በሀገራችን የተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ይከበራሉ። በዓሉን ለማክበርም ልዩ ልዩ የበዓል ማድመቂያ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡ ሰሞኑንም ለፋሲካ በዓልና ለመጪው የሰርግ ወቅት ዝግጅት በአዲስ አበባ ገበያና ግብይት ተጧጡፏል፡፡ በበዓል ሰሞን ከሚሸመቱ ሸቀጦች መካከል የባህል አልባሳት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ወጣቶች እና ጎልማሶች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለበዓል ማድመቂያ የሚሆን የተለያዩ የባህል አልባሳትን በመሸመት ላይ ተጠምደዋል፡፡ የባህል አልባሳት ገበያው ምን ይመስላል የሚለውን ባዛር እና ኤግዚቢሽን በሚካሄድባቸው ቦታዎች ተዘዋውረን ተመልክተናል፡፡
ባዛርና ኤግዚቢሽን እየተካሄደባቸው ካሉ ቦታዎች መካከል ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊት ለፊት የሚገኘው የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ እና ስታዲየም አካባቢ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ዮዲት ይርሳውን ያገኘናቸው የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ባለው ባዛር እና ኤግዚቢሽን ለትንሳኤ በዓል ለልጆቻቸው የባህል ልብስ ሊገዙ መጥተው ነው፡፡
ዘጠኝ ዓመት እና የሶስት ዓመት ልጆች እናት መሆናቸውን የነገሩን ወይዘሮ ዮዲት፤ በኤግዚቢሽኑ ስፍራ ጎራ ያሉት በመንገዱ ሲያልፉ ባዛሩ ቀልባቸውን ስለሳበው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በባዛሩ ላይም ለመግዛት የሚፈልጉትን የተለያዩ አማራጮችን አግኝተዋል፡፡
የዛሬ ወር ገደማ ለልጆቹ የባህል ልብስ ለመግዛት ወደ ሽሮ ሜዳ የባህል ልብስ መሸጫ ሱቆች ሄደው ነበር፡፡ የልብሶቹ ዋጋ ግን በጣም በመወደዱ ሳይገዙ እንደተመለሱ የሚናገሩት ወይዘሮ ዮዲት፤ በባዛሩ ላይ ግን በተመጣጣኝ ዋጋ የልጆቹን ልብስ እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡ ለዘጠኝ ዓመት ልጃቸው በ350 ብር ለሶስት ዓመት ልጃቸው ደግሞ በ200 ብር ልብሶቹን ሸምተዋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት ሽሮ ሜዳ የሚገኙ የባህል አልባሳት መሸጫ በሄዱበት ወቅት አሁን በ350 ብር የገዙትን የባህል ልብስ 800 ብር ተጠርቶ እንደነበር ያስታውሳሉ። በባዛሩ ላይ ግን ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ መኖሩን አስተውለዋል፡፡ ከዋጋ ቅናሹ ባሻገር ባዛሩ አቅራቢያቸው በመሆኑ ለትራንስፖርት የሚያወጡትን ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ መቆጠብ አስችሏቸዋል፡፡
ወይዘሮ አቤ ደምሴ በበዛር እና ኤግዚቢሽኑ የባህል አልባሳትን ይዘው ከቀረቡ ነጋዴዎች አንዷ ናቸው፡፡ በተለያዩ የእድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሚሆን በተለያየ ጥራትና ዋጋ የሚሸጥ የተለያዩ አልባሳትን በተመጣጣኝ ዋጋ ይዘው ቢቀርቡም የአልባሳት ገበያው ቀዝቀዝ ያለ መሆኑን ነው የሚያብራሩት፡፡ የአዋቂ ልብሶችን ከ2000 እስከ 3500 ብር፤ የህጻናትን ደግሞ ከሁለት መቶ ብር ጀምሮ እየሸጡ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ባዛሩ ከብዙዎች ጋር የሚገናኙበት በመሆኑ ከአልባሳት ሽያጭ ከሚያገኙት ገንዘብ ይልቅ ደንበኛ ለመያዝ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አቤ፤አልባሳትን በጣም ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በባህል አልባሳት መሸጫ ሱቆች ውስጥ በ350 ብር የሚሸጡትን የህጻናት አልባሳት በ200 ብር እየሸጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት በተመሳሳይ ባዛር ላይ መሳተፋቸውን የሚያስታውሱት ወይዘሮ አቤ፤ የባህል አልባሳት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በባዛር በ350 እየተሸጡ ያሉ የልጆች ልብሶችን በሁለት መቶ ብር ሲሸጡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የባህል አልባሳት ከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ እንዲኖር ያደረጉ የተለያዩ ምክንያች መኖራቸውንም ይናገራሉ፡፡
አልባሳቱን ለማምረት የሚወጣው ወጪ መጨመሩን ተከትሎ የአልባሳቱ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ፣ የግብዓት ዋጋ መጨመር እንዲሁም የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት የባህላዊ አልባሳት ዋጋ እንዲጨምር ብሎም ገዥ እንዲቀንስ አድርጓል የሚል እምነት አላቸው።በተጨማሪም ከቻይና ተመሳስለው ተሰርተው የሚመጡ ልብሶች በባህል አልባሳት ላይ ከባድ ጫና እያሳደሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም መንግስት የአምራቾችን የግብዓት ችግር መቅረፍ እና ከቻይና በተመሳሳይ መልክ ተመርተው እየመጡ ያሉ አልባሳት ላይ ቁጥጥር በማድረግ የባህል ልብስ ዘርፍ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና መከላከል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2013