
አዲስ አበባ:- በመጪው አገር አቀፍ ምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሪፖርት ለማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ ነጻ የስልክ መስመር ይፋ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሴቶች የሕግ ባለሙያ ማኅበር አስታወቀ ፡፡
የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚ ሌንሳ በየነ ብሔራዊ ነጻ የስልክ መስመሩ ይፋ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳስታወቁት ፤ በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ተግባራዊ የተደረገው የፕሮጀክቱ ዓላማ ዘንድሮ በሚካሄደው ምርጫ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከልና ችግሩ ከተከሰተም ነጻ የሕግ አገልግሎት፣ የህክምና እና ከሕግ አገልግሎት ጋር በተያያዘ እገዛ ለማድረግ ነው፡፡
የስልክ መስመር አገልግሎቱ በቅድመ-ምርጫና በምርጫ ሂደት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመቆጣጠር በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መረጃ ለመቀበልና እና ምላሽ ለመስጠት ያግዛል ብለዋል፡፡ በምርጫና በፖለቲካ ውስጥ የሴቶችን ደህንነትና እኩል ተሳትፎ ለማጎልበት አስተዋፅዖ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
በምርጫው ሂደት ሴቶች እንደመራጭ፣ ተመራጭ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካይ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ፣ ምርጫ ታዛቢ፣ ድምፅ ቆጠራ አስተባባሪና ሰራተኛ ፣ ጋዜጠኛ እና በመሳሰሉት በሚኖራቸው ተሳትፎ አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ ፣ ፆታዊ፣ ጥቃቶች ሊፈፀምባቸው እንደሚችል አመልክተዋል ፡፡
የጥቃቱ ሰለባዎችና ጥቃት ሲፈፀም የተመለከቱ አካላት በነፃ የስልክ መስመር 7711 በመደወል ጥቆማዎችን ፣ የሕግ ድጋፍና ማማከር አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚችሉ አስታውቀዋል ፡፡
ከክፍያ ነፃ የአገልግሎት ቁጥሩ/ 7711/ ከሁለት ወር በፊት ከሕግ ጋር በተያያዘ ከፍለው አገልግሎት ማግኘት ለማይችሉ ሴቶች በይፋ የተጀመረ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ሴቶች የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ከብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ኢንስቲትዩት (ኤንዲአይ) ጋር በመተባበር በዩ ኤስ አይ ዲ ድጋፍ አማካይነት የተተገበረ ነው፡፡
እሰዬ መንግስቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም