በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የገጠር አካባቢዎችና ከተሞች ለግንባታ ግብአትንት የሚውሉ ማእድናት በስፋት እንደሚገኙ ይነገራል። በተለይ ለመንገድ ግንባታ ግብአትነት የሚውሉ እንደ ገረጋንቲ፣ ጥቁር ድንጋይና ለሕንፃ ግንባታ የሚያገለግሉ አሸዋና ጠጠር የማይገኙበት ቦታ የለም። መአድናቱ በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በተለይም በከተሞች በስፋት እየተመረቱ ቢሆንም መአድናቱን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች እንዳሉባቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል።
የኮንስትራክሽን መአድናት በብዛት አቅፈው ከያዙ የክልል ከተሞች ውስጥ አንዷ ወልዲያ ናት። በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች አሸዋን ጨምሮ ጥቁር ድንጋይና ገረጋንቲ በስፋት ይገኛል። የከተማዋ ወጣቶችም በማህበር ተደራጅተው የኮንስትራክሽን መአድን ማምረት ሥራ ያከናውናሉ። የከተማዋ መአድን ሥራዎች ፍቃድ አስተዳደርም ከመአድን ማምረት ሥራዎች ፍቃድ የሮያሊቲ ክፍያ ይቀበላል። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የከተማዋ የግንባታ መአድናት በሚፈለገው ልክ እየተመረቱ አይደለም።
የወልድያ ከተማ አስተዳደር የመአድን ሥራዎች ፍቃድ አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ደጀኔ ይርሳው እንደሚሉት በከተማ አስተዳደሩ አሸዋና ጥቁር ድንጋይን ጨምሮ የተለያዩ የኮንስትራክሽን መአድናት ይገኛሉ። ገረጋንቲ በአብዛኛዎቹ የከተማዋ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በኢንዱስትሪ መንደር፣ ሚካኤል በርና አውራ ጎዳና አካባቢዎች ላይ ይገኛል። አሸዋና ጥቁርድንጋይ ደግሞ ጥቁር ውሃ አካባቢ መገኛው ነው ።
በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የከተማዋ ወጣቶች በአስራ ስድስት ማህበራቶች ውስጥ ተደራጅተው የኮንስትራክሽን መአድናት በማምረት ላይ ናቸው። በዚህ ዓመትም 26 ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ከተለያዩ የመአድን ማውጣት ሥራዎች ፍቃድ በዓመቱ የተሰበሰበው ገቢም 25 ሺ ብር ብቻ ሲሆን፤ ይህም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው አካባቢው በፀጥታ ስጋት ቀጠና ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከሲሚንቶ ዋጋ መወደድ ጋር በተያያዘ የኮንስትራክሽን መአድን ማምረት ሥራው ተቀዛቅዟል።
እንደ ቡድን መሪው ገለጻ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የሚገኘው መአድን በጂኦሎጂካል ሰርቬዬ በዝርዝር የተጠና አይደለም። ሆኖም ይህን ችግር ለመፍታት ከከተማው የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ፅሕፈት ቤት ጋር በመተባበርና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂካል ትምህርት ክፍል ጥናት እንዲያካሂድ እንቅስቃሴ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም እስከአሁን ድረስ የተሠራ ሥራ የለም። ምን አልባት ግን ሥራ በ2014 ዓ.ም ጥናቱ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
በከተማው በቂ የሆነ የኮንስትራክን ማአድን ሀብት በተለይም የካባ ድንጋይ ካለመኖሩ ጋር በተያያዘም በሚፈለገው ልክ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር አልተቻለም። የመንግሥትንም ሆነ የግል ሥራ ተቋራጮችን የኮንስትራክሽን መአድናት ፍላጎት በሚፈለገው ልክ ማርካትም አልተቻልም። የከተማ አስተዳደሩ ካሳ ከፍሎ የኳሪ ሳይቶችን እከልላለሁ ብሎ ነበር። ነገር ግን ለዚሁ ሥራ የተበጀተው ገንዘብ በተለይ ለካሳ ክፍያ በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ክፍያውን መፈፀም አልተቻለም። ይሁንና የካባ ድንጋይ ቦታዎቹ ጥናት ተጠናቋል። ካሳ ገማች ኮሚቴም ግምቱን ጨርሷል። አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ግን ገንዘብ አልተገኘም። በዚህም ምክንያት በሚፈለገው ልክ ሥራ አልተሠራም።
እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት በከተማው ያለውን የመአድን ሀብት የመለየትና የማጥናት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። የካሳ ግመታ ኮሚቴ በማቋቋምም የመአድን ማውጫ ቦታ ተለይቶ ሥራ ላይ እንዲውል እንቅስቃሴም ተደርጓል። በይበልጥ ደግሞ የከተማው ማስተር ፕላን ሲከለስ የገጠር ቀበሌዎችም በከተማው ስር ስለሚካለሉ ከሥራ ዕድል ፈጠራና፣ ከሥራ ተቋራጮች በኩል ሲነሱ የነበሩ ችግሮች መቅረፍ ይቻላል።
በሌላ በኩል ደግሞ ዘርፉ ላይ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርለት ፈልጎ የሚመጣ ወጣት ባለመኖሩ የመአድን ማውጣት ሥራው በእጅጉ ቀንሷል። ከዚሁ ፍቃድ የሚገኘው ገቢም በሚፈለገው መጠን ሊሆን አልቻለም። እስከአሁንም የከተማዋ የመአድን ሥራዎች ፍቃድ አስተዳደር ወጣቶችን በዚህ ዘርፍ ሲያደራጅ የቆየው ታች ቀበሌ ድረስ በመውረድና በመጎትጎት ነው።
በቀጣይም የከተማ አስተዳደሩ የካሳ ግምቱን የሚያስከፍል ከሆነ የመአድን ሥራዎች ፍቃድ አስተዳደሩ የራሱ ኳሪ ሳይት ስለሚኖረው በድንጋይ ካባ ለወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ለወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በመፍጠርና ከአጋር አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ከቴክኒክና ሞያ ትምህርት ስልጠና ተደራጅተው ለሚመጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታስቧል። የመአድን ግብረኃይሉ ወደ ሥራ እንዲገባ የማድረግና የማጠናከር ሥራዎችም ይሠራሉ። የመአድን ሀብቱን አቅም የመፈለግ፣ ማጥናትና በመረጃ አደራጅቶ መያዝ እንዲሁም ለተጠቃሚው ደግሞ በተለያዩ መንገዶች የማስተዋወቅ ሥራዎችን የመሥራት አቅዶችም ተይዘዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013