የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በ1990 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ በከተማዋ የሚገኙ ወጣቶች ማህራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለ23 ዓመታት እየሰራ ይገኛል። ማህበሩ ወጣቱ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ ምርጫዎች በሚካሄዱበት ወቅት ቅስቀሳ በማድረግና በምርጫው እለት በመታዘብ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል። ዘንድሮ በሚካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ቅስቀሳ በማድረግ፣ መራጮችን በማስተማርና ምርጫውን ለመታዘብ የሚያስችለውን ሁኔታ እያከናወነ ይገኛል። አጠቃላይ ስለ ማህበሩ እንቅስቃሴና ስለ ምርጫ ስራ ከማህበሩ ዋና ፀሀፊ ወጣት ይሁነኝ መሀመድ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ከተመሰረተ ጀምሮ ምን ምን ስራዎችን አከናወነ?
ወጣት ይሁነኝ፡– የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ምንድነው? ማነው? ምንስ እየሰራ ነው? ለሚለው ጥያቄ ማህበሩ ከተመሰረተ 23ኛ ዓመቱን ይዟል። ስለማህበሩ የተቀመጡ መዛግብትና ቀደም ብለው ይመሩት የነበሩ ሰዎች እንደነገሩን ከሆነ በተመሰረተበት ወቅት ከከተማው የተውጣጡ ወጣቶች ከወረዳ ጀምሮ በተደረገ ጉባዔ የተመሰረተ ማህበር ነው። በተመሰረተበት ወቅት የራሱ ህግና ደንብ ያለው፣ መመስረቻ ፅሁፍና መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን አሟልቶ የተቋቋመ ማህበርም ነው። በወቅቱ እንደማህበሩ የተደራጁ ሲቪክ ተቋማት አልነበሩም። መንግስት አንድም ወጣቱን ለማግኘት በሌላም በኩል ከወጣቱ ጋር ሊሰራቸው የሚፈልገውን ስራ ለማከናወን እንዲረዳው የተደራጀ ሀይል የሚፈልግበት ሁኔታ ነበር። ማህበሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር የተለያዩ ድጋፎች ተደርገውለታል።
ቀደም ብሎ በደርግ ዘመነ መንግስት የነበሩ የወጣትና የሴት አደረጃጀቶች በመፍረሳቸው ይገለገሉባቸው የነበሩና የገቢ ምንጭ ያደረጓቸው ንብረቶች የወጣቱ የነበረው ለወጣት ማህበር፣ የሴት የነበረው ለሴት ማህበራት እንዲከፋፈል ተደርጓል። በተጨማሪም ከአባላት ከሚገኝ ገቢና ከሱቆች ከሚገኝ ወርሃዊ የኪራይ ክፍያ የሚንቀሳቀስ ማህበር ነው። ከምስረታው ጀምሮ የሰራቸውና መጠቀስ ካለባቸው ጉዳዮች ውስጥ በአገሪቱ በነበረው አስተዳደር ውስጥ የወጣቶችን ጉዳይ የሚመለከት አልነበረም። በወቅቱ የነበረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ በሚል ከመከፋፈል ውጪ የሴቶችና የወጣቶች ራሱን የቻለ ነገር አልነበረም። ለዚህም የተለያዩ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማምጣት ማህበሩ የወጣቶች ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በሚል ጥያቄ አቀረበ። የወጣቶችን ጉዳይ ይዞ የሚሰራ ተቋምና ያሉትን ችግሮች ሊቀርፍ የሚችል መመስረት አለበት በሚል ራሱን የቻለ ዘርፍ እንዲቋቋም ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል።
ሌላው ደግሞ ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት ማለትም ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግር ሲፈጠር ማህበሩ ግንባር ቀደም ሆኖ የመገኘት ሁኔታ ነበር። ለምሳሌ በ1998 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ለህብረተሰቡ ገንዘብ በመሰብሰብ ቦታው ድረስ በመሄድ ድጋፍ ተደርጎ ነበር። ሌሎች መሰል ተቋማቶች ሲመሰረቱ እንደ ማሳያና ሞዴል በመሆን ያሉትን ሁኔታዎች በመንገር እንዲመሰረቱ እገዛ አድርጓል። ለምሳሌ በኤች አይቪ ኤድስ ዙሪያ ሊሰራ ተመስርቶ የነበረው ተስፋህ ጎህ ኢትዮጵያ ሲቋቋም የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ድጋፎች አድርጓል። የአክሱም ሀውልት አስመላሽ ኮሚቴ ውስጥ የወጣቶችን ድምፅ ይዞ ሀውልቱ እንዲመለስ ጥረት አድርጎም ነበር።
