በቤኒሻንጉል ጉምዝ ጉባ አካባቢ ከዛሬ አስር ዓመት የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሊጠናቀቅ ከጫፍ ደርሷል፤ በስፍራው የሚገኙ ሰራተኞች ዛሬም ደቂቃዎች ሳይባክኑ በመስራት ላይ ሲሆኑ፤ ከወራት በኋላም የብርሃን ጭላንጭል ሊያሳየን ተቃርቧል። በስፍራው ያሉ የፕሮጀክቱ ሰራተኞች ለህዳሴ ግድቡ ውጤታማ መሆን ሌት ተቀን የመድከማቸውን ያህል ለኢትዮጵያ ወድቀት ደግሞ የሐሰት ትርክታቸውን እየፈበረኩ ደፋ ቀና የሚሉ አገራት መኖራቸው አይካድም። በዲፕሎማሲውም ረገድ የተቀረውን የዓለም ክፍል በሐሰት ትርክት ለማሳመን በመፍጨርጨር ላይ ናቸውና ከዚህ ከዲፕሎማሲው ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ እንዲሁም ከኢትዮጵያ በተቃራኒው የቆሙ አገራት ጫናን በተመለከተና በሌሎች መሰል ጥያቄዎች ዙሪያ አዲስ ዘመን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመካነ ልማት ጥናት ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሽፈራው ሙለታ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሯል፤ መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ ከግንባታው ጎን ለጎን እያካሄደች ያለውን የዲፕሎማሲ ሁኔታ እንዴት ያዩታል? በተመሳሳይ ግብጽም ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ እያራመደችው ያለው የዲፕሎማሲ አካሄዷን እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ሽፈራው፡– እንደሚታወቀው የህዳሴ ግድቡ ከተጀመረ አስር ዓመት ደፍኗል። በኢትዮጵያ በኩልም ሆነ የአባይ ተፋሰስ አገሮች የተለያዩ ዲፕሎማሲዎችን ያካሄዳሉ። በኢትዮጵያ በኩል በፊት ሲካሄድ የነበረው የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ የሚባለው አጠቃላይ ማዕቀፍ ውስጥ ነበር። ማለትም አስሩም አገሮች ባሉበት ተሰባስበው ሲካሄድ የነበረውና በፊት የነበረው የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ በግብጽና በሱዳን መካከል ብቻ በሞኖፖል የተያዘው በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረመ ውል ነበር። ይህን የቅኝ ግዛት ውል የሚቃወም ዲፕሎማሲ ነበር።
በአባይ ውሃ ሁሉም በተለይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች እንዲሁም ከታችም እነ ዑጋንዳንና ታንዛኒያን፣ ኬንያና ሌሎችም አገሮች የመጠቀም መብት አለን። እነዚህም አገራት በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረመው ውል ፍትሃዊ አለመሆኑን እያነሱ ይከራከሩ ነበር። በዚያ ውስጥ እንደሚታወቀው ግብጽም ሱዳንም የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ አባል ሳይሆኑ ነው የህዳሴ ግድብ ድርድር የተጀመረው። የህዳሴ ግድብ በተጀመረ ጊዜ ኢትዮጵያ የተሻለ የዲፕሎማሲ አቅም ነበራት። ግድቡ ለምን እንደሚያስፈልግና ለምን እንደሚሰራ ለኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት እና ህዝቧን ከጨለማ ለማውጣት እንደሆነ እንዲሁም ግድቡ የሚሰራው በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ የከፋ ጉዳት በማያስከትል መልኩ እንደሆነ ነበር ሲገለጽ የነበረው።
የግብጽ ዲፕሎማሲን ስንመለከት የህዳሴው ግድብ አሁን ላይ 79 በመቶ ደርሷል። ስለዚህም ወደመጠናቀቁ እየሄደ ነው። ግብጾች በአስሩም ዓመት ተቃውሟቸውን ሲያቀርቡ ነበር። ነገር ግን ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመት ውስጥ ነው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የዲፕሎማሲ ጫና ሲያደርጉ ነበር። ግድቡን መገደብ ማስቆም እንደማይችሉ ከገባቸው በኋላ በውሃ አሞላል የቴክኒካል ሂደት ላይ ነበር ጊዜ ሲያጠፉ የነበረው። በተለይ የግብጽ ኑሮ የተመሰረተው በአባይ ውሃ ላይ ብቻ በመሆኑ በድርቅ ወቅት እንጎዳለንና መሰል ነገሮችን ነበር ሲያነሱ የዘለቁት።
በዲፕሎማሲ ረገድ ግብጾች በተሻለ ሁኔታ ላይ ነው የነበሩት። ምክንያቱም ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ካለው ከጂኦፖለቲክስ ጋር በተገናኘ ከእስራኤል ጋርም ሆነ ከምዕራባውያን ጋር በተገናኘ ያላቸው ቁርኝት ተጠቃሽ ሲሆን፤ ምዕራባውያን ባላቸው የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እንዲሁም ባላቸው የራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ለግብጽ የማዘንበል ሁኔታ ይታይባቸዋል። በዚህ በኩል ግብጽ በተጎጂነት መቀመጫ ላይ እንዳለች ነው የሚቆጠረው።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት እንደሚታወቀው ግብጽ እያራመደች ያለው የዲፕሎማሲ አካሄድ ጫና ለመፍጠር ቢመስልም በቅርቡ ግን የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአገራቸው ፓርላማ የሰጡት የአይጎዳንም መልዕክት መለሳለስን ወይስ ነገሮችን የማዳፈን ስራ ነው?
