በባላገሩ አይዶል ላይ በመሳተፍ በአሸናፊነት አጠናቋል። በ2008 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ከድምፃዊት አስቴር አወቀ ጋር በተዘጋጀው ኮንሰርት በጋራ በመሆን ስራውን አቅርቧል። የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ-በዓል ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የባህል ባንዱን ጨምሮ የባህል ውዝዋዜዎችን አቅርቧል። ዓለም አቀፍ በሆነው የቴሌቭዥን ጣቢያ ሲ.ኤን.ኤን. ላይ የኦባማ ሼፍ ለሰራው ዶክመንተሪ ፕሮግራም ኢትዮጵያን በባህል ውዝዋዜው በማስተዋወቁ ተሳትፏል። ኢትዮጵያዊነት የባህል ውዝዋዜ ቡድን።
በስድስት ወጣቶች በ2001 ዓ.ም የተመሰረተው የባህል ቡድኑ የተዋቀረው የልጅነት እድሜ የቸራቸውን ተፈሯዊ ችሎታ መጠቀም በቻሉ ታዳጊ ወጣቶች ነው። የኪነ ጥበብን ዓለም የተዋወቁ የዛሬዎቹ ወጣቶች የትላንትናዎቹ ታዳጊዎች የቡድኑን ስምና ዝና ከፍ በማድረግ ዛሬ ላይ የውዝዋዜውን መድረክ ተቆጣጥረውታል። ከአገር ቤት አልፈው እስከ ዓለም አቀፍ ተሳትፎ ማድረግ ችለዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ፕሮግራዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲሰራ እንደነበር የሚታወሰው ቡድኑ፤ ዓለም አቀፍ በሆነው የቴሌቭዥን ጣቢያ ቢ.ቢ.ሲ. አፍሪካ ባህል ላይ በሰራው ልዩ ፕሮግራም በመመረጥ በባህል ውዝዋዜ ተሳትፏል።
የህዳሴው ግድብ አራተኛ ዓመት ክብረ-በዓል በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀበት ወቅት በፕሮግራሙ ላይ ታሪክ ተናጋሪ ጊዜ የማይሽረው ስራ አቅርበዋል። የበጎ አድራጎት ስራን ከሚሰሩ ሃገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ከሆኑ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ጋር ማለትም ከመቄዶንያ ፣ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ፣ ጆይ ኦቲዝም ሴንተርና ከተለያዩ መሰል ድርጅቶች ጋር በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ተሳትፏል። የባህል አምባሳደር በሆነው በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ በቋሚነት ባህልን በማስተዋወቅ ላለፉት ከስድስት ዓመታት በላይ ሰርቷል። በመስራት ላይም ይገኛል።
ኢትዮጵያዊነት የባህል ቡድን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያን ብሔር-ብሔረሰቦችና ህዝቦች የባህል ውዝዋዜዎችን በማስተዋወቅ ደረጃ ትልቅ ሚና አለው። የአገር ባህልና ትውፊት ተጠብቆ ለሃገር እንዲሁም ለዓለም እንዲተዋወቅ ትልቅ አሻራ ማሳረፋቸውን የኪነ ጥበቡ ቤተሰብ ይመሰክርላቸዋል። የባሀል ቡድኑ ከስያሜው ጀምሮ በኪነ ጥበባዊ ሥራው ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያቀነቅን ሲሆን፤ በኪነ ጥበቡ ዓለም ያለው ወጣቱ ትውልድ ሃገራዊ አስተሳሰብ እንዲኖረውና የአገርን ባህል ጠብቆ ለሌሎች እንዲተዋወቅ በመስራት ላይ የሚገኝም ነው።
ከተወሰኑ ዓመታቶች በፊት ማለትም በ2008 ዓ.ም መቋጫውን ያገኘው በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢ.ቢ.ሲ) ለሦስት ዓመታት ሲተላለፍ የቆየውና፤ ኢትዮጵያን በማስተዋወቁ ረገድ በዓለም ላይ በተቀባይነቱ ትልቅ ቦታን ባገኘው “ባላገሩ አይዶል” ላይ ፈታኝ የሚባሉ ጊዜያትን አሳልፏል። ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቋል። ውድድሩን ካሸነፈ በኋላም ይሁን ከዚያ በፊት ከተለያዩ አንጋፋና እውቅ ከሆኑ ወጣት ድምፃውያን ጋር ባህላቸውን የጠበቁና ተወዳጅነትን ያተረፉ የሙዚቃ ቪዲዮ “ክሊፖችን” ሰርቷል፤ በመስራት ላይም ይገኛል።
