አቶ ተስፋዓለም ሸዋንግዛው የተስፋ ጋለሪ መሥራችና ባለቤት ናቸው። ጋለሪው ከተመሠረተ ሦስት ዓመት ይሆነዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ የስነጥበብ ት/ቤት ከተመረቁ በኋላ ለአንድ ዓመት በግል ትምህርት ቤቶች ስዕል አስተምረዋል። ከዚያም ግራፊክስ መሞካከር ጀመሩ፤ ይህንንም ትተው ወደ አርት ሄዱ።
አንዳንድ ቦታ እየሄዱ ዐውደ ርዕይ በመክፈት ማሳየት ጀመሩ። ከዚያም ወደ ራሳቸው ሥራ ፈጠራ በመግባት አሁን ባሉበት ቦታ ላይ ጋላሪ ከፈቱ። በዚህ ጋላሪ ዐውደ ርዕይ እያሳዩ፣ ስዕል እያስተምሩ ቆይተዋል።
አቶ ተስፋአለም ከዩኒቨርሲቲ እንደ ተመረቁ ያጋጠማቸው ትልቅ ችግር የስዕል ማሳያ ቦታዎች እጥረትና ወረፋ ነበረ። የመሸጫ ቦታዎችም ችግር ከፍተኛ ነበረ። ‹‹ነገ የተሻለ ነገር እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ። ለምን የራሴን አልከፍተም ብዬ መንቀሳቀስ ጀመርኩ›› ይላሉ። ሊከፍቱ ያሰቡበት አካባቢ ሠፈራቸው መሆኑ ደግሞ ተመቻቸው። አካባቢውንም ወደዱት።
ቦታውን ለማስፈቀድ ውጣ ውረድ ቢገጥማቸውም፣የየካ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለሥራቸው ድጋፍና ትብብር አድርጎላቸው ሀሳባቸው ተሳካ።
ቦታው የሚገኘው ከዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል አቅራቢያ ባለ በዛፎችና ዕጽዋት በተሞላ ሥፍራ ነው፤የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ አረንጓዴዎች ልማትና ውበት ኤጀንሲ ነው። ፓርኩ ከሰዓት ወጣቶች ተኮልኩለው ጫት ሲቅሙበትና ሲጃራ ሲያጨሱበት ይውሉ እንደነበረ ያስታውሳሉ። አሁን ግን የስነጥበብ ሰዎች እንዲወጡበት እየጣርን ነው ይላሉ።
በሌሎችም ፓርኮች እንዲህ ዓይነት ስራ ቢተገበር ቦታውን የጥበብ ሰዎች ማፍሪያ ማድረግ እንደሚቻል ይገልጻሉ። ብዙዎቹ ፓርኮች ዝግ፣ አልያም በከፊል ክፍት ናቸው የሚሉት አቶ ፋንታሁን፣ ጥበብ ከኅብረተሰብ ለኅብረተሰብ የሚሠራ መሆኑን በመጥቀስ ቦታዎች ለእዚህ አይነቱ ተግባር ቢውሉ መልካም መሆኑን ይናገራሉ።
አቶ ተስፋአለም በጋላሪው ታዳጊዎችን ስዕል ያስተምራሉ። የከፈትነው ለጋለሪ ነው፤ ማስተማሩ እንደ ቀልድ ነው የተጀመረው። አንዲት ወላጅ ልጃችንን ስዕል አስተምርልን ብለው ያቀረቡት ጥያቄና በጎ ምላሻችን ሌሎች ታዳጊዎችና ወጣቶችም እንዲመጡ አረጋቸው ይላሉ። የወጣቶችን መማር ሲያስቡት ይደንቃቸዋል። አሁን በርካታ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ሙሉ ቀን ስዕል እየተማሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በጋለሪው በግልና በመንግሥት ተቋም የሚያገለግሉ ሰራተኞች ጭምር ከሥራ መልስ እየመጡ ስዕል ይማራሉ። ለውጥ አላቸው ፤አብዛኛው ሰው እየመጣ ቢደሰት ስዕል ቢሠራ ራሱን ከቀለምና ከብሩሽ ጋራ ቢያገናኝ መልካም ነው።
ይህ አይነቱ ስራ በውጪ ሀገር የተለመደ መሆኑን ይገልጻሉ። ሸራ ብሩሽና ቀለም ይቀመጥላቸዋል፤ ጥቂት ዶላሮችን እየከፈሉ ከሥራ ሲወጡ ሻይ ቡና እያሉ ስእል ይስላሉ።
እኛም ጋ ቅዳሜና እሁድ አለ። ልጅን ወስዶ ስዕል ማሳልና ክህሎቱንም ማሳደግ ያስፈልጋል። ቀለማት የራሳቸው ትርጓሜዎች ስላላቸው ፣ለሁሉ ነገር በር ከፋች ናቸው ። ቀለም እያዩ ማደግ የበለጠ ነገራችንን ያጠራል ሲሉ ያስረዳሉ።
ጋላሪያቸው የስዕል ዐውደ ርዕይ ያዘጋጃል፤ ቦታውም ክፍት ስለሆነ ቢያንስ መንገደኛ ሲያልፍ ምንድነው ብሎ ጠይቆ ይገባል፤ ታክሲ የሚጠብቁ ወጣቶችም ጎራ ብለው ይጎበኛሉ ይላሉ። አብዛኛው ነዋሪ እዚህ ጋለሪ እንዳለ ያውቃል። የስዕል ዐውደ ርዕይ እንደ ሌላው አይደለም፤ ነፃ ነው፤ማንም ገብቶ ሊጎብኝ ይችላል፤ ማድነቅ ማበረታታት ወይም ለሰዓሊው ጉድለቱን ወይም ጥንካሬውን መንገር እንደሚችልም ያስረዳሉ።
በእንጦጦ ፓርክ የተከፈተውን ጋላሪም አቶ ተስፋአለም መጎብኘታቸውን ይገልጻሉ። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ክትትል በተገነባው እንጦጦ ፓርክ የተገነባውን ጋላሪ አቶ ተስፋአለም በአድናቆት ነው የተመለከቱት። በፓርኩ የተገነቡት ነገሮች በአንዳንድ ሰዎች በቅንጦት ሊታዩ ይችላሉ ። የአርት ስራን ለሚረዳ ሰው ግን ይህ ትክክል እንዳልሆነ ነው የሚገልጹት።
‹‹ሁሌ ሆዳችንን ነው የምናየው፤ ሆዳችን ጭንቅላታችን ላይ ቢሆን ጥሩ ነው፤ ሆድህ ከሚጠግብ ጭንቅላትህ ቢጠግብ ይሻላል።ሆድህ ጠግቦ መውጣቱ የማይቀር ነው›› የሚሉት አቶ ተስፋአለም ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭንቅላታችንን ያጠገቡ አመራር ናቸው ይላሉ። በጣም ጥሩ ምግብ ነው የመገቡን፤ ቦታው ስታየው፤ የተሠራው ጋለሪ በጣም ያስደስታል፤ ከተማው ላይ የሚታየው ውበት እንደ ሰዓሊ መልካም ጅማሮ ነው።”ሲሉ ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የኪነጥበባት ልማት ሀብቶች ዳይሬክቶሬት የዕይታዊ ጥበባት ልማት ቡድን መሪ አቶ አብርሃም ታምር በርካታ የስነጥበባት ጋለሪዎች እንደነበሩ አስታውሰው፣ አሁን እየተመናኑ መምጣታቸውን ይጠቅሳሉ። ተከራይተውና ውድ በሆነ ቦታ ላይ ውድ ዕቃ ይዘው እንደሚቀርቡ ተናግረው፣ በተለይ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ እየተመናመኑ መጥተው ከስድስት እስከ ሰባት የማይበልጡ ብቻ መቅረታቸውን ያመለክታሉ።
