ ጅምር ተደርጎ ይወሰዳል። እግረኛው መተንፈሻ አልነበረውም። በሁሉም ግንባታዎች ላይ እንዲህ ክፍተቶችን እያዩ ማስተካከል ይገባል። ከአስፈጻሚው ጎን ለጎን የከተማው ነዋሪም ለጥሩ ሥራ ተባባሪና የባለቤትነት ስሜት ሊኖው ይገባል። በተጨማሪም በትምህርት ተቋማት ውስጥ በዘርፉ የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ጥቅም ላይ መዋል ይኖርባቸዋል። ›› ብለዋል።
የጥናት ሥራ የሚከናወነው አጥኝው ደክሞበትና የገንዘብ ሀብትም የፈሰሰበት ስለሆነ መጠቀሙ የተሻለ ውጤታማ ያደርጋል። ብዙ ጊዜ ግን አስፈጻሚውና ጥናትና ምርምር የሚያደርገው ተቋም ተናብበው አይንቀሳቀሱም። አልፎ አልፎ የመቀናጀት ነገር ቢኖርም ጠንካራ አይደለም። ሰሞነኛ ይሆንና ይቀዛቀዛል። አስፈጻሚው ጋር እሳት የማጥፋት ሥራ ነው የሚስተዋለው ሲሉ ይተቻሉ።ብዙ ጥፋቶች ከደረሱ በኋላ ለማረም አስቸጋሪ ስለሚሆን ከወዲሁ ማሰቡ ተገቢ እንደሆነ ያስታወሱት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ በዘርፉ በተለያየ ጊዜ ጥናቶች ተደርገዋል።
ነገር ግን በሚፈለገው ልክ ኅብረተሰቡ አውቆት ጥናቱን እንዲጠቀምበት ማህበረሰቡ መረጃ አግኝቷል ለማለት አንደማያስደፍር ይናገራሉ። አስፈጻሚው አካልም ጥናትና ምርምር ወደ የሚካሄድባቸው የትምህርት ተቋማት በመሄድ ሀሳብ መጠየቅ እንዳለበት ያምናሉ። የሚከናወኑት ግንባታዎች ለ50 ዓመትና ከዚያም በላይ አገልግሎት መስጠት ስለሚኖርባቸው በጋራ መሥራቱ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ሀሳብ ሰጥተዋል።
ሌላው ያነጋገርኳቸው የእቴቴ ሪል ስቴት ባለቤትና ሥራአስኪያጅ አቶ ተስፋ ታደሰ ናቸው። እርሳቸው ደግሞ ከግንባታ ጋር ተያይዞ ችግር ብለው ያስተዋሉት የእግረኛ መንገድን ተጠግቶ የሚሰራውን የሕንፃ ግንባታ እንደ አንድ ጉድለት ያነሳሉ። የዚህ ትልቁ ክፍተት ብለው የጠቀሱት ደግሞ ለግንባታ የሚውል መሬት ፍቃድ የሚሰጠው አካል ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር አለማድረጉ ነው። በተጨማሪም ፍቃድ ያገኘው አካል በኃላፊነት ባለመሥራቱ ችግሩን አባብሶታል። ይህ ደግሞ ግንባታው ባለቤት የሌለው አስመስሎታል። በግንባታው ዘርፍ አሁን ከሚያስተውሉት በመነሳትም ያልተጠበቀ አደጋ ቢከሰት የሚጠፋው ነገር ይበዛል ብለው ይሰጋሉ።
በእርሳቸው እምነት አብዛኛው ግንባታ እየተከናወነ ያለው ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው ባለሙያዎች አይደለም። ሕንፃ መቆሙ እንጂ ለግንባታ ከሚውሉ ግብአቶች ጀምሮ ለጥራቱ የሚጨነቀው እጅግ አነስተኛ እንደሆነና ለ50 ዓመት ታስቦ የሚገነባ ሕንፃ አለ ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።በተለይም በቤት አልሚዎች (ሪል ስቴት) ለመኖሪያቤት የሚገነቡ አንዳንዶቹ ነዋሪው በቤቱ አካባቢ የሚናፈስበትና ልጆች የሚጫወቱበት ስፍራን ታሳቢ ያደረጉ ባለመሆናቸው ነዋሪው መውጫና መግቢያ መተንፈሻ የለውም። ለጤና ስጋትም የተጋለጠ ነው። ለዚህም ነው የግንባታ ሥራዎች ባለቤት የላቸውም ለማለት የሚያስደፍረው። ከዚህ አንፃር በመንግሥት የተሰሩት የጋራ መኖሪያቤቶች ክፍተት ስላላቸው የተሻሉ ናቸው። ግንባታ ከመከናወኑ በፊት ሕንፃው ሊያካትታቸው የሚገቡ ነገሮችና የሕንፃው ከፍታ ቀድሞ መወሰን ይኖርበታል።
እንደ አቶ ተስፋ ማብራሪያ፤ ድርጅታቸው በአብዛኛው የሚያከናውናቸው የግንባታ ሥራዎች በጨረታ ከመንግሥት የተረከባቸውን የግንባታ ፕሮጀክቶች ሲሆን፤ የአፈርና ሌሎችም ጥናቶች ተጠናቅቀው ነው ድርጅቱ ተረክቦ ወደ ግንባታ ሥራ የሚገባው። እነዚህም ቢሆኑ ከክፍተት ነፃ ናቸው ብለው አያምኑም። ይሁን እንጂ የተሻሉ እንደሆኑ ይጠቅሳሉ። የገንዘብ አቅም ስላለ ብቻ የመሰለውንና የሚፈልገውን ሕንፃ የሚገነባ አካል መኖሩንና በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የሕንፃ ግንባታ ጉራይማሌ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።ፍቃድ ከሚሰጠው አካል ጀምሮ በኃላፊነት ሥራዎች ካልተሰሩ ችግሩ የባሰ ሊሆን እንደሚችልና በተለይም ከፍቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያለው የእጅ መንሻ ወይንም የሙስና በር ካልተሰጋ ተቆርቋሪ የሆነ ሰው ሰሚ እንደማያገኝ የሚናገሩት አቶ ተስፋ መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ ካልተንቀሳቀሰ ችግሩ ይቀረፋል የሚል እምነት የላቸውም።