ዶክተር ሽፈራው፡– እኔ መለሳለስ ነው ብዬ አላየውም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያሉት ኢትዮጵያ ግድቡን ከመሙላቷ በፊት መጀመሪያ ግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ እንዳይሞላ ለማድረግ ነው ጥረት ሲያደርጉ የነበረው። ግብጾች የሚፈልጉት አሳሪ የሆነ ስምምነት ማስቀመጥ ነው። አሁን ግድቡ መሬት ላይ ያለ እውነት ሆኗል። ስለዚህም ግድብ ተገንብቶ ውሃ ሳይሞላ አይቀርም። ይህንን አውነት ደግሞ ሁሉም ወገን ሳይገነዘበው አልቀረም።
በተለይ እኤአ በ2015 የመርሆዎች ስምምነት ካርቱም ላይ በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር እና በግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ነው የተፈረመው። ይኸኛው ስምምነት ወደእውነታው እንዲቀርቡ አድርጓቸዋል። ከዚያ በኋላ አሁን ያለውና ትልቅ ጫና እያሳደረ ያለው ነገር የግድቡ መሞላትና ያለመሞላት ሂደት ነው። ግድቡ ለኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል በመሆኑ ኃይል ካመነጨ በኋላ ውሃው እንደሚለቀቅ ጠንቅቀው ያውቁታል። ስለዚህ ዞሮ ዞሮ በዓመት ከሚያገኙት መጠን የሚቀርባቸው የለም። ችግሩ ያለው የቴክኒካል ጉዳይ ላይ ሳይሆን የህግ ጉዳያቸው ላይ ነው። የህግ ጉዳይ ማለት ደግሞ አሳሪ የሆነና ዞሮ ዞሮ ወደውሃ ክፍፍል የሚያመዝን ስምምነት ነው። ግብጾች የሚፈልጉት መጪው የኢትዮጵያ ትውልድ አባይ ላይ ሌላ ግድብ እንዳይገነባ የሚያስር አንቀጽ ማኖር ነው። ይህን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት አያደርግም። እስካሁን ባለው ሁኔታ የመጪውን ትውልድ ጥቅም የሚነካ ምንም ዓይነት ስምምነት ላለመስማማት ነው በኢትዮጵያ መንግስት የተያዘውም አቋም የሚያሳየው እንጂ ግብጽን የመጉዳት ወይም በእነሱ ላይ ተጨባጭ የሆነ ተጽዕኖ እንደማይደርስ ሁሉም ወገን ያውቀዋል። እንደሚታወቀውም በድርድሩ 99 በመቶ ቴክኒካዊ የሆኑ ነገሮች ያለቁ ይመስላል። በግብጽ በኩል ያለው ፍላጎት አሳሪ የሆነ ህግ እንዲኖርና ኢትዮጵያ በውሃው እንዳትጠቀም በቅኝ ዘመን የነበራቸውን የአንበሣውን ድርሻ የመውሰድ ነው።
የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተናገሩት ምናልባት የምንችለው ኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር ውሃ ከሞላች በኋላ በዚያ ሰዓት የተወሰነ የውሃ መቀነስ ቢኖር እሱን መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን የሚገልጽ እንጂ መሰረታዊ በሆኑ በዲፕሎማሲያዊና በግብጽ አቋም የተቀየረ ነገር የለም። ተቀይሯል ብለንም ብዙ መጠበቅ የለብንም። ምክንያቱም በባለሙያዎችም በመንግስትም ደረጃ ሁኔታውን የሚያውቁትም እንኳን ቢሆን በግልጽ ለህዝብ ወጥተው ይናገራሉና ተጽዕኖ አያደርግም ማለት አይቻልም።
ስለዚህ ባለፈው ለፓርላማ አሰሙ የተባለው ንግግር ምናልባት የምንችለው ግድቡ ውሃ በሚሞላበት ጊዜ የተወሰኑ መቀነሶች ቢኖሩ እነሱን መቋቋም የሚያስችሉ ዝግጅቶች እያደረግን ነው ማለታቸው ነው እንጂ ለሁለት ዓመት የሚሆናቸውን ውሃ በአስዋን ግድብ ይዘዋል።