በከተማው በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ተገንብተው የሚገኙት ወጣት ማዕከላት ሳይታሰቡ በፊት ወጣቶች የሚዝናኑበት፣ የሚሳተፉበትና የሚወያዩበት ተቋም ሊኖራቸውና ወጣቶች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል የሚል ሀሳብ አነሳ። ማህበሩ ሀሳብ ከማንሳት በተጨማሪ አንድ የወጣት ማዕከል በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስገንብቷል። ይህ ማዕከል ከተገነባ በኋላ መንግስት ራሱ ወስዶ በሌሎች ወረዳዎች እንዲስፋፋ አድርጓል። በከተማው በተለያዩ ቦታዎች ላይ የኤች አይ ቪ ኤድስ ንቅናቄ በማድረግ በየዓመቱ ችግኝ ተከላ በማከናወን እንዲሁም የአካባቢ ፅዳት ስራዎችን በዋናነት በባለቤትነት ሲሰራ የቆየ ማህበር ነው። አሁንም በመስራት ላይ ይገኛል።
የወጣቶች የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ በ1995 ዓ.ም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ቤታቸው የሚመጡ ተማሪዎችን በማሰባሰብ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሰጥ ያደርግ ነበር። የክረምት የበጎ ፈቃድ ስራ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ የቆዬ ሲሆን፤ መንግስት የነገሩን አስፈላጊነትና ጠቃሚነት በመረዳት ወደ ክልሎች እንዲሰፋ በማድረግ እንዲሁም በእቅድ ውስጥ በማካተት ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል። እስካሁን ድረስ ማህበሩ በራሱ የክረምት የበጎ ፈቃድ ስራን በማስቀጠል የበጋ የበጎ ፈቃድ ስራ በማካተት እየተሰራ ይገኛል። የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋም ባልተዋቀረበት ጊዜ በሞሃ ለስላሳ መጠጥ ፋብሪካና ከኮካኮላ ማምረቻ ፋብሪካ ጋር በመነጋገር በተለያዩ ቦታዎች ሱቆች እንዲከፈቱ ተደርገዋል። ይህን እንደሞዴል በመውሰድ የጥቃቅንና አነስተኛ ስራዎች ተጀመሩ ማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ወጣቶች መናኸሪያ ከተማቸው ከመሆን ባለፈ የወጣቶች መቀመጫ መሆን አለባት በሚል የአፍሪካ ወጣቶች ማዕከል ለመገንባት ከአስር ዓመት በፊት መሬት ተረክበናል። በአቅም ማነስና የሁኔታዎች አለመመቻቸት ሊገነባ አልቻለም። በፖለቲካውም መስክ በእያንዳንዱ በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ የወጣቱን ውክልና በመያዝ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች ሲያከናውን ነበር። አሁንም በማከናወን ላይ ይገኛል። በ1997 ዓ.ም ላይ በነበረ ግርግር ታስረው ወደ ዴዴሳና ወደተለያዩ ቦታዎች የተወሰዱ ወጣቶችን ጉዳይ ማህበሩ ቦታው ድረስ በመሄድ ጉብኝት አድርጎ ነበር። በጉብኝቱ የተስተዋሉ ችግሮችን በመለየት የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ደግሞ አገሪቱ ወራሪ ሀይል ስለመጣባት ወጣቱ ተሳትፎ እንዲያደርግ በተደረገ ዘመቻ የማህበሩ አባላት እስከ አመራር ድረስ ተሳትፎ አድርገው ነበር። በዚህም መስዋዕትነት የከፈሉ አመራሮችና አባላት አሉ።
አዲስ ዘመን፡- በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የአዲስ አበባ ወጣት ማህበር ምን ስራዎች እያከናወነ ነው? ምንስ ለማከናወን አቅዷል?
