አካላዊ የስነልቦና ችግሮች/ሶማቶፎረም ዲስኦርደርስ/ አካላዊ ችግር የሚመስል ግን አካላዊ ምልክት ወይም ምክንያት የሌለው የሥነ-ልቦና ችግር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በተደጋጋሚ ወደ ህክምና ቦታዎች በመሄድ መፍትሄ እንዳላገኙ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ሰምታችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶችም በህክምና ባለሙያዎች ተስፋ ቆርጠው ከችግራቸው ጋር አብረው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ወደ ውጭ አገር በመሄድ ህክምና ለማግኘት ሊሞክሩ ይችላሉ፡፡
ችግሩ ይህ የአካላዊ የሥነ ልቦና ህመም ከሆነ እንደሚያስቡት አካላዊ ህክምና ችግራቸውን ሊፈታላቸው እንደማይችል ምሁራኖች ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ችግር የ0ተጠቃ ግለሰብ ምንም አይነት አካላዊ ምክንያት ሳይኖረው አካላዊ የህመም ምልክቶች ሲሰማውና በግለሰቡ ሥራ፣ ግንኙነት እና አጠቃላይ ህይወት እንቅፋትን ይፈጥሩበታል፡፡ ይህም ማለት እነዚህ ችግሮች ከታማሚው ግለሰብ ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ናቸው፡፡ በችግሩ የተጠቁ ሰዎች ሜዲካል ህክምና ችግሩን ይቀርፍልናል ብለው መፈለጋቸው ነው፡፡ አካላዊ የሥነ ልቦና ችግሮች አምስት አይነት ናቸው። እነርሱ፡-
1. ፔይን ዲስኦርደር /Pain Disorder/
ከአካላዊ የሥነ ልቦና ችግሮች አንዱ ለሆነው ፔይን ዲስኦርደር ችግር መከሰት፣ መቀጠልና የህመሙ መጠን በዋናነት ሥነ-ልቦናዊ ምክንያቶች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ህመሙ ጉልህ ስቃይና ጉዳት የሚያስከትል ሲሆን በዚህም ምክንያት ግለሰቡ ሥራ መስራት እንዳይችልና በማስታገሻ መድሃኒቶች ጥገኛ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ይህን አይነቱን ችግር በህክምና ምርመራ አድርጎ ለህመሙ መፍትሄ ለማግኘት በራሱ ፈታኝ ነው። ሂደቱን አዳጋች የሚያደርገው ደግሞ ግለሰቦች የሚሰማቸው ህመምን ለነሱ ብቻ የሚሰማቸው/ ግላዊ/ ስለሆነ ለመለካት ራሱ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
ግለሰቦቹ አካላዊ ህመም እንዳለበት ሰው የሚሰማውን ህመም ቦታና ምክንያቶችን እንዲያብራራው ሳይሆን በተለየ መልኩ ነው ችግራቸውን የሚገልፁት፤ ይህም ችግሩን በደንብ ለመረዳት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ችግር የተጠቁ ሰዎች በሚሰማቸው ህመም ምክንያት ሥራቸውን ለመስራት የሚቸገሩና፤ ለተለያዩ ቤተሰባዊና ማህበራዊ ችግሮች እንደሚጋለጡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
ሌላው ችግር ህመሙን ለማወቅ ዶክተሮች ብዙ ምርመራዎችን ማካሄድ ስላለባቸው በቀላሉ ችግሩን ለታማሚዎች መግለፅ ስለሚከብድ ታካሚዎች ቅር ይሰኛሉ። ስለዚህ የህመሙን ሥነ-ልቦናዊ ምክንያት መረዳት አስፈላጊና ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላል፡፡ በዚህ የሥነ-ልቦና ህመም ግለሰቦች ተጠቅተዋል ለማለት የሚከተሉት አራት መስፈርቶች ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።
– ህመሙ አደገኛ ስለሆነ የስነ-ልቦናና የሳይካቲክ ትኩረት ይሻል፣
– ለህመሙ መነሻ፣ አደገኛነትና ቀጣይነት የስነ-ልቦና ምክንያቶች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፣
– ህመሙ በግለሰቡ ሆን ተብሎ የተፈጠረ ወይም እንደማታለያ ታስቦ የሚፈጠር አይደለም፣
– ህመሙ በሌሎች ሥነ-ልቦናዊ ሁኔታዎች/ችግሮች የሚገለፅ አይደለም፡፡
2. ቦዲ ዳይስሞረፊክ_ዲሰኦርደር /Body Dysmorphic Disorder/
