መልካም መዓዛ ያለው ሽቶ ለራሳችን ስናርከፈክፍ መልካም መዓዛው በአካባቢያችን ለሚገኙ ሰዎች ጭምር የሚተርፍ የይሆናል።መልካም ሥራ መስራትም ከራስ አልፎ ቤተሰብን፣ አካባቢንና ሀገርን እንዲሁም ዓለምን መቀየር ይችላል። ዓለምን መቀየር የቻሉ በርካታ ሰዎችም በየዘመናቱ ተፈጥረው ስለማለፋቸው ታሪክ ምስክር ነው።ባለንበት ዘመንም በየዘርፉ ጥልቅና ዕምቅ ዕውቀት፤ የተለየና ሁሉን አቀፍ አስተሳሰብ ያላቸው ዕልፍ አዕላፍ ሰዎች ተፈጥረዋል።ከእነዚህም መካከል በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክልል የሚገኘው የአውራምባ ማህበረሰብ አንዱ ነው።
የአውራምባ ማህበረሰብ ላለፉት በርካታ ዓመታት በሚያራምደው አስተሳሰብ፣ በባህሉና በዕሴቱ ምክንያት ከአካባቢው ማህበረሰብ ተገልሎ የቆየና ብዙ መከራ፣ ስደትና እንግልት የደረሰበት ማህበረሰብ ነው።ይሁንና በአሁnu ወቅት ሁሉን አቀፍ በሆነውና ሰው ሁሉ አንድ ነው ብሎ ማመኑን የደገፉ፤ መረዳዳትና መደጋገፍን ያደነቁ ዕልፍ ተከታዮችን ማፍራት የቻለ ከመሆኑም በላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ችሏል።
የአውራምባ ማህበረሰብ፤ የማህበር አባልና የማህበረሰብ አባል በመባል በሁለት የሚከፈል ሲሆን፤ የማህበር አባል ማለት በቦታው ላይ ተገኝቶ ማህበሩ የሚሰራቸውን ሥራዎች ከአባላቱ ጋር በጋራ በመሆን ቡድን መሪው የሚሰጠውን የሥራ አቅጣጫ ተከትሎ የሚሰራና ከማህበሩ የሚገኘውን ትርፍም በየአመቱ የሚካፈል ነው። የማህበረሰብ አባል ማለት ደግሞ በየትኛውም ቦታ የሚኖር ነገር ግን የማህበረሰቡን ባህልና እሴት አምኖ በመቀበል ተግባራዊ የሚያደርግ ሀሳቡን የሚደግፍ ማለት ሲሆን፤ ኢኮኖሚያዊ ገቢውን ከማህበሩ ውጭ በሆነ የራሱን ሥራ ሰርቶ የሚያገኝና በየትኛውም ዓለም የሚኖር ማንኛውም ሰው ማለት ነው።
እኛም በዛሬው የስኬት አምዳችን የአውራምባ ማህበርን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ በመዳሰስ ማህበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸውንና እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን እንዲሁም የተነሳበትን እና የደረሰበትን የኢኮኖሚ አቅምና ስኬታማነት በዝርዝር በመመልከት ለሌሎች ተሞክሮ ይሆናል በማለት እንዲህ አሰናድተን አቅርበናል፡፡
የአውራአምባ ማህበረሰብ የገበሬዎች፣ ዕደጥበባትና ሁለገብ ህብረት ሥራ ማህበር፤ ተባብሮ መስራትን መሰረት ያደረገና በጥቂት አቅም ባላቸው ሰዎች በርካታ ደካሞችን በመተጋገዝ ሸፍኖ መስራትን ዓላማው ያደረገና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግርን ለመፍታት የተቋቋመ ማህበር ነው። የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘየነው ዓለሙ፤ የማህበሩ አባላት በሙሉ እንደየ አቅሙና እንደየ ችሎታው የሚሰራበትና እኩል ተከፋይ የሚሆንበት ማህበር እንደሆነ ሲያስረዱ አቅም ያለው አቅም ለሌለው ድጋፍ በመሆን በመረዳዳትና በመተጋጋዝ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት ነው።ኢኮኖሚያዊ ለውጡም ሁሉን የሚያቅፍና እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የአውራምባ ማህበረሰብ ከተመሰረተበት 1964 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፎ በ1978 ዓ.ም ማህበሩ በመቋቋሙ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘየነው ይጠቅሳሉ።ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ የሚሆንበትን ሥርዓት በማስቀረት በጋራ ሰርቶ በእኩል መንገድ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ማህበሩ እየሰራ ይገኛል።በዚህም የማይሞከሩ የሚመስሉ ሥራዎችን በመስራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
ማህበሩ 77 ወንድ እና 97 ሴት በድምሩ 175 አባላትን ያቀፈ ሲሆን የማህበሩ አባላት በሙሉ መብታቸው ተጠብቆ ጠንካራማ ደካማውን በማገዝና በመረዳዳት ይሰራል።በማህበሩ ከሚሰራቸው ወይም አምርቶና ሸምቶ ለገበያ ከሚያቀርባቸው ግብዓቶች መካከል ንጹህ የኑግ ዘይት፣ የተለያዩ የባህል አልባሳት፣ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማርባት እንቁላል በስፋት ለገበያ ያቀርባሉ፣ ክሊኒክ፣ የልብስ ስፌት፣ የእህል መጋዘን፣ እህል ወፍጮ ቤት፣ ከብቶች ማደለብ፣ ባልትና መለስተኛ ሆቴል እንዲሁም የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶችን ለአካባቢው ማህበረሰብ ያቀርባሉ።