በዚህ ዓመት የእኛ ግድብ ሁለት ተርባይን ኤሌክትሪክ ካመነጨ በኋላ ውሃው ተመልሶ እንደሚደርሳቸው ያውቃሉ። በክረምት ወራት ሊያገኙት የሚችሉት ውሃ ቢቀንስም በበጋው ወራት ደግሞ ተርባይኖቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ከጀመሩ ውሃው ኤሌክትሪክ አመንጭቶ ነው የሚወጣው። ምክንያቱም ተርባይኖቹ ኤሌክትሪክ ካመነጩ በኋላ እኛ ዘንድ ውሃው የሚቀርበት ምክንያት የለም። ዞሮ…ዞሮ በዓመቱ መጨረሻ የሚፈልጉትን የውሃ መጠን ያገኛሉ። ይህንን እውነታ መገንዘብ አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታውን እያካሄደች ያለው የራሷን ሀብት በራሷ ገንዘብ ለመጠቀም ስትል ነው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ እውነታን ይዛ ህዝቧን ከጨለማ ወደመብራት ለማውጣት በምታደርገው ሂደት ምዕራባውያን ግብጾች የሚያሰሙትን አሉታዊ ተጽዕኖ ከማስተጋባት ውጪ የኢትዮጵያን እውነት ይዞ የመሄዱ ነገር ላይ ዝምታን መርጠዋልና ይህ ምንን ያመለክታል?
ዶክተር ሽፈራው፡– አንድ መገንዘብ ያለብን ነገር ኢትዮጵያ የናይልን ወንዝ 86 በመቶ የምታመነጭ አገር መሆኗን መላ ዓለም ማወቁን ነው። ነገር ግን ይህን ሁሉ በመቶ አመንጪዎች እኛ ነንና የታችኛዎቹ አገሮች በዚህ ሀብት መጠቀም የለባቸውም ማለት አንችልም።
ነገር ግን በእኛ በኩል በምናስረዳበት ጊዜ ማለት የሚጠበቅብን ሀብታችን ነው፤ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነውና የመጠቀም መብት አለን ነው። ብዙ ጊዜ የሚባለው በዲፕሎማሲውም የሚባለውም ከሌሎች አገሮችም ተደጋግሞ የሚሰማው ይህ ነው። ነገር ግን ከዚህ ባሻገር ማስፈፀም መቻል አለብን። ማለትም ይህ ግድብ አገልግሎቱ ለኤሌክትሪክ ፍጆታ ነው፤ 80 በመቶ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠር ነው። እንኳን በገጠር ላለው ህዝብና በከተሞች አካባቢ ለሚኖረውም ህዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ በሙሉ አልደረሰም። ለኢትየጵያ እድገት አስፈላጊ ስለሆነ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የሚኖረው ጨለማው ውስጥ ስለሆነ እናቶች እንጨት እየለቀሙ ለቤት ውስጥ ማገዶ አጠቃቀም ስለሆነ እንዲህ አይነት ሁኔታ ነው ያለው።
ነገር ግን ግብጾቹ የተሻለ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት አላቸው። ይህ ግድብ ኤሌክትሪክ ካመነጨ በኋላ ውሃው ተመልሶ ወደእነሱ እንደሚሄድና የመሳሰሉ ዓይነት ነገሮችን ልንገልጽ ይገባል። ሉዓላዊነት ከሚለው ትርክት ባሻገር ሌሎች አሳማኝ ነጥቦችን በማንሳት ጠንከር ባለ መልኩ ማስረዳት አለብን። ይህንን ነገር ነው በእኔ በኩል ቀረ ብዬ የማስበው።
ነገር ግን እንዲያም ሆኖ ምዕራባውያውን የሚያስከብሩት የአገራቸው ብሄራዊ ጥቅም አለ፤ እነሱም ሆኑ ሚዲያዎቻቸው የሚከተሉት ይህንኑ ነው። ሁለተኛው ግብጽ በጂኦፖለቲካው በመካከለኛው ምስራቅም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ከኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ አላት። ዲፕሎማሲው የተሳለጠ ይሆን ዘንድ የአገራት የኢኮኖሚ ጥንካሬም ይወስነዋል። ስለዚህ በእኛ በኩል ከሉዓላዊነት ትርክት ባሻገር ሌሎች አግባብ የሆኑ ማሳመኛ ጉዳዮችን ጠንካራ በሆነ ሁኔታ ማቅረብ ይገባናል። ግብጾች ያሉበትን ደረጃ ለመቀየር መከተል የሚገባን ከትርክት ባሻገር የያዝነውን እውነት በመናገር ማሳመን ነው፤ ዲፕሎማሲ የሚባለው ጥረት ይህ ነው።