የቦዲ ዳይስሞርፊክ ችግር ያለባቸው ሰዎች በአካላዊ ገፅታቸው የሆነ የተጋነነ ችግር እንዳለ በማሰብ የሚብሰለሰሉና የሚጨናነቁ ሰዎቸ ናቸው። ምንም እንኳን ለሰዎች ማራኪ ገፅታ እንዳላቸው ቢታወቅም እራሳቸውን የሚገነዘቡት አስቀያሚና አስፈሪ ገፅታ እንዳላቸው ነው፡፡ ሴቶች ቆዳቸውን፣ ዳሌያቸውን፣ ጡቶቻቸውን እና እግራቸው ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ሲሆን ወንዶች ደግሞ ቁመታቸውን የብልት መጠን እና የሰውነት ፀጉር በተለይ የደረት ፀጉር ላይ ትኩረት በማድረግ ይጨናነቃሉ፡፡
አንዳንድ የዚህ ችግር ያለባቸው ሰዎች መስታወት ላይ አካላዊ ምስላቸውን በመመልከት ችግሩ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ በቀን ለብዙ ሰዓታትን ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የሚያስቡትን አካላዊ ችግር ያሳየኛል ስለሚሉ መስታወት አጠገባቸው እንዲኖር አይፈልጉም። አሊያም ችግሩን ይሸፍናል ብለው የሚያስቡትን አልባሳት መልበስ ሊያዘወትሩ ይችላሉ፡፡ ጥቂቶችም የሚያስቡት ችግሩን ሰዎች ያዩብኛል ስለሚሉ ውጭ ከመውጣት ተቆጥበው በቤት ውስጥ ተወስነው ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡
በዚህ የሥነ-ልቦና ችግር ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን በጥናታቸው እንዳረጋገጡት ለህመምተኞች የህመማቸው ምልክቶች በጣም የሚያስጨንቅና የሚያሳዝን ስለሚሆን ከብዙዎች ጥቂቶች እራስን ስለማጥፋት አስበው እንደሚያውቁና ሌሎች ደግሞ ቀላል የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና እንዳካሄዱ ተናግረዋል፡፡ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገናው ክፋቱ ችግሩን ሙሉ በሙሉ መቅረፍ አለማቻሉ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ በተደረገላቸው ቀዶ ጥገና ቅር ስለሚሰኙ ቀዶ ጥገናውን ያካሔደላቸውን ሐኪሞችን መክሰስና መጉዳት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ በዚህ የሥነ-ልቦና ህመም ግለሰቦች ተጠቅተዋል ለማለት የሚከተሉት ሁለት መስፈርቶች ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
– ከሚገባው በላይ በአካላቸው ገፅታ ላይ ለሚገኝ ትንሽ ጉድፍ በጣም በመጨናነቅ ወይም በሌለ ችግር በአዕምሯቸው ችግሩ እንዳለባቸው በማሰብ የሚብሰለሰሉ ከሆነ
– የሚበሰለሰሉበት ጉዳይ በሌላ የሥነ ልቦና ችግር ለምሳሌ በአመጋገብ ችግር በሚመጣ የሰውነት መጎሳቆል ምክንያት የማይገለፅ ከሆነ
3. ሃይፖኮንድራሲሲ /Hypochondriasis/
ሌላኛው ከአካላዊ የሥነ ልቦና ችግሮች /የሶማቶፎረም/ አይነት ደግሞ ሃይፖኮንድራሲሲ የሚባል ሲሆን ዋነኛ መገለጫው አደገኛ በሽታ ይይዘኛል በሚል በፍርሃት መብሰልሰል እና መጨናነቅ ነው፡፡ የአሜሪካ የሳካተሪስት ማህበር ባሳተመው የአዕምሮ ጤና ችግሮች የሚገልፀው መመሪያ /DSM criteria for diagnosis/ ይህን የስነልቦና ችግር የሚገልፀው በሽታ ይይዘኛል የሚል ከፍተኛ ፍርሃት ነው።
ችግሩ በህክምና እንደሌለ ቢረጋገጥም እንኳን ፍርሃቱ በጥቂቱ ለስድስት ወራት የሚቆይ ከሆነ ነው፡፡ የሃይፖኮንድራሲሲ ችግር በዋናነት የሚጀምረው በመጀመሪያው የጎልማሳነት የእድገት ወቅት ሲሆን እየቆየ ከሄደ ስር ሰደድ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በሽታ ከሌሎች የሚለየው ህመምተኞቹ እያንዳንዷን ነገር የአደገኛ በሽታ ምልክት እንደሆነች በማሰብ መጨናነቃቸው ነው፡፡
በዚህ የስነልቦና ህመም ግለሰቦች ተጠቅተዋል ለማለት የሚከተሉት መስፈርቶች ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
– አደገኛ በሽታ ይይዘኝ ይሆን የሚል ፍርሃት የተሞላበት መብሰልሰል
– በሚያስቡት በሽታ እንደሌለ የህክምና ማረጋገጫ ቢሰጣቸውም ጭንቀታቸው የሚቀጥል ከሆነ.