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያዊነት የባህል ቡድን የተለያዩ ዓለማቀፍ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ የቴሌቭዥን መዝናኛ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ችሏል፤ተሳትፎም አለው። በበጎ ሥራዎቹ ለሃገርም ሆነ ለወገን አለኝታነቱን በማሳየት ተቀባይነትንና ተወዳጅነትን ማትረፍ የቻለ የኪነ ጥበብ ቡድን ነው።የቡድኑ እውቂያ በባላገሩ ምርጥ ላይ የገነነ ሲሆን፤ በቅርቡ ከአሜሪካዊው የሂፕ ሆፕ ሙዚቃ ስልት አቀንቃኝ ከሆነው ታዋቂው ጄሰን ድሩሎ ጋር ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን በመወከል ከቀረቡ ብዙ አፍሪካዊ ዳንሰኞች አሸናፊ በመሆን መመረጥ የቻለ ነው። ተመርጦ በመስራትና የአገር ባህል ስራውን ለዓለም ተደራሽ በማድረግ የመጀመሪያው ኢዮጵያዊ የባህል ቡድን ሆኗል።
ከቡድኑ መስራቾች አንዱ የሆነው ወጣት ታምራት እሸቱ እንደሚናገረው፤ ኢትዮጵያዊነት የባህል ቡድን እስከ አሁን የሰራቸው ስራዎች የተሳኩና ውጤታማ የሆኑ ሲሆን፤ይህም ወደፊትም በኪነ ጥበብ የስራ መስኮች ውጤታማ ስለመሆኑ ማሳያ ነው። ቡድኑ በወጣቶች የተቋቋመ በመሆኑ በዚህ ሙያ የሚቀጥለውን ሃገር ተረካቢ ትውልድ በማፍራትና ወጣቶችን መሰረት ያደረገ ሃገራዊ ስራ እየሰራ ነው።
የወጣቱን የልብ ምት በመረዳት አመርቂ ስራን ለማስራት ስያሜውን አሳድጎ “ኢትዮጵያዊነት የኪነ-ጥበብ ማዕከል” ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ ነው። በእስካሁን ስራዎቹ ያተረፈውን ስምና ዝና በመጠቀም ማዕከሉን በማደራጀትና በማስፋፋት ባህል ፣ ወግ እና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ቀጣይነት ያለው መሰረት መጣል እና አሻራውን ማሳረፍ ይፈልጋል።
የኪነ-ጥበብ ማዕከል የመሆን እሳቤው
እንደ ወጣት ታምራት እሸቱ ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያዊነት የኪነ ጥበብ መቋቋም በመዝናኛው ዘርፍ የሃገራችንን ባህል አጨፋፈር፣ አመጋገብ፣ አኗኗር፣ ቋንቋዎች ፣ ሙዚቃዎች ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍትኛ ሚና አለው። ማዕከሉ በኢትዮጵያ በየትኛውም እድሜ ላይ ለሚገኙ የጥበብ አፍቃሪያን በመድረስ አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ይረዳል። ለሃገር ሸክም እንዳይሆኑ በማዕከሉ በማሳተፍ ባህላቸውን፣ ትውፊትና ወጋቸውን አውቀው በኢኮኖሚም በመጠንከር ለሃገራቸው ብሎም ለወገናቸው የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችንና ትውልድን ቀርፆ በማፍራት ትልቅ ግብአት ይሆናል።
አገራዊ ፋይዳው
አይጠገቤ የሆነችውንና የቱሪዝም መስህብ የሆነችውን ኢትዮጵያን የበለጠ በቱሪዝሙ ዘርፍ በማገዝ፤ ቱሪስቶች ዓይናቸው ወደ አገር ቤት እንዲያማትሩ በማድረግ የሃገርን ኢኮኖሚም በማሳደጉ በኩል ትልቅ ሚናን ሊወጣ እንደሚችል ወጣት ታምራት ያስረዳል።
የማዕከሉ ይዘት
ማእከሉ ሲቋቋም በርካታ የኪነ ጥበብ ዘርፎችን እንደሚያካትት የሚናገረው ወጣት ታምራት፤ በተለይም እንደ ባህላዊ ውዝዋዜ፣ የባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ መሳሪያ ማሰልጠኛ፣ በድምፅ (ዘፈን)፣ ስነ-ፅሁፍ ቴአትር እንዲሁም የጥናትና ምርምር ያሉ ዘርፎች እንደሚካተቱበት ያመላክታል። መንግሥትና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ዓላማውን በመረዳትና ድጋፍ በማድረግ በወጣቶቹ ውስጥ ያለውን የኪነ ጥበብ አቅም ለመጠቀም ከጎናቸው እንዲቆሙም ጥሪ አቅርቧል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2013