ይህን ስናደርግ በምን አግባብ ነው የሚባል ከሆነ በየሚዲያዎቻቸው ቀርቦ በማስረዳት ሊሆን ይችላል። አስተውለሽ ከሆነ በኢትዮጵያ በኩል የሚቀርቡት ብዙዎቹ አሳማኝ ምክንያቶችም ሆኑ ዘገባዎች በኢትዮጵያ ሚዲያ ብቻ ነው። በሌላ በውጭ ቋንቋ በደንብ ማስረዳት ይጠበቃል። ለአረቡ አገራት በአረብኛ፣ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ለሆኑ አገራት ደግሞ በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሣኛ ተናጋሪ ለሆኑት በፈረንሣይኛ እንዲሁም የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑት በተለያየ ቋንቋ የያዝነውን እውነት ተደራሽ እንዲሆን የተለያየ የሚዲያ ተቋማትን ተጠቅመን በአግባቡ ማስረዳት እኛ በቁርጠኝነት መሥራት የተገባው የቤት ሥራ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– ግብጽ ከአፍሪካ ጉዳዮችም ሆነ አፍሪካዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር መማከር ካለመፈለጓም በላይ አፍሪካውያንንም ጭምር ትሸሻለችና ለዚህ ምክንያቷ ምን ይሆን?
ዶክተር ሽፈራው፡– ምክንያቱ ግልጽ ይመስለኛል፤ ግብጾች በመልካምድራዊ አቀማመጥ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ሆነው፤ ባላቸው ደረጃም ሆነ በባህል ግንኙነታቸው ከመካከለኛው ምስራቅ በዋናነት ከአረቡ ዓለም ጋር ነው። ሁለተኛው በአፍሪካ ህብረት ሲባል የከረመው ጉዳይ የአፍሪካውያን ጥያቄ በአፍሪካውያን መድረክ ይቅረብ የሚል ነው። ይህን ብዙ ጊዜ ሞክራ አይታዋለች። ውጤቱ እርሷን የሚደግፍ እንደማይሆን በምትረዳበት ጊዜ ያላትን ተጽዕኖ በሌሎች አፍሪካ አገሮች ላይ ይህ ነው የሚባል ባለመሆኑ ስለዚህ ከሌሎች አፍሪካ አገሮች ጋር የሚያዩት እውነታውንና ፍትሃዊነቱን ነው ማለት ነው።
ነገር ግን ግብጽ ከአፍሪካ አጀንዳ ወጥታ ምዕራቡ ዓለም ብትወስድ የራሱ የሆነ ጥቅም እንዳለው ትገነዘባለች፤ ያን ጥቅማቸውን በማስጠበቅ በኩል ግብጽ ዋንኛውን ስፍራ ትይዛለች። በዚህ ምክንያት እነርሱ ዘንድ የተሻለ የመደራደር አቅም ስለሚኖራት በተቻላት መጠን ጉዳዩን መግፋት የምትፈልገው ወደዚያ ነው። ከአፍሪካ አስወጥቶ ወደዚያ መግፋት የምትፈለግበት ምክንያት በዚህ የተነሳ ነው።
አብዛኞቹ የሰሜን አፍሪካ አገራት ከአፍሪካ ህብረት ጋር የመተባበር ሁኔታ የላቸውም። የባህል መራራቁም ሊሆን ይችላል፤ አሊያም የመልካዓምድሩ አቀማመጥም ሊሆን ይችላል። የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውም ከሌሎቹ ምዕራባውያን ጋር እንጂ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እና የህብረቱን መርሆዎች የመከተልና የማመን ጉዳዮችን አያሳዩም።
አዲስ ዘመን፡– ስለዚህ የአፍሪካ ህብረት ለጉዳዮች መፍትሄ ከመስጠት አኳያ ራሱን ጠንካራ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ነው የግብጽ ሁኔታ የሚጠቁመው?