ወጣት ይሁነኝ፡- የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አላማዬ ብሎ ከያዛቸው ጉዳዮች ውስጥ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለተካዊ ጉዳዮች ይገኙበታል። የፖለቲካ ጉዳይ ሲባል ምንድነው እንደ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ምን ያደርጋል ለሚለው ማህበሩ እንደ ሲቪክ ተቋምነቱ ሲመሰረት የያዛቸውን ህግና ደንቦች መሰረት በማድረግ በየጊዜው የሚታደስ ፈቃድ ያለው ማህበር ነው። ችግር ካለ የሚጠየቅበት አሰራርና አካሄድ ያለውም ነው። ፈቃድ ሲሰጠው እንዲሰራቸው ከተሰጡት ተግባራት ውስጥ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ይገኛል። ማህበሩ በመደበኛ ወቅቶች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰራቸው ነገሮች የሉም።
የምርጫ ወቅቶች ላይ ማህበሩ ሰፊ የሆነ እንቅስቃሴ የሚደርግበት ወቅት ነው። በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት ላይ የሚደረጉ ምርጫዎች ትልቅ የሆነ ለውጥ የሚያመጡ ናቸው። ሌሎች የአፍሪካ አገራትን እያዩ እንደምንሰጋው ነገር አይደለም። ከዚህ ባሻገር ጥሩ እድልና በትክክለናው መንገድ ከተካሄደ አገሪቷ ወደ ተሻለ ሁኔታ የምታድግበት፣ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር የሚቀራረብበት እንዲሁም የተመረጠው አካል የሚያስተዳድር ከሆነ በልማትና በመልካም አስተዳደር ውስጥ ተሳትፎ እያደረገ የምታድግና ውጤታማ አገር የምትሆንበት እድል የሚፈጠርበት ስለሆነ ምርጫ ላይ ልዩ ትኩረት ይሰጣል።
በምርጫ ወቅት ማህበሩ ያለው ሚና ቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ የሚኖር ነው። በቅድመ ምርጫ ወቅት መራጮችን የመቀስቀስ፣ ስለምርጫ ስልጠና መስጠት፣ መራጮች ካርድ እንዲያወጡ ማድረግ፣ የክርክር መድረኮችን ማመቻቸት፣ መረጃዎችን መስጠት የተጓደሉ ክፍተቶች የሚታዩ ከሆነ ከምርጫ ቦርድና ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር እንዲስተካከሉ የማድረግ ስራ ይከናወናል። ይህን ወደ ወጣቱ ሲመጣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቱ ላይ የያዙትን አላማና እቅድ ወጣቱ ተረድቶት በፍላጎትና የእኔ የሚለውን ሰው ሳይሆን መምረጥ የሚገባ በትክክል የወጣቱን ችግር ሊፈታ የሚችል አላማና እቅድ ያለውን ፓርቲ ወይም ተወካይ መምረጥ ይገባል።
