እ.አ.አ የካቲት 16 ቀን 2019 ዓ.ም ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ በምትለው ናይጄሪያ ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ እየታዩ ያሉት ግጭቶችና አለመግባባቶች ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ላለመጠናቀቁ ፍንጭ ሰጪዎች መሆናቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ የዴልታ ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ አንድሪው አኒአማካ በሰጡት መረጃ መሰረት ከቀናት በፊት በደቡብ ምስራቅ ናይጄሪያ በሁለት የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት አምስት ሰዎች መገደላቸውን አስታ ውቀዋል፡፡
ሰኞ ዕለት የተገደሉት የኤፒሲ ፓርቲ ደጋፊዎች ዋሪ በተባለች የነዳጅ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ የመኖሪያ ህንጻ ላይ ነው፡፡ ሰዎቹ የተገደሉት በአካባቢው በሚኖርና የተፎካካሪ ፓርቲ ደጋፊ በሆነ አንድ ግልሰብ ሲሆን ግለሰቡ እርምጃውን ሊወስድ የቻለውም በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት በመሀላቸው በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ መሰል ጥቃቶች እንዳይፈጸሙና በተለይም ከቀናት በኋላ የሚደረገው የምርጫ ሂደት በአስተማማኝ ሰላም ውስጥ እንዲከናወን አካባቢውን የማረጋጋት ሥራ እየሠራ እንዳለ አስታውቋል፡፡ ከአምስቱ ሰዎች ግድያ ጋር በተያያዘ ከወንጀለኛው ግለሰብ ጋር ግኝኙነት አላቸው የተባሉ ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉም የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከሆስፒታል አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት አሁን ተፈጠረ ከተባለው ግጭት ቀደም ብሎም ሶስት ሰዎች የሞቱበትና በርካቶችም የቆሰሉበት ግጭት ተከስቶ እንደነበር ገልጾ፣ይህን አስመልክቶ ግን ከፖሊስ ማረጋገጥ እንዳልቻለ አስረድቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የናይጄሪያው የምርጫ ኮሚሽን በመጪው ቅዳሜ በመላ ሀገሪቱ የሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያለምንም ችግር እንደሚከናወን እያሳወቀ ባለበት በዚህ ወቅት ሁለት የምርጫ ኮሚሽኑ ቢሮዎች ከያዙት የምርጫ ቅሳቁስ ጋር በእሳት መጋየታቸውን ሲኤን ኤን ዘግቧል፡፡
የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ከሳምንት በፊት በአቢያ እና ፕላቲዉ ግዛቶች በደረሰው ቃጠሎ ከአሥር ሺህ በላይ የሚሆኑ የምርጫ ካርዶችና ሰባት መቶ ሃምሳ አምስት የድምጽ መስጫ ሳጥኖች መውደማቸውን አሳውቋል፡፡ የናይጄሪያ ምርጫ ኮሚሽን በቃጠሎው ማንንም ተጠያቂ ያላደረገ ሲሆን ቃጠሎው በተፈጸመበት አካባቢ ባሉ አካባቢዎችም ምርጫው በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት እንደሚካሔድ አሳውቋል፡፡
የወደሙ የምርጫ ቁሳቁስን በፍጥነት ለመተካትም እየሠራ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ፈቱስ ኦኮዬ እንደገለጹት ድርጊቱ መራጩን ለማስፈራራት እና የ2019 አጠቃላይ ምርጫን ለማደናቀፍ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ሴራ መሆኑን በመጥቀስ ምንም አይነት ነገር ምርጫውን ሊያስተጓጉለው እንደማይችል ገልጸዋል፡፡
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ከሰሞኑ በናይጄሪያ እየተስተዋለ ያለው ድርጊት በምርጫው ላይ አሉታዊ ጥላ ማጥላቱንና የምርጫው ሂደትና ውጤት መልካም ገጽታ እንደማይኖረው የፖለቲካ ተንታኞች እየተነበዩ ይገኛሉ፡፡ አሜሪካና እንግሊዝ ምርጫውን ለማደናቀፍ በሚሞክሩ፣ ሽብር በሚነዙና ፍትሀዊና ዲሞክራ ሲያዊ የምርጫ ሂደትን በሚጻረሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውና የቪዛ ማዕቀብም እንደሚያደርጉባቸው እያስጠነቀቁ ይገኛሉ፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሀሪ እንደ ገለጹት አንዳንድ የቀድሞ ባለስልጣኖች በሙስና ባካበቱት ገንዘብ መራጮችን በመደለል ድምጽ የመግዛት ዕቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡ እንደእርሳቸው አባባል አሁን በሀገሪቱ ከምርጫው ጋር ተያይዞ እየተከሰተያለው ህገወጥ ተግባርም በእነርሱ አቀነባባሪነት የሚፈጸም ነው፡፡
ቡሀሪ በፌስ ቡክ ገጻቸው እንዳሳወቁት የገንዘብና ኢኮኖሚ ወንጀል ምርመራ ኮሚሽን ግለሰቦች ድምጽ ለመግዛት መራጮችን የሚደልሉበት ብር ምንጩ ከየት እንደሆነ ማጣራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የሰባ ስድስት ዓመቱ ቡሀሪ ዳግም ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ከቀረቡ እጩዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ ዋናው ተቀናቃኛቸውም የሰባ ሁለት ዓመቱ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት አቲኩ አቡበከር ናቸው ፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች በምርጫው ሜዳ ላይ እየጋለቡ ካሉ ተወዳዳሪዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ቢባሉም የመመረጥ ዕድሉ ግን ወደ ቡሀሪ ያመዘነ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ግምታቸውን እያስቀመጡ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም እንደምክንያት ያስቀመጡት ለፕሬዚዳንት ቡሀሪ መንገዶች ሁሉ አልጋ በአልጋ መሆናቸውን ነው፡፡ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ሙሀማዱ ቡሀሪ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ሲያሸንፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በናይጄሪያ ጎዳናዎች ላይ ፈሰው ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡ የቀድሞው ከፍተኛ የጦር መሪ የነበሩት ቡሀሪ በወቅቱ የነበሩትን ጉድላክ ጆናታንን ከሁለት ሚሊዮን በላይ በሆነ ድምጽ ነበር አሸንፈው ወደ ስልጣን የመጡት፡፡
በእስከ ዛሬው የስልጣን ቆይታቸው እምብዛም ያልረኩባቸው አንዳንድ ደጋፊዎቻቸው ግን ከቀናት በኋላ በሚካሔደው ምርጫ ድምጻቸውን ዳግም እንደማይሰጧቸው ይናገራሉ ፡፡ የንግድ ማዕከል በሆነችው ሌጎስ ነዋሪ የሆነው ክርስቶፎር አካንቢ ለአልጀዚራ እንዳስረዳው ‹‹ ቡሀሪ በስልጣን ቆይታቸው ምንም አዲስ ነገር ሲሰሩ አላየሁም እናም በቀጣዩ ምርጫ ድምጼን አልሰጣቸውም፡፡ ባለፈው የምርጫ ወቅት ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼ ሌላው ቀርቶ ተቃዋሚዎችም ጭምር ቡሀሪን እንዲመርጡ ቅስቀሳ አደርጌ ነበር፤ ያም ሆኖ ሁላችንም ዛሬ ላይ በእርሳቸው አመራር ደስተኞች አይደለንም፡፡ ቡሀሪ ሲመረጡ የተናገሩትን ተግባር ላይ ማዋል አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ከእርሳቸው ይልቅ ድምጼን መስጠት የምፈልገው ለአቲኩ አቡበክር ነው›› በማለት ሀሳቡን ለአልጀዚራ አካፍሏል፡፡ ቡሀሪ ዋልተር ኦኖጎሄን ከዳኝነት አመራራቸው አንስተው በምትካቸው ኢብራሂም ታንኮን የሾሙት ከሁለት ሳምንት በፊት ነው፡፡ ይህም ቡሀሪ በፍትህ ሥርዓቱ ጣልቃ ይገባሉ በሚል ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ሲቪክ ማሕበራትን አስቆጥቷል፡፡
የሀገሪቱን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚጎዳ በሚልም በተባበሩት መንግሥታት ተተችተዋል፡፡ ዳኞችን ከሥልጣን የማንሳት ሥልጣን ሊኖረው የሚገባው የፍትህ ሥርዓቱና ፍርድ ቤት ብቻ ሊሆን እንደሚገባም ሙያተኞች አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን በምርጫው ዋዜማ አስቀድሞ በፍትህ ሥርዓቱ ጣልቃ መግባታቸው በምርጫው ፍትሀዊነት ላይ ጥርጣሬን አሳድሯል፡፡ ቡሀሪ ባሳለፉት የስልጣን ዘመን በተለያዩ ጉዳዮች ትችቶች ይሰነዘርባቸዋል፡፡ በነበራቸው የውትድርና ልምድ ታግዘው በሀገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ በቦኮሀራም የታገቱትን ሁለት መቶ ልጃገረዶች ማስለቀቅ ያለመቻላቸውም እንደ ድክምት ይነሳባቸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ መከላከያ ሰራዊቱ በቦኮሀራም ላይ ወታደራዊ የበላይነትን ይዣለሁ ቢልም በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ ቦኮሀራም እያንሰራራ ጥቃት መሰንዘሩና ግዛቱንም ማስፋፋቱ፣ በርካታ አርሶ አደሮች በቦኮሀራም መገደላቸውና በርካቶችም መፈናቀላቸው ቡሀሪን ተወቃሽ አድርጓቸዋል። ኢኮኖሚውን በተመለከተም የቡሀሪ አስተዳደር ከትችት አላመለጠም፡፡ ናይጄሪያ በነዳጅ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ላይ መንጠልጠሏ ሀገሪቱ የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል በተከሰተ ቁጥር እየበረገገች እንድትኖር አድርጓታል፡፡ እ.አ.አ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ሀገሪቱ ይህ ነው የተባለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን አስመዝግባለች ማለት እንደማይቻል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በአጠቃላይ የናይጄሪያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከህዝቡ ቁጥር ሲሰላ እስከ ሶስት ነጥብ አምስት በመቶ ዓመታዊ እድገት ማሳየት ቢጠበቅበትም ከሁለት በመቶ የበለጠ ዕድገት ያለማሳየቱ ኢኮኖሚው መሻሻል እንደሌለው አመላካች ነው ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያው ሙሀመድ አብዱላሂ አስረድተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የቀረበው የጥናት ውጤት እንዳሳየው የናይጄሪያ የድህነት መጠን ከባለፉት ግዜያት ሁሉ ብልጫ ታይቶበታል፡፡
ከስልሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት ናይጄሪያዊያን ከድህነት ወለል በታች እንደሆኑና የዕለት ገቢያቸውም አንድ ዶላር ከዘጠና ሳንቲም መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ቡሀሪ በሀገሪቱ ሥር እየሰደደ የመጣውን ሙስና ለመዋጋት ቁርጥ አቋም ይዘው እርምጃዎችን ያለመውሰዳቸውም ሌላው አስተዳደራቸው ከሚተችበት ምክንያት አንዱ ነው፡፡ በተለይ በሀገሪቱ የሚገኙት ታላላቅ ኩባንያዎች የሚፈለ ግባቸውን ግብር ላለመክፈል ከባለስልጣናት ጋር ውስጥ ለውስጥ የሚያደርጉት ድርድር የሀገሪቱን ገቢ እንደጎዳ ይነገራል፡፡ በእነዚህና በተለያዩ ምክንያቶች የቡሀሪን በስልጣን መቀጠል የማይደግፉ ቢኖ ሩም አብዛኛዎቹ ደጋፊዎቻቸው ግን ዳግም ሊመርጧቸው ተዘጋጅተዋል፡፡ ለምርጫው ከሰማንያ ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን በምርጫው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ አንድ መቶ ዘጠኝ ሴናተሮችና ሶስት መቶ ስልሳ የፓርላማ አባላት እንደሚመረጡ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
ኢያሱ መሰለ