ዶክተር ሽፈራው፡– እሱ እውነት ነው፤ ለምሳሌ ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ሌላኛዋ ከአፍሪካ ህብረት በራሷ ጊዜ ራሷን አግልላ ነበር። ምናልባት ከሰሜን አፍሪካ አገሮች መካከል በአፍሪካ ህብረት የማመንና የመሳተፍ ነገር የሚታይባት የሙአመር ጋዳፊ አገር ሊቢያ ስትሆን፤ በሊቢያውያን ዘንድ በአንድ አህጉር ከመኖር ባሻገር በአፍሪካ ህብረትም የማመን ነገር ይታይባቸዋል።
ዲፕሎማሲ ሲባል የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሌሎቹ የተፋሰሱ የአፍሪካውያንም ጉዳይም ነው። አሁን በዓለም መድረክም በአፍሪካ ህብረትም እየቀረበ ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያ በአንድ ወገን ግብጽና ሱዳን ብቻ ደግሞ በሌላ ወገን የሚመስል እንጂ ሌሎች አፍሪካ አገሮች ጠንክረው እየተሳተፉ አይደለም። የናይል ኢንሼቲቭ ጊዜ ሁሉም በመጀመሪያው አካባቢ ጠንክረው ይሳተፉ ነበር። አሁን ተቀዛቅዘዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት መስራች እንደመሆኗ እና ናይል ኢኒሼቲቭም ሐሳብ አመንጪና ግንባር ቀደም ሆና ስትመራ የነበረች እንደመሆኗ እሱን ለዲፕሎማሲ ማጠናከርም ወሳኝ ነው። እሱ ላይ አተኩሮ መስራት ያስፈልጋል። በተለይ በተፋሰሱ ውስጥ ያሉ አስሩ አገሮች ማለት ነው። እነዚህን አገራት በኢትዮጵያ ወገን ማሰለፍን ይጠይቃል። በርግጥ የህዳሴው ግድብ በተጀመረበት አካባቢ ተሰልፈውም ነበር። አሁን ያለው የመቀዛቀዝ ሁኔታን ወደቀድሞው ተነሳሽነት ለመመለስ ጥረት ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ በየአገሩ ያሏት ዲፕሎማቶቿ ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ መስራት የተገባቸውን ያህል ሰርተዋል ማለት አይቻልም የሚሉ አካላት አሉና ይህን እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ሽፈራው፡– ተሰርቶ ቢሆንማ ኖሮ ይህ ሁሉ ተጽዕኖ ባላደረሰብን ነበር። በርግጥ በአንድ አገር ዲፕሎማት ሆነው ዝም ብለው ይቀመጣሉ ማለት አይደለም። ምክንያቱም የየራሳቸውን ጥረት ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ የሚያደርጉት ጥረት በቂ አይደለም። በዲፕሎማሲ መድረክ ብልጫ ተወስዶብናል። ስለዚህ በዚህ ላይ ይበልጥ አተኩሮ መስራት ያስፈልጋል።
ከዚህ ረገድ የዲፕሎማቲከ መልዕክተኞቻችንን መመርመር ያስፈልጋል። ያስቀምጥነው ምን ዓይነት ዲፕሎማት ነው በሚል ማጤን ተገቢ ነው። ወደውጭ አገር የምንልከውስ አምባደሣደር ምን ዓይነት የሚለውን ጉዳይ መፈተሸ ያስፈልጋል። የአንድ አገር አምባሣደር ወይም ዲፕሎማት ወደተመደበበት አገር ሲሄድ በእውቀትም ሆነ በልምድ ጠንካራ ሆኖ መገኘት መቻል አለበት።
ቀድሞ ከነበሩን ዲፕሎማቶች አኳያ ዛሬ በዘርፉ በጣም ብዙዎችን ማፍራት የቻልንበት ወቅት ላይ ነን። ይሁን እንጂ በጣም ጥቂት ዲፕሎማቶች በነበሩበት ዘመን ለምሣሌ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እነ አክሊሉ ሐብተወልድ የሚሰሩትን ሥራ ስናስተውል በዲፕሎማሲው ረገድ የኢትዮጵያን አቋምና ፍላጎት ጎላ ብሎ እንዲታይ በማድረጉ በኩል ትልቅ ነገር መኖሩ የሚካሄድ አይደለም። ስለዚህ አሁን ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡– የኪንሻሳው ስምምነት ያለውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እኤአ የ2015ን የመርሆዎች ስምምነት መሠረት አድርገው የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትርንና የግብጹን ፕሬዚዳንት በጉዳዩ ላይ ለማወያየት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፤ ይህ ጥሪ ውዝግቡን ያረግበዋል ተብሎ ይታሰብ ይሆን? ለዲፕሎማሲውስ ምን ፋይዳ አለው?
