
ቢሾፍቱ፦ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ከመንግሥት ከግል ድርጅቶች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ተገለጸ።
የኢፌዲሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ትናንት በአዳማ ከተማ ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው በዳኔ እንዳስታወቁት ፤ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአዋጁ በተቀመጠው መሰረት በአገር ግንባታ ሂደት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተሰራ ነው።
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር ለመዘርጋትና ዘርፉን መደገፍና በአዋጁ ዙሪያ ግልጽነት በመፍጠር ወጥነት ያለው የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።
በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር አገርንና ሕዝባችንን ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመለየት፣ የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥና ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ምክክሩ እንደሚጠቅምም ጠቁመዋል።
ዘንድሮ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንደሚካሄድ የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከምርጫው ጋር በተያያዘ የሚኖራቸውን ሚና እንደሚያስገነዝብና ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው፤ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት ሊያበረክቱ የሚችሉት ሚና ኢትዮጵያ ያለመችውን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚያግዝ ነው።
ለዘርፉ እድገት አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል አዋጅ ከሁለት ዓመት በፊት መውጣቱን አስታውሰው፤ አዋጁ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን የመደራጀት መብት ለማስከበርና ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ፣ የሕዝብን የላቀ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ጂማ ገለጻ፤ አዋጁን ተከትሎ አስፈጻሚው አካል ራሱን በአዲስ መልክ በማዋቀርና ተቋማዊ ሪፎርም በማከናወን፤ የግልጸኝነትና የተጠያቂነትን አሰራሮችን ለማስፈንና ቀልጣፋ አሰራር በመዘርጋት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በመመዝገብና እውቅና በመስጠት ሕግን ተከትለው እንዲሰሩና የሚያስችል የለውጥ አስተሳሰብ ለመፍጠር ጥሩ ጅምር ላይ ነው።
አዲሱ አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ ከሆነበት መጋቢት 2011 ጀምሮ ከአንድ ሺ400 በላይ አዳዲስ ድርጅቶች መመዝገብ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም ሕገመንግስታዊ የመደራጀት መብትን ከማረጋገጥ ባለፈ ብዙ ድርጅቶች አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እድል የሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚካሄደው ውይይት ዘርፉን ለመደገፍና በአዋጁ ይዘትና አፈጻጸም ላይ ግልጸኝነትን በመፍጠር ወጥነት ያለው ስርዓት በመዘርጋት ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ 2 ሺ738 የአገር ውስጥና 456 የውጭ በድምሩ 3ሺ 194 ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኤጀንሲው ተመዝግበው እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም