አሁን ላይ ዓለም በዘመነ ግሎባላይዜሽን ወደ አንድ መንደር እየጠበበች ባለችበት ወቅት ከሁሉም በላይ ዲጂታል ዲፕሎማሲ እያሳደረ ያለው ትልቅ ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘመኑ የሚጠይቀውን ፈጣን መረጃ በአንድ ጊዜ በተመሳሳይ ሰዓት ለሁሉም የዓለም ሀገራት በማዳረስ ሀገራትን በመረጃ እያስተሳሰረ ያለበት ዘመን ላይ ደርሰናል ፡፡ በዚህም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዲፕሎማሲ በብዙ መልኩ በዘመናዊ የመገናኛ ዘዴ በተለይ ደግሞ የሳይበር ዓለም ተጽዕኖ እየደረሰበት ወይም አዲሱን የመገናኛ ዘዴ እየተጠቀመ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። የዓለም ሀገራት ይህንን ተጽዕኖ ለመመከት የሚያስችል ስትራቴጂ በመቀየስ ዲጅታል ዲፕሎማሲውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየሰሩ መሆኑን በርካታ አመላካቾች አሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የሳይበር ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚታየው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርና ለውጥ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን፤ አገራት የዚህ ቴክኖሎጂ ጥገኛ የመሆናቸው ሂደትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የሳይበሩ ዓለም መረጃን በፍጥነት ወደ ህዝቡ ለማድረስ ዓይነተኛ መሳሪያ በመሆኑ ዜጎች የሀገራቸውን ማናቸውም የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የትም ሆነ የት ባሉበት ሆነው እንዲከታተሉ ዕድልን የሚሰጥ ነው። በተለይ የማህበራዊ ሚዲያው ዘርፍ የዲጅታል ዲፕሎማሲው በእጅጉ እንዲስፋፋ አድርጓል።
ከዚህ አንጻር ውጤታማ ዲጅታል ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እያከናወኑ ከሚገኙ የዓለም አገራት ውስጥ ግንባር ቀደም ከሆኑት መካከል አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጃፓን፣ ሲንጋፖር፣ ስዊድን፣ ኒውዝላንድ፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ስፔን፣ ኖርዌይና ሩስያ ተጠቃሾች ናቸው ፡፡
በዲጅታል ዲፕሎማሲ ዙሪያ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው በርካታ ሀገራት ለመስኩ ትኩረት በመስጠት ዲጂታል ዲፕሎማሲ ይዞት የመጣውን ዕድል እና መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም በከፍተኛ ደረጃ በጀት በመመደብ፣ የሰው ኃይል በማሰልጠን እና በማሰማራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርገው በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፡፡
ለአብነት ካናዳን ብንመለከት፤ ካናዳ የዲጂታል ዲፕሎማሲን እና የዲፕሎማቶቿን የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ በተመለከተ “የተግባቦት ፖሊሲ (Communications Policy)”፣ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን የሚወስኑ የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ አስተዳደር ደረጃ እና የኦፊሴላዊ ማህበራዊ ሚዲያ ገጽ አጠቃቀም መመሪያ የሚሉ ተጨማሪ ሰነዶችን በማዘጋጀት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
እነዚህ ሰነዶችም የካናዳ መንግሥት የሀገር ውስጥ ተቋማትንም ሆነ የሚሲዮኖችን የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ይቃኛሉ። ካናዳውያን ዲፕሎማቶች ካናዳን ወክለው በማህበራዊ ሚዲያ መንግሥት ያወጣቸውን መመሪያዎች ተከትለው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ የተደነገገበት ሁኔታ መኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡
ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ደግሞ ግብፅ ዲጅታል ዲፕሎማሲው ግንባር ቀደም ተጠቃሚ ናት፡፡ ግብፅ በአረቡ ዓለም ቀዳሚ የፌስቡክ ተጠቃሚ ቁጥር ያላት አገር ስትሆን በካቢኔ ደረጃ የፌስቡክ ሚኒስትር ለማዋቀር ጥረት እያደረገች መሆኗን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡የግብጽ የዲጅታል ዲፕሎማሲ በዋናው መስሪያ ቤት እና በሚሲዮኖች የሚከወን ነው።