ዶክተር ሽፈራው፡– በርግጥ አብደላ ሀምዶክ ያነሱት ነገር እኤአ በ2015 በአገራት መሪዎች በተፈረመው መርሆዎች ላይ አንድ አንቀጽ አለ፤ በቴክኒክ የሚተዳደሩት ወይም በውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረጉ ድርድሮች እልባት ካላገኙና የርዕሳነ ብሄራትን ውሣኔ የሚፈልግ ጉዳይ ሲኖር በመጨረሻ ላይ የሦስቱ አገራት ርዕሰ ብሄሮች ተገኝተው ጉዳዩን እንደሚመለከቱ ችግር ሲፈጠር ብቻ ሳይሆን በቴክኒክ ደረጃ ወይም በሚኒስትር ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶችን የሚያፀድቁትና የመጨረሻ ፊርማቸውን የሚያኖሩት ሦስቱ ርዕሳነ ብሔራት ናቸው ነው የሚለው።
ነገር ግን በቴክኒክ ደረጃ በባለሙያዎች ደረጃ የሚደረገው ውይይት እልባት ባላገኘበት ሁኔታ በሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረገው ውይይት ባላለቀበት ሁኔታ እስካሁን ሲካሄዱ የነበሩ ድርድሮች እልባት ባላገኙበት ሁኔታ ነው የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት።
ይሁንና የእኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለዚህ ጉዳይ ጥሩ ምላሽ እንደሰጡ ነው የምንገነዘበው። ምክንያቱም መጀመሪያም በቴክኒክ ደረጃ ያለው ስምምነት በባለሙያዎች ደረጃ ሲካሄድ የነበረውን ሁኔታ ወደኋላ የሚመልስ ዓይነት ነገር ስለሆነ እሱን መቋጨት ያስፈልጋል። መቼም የአገር መሪዎች የፖለቲካ መሪዎች እነዚህ ዝርዝር በሆኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ እውቀቱም ላይኖራው ይችላል። ስለዚህ በቴክኒክና በባለሙያዎች ደረጃ የሚደረጉ ድርድሮች ካለቁ በኋላ ነው እነሱ መምጣት የሚኖርባቸውና የቴክኒክ ቡድኑና የባለሙያዎች ውይይት ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ ይህን ጥሪ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማድረጋቸው አንድ እርምጃ ወደፊት መግፋት ዓይነት ነገር ነው።
ምክንያቱም እንዳልኩሽ በአገር መሪዎች ደረጃ የሚካሄደው የመጨረሻው ማጠናቀቂያ ነው የሚባል ስለሆነ ከዚያ በፊት መቅደም ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ለምሣሌ ልክ በእግር ኳስ ጨዋታ ህግ መጫወት የሚገባቸው 90 ደቂቃ ነው። 90 ደቂቃው ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ የመለያ ምት መስጠት አይጀመርምና በተመሳሳይ በግድቡ ዙሪያ ባለሙያዎቹ 90ውን ደቂቃ ተጫውተው ባልጨረሱበት አግባብ ወደቀጣዩ ደረጃ መሄድ አይቻልም። ስለዚህ ዶክተር አብይ ይህን አጢነው ጉዳዩን ውድቅ ማድረጋቸው በእኔ በኩል ትክክል ነው ብዬ እገምታለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ሱዳን በኢትዮጵያ ድንበር ላይ የጠብ አጫሪነት ሚናዋን በመጫወት ላይ እንደሆነች ይታወቃል፤ ይህ አካሄዷ በህዳሴ ግድብ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ይኖር ይሆን?
ዶክተር ሽፈራው፡– በደንብ ይኖረዋል፤ ምክንያቱም የድንበር ፍላጎታቸውንና ድርድራቸውን ወደህዳሴ ግድብ የማሸጋገር ሁኔታ አለ። ለምሣሌ ቀላል ምሣሌ ለማንሳት ያህል ኢትዮጵያ ግድቧን በራሷ ድንበር ላይ ነው የገነባችው። የህዳሴ ግድቡ ያለው ከሱዳን ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። ይሁን እንጂ በተለያየ ዋና ዋና በሚባሉ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ የሱዳን ተወካዮች ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ለምሣሌ በቅርቡ በአልጂዚራ ላይ የቀረቡ የሱዳኑ ተወካይ የህዳሴ ግድቡ የተሰራበት ቤኒሻንጉል ጉምዝ የኛ ነው ብለዋል። ይህን ስትሰሚ ቀልድ የሚመስል ዓይነት ነገር ነው። ነገር ግን እንዲሁ ዝም ተብሎ የሚታለፍ ነገር አይደለም።
በሱዳን በኩል የድንበር ክርክር የነበረው በምዕራብ ጎንደር ላይ ነው፤ በመካከል ያለውን ርቀት ማጤን ይቻላል። ስለዚህ የድንበር ላይ ግጭቱን ወደውሃ ሁኔታ ማላከክ ትልቁን ጠይቄ ትንሹን ላግኝ ዓይነት ጨዋታ ይመስላል። በዚህ አስፈራርተው የምዕራብ ጎንደሩ ይሁንላችሁ እንዲባሉ የመፈለግ ዓይነት ይመስላል እንጂ እውነት እንዳልሆነ እነርሱም የሚያውቁት ነው። ምክንያቱም ይህን ሁሉ ዘመን እንዲህ ዓይነት ‹‹ቤኒሻንጉል ጉምዝ የእኔ ነው›› ዓይነት ጥያቄ ሲያነሱ ሰምቼ አላውቅም። ይህ አዲስ ነገር ነው። ስለዚህ ሱዳኖች በድንበር አሳብበው ወደግድቡ የመጠጋት ሁኔታ ያለ ይመስላል።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት ቁርጠኛ የሆነችው በመርሆዎች ስምምነት ላይ በግልጽ ስለአሞላሉ በመስፈሩም ጭምር ነው፤ ይህ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያን ከመሙላት የሚያግዳት እንደሌለ ሁለቱ አገሮች ደግሞ በሐሳቡ ያለመስማማታቸውን ልዩነት ያመጣው ነገር ምንድን ነው ይላሉ? ያለመስማማታቸው ነገር በቀጣናው የዲፕሎማሲያዊ ሂደት ላይ የሚያሳድረው ጫና ይኖራል?
ዶክተር ሽፈራው፡– በትክክል፤ ለወደፊቱ ለቀጣናው አለመረጋጋትን የሚፈጥር ሁኔታ አለው። ምክንያቱም በተለይ በሱዳኖች በኩል በፊት ከነበራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የመተባበር መንፈሳቸው ሙሉ በሙሉ ትተውታል። የህዳሴ ግድብ ከተጀመረ አሁን አስር ዓመት ሆኖታል። ሁሉም በውሃ ባለሙያዎቻቸው ይሁን በፕሬዚዳንታቸውም ጭምር ሱዳንም ለሱዳን ብዙ ጥቅም እንደሚያመጣ እንዲሁም ጎርፍ እንደሚከላከልላት፣ ዓመቱን ሙሉ ተመጣጣኝ የሆነ የውሃ ፍሰት እንደሚኖራት የመሳሰሉ ጥቅሞች እንዳሉት ሲገልጹ ነበር የከረሙት።
ሱዳን ብሄራዊ ጥቅሟ እንደማይነካና ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን በሚያረጋገጥ ሁኔታ እየሄደ ሳለ ለምንድን ነው ይህን አቋሟን የቀየረችው የሚለውን በምናይበት ጊዜ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ጥቅል የነበረውን ስምምነት ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የሁለትዮሽ ድርድር ማድረጓ ምናልባት ሱዳኖች ወደጎን እንደተተው እንዲሰማቸው አድርጎ ሊሆን ይችላል። ይህ ብቻ ግን ገፊ ምክንያት ነው ብዬ አላስብም።
የአስተሳሰብ ለውጥ የመጣው በሱዳን ውስጥ የመንግስት ለውጥ ከመጣ በኋላ ማለትም ፕሬዚዳንት አልበሽር ከተቀየሩ በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ ብዙ ዓይነት ለውጦች በውጭ ግንኙነታቸው ላይ እያካሄዱ ነው። ከአሜሪካ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በማሻሻል፣ ከእሥራኤል ጋር የነበራቸውን የረጅም ጊዜ እውቅና ሳይሰጡ የቆዩትን ጉዳይ በማሻሻል፣ ከሌሎች የአረብ ሊግ አገራት ጋር እና መሰል ጉዳዮች ሲታዩ በሱዳን የውጭ ግንኙነት ውስጥ የተለወጠ ትልቅ አሰራር አለ። ስለዚህም የዚህም አንዱ አካል ሊሆን ይችላል።
ዞሮ…ዞሮ ግድቡ ካልተሰራ የሚያገኙትን የተወሰነ ጥቅማቸውን እንደያዙ ይቀጥላሉ። ምንም አይጠቀሙም ማለት ደግሞ አይደለም፤ ምክንያቱም ብዙ ግድቦች አሏቸው። ግድቡ የሚሞላም ከሆነ ዞሮ…ዞሮ የሚያገኙት የውሃ መጠን አይቀርም። ስለዚህ በሁለቱም ወገን ተጠቃሚ መሆናቸው ካልቀረ ከግብጽ ጋር ለምን እንሻከራለን የሚልና በተለያየ መልኩ የእነሱንም ድጋፍ የሚፈልጉበት ሁኔታ ካለ እሱንም የመጠቀም ሁኔታ መሰለኝ የሚያንፀባርቁት፡፤