ከአካባቢው ማህበረሰብ ውጭም እንዲሁ በተለይም የኑግ ዘይት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ማለትም ጀሞ አንድ አካባቢና ሳሊተምህረት አካባቢ ባላቸው ሁለት የመሸጫ ሱቆች በተለይም የኑግ ዘይት እና የባልትና ውጤቶችን በስፋት ለገበያ ያቀርባሉ።ከዚህ በተጨማሪም በሽመና የሚያመርቷቸውን አልባሳት በአካባቢያቸው የሚሸጡ ሲሆን ወደ አዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች በትዕዛዝ ያቀርባሉ።በተለያዩ ጊዜዎችም በሚዘጋጁ ባዛሮች ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም ይዘው ይቀርባሉ።በአሁኑ ወቅት እያጋጠማቸው ባለው የምርት እጥረት በሙሉ አቅም ማምረት ባይችሉም የኑግ ዘይት በቀን ሶስት ሺ ሊትር በማምረት ለገበያ ያቀርባሉ።
ማህበሩ በፈጠረው ሥራ የአካባቢውን ማህበረሰብ ማገልገል እና አባላቱንም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በመቅረፍ ረገድም የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ከዚህም ባለፈ የሰው ልጅ የሆነ ፍጥረት ሁሉ የማህበሩን የሥራ ባህል በመውረስ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጣቃሚ በመሆን አካባቢውን መቀየር የሚችልበት መንገድ እንደሆነ በማመን ለሌሎች አርዓያ ለመሆን ይሰራል።ሁሉም ሰው የማህበሩን ዓላማ ተረድቶ በቅን ልቦና በእኩልነት አስተሳሰብ ተረዳድቶ ቢሰራ በቀላሉ ማደግና መለወጥ እንደሚቻል የማህበረሰቡ ጥልቅ እምነት ነው።
አባላቱ በየዘርፉ ተሳትፈው ከሚሰሩት ሥራ በተጨማሪ የራሳቸውን ሥራም እየሰሩ የሚያገኙት ገቢ እንዳለ ሆኖ በየዓመቱ ከማህበሩ የሚገኘው ገቢ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆነው ታስቦ የተጣራ ትርፍ ለእያንዳንዱ አባላት እኩል ክፍፍል ይደረጋል።በዚህም አባላቱ ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን በመፍታት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።130 ሺ ብር መነሻ ካፒታል ይዞ የተነሳው የአውራምባ ማህበር በ2000 ዓ.ም እንደ አዲስ እውቅና ካገኘበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ 12 ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺ ብር ካፒታል ማፍራት ችሏል።
ማህበሩ ከሚያገኛው ገቢም የተጣራ ትርፍ ለአባላቱ በማከፋፈል እኩል ተጠቃሚ ያደርጋል።ለአብነትም በዘንድሮ ዓመት ብቻ ሶስት ሚሊዮን 553 ሺ 975 ብር የተጣራ ትርፍ ያገኘው ማህበሩ ለአባላቱ እኩል በማካፈል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።
ማህበራዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አንጻርም የአውራአምባ ማህበር አባላት ሰፋፊ መሰረተ ልማቶችን ሰርቷል።ለአብነትም ከማህበሩ በተገኘ ገቢ የተለያዩ የመሰረተ ልማቶችን በማሟላት ማህበረሰቡን እያገለገሉ ይገኛሉ።ለአብነትም ከ80 በመቶ የሚበልጠውን ወጪ የአውራምባ ማህበረሰብ ባደረገው ተሳትፎ በአካባቢው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገንብቷል።በተጨማሪም 15 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለ ሁለት ፎቅ የመሰናዶ ትምህርት ቤት በራሳቸው ተነሳሽነት አጠቃላይ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ግንባታ ተገንብቷል።ከአጠቃላይ የግንባታ ወጪው 50 በመቶ የሚሆነውም በአውራምባ ማህበረሰብ የተሸፈነና ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ ከትምህርት ቢሮና ከአካባቢው ማህበረሰብ በተገኘ ወጪ የተሰራ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የጤና ችግር እና በዕድሜ መግፋት አቅም ያነሳቸውና እራሳቸውን መምራት ላልቻሉ የማህበረሰቡ አባላት ምግብ መጠለያና መሰል አገልግሎቶችን በመስጠት ይንከባከባሉ። ከአባላቱ ውጭ ለሆኑ የማህበረሰቡ አካላትም እንዲሁ ባላቸው አቅም ሁሉ ድጋፍ ያደርጋሉ።አገራዊ በሆኑ ጉዳች ላይም ማህበሩ ያለውን ሙሉ አቅም በመጠቀም ምላሽ ይሰጣል።ማህበረሰቡ ከራሱ የግል ጥቅም በበለጠ ለወገኑ መድረስን መደጋገፍን ዓላማው አድርጎ የተነሳ በመሆኑ እያንዳንዱ ማህበረሰብ የልማት ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ በማመቻቸት ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥና የሰው ልጅ ሁሉ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ እንዲኖር ይሰራል።
በአውራምባ ማህበረሰብ ውስጥ የወንድ እና የሴት ተብሎ የሚከፋፈል የሥራ ዘርፍ የለም።ሁሉም ሰው እኩል ነው ብሎ የሚያምን አቅምና ችሎታን ብቻ መሰረት አድርጎ ለሥራ የሚሰለፍ ታታሪና ልዩ ማህበረሰብ ነው። በሃሳብ የበላይነትና በችሎታ አምኖ ማንኛውንም ሥራ ሁሉም ሰው ሰርቶ መለወጥ መቻሉን የተገነዘቡ በዙሪያቸው ያሉ በርካታ ሰዎች አሁን ላይ የሥራ ባህላቸውን ተቀብለው የበጎ ተጽዕኗቸው ተካፋይ ሆነዋል።
ማህበረሰቡ ያለው መልካም ተሞክሮ ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ በመሆኑ አንድነትን፣ ሰላምን፣ መተጋገዝንና በጋራ ሰርቶ መለወጥን ያስተምራል።በቀጣይም ዓላማውን በማስቀጠል ሁሉም የሰው ልጅ ለሁሉም የሰው ልጅ አጋር ሆኖ በደረሰበት ቦታ ሁሉ የሚያገኘው ሰው ወንድምና እህቱ እንደሆነ በማሰብ ወገናዊነትን ማጠናከር ነው።
ድንበር የለሹ የአውራምባ ማህበረሰብ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው የመጣውም ከአንድ ሀረግ ነው ብሎ ያምናል።አጠቃላይ ማህበረሰቡም ‹‹ዘር በዛ እንጂ ግንዱ አልተቀየረም›› በሚለው የዙምራ ፍልስፍና ተቃኝቷል። ስለዚህ ሁሉም የሰው ልጅ የዚህ ብሔር የዛ ብሔር ብሎ ሳይል ሁሉም እህት ወንድም ነው ሰው ሊከበርም ሆነ ሊጠላ የሚገባው በአስተሳሰቡ እንጂ በሰውነቱ አይደለም ብሎ ያምናል።እምነትን በተመለከተም ማህበረሰቡ አንድ ፈጣሪ እንዳለ ያምናል።ነገር ግን እምነት መገለጥ ያለበት ሰዎች በሰዎች ላይ በሚሰሩት መልካም ሥራ ነው።ስለዚህ በተግባር የሚታይ መልካም የሆነ በጎ ሥራ በመስራት እምነት ይገለጻል ብለው ያምናሉ።
የአውራምባ ማህበረሰብ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከማህበረሰቡ ይደርስበት በነበረው መገለል ለስደት የተዳረገና በርካታ ውጣ ውረዶችን በማሳለፍ ከቦታ ቦታ ሲሰደድ ኖሯል።ከስደት በኋላ ወደ አካባቢው ሲመለስ ሲያመርትበት የነበረው የእርሻ መሬት በሙሉ ተይዞ ለመኖሪያ ብቻ የሚሆን ቦታ የጠበቀው ሲሆን፤ የማህበረሰቡ መሪ ተብሎ የሚታወቀው ዙምራ ከወንድሞቹ ጋር በመሬት ምክንያት መጋጨት የሌለበት መሆኑን በማመን በግብርና ብቻ አይደለም በኢንዱስትሪም መስራትና ማደግ መለወጥ ይቻላል በሚል አስተሳሰብ የሚያውቀውን የሽመና ሙያ አብረውት ላሉ ተከታዮቹ በማሰልጠን ወደ ሥራ ተሰማርቷል። በዘርፉ የተለያዩ ስልጠናዎችን ማግኘት በመቻላቸውም ሥራውን ማስፋት ችለው ዛሬ ላይ በርካታ ባለሙያዎችን በማፍራት እንዲሁም በኢንዱስትሪው ዘርፍም ተሰማርተው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ስኬታማ መሆን ችለዋል።
በቀጣይም አምስት ዓመትም የአውራምባ ማህበር የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ በዋናነት የጨርቃ ጨርቅና ጋርመንት ፋብሪካ በማቋቋም 500 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ የህንጻ ተቋራጭነት፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍም እንዲሁ ባለሶስት ኮከብ ሆቴል ወረታ ከተማ ላይ ለመገንባት፣ የተለያዩ የግንባታ ዕቃዎችን ለማምረት፣ እንዲሁም አውራምባ ማይክሮ ፋይናንስ የሚል ማህበረሰቡ እየቆጠበ ፋይናንስ አቅማቸውን ይበልጥ የሚያጎለብቱበትን መንገድ ለማመቻቸት አቅደው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።እኛም ይህ ሰፊና ሀገራዊ ዕቅዳቸው እንዲሳካ ተመኘን ሰላም።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2013