የግብጽ ዲፕሎማቶች የግለሰብ የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ቢኖራቸውም ከራሳቸው ግለሰባዊ ጉዳይ በዘለለ ምንም ዓይነት አስተያየት አይሰጡም። በሌሎች አካላት የተጻፉ መንግሥት ነክም ሆነ የውጭ ጉዳይ ነክ ጉዳዮችን አያጋሩም እንዲሁም የውደድ (like) ምልክትን በመጫን መውደዳቸውን አያሳውቁም።
በሌላ በኩል ሌላኛዋን አፍሪካዊት አገር ኬንያን ስንመለከት ደግሞ ኬንያ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ የሚመለከት መመሪያ (directive) አዘጋጅታ ተግባራዊ አድርጋለች። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ ሚኒስትር እና አምባሳደሮች ኦፊሴላዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ያላቸው ሲሆን፤ እንደየኃላፊነታቸው እና የሥራ ድርሻቸው በገጻቸው ሃሳቦችን ሊያሰፍሩ ይችላሉ።
ዲፕሎማቶች የራሳቸው የማህበራዊ ሚዲያ (ፌስቡክም ሆነ ቲዊተር) ገጽ መክፈት የሚፈቀድላቸው ሲሆን፤ በማናቸውም መልኩ ግን የሀገሪቱን የውስጥም ሆነ የውጭ ጉዳዮች በተመለከተ አስተያየት መስጠትም ሆነ ሃሳብን ማንጸባረቅ አይችሉም። በከፈቱት የግለሰብ ገጽ የራሳቸውን ግለሰባዊ ጉዳይ ሊያጋሩ ግን ይችላሉ። ይህ ሲሆን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሂደቱን ይከታተላል።
የእነዚህ አገሮች ተሞክሮ በተጨባጭ የሚያሳየን አሁን ባለው የዓለም ስርዓት የዲፕሎማሲ ሥራ በዲጂታል ዘርፍ ሊታገዝ እንደሚገባ ነው። በዚህ ረገድ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የዲጂታል ዲፕሎማሲ የራሱ የሆኑ ተግዳሮቶች እና አደጋዎችም ያሉት መሆኑ ነው።
የመረጃ የማሽሎክ (leak)፣ የመረጃ ስርቆት፣ የመረጃ-ገጽ ጠለፋ(hacking)፣ የገጽ ማስመሰል እና ስም አልቤነት(anonymity) ተጠቃሸ አደጋዎች ናቸው። በተለይ ገጽን በማስመሰል እና በስምአልቤዎች እንቅስቃሴ የአንድን ዲፕሎማት ወይም ሚሲዮን ስም እና ፎቶ ተጠቅሞ የውሸት ገጾችን (fake accounts) በመፍጠር መረጃዎችን የማሽሎክ እንዲሁም የተሳሳተ መረጃ የማሰራጨት ወ.ዘ.ተ. ድርጊቶች የዲጂታል ዲፕሎማሲ ፈተናዎች ናቸው። ስለሆነም የዲጂታል ዲፕሎማሲ ሥራ፣ አጠቃቀምና አስተዳደር በስርዓት እና በአሰራር እንዲመራ ማድረግ ተገቢና ጠቀሜታውን የትየለሌ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የስማርት ስልኮች እና የኢንተርኔት ተደራሽነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ይህንን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የሚፈፀሙ ወንጀሎችም ድንበር ሳያግደው በየትኛውም ቦታ የመከሰት እድሉ ሰፊ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ በዚህም የማህበራዊ ትስስር ድህረገፆች (ሶሻል ሚዲያ) ተጠቃሚዎች ቁጥር ካለው ስፋት አንፃር እነዚህን ገፆች በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎች ለምሳሌ የአመፅ እና የጥላቻ ቅስቀሳ ፣ ለሽብር አገልግሎት የሚሆኑ ግለሰቦችን ለመመልምል፣ ለማሰልጠን ፣ መረጃዎችን ለመለዋወጥ እየዋለ እንደሚገኝም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ስለሆነም ሀገራት በዲፕሎማሲ መስክ የሚሰሩትን ሥራ ዲጂታል ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆን አለበት፡፡ የዲፕሎማቶች ሥራ ሀገርን፣ መንግሥትን እና ህዝብን በመወከል ግንኙነቶችን በማድረግ የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም፤ ነገር ግን በሀገራችን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው ወጥ እና ገዥ መመሪያ ወይም ደንብ የተዘጋጀ ባለመሆኑ አጠቃቀሙ አልፎ አልፎ በዘፈቀደ የተሞላ፣ ኃላፊነት የጎደለው እንዲሁም ከዲፕሎማቶች የማይጠበቁ ቃላቶችን እና አስተያየቶችን የያዘ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
አንድ ዲፕሎማት ሀገር ወክሎ እስከተገኘ ድረስ በማናቸውም ሁኔታና ጊዜ የሀገሩን ሁኔታ በተመለከተ የሚያስተላልፈው መልዕክት ሀገርን የተመለከተ ነው መሆኑ ያለበት፡፡ሀገር የሰጠችውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት የሀገሩን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነቷን ማስከበር ላይ አትኩሮ መስራት ይጠበቅበታል ። በተለይ በውጭ ለሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በሀገሪቱ ያለውን ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ላይ ያተኮረ ሥራ መስራት አለባቸው ፡፡ ሀገራችን በዲጅታል ዲፕሎማሲው ረገድ በርካታ የቤት ሥራዎችን መስራት እንደሚጠበቅባትም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2013