እንዲያም ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ለውጡንም ሆነ የኃይል አሰላለፉን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የመገምገምና ኢትዮጵያ አሁን ላይ በቀድሞው ሁኔታ አይደለችም በሚል ስለሆነ የሚያዩት እኛ ደግሞ የውስጥ ችግሮቻችንን ፈትተን በመጠናከር መንቀሳቀስ ወሳኝነት አለው። ስለዚህም የውስጥ ሠላም ሊኖረን ይገባል። ምክንያቱም የአገራት የውስጥ ጥንካሬያቸው ነው ለውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴያቸው ብርታት የሚሆነው። የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውንም ጠንካራ የሚያደርገው።
አዲስ ዘመን፡– ግብጽና ሱዳን እውን የህዳሴ ግድብ መገንባቱ ትልቅ ተጽዕኖ ስለሚያሳድርባቸው ፈርተው ነው ኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚፈጥሩት? ኢትዮጵያ ግድቡ የሚጎዳችሁ ከሆነ ይቅር በቃ ብትል እንኳ ፍላጎታቸው በዚህ ይቆማል ይላሉ?
ዶክተር ሽፈራው፡– በዚህ አይቆምም፤ ዋና ነገር እና ሁላችንም ማወቅ ያለብን ነገር ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ምንም አይነት ልማት እንዳታከናውን መፈለጋቸውን ነው። ይህ ፈሊጥ ዛሬ የተያዘ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ የመጣ ነው። ዛሬ ሳይሆን ዘመናዊ የኢትጵያ ታሪክ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ግብጾች ኢትዮጵያን ለመውረር ብዙ ሞክረዋል። በዚያን ወቅት ኢትዮጵያ አቅም ኖሯት ግድቡን ትገነባዋለች በሚል አይደለም። የአባይን ውሃ ምንጩን ለመቆጣጠር ነበር። ብዙ ጊዜ ሞክረው ከሸፈባቸው እንጂ ብዙ ጥረዋል።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ግድቡንም አልሰራም፤ ውሃውንም አልሞላም ብትል የሚተውት ነገር አይደለም። በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን በማስገባት ኢትዮጵያ የተረጋጋች አገር እንዳትሆን ነው የሚሰሩት፤ ይህን ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ስለዚህ ፍላጎታቸው ከግድቡ መገደብ አለመገደብ ጋር ብቻ ሳይሆን ሌላም መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ለዛም ይመስለኛል ግድቡ ሲሰራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የበኩላቸውን በማድረግ ርብርብ ያደረጉት ይህን ድብቅ ፍላጎታቸውን በማወቃቸውም ጭምር ነው። አሁንም በተባበረ ክንድ ግድቡን ወደመጨረሻው ደረጃ አድርሰናልና። ይህን ለማጠናቀቅ እንዲሁ የበኩላችንን ልናደርግ ይገባል። ከዚህ በኋላ ወደኋላ አይኖርም።
በዲፕሎማሲው ረገድ ያለው እንቅስቃሴ በመንግስት ብቻ የሚሰራ አይደለምና መላ ህዝቡን ያሳተፈና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በያለበት አምባሣደር ሆኖ የሚንቀሳቀስበትን ሥራ አጠናክረን መቀጠል አለብን። ሁለተኛ ደግሞ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር ይጠበቅብናል። በአንድ ወቅት ተጀምሮ የነበረው ጥሩ የሚባል አካሄድ ነበር። የእኛ ምሁራን፣ የፓርላማ አባላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደእነርሱ ሄደው ስለግድቡ ጠቃሚ ጎን በመናገርና ኢትዮጵያ እነሱን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት ሲገልጹ ነበር። አሁንም በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በመንግስት ደረጃ የሚነገረው ብቻ በቂ ስላልሆነ ፐብሊክ ዲፕሎማሲን ማጠናከር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሠግናለሁ።
ዶክተር ሽፈራው፡– እኔም አመሠግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013