ይህን ለመረዳት ፓርቲዎች በራሳቸው መንገድ የሚያቀርቡት እንዳለ ሆኖ ማህበሩ በሚያመቻቸው መድረኮች ፓርቲዎቹ በሚያደርጉት ክርክር እንዲወስን ይደረጋል። በክርክሩ አጀንዳዎችን በመስጠት በአጀንዳው ዙሪያ ተዘጋጅተው ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ ከወጣቱ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በማስተናገድ ፓርቲዎቹ የሚመልሱትን በመመልከት ወጣቱ ይጠቅመኛል የሚለውን በነፃነት እንዲመርጥ ማድረግ ነው። ከዚህ ባለፈ የመኪና ላይ ቅስቀሳ በማድረግ የመራጭነት ካርድ እንዲያወጣ ወጣት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ዴሞክራሲዊ መብቱን ተጠቅሞ ይሆነኛል የሚለውን ፓርቲ እንዲመርጥ ለማድረግ ማህበሩ እየሰራ ነው።
በምርጫው እለት ከምርጫ ቦርድ ከሚሰጥ ፈቃድ ጋር በማያያዝ የታዛቢነት ስራ ማህበሩ ይሰራል። ምርጫው በትክክል መራጮች በተገኙበት ሁኔታ መፈፀሙን፣ መራጮች በነፃነት እየመረጡ ነው ወይ፣ የምርጫ ስርዓቱ አልተስተጓጎለም ወይ፣ የመራጮች የምርጫ ወረቀት በትክክል ገብቷል ወይ የሚለው ጉዳይ በአግባቡ ይታይና ምሽት ላይ ደግሞ የምርጫ ወረቀት ቆጠራ ሲካሄድ በአግባቡ መከናወኑን ይታዘባል። ይህን የሚያደርገው የአዲስ አበባን ወጣቶች ወክሎ ነው። በነዚህ ወቅቶች ችግሮች ካሉ ችግሮቹ እንዲታረሙ በሪፖርት ወይም በመገናኛ ብዙሀን በኩል የማሳወቅ ስራ ያከናውናል። ትክክለኛም ነገር ከተከናወነ በተመሳሳይ ያለውን ሁኔታ ያሳውቃል። ይህን በማድረግ አገሪቱ ወደተሻለ ደረጃ እንድታድግ የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል።
ሌላኛው ስራ ከምርጫ ውጤት መገለፅ በኋላ ወጣቱ እንደ ግለሰብ የመረጠው ፓርቲ ካላሸነፈ ምርጫው ተጭበርብሯል፣ ተስተጓጉሏል ወይም ሌሎች ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ። የምርጫ መጭበርበር በሚል ችግር እንዳይፈጠር የማህበሩ ታዛቢዎች በምርጫው ወቅት የተለያዩ ስራዎች ይሰራሉ። እንዲሁም ሌሎች ሲቪክ ተቋማት በታዛቢነት ስራቸው ላይ አትኩሮት ሊሰጡ ይገባል። እንደ ማህበር ግን በታዛቢነት ወቅት የታዩ ትክክለኛ ነገሮችን ለህዝቡ የማሳወቅ ስራ ያከናውናል። ከምርጫው ውጤት በኋላ በአግባቡ የታዩትን ነገሮች ለሚመለከተው አካልና ለህዝብ ሪፖርት ይደረጋል። የምርጫውን ውጤት ተከትለው የሚመጡ አለመግባባቶችና ግርግሮች ካሉ ደግሞ እንደ ወጣት ተወካይነት ችግሮች የሚፈቱት በውይይት፣ በንግግርና በክርክር እንዲሆኑ ጫና የሚያደርግ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በማህበሩ ስራ ላይ ቀድሞ ከነበሩት ምን የተለየ ነገር ይዞ መጥቷል? ቀደም ተብለው ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችስ ምን ነበሩ?