‹‹በአገሪቱ የግንባታ ሥራ በሕንፃ ተቋራጭ እንዲሰራ ሕግ ወጥቷል። ነገር ግን ይህን የሚሰሩ ሰዎች በአብዛኛው የሉም። የንግድ ፈቃዳቸውን በግንበኝነትና በተለያየ ዘርፍ ለተሰማሩ አከራይተዋል። በዘርፉ ቸልተኝነት እየተፈጠረ በመሆኑ ዋጋ እየስከፈለ ነው›› የሚሉት የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማርያም፤ ተቆጣጣሪው አካል ላይም ጥያቄ እያስነሳ መሆኑን ያስረዳሉ። በትክክል እየሰሩ ያሉ ድርጅቶች መኖራቸውን ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም። ማህበራቸው ተጠያቂነት እንዲኖር ከመንግሥት አካላት ጋር በሚያገኛቸው መድረኮች ላይ ክፍተቶችን ከማንሳት እንዳልተቆጠበ ይናገራሉ።የጥግግቶሽ ግንባታን በተመለከተም ሕንፃውን የሚያስገነቡት በስምምነት ቦታውን ካልተጠቀሙበት ሕንፃው ውበት እንዳይኖረው ከማድረጉ በተጨማሪ የመሬት ብክነት እንደሚፈጠር፣ የባከነው መሬት ደግሞ ለሁለቱም ሳይውል የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆኖ አካባቢን እንደሚበክል አስረድተዋል።
ኢንጂነር ግርማ፤ ክፍተት ሳይኖር መሬትን በሕንፃ ግንባታ መሸፈን ተገቢ ነው ብለው አያምኑም። ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የነበረውን የግንባታ ሁኔታ በማስታወስ በወቅቱ እንደዛሬ ግንባታው ሰፊ ባይሆንም ነገር ግን ለጥራትና ለሕንፃ ዲዛይን ትኩረት ይሰጥ እንደነበር ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ በሚከናወኑ የሕንፃ ግንባታዎች ላይ በሚነሱ ቅሬታዎች ላይ በአንዳንዶቹ እንደባለሙያ የሚቀበሉት ነገር መኖሩን ኢንጂነር ግርማ አልሸሸጉም።
ከፖሊሲ አንጻር የምጣኔ ሀብትና የፖሊሲ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ የታዘቡትን መሠረት አድርገው እንዳስረዱት አብዛኞቹ ሕንፃዎች በጣም ተጠጋግተውና አስፓልት ዳር ላይ የወጡ በመሆናቸው መጨናነቅን የሚፈጥሩ ናቸው። በነዚህ አካባቢዎች መኪና ማቆም አይቻልም። ለአብነትም መገናኛ፣ ቦሌ፣ ቦሌመድኃኒዓለም አካባቢዎች ይጠቀሳሉ። ትላልቅ ስም ያላቸው በቅርብ ጊዜ የተገነቡ የመኪና ማቆሚያ የሌላቸው ሆቴል ቤቶች በከተማዋ ውስጥ ይገኛሉ። ከተማዋ የበለጠ እያደገች ስትሄድ ችግሩ ይባባሳል። የተፈራው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋም ሊያጋጥም ይችላል። ቀድመው የተገነቡትን ባሉበት ሁኔታ ማስተካከል ከተቻለ አርክቴክቸሮች ወይንም የሕንፃ ባለሙያዎቹን ማማከር ይገባል። ገና የሚገነቡትን ግን ከባለፈው ስህተት በመማር ማስተካከሉ ይበጃል ይላሉ።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ከዚህ ቀደም ለንግድ ተብለው የሚገነቡ ትላልቅ ሕንፃዎች ከላይ ያሉት ለመኖሪያቤት እንዲውሉ በመንግሥት ቀርቦ የነበረውን ሀሳብ በማስታወስ፣ ይህ ተግባራዊ ቢሆን ግንባታውን በመቀነስ ስጋቱን መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል። እርሳቸው እንዳሉት የከተማ ማስተር ፕላን በተለያየ ጊዜ ተቀያይሯል። በርግጥ ከተማዋ እየሰፋች ስትሄድ ማስተርፕላኑን መከለስ አስፈላጊ ነው። የከተማ ማዘጋጃ ቤት ፖሊሲ ሊኖረው ይገባል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተነሳሽነት እየተከናወነ ያለው መናፈሻ ፓርክ ሊበረታታ ይገባል። እንዲህ ያሉ ሥራዎች ናቸው አንድን ከተማ ከተማ ሊያሰኙ የሚችሉት።
እንደአስተያየት ሰጪዎቹ ሀሳብ አንድን ከተማ ከተማ የሚያሰኘው የሕንፃ ብዛት ሳይሆን በረጅም ጊዜ ሊያስከትል የሚችል ችግርን ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል። አለበለዚያ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም ሳይሰጥ ከፍተኛ የአገር ሀብት የፈሰሰበትና የባለሙያ ድካም የታከለበት ሥራ ከንቱ ድካም ይሆናል። በመሆኑም የግንባታው ዘርፍ ረጅም ጊዜን ታሳቢ ያደርጋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2013