እንደ አቶ አብርሃም ገለጻ፤ ጋለሪዎች በጣም ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፤ ሰዓሊው ስዕሉን ስሎ ለታዳሚው የሚያቀርብበት አንዱ ዐውድ የስነጥበብ ጋለሪ ነው። እነዚህ ተጠናክረው መቀጠላቸው ለጥበቡም ዕድገት ፣ ለጥበብ አፍቃሪውም ወሳኝ ነው።
ጋለሪዎች ዐውደ ርዕይ (ኤግዚቢሽን) ማሳየት አለባቸው ፤ገቢ አግኝተው ራሳቸውን የሚመሩት በዚያ ነው። በዚህም የስዕል ጥበቡን እየሠሩ እያሳዩ ወደ ባለሀብትነት የተቀየሩ ብዙ ናቸው።›› ሲሉ ያብራራሉ።
ጋላሪዎቹ ፈተና እንዳለባቸው ይጠቅሳሉ። ‹‹እኛም ከተቋቋምን ዓመታችን ነው ።ገና መረጃዎችን በማደራጀት ላይነን ።በቅርበትም ከአንዳንዶቹ ጋር እየሠራን ነው።›› የሚሉት አቶ አብርሃም፣ የምቹ ቦታ አለመኖር፣ በተለይ የኮቪድ መምጣት በእጅጉ እንደጎዳቸው ይናገራሉ። በኮቪድ ምክንያት በርካታ ጎብኚዎች ወደ ሀገራችን መምጣት ስላልቻሉ ጋለሪዎች የመጀመሪያ ተጎጂ ሆነዋል ነው የሚሉት። በድኅረ ኮቪድ ለሆቴሎች ድጎማ ቢደረግም፣ እነዚህ ምንም ድጎማ ብድር አላገኙም ይላሉ።
አንድ የስዕል ዐውደ ርዕይ በቢሮው በጎላ የስነጥበባት ማዕከል ተዘጋጅቶ እንደነበር የሚጠቅሱት የቡድን መሪው፣ የከተማው ማኅበረሰብ እንዲጎበኘው መደረጉን ይገልጻሉ። ‹‹እዛ ያዘጋጀንበት ትልቁ ጭብጥ የከተማው ኅብረተሰብ ጋለሪዎችን መጥቶ እንዲጎበኝ፣ እንዲያያቸውና ከጎናቸው እንዲሆን ለማድረግ ነው ይላሉ። ይሄን የማድረግ ባህል በከተሞች ደረጃ እንደሌለም ጠቅሰው፣ የከተማው ህዝብ እንዲጎበኝ እንዲገዛ የምናበረታታው በዐውደ ርዕይ ነው ብለዋል።
እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ ፤ህብረተሰቡ ወደ ጋላሪዎች ለመሄድ መጀመሪያ ስዕልን ማፍቀር አለበት። ስለዚህ ስነጥበብን እንዲያፈቅር ከወረዳ እስከ ከተማ ባለው መዋቅር በርካታ ሥራዎች ወደ ታች እንዲወርዱ እየተደረገ ነው።
በዚህም ስዕልን የሚያፈቅር ስዕልን የሚወድ የሚጎበኝ የት እንዳለ የሚጠይቅ ሰው ከቀረጽን በኋላ ጋለሪዎች እንዲጎበኝ ማድረግ እንችላለን ሲሉ ይገልጻሉ። እንደ ቢሮ በሚኖሩን የኪነጥበብ ዝግጅቶች ላይ ባለጋላሪዎች እንዲሳተፉ በመጋበዝ በጋራ ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ እየጣርን ነው ሲሉ አቶ አብርሃም ተናግረዋል።
አቶ አብርሃም እንደሚሉት፤ ጋለሪ ቤቶች በርካታ ተግዳሮቶች አሉባቸው፤ በተለይ የቦታ ችግር በሠፊው አለባቸው። ተከራይተው ነው የሚሠሩት፤ የኪራይ ዋጋ ሲጨምር የሚጎበኝ ሰው ሳይኖር ሲቀር በኪሣራ መንቀሳቀስ ውስጥ ሊገቡ ይገደዳሉ።
እኛም በቀጣዩ ዓመት ይህን ችግር ለከተማ አስተዳደሩ በማቅረብ ለመፍታት እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ሲሉ አቶ አብርሃም አስረድተዋል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2013