– በአስታሳሰብ መዛባት ወይም በቦዲዳይስሞርፊክ ችግር የማይገለፅ ነው፡፡
4. ሶማታይዜሽን_ዲስኦርደር /Somatization disorder/
ይህኛው የህመም አይነት ደግሞ እንደማንኛውም የሶማቶፎረም ህመም ምንም አይነት አካላዊ የበሽታ ምክንያት እንደሌለው ይነገራል’። ነገር ግን ከሌሎች የሚለየው የህመም ቅሬታዎች ብዙ መሆናቸውና ተደጋግመው የሚነሱ የአካላዊ ህመም እንዳለ ግለሰቦች ማመልከታቸውና ህክምና እንዲፈልጉ ምክንያት መሆኑ ነው፡፡
የዚህ ችግር ተጠቂዎች በተደጋጋሚ ወደ ሐኪሞች የሚሄዱና በእያንዳንዱ ምልክቶች የተለያዩ ሐኪሞች ጋር የተለያየ ህክምና ለማግኘት መሄድ የሚያዘወትሩ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ጊዜ ችግራቸውን የቆየና ውስብስብ እንደሆነ በስሜትና በተጋነነ መልኩ ይገልፃሉ፡፡
በዚህ የሥነ ልቦና ህመም ግለሰቦች ተጠቅተዋል ለማለት የሚከተሉት መስፈርቶች ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
– ከ30 ዓመት እድሜ በፊት የጀመረ ብዙ የአካላዊ ህመም ቅሬታዎችና ህክምና የመፈለግ ከነበሩና ችግሮቹ ለብዙ ዓመታት የቆዩ ከሆኑ
– በጥቂቱ አራት የህመም ምልክቶች አንዲሁም ሁለት የአንጀት ህመም ምልክቶች፣ አንድ የወሲብ ችግር ምልክት እና አንድ የነርቭ ህመም የሚመስል ግን ያልሆነ ምልክት በህመምተኞቹ ከተገለፁ፤
– በህክምና ሁኔታ ያልተከሰቱ የህመም ምልክቶች ከሆኑ አሊያም ህክምና የሚዳርጉ የህመም ምልክቶች ከሆኑ ምልክቶች ሆን ተብለው የተፈጠሩ አይደሉም።
5. ኮንቨርሽን ዲስኦርደር /Conversion Disorder/
የኮንቨርሽን ዲስኦርደር ችግር በስሜት ህዋሳት ላይ አሊያም በጡንቻዎች ላይ በድንገት የሚጀምር እክል ሲሆን፤ በድንገት አለማየትና ፓራላይዝ መሆን እንደምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ምልክቶቹ ከነርቭ መጎዳት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ቢመስሉም የህክምና ምርመራ ግን በነርቭ ስርዓት እና በአካል ክፍሎች ምንም ችግር እንደሌለና በመልካም ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ነው፡፡ ግለሰቦች በከፊል አሊያም ሙሉ በሙሉ በእጆቻቸውና በእግሮቻቸው ላይ ፓራላይዝ ሊገጥማቸው የሚችል ሲሆን የመውደቅና እንደልብ ማንቀሳቀስ አለመቻል፣ በሰውነት ቆዳቸው ላይ የመቧጨር፣ የመደንዘዝ እና የመጨማደድ ስሜት መሰማት ይጠቀሳሉ።
ይህም አንስቴዥያ ተብሎ ይጠራል፡፡ የሚፈጥረው ጉዳትም እይታን በጣም ሊጎዳ የሚችል ሲሆን፤ ግለሰቡ በከፊል አሊያም ሙሉ በሙሉ ማየት ሊሳነው የሚችል መሆኑ ጉዳቱን ከፍ ያደርገዋል። በተጨማሪም ተነል ቪዥን /tunnel vision/ አሊያም አፎንያ /Aphonia/ ድምፅ ማውጣት ሊሳናቸው ይችላል፡፡ ማሽተትም ሊሳናቸው ይችላል ይህም ሁኔታ አኖስሚያ ይባላል፡፡
በዚህ የሥነ ልቦና ህመም ግለሰቦች ተጠቅተዋል ለማለት የሚከተሉት መስፈርቶች ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
– አንዱ ወይም ብዙ ምልክቶች የስሜት ህዋሳትን ተግባር እና ጡንቻዎችን ተግባር ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የነርቭ በሽታ አሊያም ሌላ የህክምና ሁኔታን የሚያመላክት የሚመስሉ ከሆነ፤
– ከጭንቀትና ከግጭት ጋር የተያያዙ ምልክቶች ናቸው።
– ምልክቶች ሆን ተብለው ያልተፈጠሩ እና በህመም የማይገለፁ ናቸው።
– ምልክቶች ጉልህ ጭንቀትና ጉዳት ያስከትላሉ። ምንጭ፦ ስለ ጤናዎ ምን ያውቃሉ ድረገጽ
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2013