ወጣት ይሁነኝ፡- ቀደም ብሎ በነበረው ሁኔታ ስለምርጫ ሁሉም ህብረተሰብ የሚያውቃቸው ችግሮች ይፈጠራሉ። ለምሳሌ የኮሮጆ መገልበጥ፣ በነፃነት አለመምረጥ እንዲሁም አንድ ፓርቲ ብቻ እንዲመረጥ በምርጫው ወቅት የሚታዩና የሚያደርጓቸው ተፅዕኖዎች ነበሩ። እነዚህን ችግሮች በየደረጃው ለመፍታት ማህበሩ የማሳወቅ ስራዎችን ሲሰራ ነበር። በደረሰበት ልክም እንዲስተካከል ጫና ፈጥሯል። ቀደም ብሎ ከምርጫ ቦርድ ጋር አሁን እንዳለው ግልፅ በሆነ መንገድ ግንኙነት አይደረግም ነበር። የምርጫ ቦርድ አሰራር ተደራሽ በሆነ ሁኔታ እየሰራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ለውጦች እየተስተዋሉ ሲሆን፤ ለውጡ የሚለካው በውጤት ነው። ከለውጦቹ መካከል ምርጫ ቦርድ በግልፅ ጥሪ በማድረግ ከ30 በላይ ታዛቢ ቡድኖች እንዲሳተፉ አድርጓል።
ይኼ ሁኔታ ቀደም ብሎ ያልነበረ ነው። ሌላኛው መራጮችን የማስተማርና የማንቀሳቀስ ጉዳይ ላይ ብዛት ያላቸው ሲቪክ ተቋማት እንዲሰሩ ተፈቅዷል። የመራጮች ካርድ አልቆ ጣቢያዎች ተዘጉ ለሚሉና ለሌሎች ቅሬታ መቀበያ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ አማራጮችን አስቀምጧል። ይህ እንደ አንድ ለውጥ መታየት ይችላል። ህግና ስርዓት እንዲኖር በግልፅ መራጮች ለመምረጥ ምን ያስፈልጋቸዋል የሚሉ ነገሮች በምርጫ ቦርድ በራሱ መሰራቱ እንደለውጥ መታየት አለበት። በችግር ሊነሱ የሚችሉት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የመራጭነት ካርድ ሳያወጣ ጣቢያዎች ኮታችንን ጨርሰናል መባሉ አግባብ አይደለም። ይህን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑ ከምርጫ ቦርድ ተሰምቷል።
አዲስ ዘመን፡- ከምርጫ ውጤት ጋር ተያይዞ ችግሮች ቢፈጠሩ ማህበሩ ምን ያህል ዝግጅት እያደረገ ነው?
ወጣት ይሁነኝ፡– ከምርጫ በኋላ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል የማህበሩ ሀሳብ ቀድሞ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት መስራት ያስፈልጋል የሚል ነው። ዋነኛው ጉዳይ ከምርጫው በፊት የሚሰሩ ስራዎች አስፈላጊ ናቸው ተብሎ ይታመናል። ከዚህ ውስጥ አንዱ ወጣቶችን ማሰልጠን ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ስልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ። የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት እየተሰራም ነው። በማህበራዊ ሚዲያዎች ሁሉም መረጃዎች እንዲዳረሱ እየተደረገ ነው። ሰው የሚመዘነው በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በአካባቢና በሌላ ጉዳይ ሳይሆን በእቅድ፣ በአላማና ባለው እውቀት ሊመዘን ይገባል።
ይህ ስራ መከናወኑ ወጣቱ የሚመርጠው ሰው ባይመረጥ ሌሎች ያመኑበትን በብዛት መርጠዋል በሚል ውጤቱን እንዲቀበል ያስችለዋል። ወጣቶች ስለምርጫው ሁኔታ ከመገናኛ ብዙሃን እንዲያዳምጡና ክርክሮችን እንዲመለከቱ ከዚህም ውስጥ ይጠቅመናል የሚሉትን በመውሰድ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችን በመለየት ምርጫ ማካሄድ አለባቸው። የመረጥነው አካል ቢሸነፍ ምርጫው ተጭበርብሯል ማለት ሳይሆን ሌሎች ሰዎች በብዛት ለሚፈልጉት ሰጥተዋል ብሎ መቀበል መቻል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጠኸን ማብራሪያ እናመሰግናለሁ።
ወጣት ይሁነኝ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 29/2013